ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም የሰሜን ዕዝ ጥቃት እና የጥቅምት 30ን የማይካድራን፤ በተከታይ ወራት ደግሞ የጋሊኮማን የአጋምሳን የጭናን የደብረ ታቦርን የውጫሌን የኮምቦልቻን የቆቦን የደሴን የጭፍራን ወዘተረፈ ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይላቸው የደም መሬቶች (አኬል ዳማዎች)”ጌታ”ወይም ከበርቴ የሆነው እና የክፍለ ዘመኑን ታላላቅ ክህደቶችንና ጭፍጨፋዎችን ለመፈጸም ዝግጅቱንና ልምምዱን የጀመረው ከደደቢት ውልደቱ ከየካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም አንስቶ ነው። ለግማሽ ክፍለ ዘመን በዝግ የተዶለተበት የክህደት ደባ እና የጭካኔ ልምምድና ዝግጅት ውጤት ነው።
ግማሽ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ዘመን በክህደት በጭካኔና በአረመኔነት ባፈሰሰው ህልቆ መሳፍርት በሌለው የንጹሐን ደም የበርካታ የደም መሬቶች ባለቤት ቢሆንም ከጥቅምት 24 ቀን 2013 እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በወረራቸው የአማራና የአፋር አካባቢዎች የንጹሐንን ደም እንደ ጎርፍ እያፈሰሰ ነው።” … የመከላከያ ትጥቁም ስንቁም ለዓመታት እዚያ ብቻ እንዲከማችበት የተደረገበት ምክንያት አሁን የመጣው ለውጥ ቢመጣም ባይመጣም፤ የሀገሪቱ የመከላከያ እዚያ ብቻ እንዲሆን ታስቦ ነው። ይህ የክቡር ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ንግግር በሰሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመው ትውልድም ታሪክም ይቅር የማይለው ክህደትና ዘግናኝ ጥቃት ቀድሞ ነሳሳት ልሞክር።
ህወሓት በአዲስ አበባየታሰበበትና የተመከረበት ስለመሆኑ ያነሳሁትን ሙግት ያጠናክርልኛል። ክህደቱን ታሳቢ በማድረግ አበክሮ ዝግጅት ስለመደረጉ የምመለስበት ሆኖ፤ የክህደት ልምምዱ አሀዱ ብሎ ከጀመረበት እስከ ፍጻሜው የሚመዘዙ ቅጥልጥል ክህደቶችን ለማ ፒያሳ በኬቭ ካፌ በራድ ሻይ እፉት እያለ ሆነ በሌላ ቦታ ሆኖ ወደ “ትግል” ሜዳ ለመውጣት ሲወስንም ሆነ እንደወጣ ታሪክን፣ እውነትን፣ ሰንደቃላማን፣ አብሮነትን፣ ሰብዓዊነትን፣ ኢትዮጵያዊ ማንነትን፣ ፍቅርን፣ ሰውነትን፣ ፈጣሪን፣ ወዘተረፈ ሽምጥጥ አርጎ ክዶ የራሱን የፈጠራ ትርክት ነው ያነበረው።
የሀገሪቱን ታሪክ ወደ 100 ዓመታት አራክሶ፤ እውነትን ኅልቁ መሳፍርት በሌለው ውሸት ተክቶ፤ ሰንደቃላማን ጨርቅና የአንድ ሀይማኖት አርማ ነው ብሎ፤ አብሮነትን በመለያየት ቀይሮ፤ ሰብዓዊነትን በአረመኔነት ለውጦ፤ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በጎሳ ለንጥቆ፤ የትግራይ ሕዝብ ጠላት የአማራው ገዥ መደብና ኦርቶዶክስ ነው ብሎ፤ ፈጣሪን ክዶ ራሱን ወደጣኦትነት ቀይሮ እስከማምለክ የደረሰ ወዘተረፈ የራሱን ተረክና እውነት በይኖ በራሱ አለም ሲዳክር የኖረ ባተሌ ስብስብ ነው።
የእውነትን፣ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን፣ የዜጋውን የልቦና ውቅርና የታሪክን ፈለግ ተከትሎ ርዕዮት አለም መንደፍ የማታገያ ስልት መትለም ሲገባው፤ በተቃራኒው እውነትን፣ ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን፣ የዜጋውን ልቦና ውቅርና ታሪክ በድቡሽት ላይ ለተቀለሰ ማንፌስቶው እንዲመጥኑ እጃቸውን ጠምዝዞና አጣሞ እንደገና መበየኑ እና ካፈርሁ አይመልሰኝ በሚል በስሁት መንገዱ ልምምዱን መቀጠሉ የዚች ሀገር ጎልማሳው ከሀዲ አድርጎታል። ከጥፋቱና ከዕድሜው የማይማር ልበ ቢስ። ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እወርዳለሁ፤ ኢትዮጵያ ስትፈርስ ቆሜ በማየቴ እድለኛ ነኝ፤ ኢትዮጵያዊነት ተንከሲስ አስተሳሰብ ነው፤ ከአማራ ጋር የማወራርደው ሒሳብ አለኝ፤ ወዘተረፈ እስከማለት የደረሰ መርገምት ነው። ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዳሉት ያለፈውን ታሪክን የመርሳት አባዜ ስላለብን ዋና ዋና የትህነግ ክህደቶቹን ብቻ ላስታውስ።
ቢያንስ ወደ ስምንት ሺህ ዓመት የሚጠጋ ቀደምት ሀገረ መንግስትና ታሪክ ያላትን ጥንታዊት ሀገር በልኩ ካሰፋው የታሪክና የርዕዮት አለም ቁምጣ ጋር ለማስኬድ ሲል ትላንት እንደ እነ አሜሪካ በአሳሽ የተገኘች ይመስል ታሪኳን የ100 ዓመት ነው ሲል በአደባባይ የካደ የነውረኞች ስብስብ ነው። የዛሬዋ ኢትዮጵያ ቅርጽ ስሪት በአጼ ምኒልክ የተፈጠረ ነው አለ። በጎሳ ላይ የተመሰረተው አስመሳይ ፌደራሊዝም የተዋቀረው በዚህ የክህደት መሠረት ነው። የአንድ ሀገር ጥንታዊነት ተካደ ማለት የቁጥር ጉዳይ ብቻ አይደለም። የዜጎችን አብሮነት፣ የሀገሪቱን የሀገረ መንግስት ልምምድና አጠቃላይ ማንነቷን የሚያኮሰምን ክህደት ነው።
ዜጋው በሀገሩና በታሪኩ ያለውን እምነት ለመሸርሸርና አንድ አርገው አጋምደው ያቆዩትን ወረቶች ለማስጣል የተከናወነ መሰሪ ክህደት ነው። ይህ ብቻ አይደለም ለሀገሪቱ ያለው ጥላቻ ግዘፍ ነስቶ የተገለጠበት ክህደት ጭምር ነው። በአለማችን ላይ የሀገሩን ታሪክ አሳንሶ ሽንጡን ይዞ የተከራከረ እና አምርሮ የሚጠላትን ሀገር የገዛ እንደ ከሀዲው ትህነግ ያለ ቡድን የለም። ይህን ጥላቻውን አገዛዝ ላይ እያለ በሚያራምዳቸው ስሁት ፖለቲካዊ አቋሞቹና አይን ያወጣ ዘረፋው አረጋግጧል። ከገዢነቱ በሕዝባዊ ማዕበልና በለውጥ ኃይሉ ከተሽቀነጠረ በኋላ እኔ ረግጬ የማልገዛትና የማልዘርፋት ሀገር ትውደም በሚል የሔደበትን እርቀት ታሪክም ትውልድም በቁዘማ ሲያስታውሰው ይኖራል።
ከሀዲው ትህነግ ብሔርን የትግሉን የማዕዘን ራስ አድርጎ መነሳቱ የሀገሪቱን ቀጣይ የፖለቲካ መልክዓ በአሉታ በይኖታል። ገለባብጦታልም። የሚያሳዝነው ይህን ያደረገው ለብሔር መብት ተቆርቁሮና ጠበቃ ሆኖ ሳይሆን ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲያመቸው መሆኑ ነው። ለእነሱ መብት ግድ የሚሰጠው ቢሆን ኖሮ በውሸት ፌደራሊዝም ለ27 ዓመታት የግፍ ጽዋ ባላስጎነጫቸው። የሚገባቸውን ፖለቲካዊ ውክልናና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ባልነፈጋቸው። ከሁሉም በላይ እርስ በርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ እንዳይተማመኑና እንዲጋጩ ሌት ተቀን ባልሰራ። በፌደራል ስርዓቱ ትልቁን ድርሻ ሊይዙ በሚችሉት አማራና ኦሮሞ ላይ የጥል ግድግዳ ከመገንባት ባሻገር ወደ ማይታረቅ ግጭት እንዲገቡ ጥሯል።
የሚገርመው ትህነግ ይህን ሁሉ ሴራ ይሸርብ የነበረው በሀገሪቱ ይስተዋል የነበረውን የመደብ ጭቆና በብሔር ጭቆና በመተካት ነው። በዚች ሀገር ታሪክ አንድ ብሔር ገዢ መደብ ሆኖ አንድ የተወሰነ ብሔርን ጨቁኖ ገዝቷል የሚል መረጃም ሆነ ማስረጃ የለም። የገዥው መደብ አማርኛ ይናገር ስለነበር አማራ ገዝቷል ከሆነ መከራከሪያው ውሃ አያነሳም። እንግሊዘኛ የሚናገር ገዥ ሁሉ እንግሊዛዊ እንዳልሆነው ሁሉ። ከአፄ ምንሊክ እስከ ደርግ የነበሩ አገዛዞችን ገዥዎች የማንነት ስብጥር በአብነት ማንሳት ይቻላል።
አማራው፣ ኦሮሞው፣ ትግሬው፣ ጉራጌው፣ ወዘተረፈ የገዥው መደብ አባል ነበሩ። ሆኖም ትህነግ ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲል እነ ዋለልኝ ከእነ ስታሊን የኮረጁትን የብሔር ጥያቄ ለጥጦና አጡዞና አጉኖ የስውር አላማው ማስፈጸሚያው አድርጎታል። ይህ የትህነግ ስሁት የማንነት ፖለቲካ ዛሬም እንደጥላ የሚከተለንና ወደፊትም በቀላሉ የማይፋታን መሆኑ እንደ ዜጋ ያሳስባል።
ከዚህ አዙሪት የምንወጣበት በር ላይ መስማማት አለመቻላችን ደግሞ ነገሩን በእንቅርት ላይ ቆረቆር ያደርገዋል። የትህነግ የክህደት ጉዞ በዚህ አጭር መጣጥፍ አይደለም ራሱን በቻለ ዳጎስ ያለ ባለ ተከታታይ ክፍል መፅሐፍም ስለማይዘለቅ በዚህ ገታ አድርገን ለጥቅምት 24ቱ ክህደት መከላከያውን እንዴት አበክሮ ያዘጋጀው እንደነበር እንመልከት።
ከፍ ብሎ በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደተገለጸው ደግሜ እጠቅሰዋለሁ፤ “ … የመከላከያ ትጥቁም ስንቁም ለዓመታት እዚያ ብቻ እንዲከማችበት የተደረገበት ምክንያት አሁን የመጣው ለውጥ ቢመጣም ባይመጣም፤ የሀገሪቱ የመከላከያ እዚያ ብቻ እንዲሆን ታስቦ ነው። …” ትህነግ ክህደቱን በወታደራዊ ኃይል ለማፈርጠም የሸረበውን ሴራ ጠቅላይ ሚንስትሩ በእንደራሲዎች ሸንጎ ሲያብራሩ፤ “ … በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የመከላከያ ዕዞች ተደምረው በትግራይ ክልል የሚገኘውን የሰሜን ዕዝ የሰው ኃይል አያክልም። …” ይህ ሰሜን ዕዝ ከመከላከያ ሰራዊት እኩሌታም የሚበልጥ መሆኑን ያሳያል። ለምን ቢባል ትህነግ አንድ ቀን ይሄን ክህደት እንደሚፈጽም ያውቅ ስለነበር አበክሮ ማመቻቸቱ ነው።
የዕዙ ትጥቁም ሆነ ስንቁ ከተቀረው መከላከያ ይበልጥ ስለነበር ለዚህ እኩይ አላማው ቀድሞ አደላድሏል። የመከላከያ የጦር መሳሪያ መጋዘን፣ ታንኩ፣ ሮኬቱና ሚሳይሉ ሆን ተብሎ በትግራይ ክልል መከዘኑ፤ የነዳጅ ዲፖው በዛ መሆኑ፤ የዕዝና የክፍለ ጦር አዛዦች ከትግራይ ብቻ መሆናቸው፤ ከጀነራሎች 60 በመቶ፣ ሌተናል ጀነራሎች 40 በመቶ፣ በሜጀር ጀነራል 45 በመቶ፣ ወዘተረፈ መሆኑ ከፍ ብሎ ለመግለጽ እንደተሞከረው ከሀዲው ትህነግ ለዚህ ጥቃት ቀድሞ ሲዘጋጅ፣ ሲመሰረትና ሲደላደል መኖሩን ያለምንም ውልውል ያረጋግጣል።
ከሀዲው ትህነግ የሰሞነኛው የሀገር፣ የሕዝብና የሰራዊት ክህደት ላይ የደረሰው ከ46 ዓመታት ልምምድና ዝግጅት በኋላ ነው። ማንነቱን በመካድ አሀዱ ያለው ቡድን፤ በመቀጠል የትግል ጓዶቹን፤ በመሰለስ ሌሎች የትግራይ ድርጅቶችን እነ ኢዲዩን፣ አህአፓን፣ ኦነግንና ሸዓብያን ወደ መክዳት ተሸጋግሯል። በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምኑ፤ የኤርትራን መገንጠል ይቃወሙ፤ በውስጠ ድርጅት ዲሞክራሲ እንዲጎለብትና አውራጃዊነት እንዲወገድ ይሟገቱ የነበሩ ሀገር ወዳዶችን አንድ ባንድ አስገድሏል።
የራራላቸውንም አሰድዷል። በ1977 ዓ.ም ድርቅና ርሀብ የትግራይ ሕዝብ እንደ ቅጠል እየረገፈ የእርዳታ እህል፣ አልሚ ምግብና ዘይት ሽጦ የጦር መሳሪያ የሸመተ አረመኔ ነው። ነጻ አወጣዋለሁና እታገልለታለሁ የሚለውን የትግራይ ሕዝብ ስም መነገጃ ማድረግን የተለማመደው ከዛ ሩቅ ዘመን አንስቶ ነው። በእውኑም ሆነ በህልሙ አስቦት የማያውቀው በለስ ቀንቶት ስልጣን ከያዘ በኋላ ለ27 ዓመታት በትግራይ ሕዝብ ሲነግድ የግል ጥቅሙን ሲያሳድድ ኖረ እንጅ ዘወር ብሎ አልጠየቀውም።
እንደተኩላ ልጆቹን ከጉያው ሲነጥቅ የገባለትን ቃል ኪዳንም ሲክድ ጊዜ አልወሰደበትም። ለዚህ ነው የትህነግን አፈጣጠርና አስተዳደግ ቀረብ ብለው የሚያውቁ በሰሞነኛ ክህደቱ እንደኛ ያልደነገጡት። ያልተገረሙት። አዎ ! የከሀዲውን ማንነት ጠንቅቀው ለሚያውቁት ክህደቱ የሚጠበቀና ጴጥሮሳዊ ነበር።
ለዚህ ነው እንደ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ያሉ ነባር ታጋዮች እና የሻዓብያ ጉምቱ ሰዎች ትህነግን ከፍጥርጥሩ ጀምረው ስለሚያውቁት በዚህ አሳፋሪ ክህደት እንደተቀረው ኢትዮጵያዊ ያልደገነጡት። ያልተገረሙት። ይሁንና ኢትዮጵያውያንን ያለ ልዩነት በድንጋጤ እጃቸውን በአፍ ያስጫነው፤ በፍርሀት ያስራደው ክህደቱም ሆነ ጭካኔው በሀገሪቱ ታሪክ ተከስቶ የማያውቅና ከሕዝቡ የስነ ልቦና ውቅር ፍጹም ያፈነገጠ ስለነበር መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።
እንደ መውጫ
ከሀዲው ትህነግ ከደርግ ጋር እየተዋጋ ለሰሞነኛው ጦርነት ይዘጋጅ ነበር። ዝግጅቱ ተደጋግሞ እንደተገለጸው የሶስት ዓመታት ብቻ አይደለም። የ47 ዓመታት እንጂ። ከሀገሪቱ ሕዝብ አምስት በመቶውን ብቻ ወክሎ ሕዳጣን ሆኖ ሕዝብን እየከፋፈለና እያለያየ፤ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ቀጥቅጦ እየገዛ፤ እየዘረፈ፤ በገዛ እጁ ጠላት እየቀፈቀፈ፤ ወዘተረፈ ዘላለም ስልጣን ላይ መቆየት ስለማይችል፤ በዚህም ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊነሳበት እንደሚችል ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ሁል ጊዜም ለጦርነት ዝግጁ ነው።
የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት ተጠቅሞ በቅርብ ሊቆጣጠረውና አንድ ቀን ሊጠቀምበት ወይም ሊክደው የሚችለውን ሰሜን ዕዝ አደራጀ። ኤርትራ ትወረኛለች ብሎ ካሰብ በአሰብ መስመር አፋር የሚገኘውን የቡሬ ግንባር ለምን እንደ ሰሜን ዕዝ አላደራጀውም። መልሱ ቀላል ነው ኤርትራ እንደማትወረው ግጥም አርጎ ያውቃል። ለዚህ ነው ሰሜን ዕዝን ለዚህ ክህደት ማስፈጸሚያነት ሲገነባው የኖረው።
አበክሮ ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር እንደ ኤፈርት ያለ ግዙፍ ኩባንያ በዘረፋ የገነባው፤ የስነ ልቦና ዝግጅት ሲያደርግ የኖረው ይህ ቀን እንደሚመጣ ስለሚያውቅ ነው። በነገራችን ላይ በሕዝባዊ አመፅና በለውጥ ኃይሉ በኢፍትሐዊነትና አላግባብ ከያዘው ስልጣን ያለምንም ማንገራገር ጓዙን ጠቅልሎ መማፀኛ ከተማው መቐሌ የገባው ተመልሶ ስልጣን ላይ እንደሚመጣ እርግጠኛ ስለነበር ነው።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና በሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2014