የሰው ልጅ በፈጣሪ አምሳያ የተፈጠረ ክቡር ፍጡር ቢሆንም አሸባሪው ሕወሓት ግን ይህንን የሚቀበል አለመሆኑን ለሰው ልጅ ህይወት ባለው ዝቅተኛ ግምት አሳይቷል።ይህ ቡድን ለስልጣኑ ሲል የትግራይን ህዝብ በማይጠቅመው ጦርነት እና ስቃይ እየማገደ ነው።ከዚህም አልፎ ለአጎራባቹ የአማራና የአፋር ህዝብ እዲሁም ለመላው ኢትዮጵያም የሰላምና የእድገት ጠንቅ እየሆነበት ይገኛል፡፡
ይህ ቡድን ገና ከምስረታው ጀምሮ እሱ የሚፈልግበት ስልጣን እርከን ላይ መውጣት እንጂ በምን መንገድ ወደስልጣን ልምጣ የሚለውን መሰረታዊ ጉዳይ ሊያስብበት አልፈለገም።ለሱ ብቸኛው የስልጣን መንገድ ጦርነት ነው።በዚህ የተነሳ በአመፅ ተወለደ፣ በአመጽ አደገ፣ ዛሬም አመጽን ብቸኛ መንገድ አድርጎ እየሄደ ይገኛል።ለ17 ዓመታት ባካሄደው ጦርነት ከ60 ሺህ በላይ የትግራይ ዜጎች ህይወት እንዲጠፋ አድርጎም የጦርነትን አስከፊነት መማር ያልቻለ አሸባሪ ድርጅት ነው። በዚህም በርካታ እናቶች አልቅሰው እንባቸውን ለፈጣሪ ሰጥተው ተቀምጠዋል።
ይህ የፈሰሰ እምባ በአግባቡ ሳይደርቅ ደግሞ ቡድኑ ህዝብን ወደከፋ ሌላ ጦርነት በመክተት ዳግም የትግራይንና የሌሎች ኢትዮጵያውያንን እንባ እያፈሰሰ ይገኛል።ቡድኑ በአንድ በኩል ለትግራይ ህዝብ ተቆርቋሪና ብቸኛ ተወካይ በመምሰል ለእሳት ሲማግደው ይስተዋላል።ለዘመናት በተካነው የሃሰት ፕሮፓጋንዳም የትግራይን ህዝብ አደጋ የተጋረጠበት በማስመሰልና ከዚህ አደጋ የሚታደገው ብቸኛ ድርጅት እሱ መሆኑን በማሳመን፤ ይህንን የማይቀበሉትንም በማስገደድ ከጎኑ እንዲሰለፉና እንዲሞቱ ሲያደርግ ኖሯል።ይህንን ግን መላው የትግራይ ህዝብ ቆም ብሎ ሊያስብ ይገባል፡፡
እንደሚታወቀው ህወሓት ገና በሃምሳ ዓመት ታሪኩ በብዙ ሸፍጦች የተሞላ የሴረኞች ስብስብ ነው።መሪዎቹ በውሸትና በጦርነት አባዜ የተለከፉ ናቸው።ከጦርነት ውጭ የሚያውቁት ቋንቋ የላቸውም።የትግራይ ህዝብ ግን የሺህ ዓመታት አንፀባራቂ ታሪክ ያለው ነው።ከአክሱም ዘመን ጀምሮ የደመቀ የኋላ ታሪክ ባለቤት ነው።በታላቁ የአድዋ ጦርነት ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር በመሆን ለኢትዮጵያ ትልቅ የጥቁር ህዝቦች ድል ያስመዘገበ ህዝብ ነው።ይህ ህዝብ እንደትናንቱ ሁሉ ነገም ይኖራል፤ ህወሓት ግን ታሪክ ሆኖ የሚቀር የጥቂት አፈንጋጮች ስብስብ ነው። የቡድኑመሪዎችም ለትግራይ ህዝብ የሚመጥን ስብእናም ሆነ ቁመና የላቸውም።ገዢ መሆን ያለበት የትግራይ ህዝብ ፍላጎት እንጂ የዚህ ፅንፈኛ ቡድን የስልጣን ጥማት ሊሆን አይገባም፡፡
በተለይ የትግራይ ወጣቶች ይህንን እውነታ በአግባቡ በመረዳት የቀደመውን የትግራይ ህዝብ የደመቀ ታሪክ ላለማበላሸት ቆም ብሎ ማሰብ ይጠበቅባቸዋል።ከፊቱ በርካታ እድሎች እንዳሉ አስቦ በዚህ ቡድን የተሳሳተ ሴራ ተጠልፎ በአጭሩ እንዳይቀጭ ሊጠነቀቅ ይገባል።የትግራይ ወጣት የነገ ተስፋ የተሻለ የሚሆነው ከመላ ኢትዮጵያውያን ጋር በአንድነት ሲቆምና ለጋራ ድል በአንድነት ሲሰለፍ መሆኑን ሊረዳ ይገባል።ስለዚህ የባከኑ ትናንትናዎችን ለማካካስ ቆም ብሎ ማሰብ አለበት።የትግራይ እናቶች እድሜ ዘመናቸውን ሲያለቅሱ እንዲኖሩ የተከፈተውን በርም በመዝጋት ታሪኩን ለማደስ አሸባሪውን ህወሓት ዓላማ ከማስፈፀም ራሱን ማቀብ ይጠበቅበታል፡፡
የአሸባሪው ህወሓት መሪዎች አንደበታቸው እየዋሸ ወደሞት መሄድን ተለማምደዋል።በደሴ ግንባር በነበረው ጦርነት የተማረከው ኮሎኔል ግኡሽ ገብረ እንዳለው ቡድኑ ተስፋ የቆረጠ ቡድን ነው።አብዛኛው የቡድኑ አባላት መሳርያ ያለውን ተከትሎ ይጓዛል።መሳርያ የያዘው ሰው ሲሞት እሱን ተክቶ ለመዋጋት እንዲሄድ ይደረጋል።ይህ በሰዎች ነፍስ መቀለድ ነው።
ቡድኑ የትግራይ ህዝብ የጥቃት ሰለባ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል።በደሴ የተፈጠረውም ይኸው ነው።ቡድኑ አስቀድሞ በደሴ በሰገሰጋቸው ደጋፊዎቹ አማካኝነት የአሸባሪው ቡድን አባላት ደሴ አካባቢ ሲደርሱ ከውስጥ ሆነው ሲጠባበቁ የነበሩና ከደሴ ህዝብ ጋር አብረው የኖሩ አባሎቻቸው ጥቃት እንዲፈጽሙ በማድረግ ህዝቡ የትግራይ ተወላጆችን ሁሉ እንዲጠራጠር ለማድረግ ሰርቷል።ከዚህ አንጻር አብዛኛው ማህበረሰብ በነሱ ፕሮፓጋንዳና ሴራ ቢጠለፍ የሚያደርሰው ጥፋት የከፋ ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡
ከዚህም አልፎ በደረሰባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚፈፅማቸው ግፎችና አረመኔአዊ ተግባራት ኃላፊነት የማይሰማው ስለመሆኑ ደግሞ ደጋግሞ ያስመሰከረው እውነታ ነው።ለዚህ ደግሞ የዛሬ አንድ ዓመት አካባቢ በማይካድራ ከፈፀመው የጅምላ ጭፍጨፋ ጀምሮ በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ በንፁሃን ዜጎች ላይ ያደረሰው ጥፋት ህያው ምስክር ነው፡፡
ይህ ቡድን እነዚህን ሁሉ በደሎች የሚፈፅመው የትግራይን ህዝብ ሙሉ ለሙሉ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠልና ዘላቂ ዋሻው ለማድረግ ካለው ፍላጎት ነው።ቡድኑ አሁን አሁን እንደፈሪ ዱላ ገባ ወጣ እያለ የአጎራባች ከተሞችን ህዝብ እያሸበረ መልሶ በትግራይ ህዝብ ጉያ ውስጥ መወሸቅን ስትራቴጂካዊ ስልት ብሎ መጥራት ጀምሯል።ይህ ግን አዋጭ አለመሆኑን ማሳየት ይገባል።ይህ ቡድን ሞቱ ተቃርቦ እያለ እንኳን የትግራይን ህዝብ አጥፍቶ ለመጥፋት የሚፈጽማቸው ግፎች ታሪክ የማይሽራቸው ናቸው።ስለሆነም ብቸኛው መፍትሄ ይህ ቡድን ዳግም በኢትዮጵያ ውስጥ ጥፋት ለመፈጸም የሚያስችል ቁመና እንዳይኖረው አድርጎ መቅበር ብቻ ይሆናል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 28/2014