ዛሬ ሀገር ውጥረት ውስጥ ናት። ችግሮች በየፈርጃቸው አይናቸውን አፍጥጠው ጥርሳቸውን አግጥጠው መጥተውባታል። አሸባሪው የህወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ታሪክ የማይረሳውን ዘግናኝና አሰቃቂ ጥቃት ፈጽሞ ጦርነት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ በርካቶች ቆስለዋል፤ የህይወት መሰዋዕትነት ከፍለዋል። የግልና የመንግስት ንብረቶች ወድመዋል። በሚሊየን የሚቆጠሩት ተፈናቅለዋል። ሌላም ሌላም… ።
ይሄ በአሸባሪው ህወሓት መሪነት የተቀሰቀሰው ሀገርን የማፍረስና አንድ ብሄርን የማጥፋት ዘመቻ እንደነ አሜሪካን ባሉና በሌሎች የምዕራባውያን ሀገሮች ጭምር ድጋፍ አግኝቶ ቀጥሏል። በሰብአዊ እርዳታ ስም የገቡ የእርዳታ ሰጪ ድርጅት አንዳንድ ሰራተኞች ሳይቀሩ የተሰማሩበትን ዓላማና ተግባር ወደጎን አድርገው ከተቋቋሙበት ዓላማና ግብ በተቃራኒ ቆመው ከሀገር አፍራሹ ጋር ሲተባበሩ ተገኝተዋል። ይሄንንም በተጨባጭ ማስረጃ ያረጋገጠው መንግስትም በሰባት ዓለም አቀፍ እርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ሰራተኞች ላይ እርምጃ ወስዷል።
ሀገራችን ለበርካታ ጊዜያት የሀገርን ህልውና የሚፈታተኑ ችግሮች ገጥመዋታል። የገጠሟትን ችግሮች የተወጣችው በህዝቧ ቆራጥነትና አልበገር ባይነት፤ እንደ አንድ አስቦና አንድ ቋንቋ ተነጋግሮና ተግባብቶ በቆራጥነትና በጥበብ በአንድነት በተነሳው ህዝቧ ነው። ይሄ ደግሞ ውጤት አምጥቷል። ውጤቱ ዛሬ ሀገራችንን እደረሰችበት ደረጃ ላይ እንድትደርስ አድርጓታል። ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ሆና እንድትቀጥል ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሏል። ለዚህም የአደዋን ዘመቻና ድል ማንሳት ብቻ ይበቃል።
ጣሊያን ሀገራችንን በቀኝ ለመያዝ የሀገራችንን ሉአላዊነት በተዳፈረ ወቅት የወቅቱ መሪዎች ለህዝቡ ያቀረቡት ጥያቄ ጠላትን ለመመከት በአንድነት ክተት የሚል ነበር። ክተት ለነጻነትህ፣ ክተት ለሀገር የሚል ነበር። በወቅቱ ህዝቡም በውስጡ ያለውን ልዩነት በይደር አሳድሮ ሁሉም በአቅሙ ለጥያቄው የሰጠው አፋጣኝ ምላሽ ነው። ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ተሰልፏል። ሴቶች ስንቅ በማቀበል፣ ቁስለኛ በማንሳት፣ በአውደ ውጊያው ሞራል በመሆን፤ ሌላውም በደጀንነት የሀገሩን ሉአላዊት ለማስከበር ተሟል። አጥንቱን ከስክሶ ደሙን አፍስሶ ይሄወ እስከዛሬ የእናት ሀገሩን ነጻነት አስከበሮ ኖሯል። በወቅቱ የዘመነ መሳሪያ ባልነበረበት፣ ቴክኖሎጂ ባረቀቀበት፣ ስልጣኔ በማይታሰብበት የወቅቱን ስልጣኔ የያዙትንና ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቁትን የውጪ ወራሪ ሀይል ነው ያሸነፉት።
ይሄ እንዴት ይሆናል ? ከተባለ ተችሏል። ተችሎ አይተነዋል። ምክንያቱም ያኔ ከጣሊያን ዘመናዊ መሳሪያና ስልጣኔ በላይ ኢትዮጵያውያን ትልቅ የአሸናፊነት ሞራል ሰንቀዋል። ትልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ነበራቸው፤ ትልቅ ወኔን የታጠቁ ነበሩ። ያንን አስተባብረው እና በአንድነት መንፈስ ተነሳስተው የድሉ ባለቤት መሆን ችለዋል ።
ዛሬም ሀገራችን የገጠማትን የውስጥና የውጪ ጫና መቋቋም የሚቻለው በዚሁ መንገድ ነው። በዚሁ ጥንካሬ ነው። ማንም ተነስቶ ሀገር አፈርሳለሁ ሲል ቁጭ ብሎ ከዳር ተመልካች ሆኖ ማየት አይኖርበትም። የተጠየቀው ለህልውናህ፣ ለነጻነትህና ለፍትህ ክተት የሚል ጥሪ ነው። የተጠራው ክተት የሚል የእናት ሀገር ጥሪ ነው። እናት ሀገር ትጣራላች ጊዜው አሁን ነው አድኑኝ ትላለች። ይሄ የእናት ጥሪ ፋን ምላሽ ይሻል። አካባቢህን ጠብቅ፣ ለመከላከያው ድጋፍ ሁን። ዛሬ ነገ ሳትል ለዚህ የእናት ሀገር ጥሪ አፋጣሽ ምላሽ መሰጠት አለበት፤ ይገባልም።
ሀገር ለማፍረስ እየተንደረደሩ ያሉት አሸባሪዎቹ የህወሓት ቡድንና ሸኔ ያልተቀደሰ ጋብቻ መስርተው በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በሚያስብ መልኩ ጦርነት ከፍተዋል። ንጹሀን ዜጎች በዘራቸው እየታረዱና እየተገደሉ ናቸው። ከሞት የተረፉ ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየአቅጣጫው ስደተኛ ሆነዋል። ሰርተው የማይጠግቡ እጆች ተሰብስበው ቆርሰው የሚያጎርሱ እጆች ተጣጥፈው ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። ቀያቸውን ለቀው ሳይወዱ በግድ ተፈናቅለዋል።
ዛሬ የሚጠባበቁት የዕለት ጉርስ ነው። የዕለት ልብስ ነው። መጠለያ ነው። ይሄ ሁሉ የሆነው በአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ነው። ታዲያ ይሄንን የሀገርና የህዝብ ስቃይ እየሰማና እያየ ቁጭ የሚል ኢትዮጵያዊ አለን ? ይሄ ጥያቄ ሁሉንም ዜጋ ይመለከታል። መንግስት የክተት ጥሪ አድርጓል፤ አፋጣኝ መልስ ይፈልጋል። አቅምና መሳሪያ ያለው፣ ወታደራዊ ስልጠና የወሰደና ሊወስድ የተዘጋጀ ወገን ሁሉ አቤት ሊል ይገባል። ጉልበት ያለው ሁሉ የመከላከያ ሰራዊቱን ተቀላቅሎ ሀገርን ከብተና ህዝብን ከስደትና ሞት፤ ከአስከፊ መከራ ሊታደግ ይገባል።
ገንዘብ ያለው ገንዘቡን ሊሰራበት የሚችለው ሀብት የሚያፈራው ሀገር ሲኖር መሆኑን አውቆ ሀገሩን፣ የሀገሩን መከላከያ ሰራዊቱንና ተፈናቃይ ወገኑን ሊደግፍ ይገባል። ቀሪው ህዝብ ደግሞ ደጀን ሆኖ አጋርነቱን ማሳየት አለበት። አሁንም ምንም ነገር ማድረግ የሚቻለው ሀገር ሲኖር ብቻ መሆኑን መዘንጋት የለበትም። ሀገር ከምንም በላይ ናት። ሀገር እናት ናት። መሸሸጊያና መቀበሪያችን ናት። ስለዚህ ሀገራችንን ዛሬ ማዳን አለብን። ለሀገራችን ክብር ነጻነትና ፍትሀዊነት መነሳት፣ መዝመትና መሞትአለብን።
ሞት ለእያንዳንዳችን የማይቀር የተፈጥሮ እዳ ነው። ሁለት ጊዜ ሞት የለም፤ ሞት አንዴ ነው። በእንቅፋትም በድንገተኛ አደጋም ሞት ይኖራል። ለሀገር እንደመሞት ያለ ሞት ግን የለም። ለሀገር መሞት ጀግንነት ነው፤ ኩራት ነው። ለሀገር መሞት መሞት ሳይሆን ታሪክን በወርቅ ብዕር መጻፍ ነው። ለሀገር መሞት ሞት ሳይሆን የሀገርን ህልውና ማስቀጠል ነው። ሀገር የየትኛው ብሄር የየትኛው ሀይማኖት ብቸኛ መኖሪያ አይደለችም። ለሁሉም እኩል ናት። ሁሉንም እኩል የምታቅፍ እናት ናት። ስለዚህ ለሀገር መሞትን ክብር ነው ብለን መቀበል አለብን።
ዛሬ በእኛ ዘመን በእኛ እጅ ላይ የገባችው ሀገራችን የያኔዎቹ አያት ቅድመ አያቶች የሞቱላት ሀገር ናት። ዛሬም ለቀጣዩ ትውልድ የምናቆያት ሀገራችን እኛ ዛሬ የምንቆምላት፣ የምንወድቅ የምንነሳላት ሀገር ናት። ለዚህ ደግሞ ዝግጁ መሆን ይገባል። ለዚህ ደግሞ ዛሬ ሀገርን ከብተና ለማዳነ ለሚደረገው ዘመቻ መዝመት ያስፈልጋል። ለሀገር መሞት ክብር ነው። ይሄንን ክብር ከፊት አስቀድመን በመንግስት እየቀረበ ላለው የክተት ጥሪ ምላሽ እንስጥ። በከፍተኛ ቁጭትና ሞራል ‹‹እኔ እያለሁ ኢትዮጵያ አትፈርስም›› ልንል ይገባል።
እንደትናንቱ ሁሉ ዘማች የሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ሚሊሽያና ፋኖ ነው ብሎ መቀመጥ በራስ ላይ ሞትን መጥራት ነው። ሀገርን አፍርሶ ከንቱ ሞት ከመሞትና የታሪክ ተወቃሽ ከመሆን ዛሬ ለሀገሬ አለሁላት ማለትን ያስፈልጋል። ሀገር በአንድ ሰው ትከሻ በጥቂቶች ትብብር አትቆምም፤ ሀገር እንደመስቀል ደመራ ሰብሰብ ብለው በተሰሩ ችቦዎች ጎልታ የምትታየው ደምቃ የምትበራው ሁሉም ሲተባበር ነው። ሁሉም ለህልውና ዘመቻው፣ ሀገርን ከመፍረስ፣ ህዝብንም ከብተና ለመታደግ ሲተባበር ብቻ ነው። እናም የፖለቲካ አመራሩ፣ በየደረጃ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ ሌላውም አቅምና ጉልበት ያለ ሁሉ በዚህ ታሪካዊ ጊዜ ታሪክ ለመስራት በግንባር ቀደምትነት እንዝመት። አርአያ ሆነን ጀግነን እናጀግን።
ሀገር የሁሉም ናት። ከሀገር ወዲያ ሞት የለምና ለሀገራችን እንሙት፤ ለሀገረ መሞት ክብር ነው፤ ታሪክ ነው። ስለዚህ ቀን ሳንቆርጥ ዛሬ ለሀገራችን እንሙትላት ብለን እንዝመት፤ ስንቅና ትጥቅ እናቀብል። ደም እንስጥ፣ የተጎዳውን ወገን እንድረስለት። በሁሉም በኩል እናት ሀገር ጥሪ ባቀረበችበት መስመር ሁሉ ተሰማርተን የአቅማችንን ለሀገራችን እንስራ። አዎ! አሁንም ምንም ነገር ከሀገር በላይ አይደለምና ለሀገራችን እንሙት። ሞት ለሀገር ሲሆን ሞት አይደለም።
አዶኒስ (ከሲኤምሲ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2014