የበሽታዎችን ውጤት በምርመራ ለማወቅ በጤና ተቋማት ውስጥ ከሚገኙና እጅግ አስፈላጊ ከሆኑ ክፍሎች ውስጥ አንዱ ላብራቶሪ ነው።ይህ ሲባል ታዲያ ላብራቶሪዎች በጤና ተቋማት ውስጥ መኖር ብቻ ሳይሆን ወቅቱ የሚጠይቀውን ቴክኖሎጂ በበቂ ሁኔታ ያሟሉና በበቂ ሁኔታ የተደራጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል።
በተለይ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭት እየተስፋፋ የመጣበት ጊዜ ከመሆኑ አንፃር ለዚህ የሚመጥን፣ በቴክኖሎጂ እና በሰለጠነ ባለሙያ የተሟላ ላብራቶሪ ያስፈልጋል።ወቅቱም የኮቪድ- 19 ቫይረስን የሚመረምሩና ውጤቱን በብዛትና በተቀላጠፈ ሁኔታ የሚያቀርቡ ማሽኖችን ያሟሉ ላብራቶሪዎች እንዲኖሩ የሚጠይቅበት ነው።
በኢትዮጵያም በሁሉም ክልሎች በሚገኙ ጤና ተቋማት ውስጥ በሽታዎችን የሚመረምሩ ላብራቶሪዎች አሉ።ይሁንና ላብራቶሪዎቹ ከተደራሽነት፣ አገልግሎት ስፋት፣ ጥራትና አቅም አንፃር ከቦታ ቦታ ይለያያሉ።በአገሪቱ የተከሰተውን የኮቪድ- 19 ወረርሽኝን ተከትሎ ግን የተወሰኑ ላብራቶሪዎች ለዚሁ ምርመራ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርጓል።
በአዲስ አበባም የተወሰኑ ትላልቅ ሆስፒታሎች ከሚሰጡት መደበኛ የላብራቶሪ አገልግሎት በተጨማሪ የኮቪድ-19 ምርመራንም እንዲያደርጉ በአዲስ መልክ ተደራጅተዋል።የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ ደግሞ ከዚህም በላይ ሄዷል ይሉናል በሆስፒታሉ የላብራቶሪ ዳይሬክተር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃነ መስቀል ተገኔ ።
ዳይሬክተሩ እንደሚናገሩት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚገኘው የሕክምና ላብራቶሪ ቀደም ሲል የነበረውን አሰራር በማሻሻል ወደ ዘመናዊነት እንዲቀየር ተደርጓል።ወደ ሞሎኪዩላር የምርመራ ቴክኒክም ተሸጋግሯል።
በሌላ አባባል ላብራቶሪው የባክቴሪያዎችን ዲ ኤን ኤ እና አር ኤን ኤ በመለየትና በማባዛት የኤፓታይተስ ቢ፣ሲ፣ ኢ፣ኤ፣ የማህፀን ጫፍ በር ካንሰር፣ ሳይቶሜጋሎ ቫይረስ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ቲዩበር ክሎዝስ፣ ኮቪድ- 19 ቫይረስን ለመለየት የሚያስችለውን መመርመሪያ ማሽን አስገብቷል።አቅሙን ማሳደግና ለማሽኑ አስፈላጊ የሆኑ ሬኤጀንቶችን /የኬሚካል ለውጥ የሚያመጡ አዋጆችን/ ማሟላት ከተቻለ ደግሞ ከዚህም በላይ ምርመራዎችን ለማከናወን ያስችላል።
ማሽኑ 4 ሚሊዮን ብር ዋጋ ያለው ሲሆን ሬቲና ፋርማሲዮቲካል ከተሰኘው የአገር ውስጥ ኩባንያ ጋር በመተባበር ሮች ከተሰኘ የሲውዘርላንድ ኩባንያ በነፃ የተገኘ ነው።በዚሁ ማሽንም እስከ ሃያ የሚሆኑ የጤና ባለሞያዎች ይሰራሉ። በላባራቶሪ ክፍሉ ውስጥም ባጠቃላይ 200 የሚጠጉ ሠራተኞች ይገኛሉ።ይህንኑ ማሽን ታሳቢ በማድረግም የሆስፒታሉ ላብራቶሪ ሙሉ በሙሉ በአዲስ፣ ዘመናዊ፣ ሁሉን በሚያሳትፍና የሥራ አካባቢው ለሠራተኞችና ታማሚዎች በሚመች መልኩ እንዲስተካከል ተደርጓል።
በሽታዎችን መርምሮ ማወቅ ብቻ ሳይሆን ታማሚው መድኃኒት ከጀመረ በኋላ መድኃኒቱ በምን ያህል ደረጃ በሰውነቱ ላይ አልያም በበሽታው ላይ ተፅእኖ እያሳደረ እንደሆነ የሚቆጣጠር በመሆኑ መመርመሪያ ማሽኑ ከሌሎች ማሽኖች ልዩ ያደርገዋል።የመድኃኒት ብግርነትን ወይም ደግሞ የመድኃኒቶችን በጀርሞች መለመድን መቆጣጠሩም የተለየ ያደርገዋል።
በተለይ ደግሞ ማሽኑ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣውን የኤፒታይተስ ቢ ህመምተኞች በዚህ በሽታ ከተያዙ በኋላ መድኃኒት ለመጀመር የሚያስፈልጋቸውን ምርመራ ለማካሄድና በጉበታቸው ላይ ያለውን የቫይረስ መጠን ለማወቅ ይረዳል።መድኃኒት ከተጀመረ በኋላም ቫይረሱ እየቀነሰ ስለመሄዱ ለማረጋገጥ ያግዛል።
ማሽኑ በአንድ ጊዜ ብቻ እስከ 1 ሺ ምርመራዎችን የማድረግ አቅም ያለው ሲሆን ሁሉንም በሽታዎች ይመረምራል።የተወሰኑ ሬጀንቶች አልተሟሉም እንጂ ማሽኑ በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።ከውጭ አገር በመጡ ሰዎችም ማሽኑን የሚያንቀሳቀሱ ባለሙያዎች ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ በሆስፒታሉ አዲስ የገባው የላብራቶሪ ማሽን ዘመናዊነትን የተላበሰ የላይብራሪ አገልግሎት ለታማሚዎች በመስጠት ረገድ አስተዋፅኦ የጎላ ነው።በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው የበሽታዎች ምርመራ ውጤት መስጠት የሚችል መሆኑም ጥቅሙን ከፍ ያደርገዋል። አንድ ህመምተኛ ደም ሰጥቶ ውጤቱን እስከሚያውቅበት ጊዜ ድረስ የሚፈጀውን ጊዜም በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሳል።በተለይ ደግሞ ወደ ውጭ አገር ናሙና ልኮ ውጤቱን ለመቀበል የሚፈጀውን ጊዜ በማሳጠር ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
በሌላ በኩል ደግሞ እንደ አገርም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ወደ ውጭ አገር ናሙና በመላክ ለምርመራ የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት ረገድ የማሽኑ ሥራ መጀመር ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።የሕክምና ባለሙያዎችም በሚፈልጉት ፍጥነት የምርመራ ውጤቱን እንዲያገኙና ለታማሚው ውጤቱን ለማድረስ ያስችላቸዋል።ከሁሉ በላይ ደግሞ የምርመራ ውጤት ጥራት አስተማማኝነትን በመጨመር ረገድ ፋይዳው የጎላ ነው።በጥቅሉ ማሽኑ የሆስፒታሉን የላብራቶሪ አገልግሎት አንድ እርምጃ ወደፊት አራምዶታል።ሞዴልም ሪፈራል ላብራቶሪ ለመሆንም በቅቷል።
ዳይሬክተሩ እንደሚሉት ይህ በሆስፒታሉ የላብራቶሪ አገልግሎት ላይ የተከናወነ አንድ እርምጃ ቢሆንም በቀጣይ ተከታታይነት ያላቸው ሥራዎች በላብራቶሪው ውስጥ ይከናወናሉ።በተለይ ደግሞ ወደ ውጭ አገር ተልኮ የሚሰራውን የአባትነትና የእናትነት መለያ ምርመራ /ፓተርኒቲ ቴስት/ ወይም ዲ ኤን ኤ ምርመራና ለኩላሊት ንቅለ ተከላ የሚያስፈልጉ ቅድመ ምርመራዎችን /ኮምፓቴቢሊቲ ቴስት/ በአገር ውስጥ ለማከናወን በእቅድ ተይዟል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2014