ነስር ወይም የአፍንጫ መድማት ብዙዎች ላይ የሚከሰት ችግር ነው።በጊዜው ሲፈጠር ቢስደነግጥም፣ በአብዛኛው ከባድ ወይም አስከፊ የሚባል ሁንታን አያመለክትም።ውስጠኛው የአፍንጫችን ክፍል (ከፊት ወይም ከኋላ) ብዙ የደም ስሮች አሉት፤ በጣም ስስ ስለሆኑ በቀላሉ ሊደሙ ይችላሉ።ነስር አዋቂዎች ላይ እና ከ3-10 ዓመት የሆኑ ሕፃናት ላይ የበለጠ ይታያል።ነስርን በሚደሙት የደም ሥር አይነቶች ለሁለት የፊተኛው ነስር እና የኋለኛው ነስር በማለት እንከፍለዋለን።
የፊተኛው የአፍንጫ መድማት በውስጠኛው የአፍንጫ ክፍላችን ከፊት የሚገኙ ደም ሥሮች ተበጥሰው ሲደሙ የሚከሰት ሲሆን የኋለኛው የአፍንጫ መድማት ደግሞ በውስጠኛው የአፍንጫ ክፍላችን ከኋላ ወይም ከሥር የሚገኙት ሥሮች ሲደሙ ነው።በዚህ ጊዜ ደም ወደ ጎሮሯችን ሊሄድ ስለሚችል የኋለኛው የአፍንጫ መድማት አስከፊ ሊሆን ይችላል።
ነስር በምን ምክንያት ሊመጣ ይችላል?
የአፍንጫ መድማት ወይም ነስር ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላል።ድንገት የሚመጣ ወይም ብዙ ጊዜ የማይደጋገም ከሆነ ብዙውን ጊዜ አሳሳቢ ላይሆን ይችላል፤ ነገር ግን ድግግሞሹ ከጨመረ አስቸኳይ የጤና እርዳታ ሊያስፈልግ ይችላል።ደረቃማ አየር የነስር ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል።
ነፋሻማ እና ደረቃማ የአየር ንብረት ላይ የሚኖሩ ሰዎች ለዚሁ የቤት ማሞቂያ የሚጠቀሙ ሰዎች የአፍንጫቸው የውስጠኛው ክፍል በጣም ይደርቃል።ይህ ድርቀት ቀስ በቀስ ሲቀረፍ ወይም አካባቢው ሲቆጣ እና ድንገት ከነካነው ይደማል።የአለርጂ መድኃኒቶች የሚወስዱ ሰዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የውስጠኛው የአፍንጫ ክፍል ስለሚደርቅ እንዲሁ ሊደማ ይችላል።በተደጋጋሚ አፍንጫ ላይ የሚደርስ ምት ወይም አደጋ እንዲሁ የአፍንጫ መድማትን ሊያመጣ ይችላል፡፡
የተለመዱ መንስኤዎች
– አፍንጫ ውስጥ ባእድ ነገር ካለ
– ኬሚካሎች
– አለርጂ
– አፍንጫ ላይ ጉዳት ከደረሰ
– በተደጋጋሚ ማስነጠስ
– አፍንጫን የመጎርጎር ልማድ
– ቀዝቃዛ አየር
– ጉንፋን
– ከፍተኛ የአስፕሪን መጠን መውሰድ
ብዙ ያልተለመዱ የነስር መንስኤዎች
– ከፍተኛ የደም ግፊት
– የመድማት ችግር
– የደም መርጋት
– ካንሰር
ምርመራ፦ ሐኪሞ የአፍንጫዎን ውስጠኛ ክፍል በመሳሪያ በማየት ባእድ ነገር መኖር አለመኖሩን ያረጋግጣል።የተለያዩ ጥያቄዎችን ይጠይቀወታል።እንዲሁም ብዙ የደም ምርመራዎችን በማዘዝ ምክንያቱን ለመለየት ይሞክራል፡፡
ሕክምና፦ የአፍንጫ መድማት ሕክምናው በአይነቶቹ ይለያያል።አንደኛው የፊተኛ የአፍንጫ መድማት ሲሆን በውስጠኛው የአፍንጫ ክፍል ከፊት በኩል ያሉት የደም ሥሮች በተለያየ ምክንያት ሲደሙ የሚከሰት ነው።ይህ አይነት ነስር በቤት ውስጥ መታከም ይችላል።ቁጭ በማለት ስሱን የአፍንጫ ክፍል ጠበቅ አድርጎ መያዝ ይመከራል።የአፍንጫዎ ቀዳዳዎች ሙሉ ለሙሉ መዘጋጃታቸውን ያረጋግጡ፤ ይህንን ቢያንስ ለ10 ደቂቃ ይቀጥሉ።ከዛ በኋላ ትንሽ ወደፊት በማጋደል በአፍዎ ለመተንፈስ ይሞክሩ፡፡
ነስርን ለማቆም በጭራሽ በጀርባዎ እንዳይተኙ።በጀርባ መተኛት ወደ ጉሮሮ እንዲሄድ በማድረግ ጨጓራ እንዲቆጣ ሊያደርግ ይችላል።ከ10 ደቂቃ በኋላ አፍንጫዎን በመልቀቅ መድማት ማቆሙን ያረጋግጡ፤ ካላቆመ ይህንኑ በቅደም ተከተል ይድገሙ።በተጨማሪም ሰርኖ ላይ በረዶ መያዝም ይረዳል።እነዚህን አድርገው ለውጥ ካልመጣ ግን ወዲያው ሐኪሞ ጋር መሄድ ይኖርበዎታል፡፡
ምንጭ፦ ከዶክተር ጤና ፌስቡክ ገፅ
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2014