የረጅም ርቀትና የአገር አቋራጭ ውድድሮች የምንጊዜም ምርጡ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ ነገ ስምንት ሰዓት ላይ በሚካሄደው የኒውዮርክ ማራቶን ለአሸናፊነት ይጠበቃል። በዓለማችን ታላላቅ ከሚባሉ አምስት የማራቶን ውድድሮች አንዱ የሆነው የኒውዮርክ ማራቶን ነገ ሃምሳኛ ዓመቱን ሲያከብር የኦሊምፒክ የሶስት ወርቅ ሜዳሊያዎች አሸናፊው አትሌት ቀነኒሳ በቀለ የውድድሩ ታላቅ ድምቀት ሆኗል።
የሰላሳ ዘጠኝ ዓመቱ ድንቅ ኢትዮጵያዊ አትሌት በዚህ ውድድር የአሸናፊነት ግምት ማግኘቱ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ አሰልቺና ፈታኝ የሆነውን የማራቶን ውድድር በስድስት ሳምንታት ልዩነት ለመሮጥ መዘጋጀቱ ብዙዎች ያልጠበቁት ነው። ቀነኒሳ ባለፈው መስከረም በበርሊን ማራቶን የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን ለመስበር ከፍተኛ ዝግጅት አድርጎ ወደ ውድድር ቢገባም ያሰበውን ማሳካት ሳይችል ቀርቶ ስድስተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁ ይታወሳል። ይህም በተደጋጋሚ ጉዳቶችን ለሚያስተናግደው አትሌት በስድስት ሳምንታት ልዩነት ማራቶንን በድጋሚ ለመሮጥ ማሰብ ያልተለመደ በመሆኑ ብዙዎች ያልጠበቁት ሆኗል።
ይሁን እንጂ የአትሌቱ የቅርብ ምንጮች ቀነኒሳ ማራቶንን ለአስራ ሁለተኛ ጊዜ ነገ በኒውዮርክ የሚሮጠው ካለፈው የበርሊን ማራቶን ብቃቱ በጣም በተሻለ ብቃት ላይ ሆኖ ለማሸነፍ መሆኑን አመልክተዋል። በተለይም የአትሌቱ ማኔጀር የሆኑት ጆሴ ኸርሜንስ፣ በስድስት ሳምንታት ልዩነት ሁለት ታላላቅ የማራቶን ውድድሮችን መሮጥ ያልተለመደና በታሪክም ያልታየ ክስተት መሆኑን በማስታወስ ቀነኒሳ ግን ባለፈው መስከረም በበርሊን ማራቶን ከነበረው ድንቅ አቋም በመነሳት ባለፉት ሳምንታት ተዘጋጅቶ ኒውዮርክ ላይ ለመሮጥ በጥሩ ብቃት ላይ እንደሚገኝ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ ከሚገጥመው ጉዳት ጋር በተገናኘ ባለፉት ዓመታት ከተወዳደረባቸው ሰባት የማራቶን ውድድሮች ሶስቱን አቋርጦ ለመውጣት የተገደደው ቀነኒሳ በቀለ፣ ከሚገጥሙት ጉዳቶች ፋታ አግኝቶ ባገገመበት አጋጣሚ ውድድሮችን ከማሸነፍ ባሻገር ፈጣን ሰዓቶችን የማስመዝገብ ትልቅ አቅም እንዳለው በበርካታ አጋጣሚዎች አሳይቷል። ለዚህም ለረጅም ጊዜ በጉዳት ከውድድር ርቆ በተመለሰበት የ2019 የበርሊን ማራቶን 2:01:41 የሆነ የማራቶን የዓለማችን ሁለተኛው ፈጣን ሰዓት ማስመዝገብ መቻሉ በጉልህ ይጠቀሳል። ይህም ሰዓት የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ከሆነው የኬንያዊው አትሌት ኢሉድ ኪፕቾጌ ሰዓት በሁለት ሰከንድ ብቻ የዘገየ መሆኑ ይታወቃል።
ቀነኒሳ የማራቶን ሁለተኛው የዓለም ፈጣን ሰዓት ባለቤትና የኢትዮጵያ የርቀቱ ባለክብረወሰን ቢሆንም ባለፈው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያን ወክሎ ለመወዳደር እድል ባለማግኘቱ ትልቅ ቁጭት ፈጥሮበት እንደነበረ ይታወሳል። ይህን ቁጭቱን ባለፈው መስከረም በበርሊን ማራቶን የዓለም ክብረወሰን አሻሽሎ ለመወጣት ያደረገው ጥረትም የተሳካ አልነበረም። ከበርሊን ማራቶን ያልተሳካ ሙከራው በኋላም በትንሽ ጊዜ ልዩነት በአሜሪካ ምድር ለመጀመሪያ ጊዜ በማራቶን ለመሮጥና ለማሸነፍ እድሉን አግኝቷል።
የኒውዮርክ ማራቶን እንደ በርሊን ማራቶን የዓለም ክብረወሰኖች የሚመዘገብበት የተለመደ አጋጣሚ የሚፈጠርበት እድል ጠባብ በመሆኑ ቀነኒሳ በነገው ውድድር ክብረወሰን ለመስበር ይሮጣል ተብሎ አይጠበቅም። ይሁን እንጂ የኒውዮርክ ማራቶን ዳገታማና ቴክኒኮችን የሚጠይቅ እንደመሆኑ ቀነኒሳ ታላቅ ዝናና ስኬትን ያጎናጸፈው የአገር አቋራጭ ውድድሮች ልምዱን ተጠቅሞ ውድድሩን የማሸነፍ ሰፊ እድል እንዳለው ይጠበቃል። ቀነኒሳ በነገው ውድድር ማራቶንን ከ2:06 በታች ማጠናቀቅ የቻለ ብቸኛው አትሌት መሆኑም የአሸናፊነት ግምቱ ቢሰጠው የሚደንቅ አይደለም።
በውድድሩ ላይ በርካታ ልምድ ያላቸው የማራቶን አትሌቶች በተለይም ኬንያውያን ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በተለይም ኬንያዊው የግማሽ ማራቶን ባለክብረወሰን ኪቢዎት ካንዲ ቀላል ተፎካካሪ እንደማይሆን ይጠበቃል። በሌላ በኩል እኤአ በ2015 የቤጂንግ የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና የማራቶን አሸናፊ የነበረው ኤርትራዊው አትሌት ግርማይ ገብረስላሴም ከዚህ ቀደም የኒውዮርክ ማራቶንን ማሸነፍ የቻለ እንደመሆኑ ጠንካራ ተፎካካሪ ይሆናሉ ተብሎ ከሚጠበቁ አትሌቶች መካከል አንዱ ሆኗል። እኤአ ከ1970 አንስቶ መካሄድ የጀመረው የኒውዮርክ ማራቶን ከትንሽ ተነስቶ ዛሬ ላይ በዓለማችን ትልቅ ከሚባሉ አምስት የማራቶን ውድድሮች አንዱ ሆኗል። ባለፈው ዓመት በኮቪድ-19 ምክኒያት በቀጥታ እውቅ አትሌቶች በተሳተፉበት ባይካሄድም ነገ ሃምሳኛ ዓመቱን ሲያከብር በሚካሄደው ውድድር ከሰላሳ ሶስት ሺ በላይ ተሳታፊዎች ይጠበቃሉ።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2014