ትውልድና እድገታቸው ቢሾፍቱ ከተማ ነው። የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉትም እዛው ከተማ በሚገኘው ሐረር ሜዳ ሞዴል በተባለ ትምህርት ቤት ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በተፈጠረው የፖለቲካ ችግር ምክንያት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ሳይገቡ ቀሩ። ከልጅነታቸው ጀምሮ ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር ነበራቸው። ይህ የሙዚቃ ፍቅር ታዲያ ጊታርና ኪቦርድ የመሳሰሉትን ዘመናዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች ወደ መጫወት አደገ። እናም ከጓደኞቻቸው ጋር ባንድ አቋቁመው የተለያዩ ከተሞች እየተዘዋወሩ ሙዚቃ መጫወት ጀመሩ።
በዚሁ የሙዚቃ ሙያቸውና በሰዓት ተቆጣጣሪነት ሞጆ በሚገኘው ኢትዮ-ጃፓን ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ተቀጠሩ። ከፋብሪካው ሥራቸው በተጓዳኝ በተለምዶ አየር በአየር የሚባለው የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርተውም ነበር። በኋላም የአየር በአየሩ ሥራ ከፋብሪካው የተሻለ ጥቅም እያስገኘላቸው ሲሄድ ሙሉ ትኩረታቸውን ንግዱ ላይ አደረጉ። ወደ የመንና ሌሎች ጎረቤት አገሮች እየተዘዋወሩ እቃ ማስመጣትና የመሸጥ ሥራቸውን አቀላጥፈው ተያያዙት። የንግድ ሥራቸው ለጥቂት ዓመታት እየጎለበተ እንደመጣ ግን በአገሪቱ የሥርዓት ለውጥ ተከሰተ። በተለይም ሕወሓት መራሹ መንግሥት አገሪቱን መቆጣጠሩን ተከትሎ ሥራቸው እንደቀድሞው ውጤታማ አልሆን አላቸው።
እንግዳችን ምንም እንኳን ከመንግሥት የፖለቲካ ችግር ባይኖርባቸውም አገሪቱን የተቆጣጠረው የአዲሱ መንግሥት አካሄድ አላምር አላቸው። በመሆኑም በአጋጣሚ ያገኙትን ጣሊያን የመሄድ እድል ለመጠቀም አላቅማሙም። ከዚያም አልፈው እዛው ለመቅረት ወሰኑ። ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በቆዩባት ጣሊያን እንደእሳቸው ላለ ጥቁር አፍሪካዊ አይቻልም የተባሉ ሥራዎችን ሁሉ በድፍረት በመሥራት ስኬታማ ሥራ ማከናወን ስለመቻላቸው የሚያውቋቸው ሁሉ ይመስክሩላቸዋል።
ከሰሩባቸው ተቋማት መካከልም የኮምፒውተር ኩባንያ፤ የእንጨት ኢንዱስትሪ፤ የራግቢ ስፖርት ክለብ ተጠቃሽ ናቸው። ተቀጥረው ከሚሰሩበት ሥራ ባሻገር በርካታ የጣሊያን ከተሞችን በብስክሌት በመዞር ለዓለም ሕዝብ ሰላምና ፍቅርን በመስበክ በተሰደዱባት አገር ከፍተኛ እውቅናን አግኝተውም ነበር። በተለይም ወቅቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት የሚካሄድበት ስለነበር ‹‹ሠላም በዓለማችን ይስፈን›› በሚለው መፈክራቸው በብዙ የውጭ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ለመሆን በቅተዋል። እዚህም በታዋቂው ኮሜዲያንና የኪነጥበብ ሰው አለባቸው ተካ ይካሄድ በነበረው ‹‹አለቤ ሾው›› የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ እንግዳ ሆነው ቀርበውም ነበር።
እንግዳችን እንደብዙዎቹ ዲያስፖራዎች ‹‹ፖለቲካው አልተመቸኝም›› ብለው ከሚወዷት ርቀው መኖር አላስቻላቸውም። ይልቁንም መለስ ቀለስ እያሉ ያሳደጋቸውን ማህበረሰብ ይጎበኛሉ፤ ይጠይቃሉ። ታዲያ ወደ ኢትዮጵያ በመጡ ቁጥር የሕዝባቸውን ችግር አይተው ብቻ አይመለሱም፤ የጣሊያኖችን በር በድፍረት እያንኳኩ እርዳታ ያሰባስባሉ። በርካታ የበጎ አድራጎት ሥራዎችን በማከናወን በብዙዎች ዘንድ ምስጋና እና እውቅና ተችረዋል። ከእነዚህም ውስጥ ለቦክስ ስፖርት ፌደሬሽን እና ለምኒልክ ሆስፒታል ያደረጉት ድጋፍ ተጠቃሽ ነው።
የዛሬው የዘመን እንግዳችን ካለፉት ሰባት ዓመታት ወዲህ ወደአሜሪካ ሄደው ትዳር መስርተው በመኖር ላይ ነው የሚገኙት። ወደ አሜሪካ ከገቡ በኋላም አገራቸውንና ህዝባቸውን ከመደገፍ ወደኋላ አላሉም። ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ለሌሎች አገር አቀፍ ፕሮጀክቶች በሚደረጉ የገንዘብ ድጋፎች ሁሉ በማሳተፍ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር በማረጋገጥ ላይ ናቸው። በቅርቡ ደግሞ ኢትዮጵያ ያጋጠማትን ዓለም አቀፍ ጫና በመቃወም ከሌሎች ዲያስፖራዎች ጋር የተለየያ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።
ከዚሁ የድጋፍ እንቅስቃሴ ጋር በተያየዘም ከሰሞኑ ወደ አገራቸው ገብተዋል። አዲስ ዘመንም ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም እንግዳ አድርጎ ጋብዟቸዋል። የዛሬው እንግዳችን የሠላምና አንድነት ለኢትዮጵያ የዲሲ ግብርሃይል ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ጥበበ ታደሰ ናቸው። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በቅድሚያ ትንሽ ስለበጎ አድራጎት ስራዎቾት ይንገሩንና ውይይታችንን ብንጀምር?
አቶ ጥበበ፡- በመሠረቱ የበጎ አድራጎት ሥራ ማንኛውም ጤነኛ የሆነን ሰው የሚያስደስት ተግባር ነው። እኔ ከአገሬ ስለወጣሁ ያሳደገኝን ደሃ ሕዝብ የምረሳ ሰው አይደለሁም። ወደ አገሬ በመጣሁ ቁጥር በአቅሜ የምችለውን ለመርዳት ጥረት ሳደርግ ነው የኖርኩት። ደግሞም በመጣሁ ቁጥር የማየው ነገር ሁሉ ልቤን የሚሰብርና የሚያሳዝን ስለነበረ በራሴ አቅም ችግሮቹ እንዲፈቱ እጥር ነበር። ለምሳሌ ባነሳልሽ ከአገሬ ከወጣሁ ከስድስት ዓመት በኋላ ተመልሼ በመጣሁበት አጋጣሚ የቦክስ ስፖርት ፌደሬሽንን የማየት እድል አግኝቼ ነበር።
በወቅቱ ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም ላይ የሚወዳደሩ የቦክስ ስፖርተኞች በሚያሳዝን ሁኔታ የጥርስ መጋጫ የሚጠቀሙት እርስበርስ እየተዋዋሱ ነበር። በወቅቱ ደግሞ ኤች.አይ.ቪ ኤድስ በእጅጉ የተስፋፋበት ጊዜ ነበር። ሆኖም የጥርስ መጋጫውን ይጠቀሙት የነበረው አንዱ ተጠቅሞ እንደጨረሰ በአልኮል ብቻ እየጠረጉት ነው። ይህንን ስመለከት ማልቀስ ነው የቃጣኝ። እነዚህ ልጆች ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም አደባባይ የሚቀርቡ ስፖርተኞች ናቸው። መንግሥት ታዲያ በወቅቱ ምንም አይነት በጀት አይመድብላቸውም ነበር። ሁሉም ስፖርቶች ጋር ስትሄጂም ተመሳሳይ ችግር ነው የነበረው።
ይህንን ችግር አይቼ ግን ዝም አላልኩም፤ ወደምኖርበት ጣሊያን አገር እንደተመለስኩኝ በወቅቱ ታዋቂ የነበረውን የጣሊያን እግር ኳስ ተጫዋች ሮቤርቶ ባጂዎን አነጋግሬ የኢትዮጵያን ስፖርት እንዲደግፉ ብዙ ጥረት አደረኩኝ። ግን በወቅቱ የነበረው መንግሥት ኢትዮጵያን የሚደግፍ ባለመሆኑ ሞራሌ ተነክቶ በግሌ ማድረግ የምችለውን ነገር አድርጊያለሁ። ለዚህም ከተለያዩ ተቋማት ሰርተፊኬት አግኝቻለሁ። እንዳልኩሽ ከራሴና ከጓደኞቼ ገንዘብ በማሰባሰበ መጋጫዎችን፤ ትጥቆችን፣ ብስክሌቶችን በብዛት አምጥቼ የበኩሌን አስተዋፅኦ አድርጌ ነበር። ግን ደግሞ እዚህ በሕወሓት መንግሥት ያገኘሁት ምላሽ በጣም አስቀያሚ ነበርና ብዙ ተስፋ ወደመቁረጥ ገብቼ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ይህንን ሲሉ ምን ማለቶ ነው?
አቶ ጥበበ፡- እኔ ተወልጄ ያደኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ የምሰራውም ለኢትዮጵያ ነው። ለግሌ ብሔር ወይም ክልል ብዬ ለይቼ የማደርገው ነገር የለም። እነሱ ግን የማመጣውን እርዳታ ሁሉ እነሱ ወደሚፈልጉት ክልል ብቻ እንዲደርስ ይፈልጉ ነበር። ብዙዎች እንደሚያውቁት ምኒልክ ሆስፒታል ከ100 ዓመታት በላይ የቆየ አንጋፋ የህክምና ተቋም ነው። በአጋጣሚ ሆስፒታሉን ሊረዳ ይችላል ብዬ ጥቂት መድሃኒቶችን ይዤ መጥቼ አስረክቤ ነበር። የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ስምንት ጣሊያናዊ ጓደኞቼን ይዤያቸው መጥቼ አገሬን አስጎብኚቻቸው ነበር። በህክምና በኩል አንዳንድ ችግሮች እመለከት ስለነበር በተለይ የስኳርና የኮሌስትሮል መድሃኒት እጥረት እንደነበር ስለማውቅ እነዚያንም እግረ መንገዴን ይዤ መጥቼ ነበር።
በመስቀል ማግስት የቱሪዝም ቀን ስለነበር ከጣሊያኖች ጋር ይዘን የመጣነውን መድሃኒት ለምኒልክ ሆስፒታል አመራሮች አስረከብን። በወቅቱ ሆስፒታሉን ጎብኝቼ አልቅሼ ነው የወጣሁት። ይህንን የምልሽ እኔ የሰለጠነ ዓለም ስለኖርኩኝ አይደለም፤ ግን በወቅቱ ሆስፒታሉ የሰው ልጅ ቀርቶ እንስሳትም የሚታከሙበት አይመስልም ነበር።
እኛ በጎበኘንበት ወቅት የነበረው ከ100 ዓመት በላይ ያገለገለ አልጋና የህክምና መሳሪያ ብቻ ነው። መኝታ ቤቶቹም ሆነ የህክምና መስጪያ ክፍሎቹ ሽታ ሊገለፅ በማይችል መልኩ ከባድ ነበር። የሚገርምሽ እኛ እንኳን ያየነው አንደኛ ማዕረግ የተባለው ክፍል ንፅህና በጣም የሚቀፍ ነበር። የዛገ የሽንት ቤት መቀመጫና መታጠቢያ ያሉት፣ ለመፀዳዳት እንኳን የምትጠየፊውአይነት ነበር። ወደ ኦፕሬሽን ክፍል ሲወስዱኝ በተመሳሳይ የሚጠቀሙበት መሳሪያ በድንጋይ የተደገፉ ኋላቀር ቁሳቁስ መሆኑን ተመለከትን።
በነገራችን ላይ ያንን ሆስፒታል እንድረዳ ከፍተኛ ግፊት ያደረብኝ የሆስፒታሉ አመራር ዶክተር አለማየሁ የተባለ ሰው ነበር። ዛሬ ላይ የዚያ ሰው አድራሻ ጠፍቶብኛል፤ በዚህ አጋጣሚ በእናንተ ጋዜጣ አማካኝነት ባገኘው ደስ ይለኛል። እናም ሆስፒታሉን ጎብኝቼ ከወጣሁ በኋላ ምንም አይነት ቃል ባልገባላቸውም በቀጥታ ጣሊያውያኑን ጓደኞቼን ሰብስቤ የእናንተ አያቶች የእኛን ሕዝብ ጨፍጭፈዋል፤ በድለዋል፤ የእናንተ ትውልድ ደግሞ በዚያ ነገር እንደሚያፍር አውቃለሁኝ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ያንን ስለማያውቅ ለዚያ ህዝብ በጎ ነገር በመስራት መልካምነታችሁን አሳዩን አልኳቸው።
እንዳልኳቸውም ምኒልክ ሆስፒታል መጥተው ከጎበኙ በኋላ ከእኔ በላይ ነው አልቅሰው የወጡት። ወዲያው የመረጃ መረብ ለኢትዮጵያ ተከፍቶ በሚገርም ሁኔታ ትልቅ ገንዘብ ተሰብስቦ 230 የሚሆኑ ዘመናዊ አልጋዎች መግዛት ችለናል። ዛሬ ሄዳችሁ ብትጎበኚ የምታገኙት እነዚህን አልጋዎች ነው። የምኒልክ ሐውልት ከጥሻ ውስጥ ወጥቶ በጣሊያና ኢንጂነሮች እድሳት ተደርጎለታል።
ወደጠየቅሽኝ ጥያቄ ስመለስ በወቅቱ በነበረው መንግሥት በዜግነቴ ባደረኩት የበጎ ሥራ ከማመስገን ይልቅ ‹‹ለምን ምኒልክ ሆስፒታልን በተለየ መልኩ ለመርዳት ፈለግህ?›› የሚል ጥያቄ ነው ያቀረበልኝ። ይቅርታ አድርጊልኝና እኔ ዶክተር ዐቢይን የምወደው ዛሬ ላይ ቢሆን እኔ ያንን ሥራ የሠራሁት እንዲህ አይነቱን ከንቱ ጥያቄ የሚጠይቅ ሰው ባለመሆኑ ነው። ከዚያ ይልቅም በጣም እንደሚደሰትና እንደሚያበረታታኝ አልጠራጠርም። የሕወሓት መሪዎች ግን በበጎ ሥራዬ ‹‹ለምን?›› ብለው ማፋጠጥን ነው የመረጡት። ይባስ ብለው ያለምንም ሃፍረት ‹‹ለምን ወደመቀሌ መጥተህ አትሰራም?›› የሚል ዘረኛ ጥያቄ ነው በግልፅ ያቀረቡልኝ። እኔም በወቅቱ አልተቃወምኳቸውም፤ ግን ደግሞ ሁለት እግር ስላለኝ ሁለት ዛፍ ላይ አልወጣም፤ በቀጣይ መቀሌም ሆነ ባሌ እየሄድኩኝ አቅሜ በፈቀደ መጠን እረዳለሁ የሚል ምላሽ ነው የሰጠኋቸው። አየሽ በዚያን ጊዜ ቢያበረታቱኝ ኖሮ ብዙ ነገር ማድረግ እችል ነበር።
ከዚያ በተጨማሪ ቢሾፍቱ እኔ በተማርኩበት ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ ኮምፒውተር ያስገባሁት እኔ ነኝ። እንዲሁም ከጎኑ ያለው መዋዕለ ህፃናት ትምህርት ቤትን እነዚያን ጣሊያኖችን አሳይቼያቸው ነበር። በወቅቱ ታዲያ ህፃናቱ የተቀዳደ ልብስና ጫማ ለብሰው ለእኛ አቀባበል ለማድረግ መዝሙር ሲዘምሩ ያዩት ጣሊያኖቹ ክፉኛ ልባቸው ተነካ። በተለይም ህፃናቱ ፀሐይና ቁሩ እየተፈራረቀባቸው የሚማሩት ዛፍ ስር መሆኑን የተገነዘበው አንዱ ጣሊያናዊ ባለሃብት በሁኔታው በጣም አዝኖ ቁጭ ብድግ እያለ አለቀሰ። ያ ሰውዬ ግን አልቅሶ አልቀረም፤ አምስት ክፍል ቤት በራሱ ወጪ አስገንብቶ ዛሬ ላይ በርካቶች እየተማሩበት ይገኛል። በአጠቃላይ እኔ የበጎ ሥራዎችን ለአገር ማድረግ በጣም ያስደስተኛል።
አዲስ ዘመን፡- በሙዚቃውስ ለምንድነው ገፍተው ያልሄዱት?
አቶ ጥበበ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው ያነሳሽው፤ እኔ ወደ ጣሊያን ከገባሁኝ በኋላ ከተወሰኑ ልጆች ጋር ባንድ አቋቁመን አንዳንድ ሥራዎችን ጀምረን ነበር። በመሠረቱ እኔ እዚህ እያለሁም ቢሆን ሙሉ መሳሪያ ነበረኝ። ‹‹ሆራ›› የሚባል ባንድ ነበረኝና በጣም ብዙ ቦታዎች እየዞርን እንሰራ ነበር። የሚገርምሽ እነፀሐዬ ዮሐንስ፤ አረጋኸኝ ወራሽና ሌሎችም በወቅቱ የነበሩ ሙዚቀኞች እኔ ቤት ነበር ልምምድ የሚያርጉት። ለምሳሌ የፀሐዬ ‹‹ማን እንደ እናት፤ ማን እንደ አገር›› የሚለው ሙዚቃው እኔ ቤት ነው የተቀናበረው። እኔም ብሆን በዋናነት ሊድ ጊታር ብጫወትም ኦርጋንና ሌሎችንም መሳሪያዎች እጫወታለሁ። ከዚያ በኋላ ግን መሳሪያዎቹ ቢኖሩኝም የመጫወቻ ጊዜ አጣሁና ከሙዚቃው እየራቅሁኝ መጣሁ። አሁን ላይ ደግሞ ሙዚቃ እየተሰራ ያለው በኮምፒውተር እየተቀናበረ በመሆኑ ብዙም ወደዚያ የመመለስ ፍላጎት የለኝም።
አዲስ ዘመን፡- አሁን ደግሞ ወደ ፖለቲካው ልመልሶት፤ ሕወሓት መራሹ መንግሥት የአገሪቱን ሕዝብ በብሔርና በቋንቋ በመከፋፋል የዘረጋው የፖለቲካ ሥርዓት ያስከተለውን ጉዳት ሲያስቡ እንደ አንድ አገር ወዳድ ዜጋ ምን ይሰማዎታል?
አቶ ጥበበ፡- የነበረው የፖለቲካ ሥርዓት አይደለም እዚህ ላለው ሕዝብ በውጭ ተሰደን ለነበርነው ዜጎችም በጣም ከባድና ከፋፋይ እንደነበር ይታወቃል። በዚህ የተነሳ ብዙዎች ሥርዓቱን ጠልተው ከአገራቸው ርቀው ለመኖር ተገደውም ነበር። በአጠቃላይ አገሪቱና ሕዝቦቿ አሁን ለገጠማቸው ከባድ የሕልውና ፈተና መንስኤ ያ ከፋፋይ ሥርዓት መሆኑን አምናለሁ።
ለዚህም ነው የዶክተር ዐቢይ መምጣት ብዙዎቻችን የተቀበልነው። እርግጥ እኔ ዶክተር ዐቢይ ሲመጡም ቶሎ ለማወደስም ሆነ ለማመስገን አልወጣሁም። ምክንያቱም በተፈጥሮዬ ቸኩሎ ማመስገንና በኋላ መተቸት አልወድም። እናም ቀስ በቀስ የሰውዬውን ትክክለኛ ማንነት እየተረዳሁ በመጣሁ ቁጥር ቀድመው ካመሰገኗቸው በላይ ቀንደኛ ደጋፊያቸውና ወዳጃቸው ሆኜአለሁኝ። በየጊዜው በሚሰሩት ሥራ ይህችን አገር ወደ መልካም አቅጣጫ ይወስዷታል የሚል እምነት አደረብኝ። አሁን ላይ እኔ ቁጥር አንድ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊ ነኝ። እሳቸውን በመደገፌም ፈርቼም፤ አፍሬም አላውቅም።
አዲስ ዘመን፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩን በዚህ ደረጃ ለማመን ያስቻሎት የተለየ ምክንያት ካለ ቢጠቅሱልኝ?
አቶ ጥበበ፡- ይቅርታ አድርጊልኝና እኔ እሳቸውን የምጠላበት አንድ ነገር ምረጥ ብትዬኝ ነው የማላውቀው። በነገርሽ ላይ ‹‹እስከነስህተታቸው›› የሚባል አባባል አለ፤ እኔ ግን የትኛው እንደሆነ ስህተታቸው አልገባኝም። እንዳልኩሽ ደግፌ ቶሎ አልወጣሁም፤ ከደገፍኳቸው በኋላም አሁንም ድረስ በአቋሜ ፀንቼ ቆይቻለሁ። እነዚያ ሲደግፏቸውና ‹‹ለምን ሰልፍ አትወጣም?›› ብለው ሲጨቀጭቁኝ የነበሩት ሰዎች አሁን አንድ ቁጥር ተቋዋሚ ሆነው በሌላ ጎራ ተሰልፈው ነው ያሉት።
በእኔ እምነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደፊት እንዲሄዱ አጠገባቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል። በሌላ በኩል ዶክተር ዐቢይ ለእኔ ታናሼ እንደመሆናቸው እንደታላቅነቴ ልደግፋቸው ግድ ይለኛል። ምክንያቱም ትልልቅ ነን የምንል ሰዎች ዛሬ ላይ ሳንደግፋቸው ብንቀር ነገ ጠዋት ከተጠያቂነት አናመልጥም። ለምሳሌ ወለጋ ላይ ለተፈጠረው ነገር አንዳንዶች ‹‹እሱ ራሱ ነው የሚያስጨፈጭፈው›› ይላሉ። ለእኔ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ከያዙት በላይ ሥልጣን ያለ ስለማይመስለኝ ይህንን ለማድረግ የሚያስገድዳቸው አለ ብዬ አላምንም። ምንአልባት የተሻለ ሥልጣን ቢኖር ኖሮ ለዚያ ሲሉ ሰው ‹‹አስጨፈጨፉ›› ብንል ተቀባይነት ይኖረን ነበር፤ እውነታው ግን ይሄ አይደለም።
በሌላ በኩል አሜሪካም ሆነ በሌሎች የአውሮፓ አገራት ሰዎች በየቀኑ ይገደላሉ። በእነዚያ አገራት በየቀኑ ለሚገደሉት ሰዎች ሁሉ መንግሥት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ ተጠያቄ ተብለው በሰዎች ሲከሰሱ፤ ሲወነጀሉ አናይም። ሁሉም በተዋረድ ያለው ኃይል ነው ሃላፊነቱን መወጣት ያለበት። እነዚህ ሰዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቤተመንግሥት ወጥተው ወለጋ ላይ እንዲዋጋላቸው የሚፈልጉ ከሆነ ሊሆን እንደማይችልና ከአገር መሪ የማይጠበቅ መሆኑን ሊገነዘቡ ይገባል። ይልቅ ወያኔ ይህንን ሁሉ ሕዝብ እየጨፈጨፈ ያለው ያጣውን ሥልጣን ለማስመለስ ነው። ስለዚህ በየቦታው ለሚፈጠረው ነገር ሁሉ ተጠያቂ ሊሆን የሚችለው ወያኔ ነው። በአጠቃላይ ዶክተር ዐቢይ በእጃቸው የያዙትን ስልጣን ሰው እያስጨፈጨፉ ሕዝብ እንዲጠላቸው ያደርጋሉ ብዬ አላምንም።
ለእኔ ዶክተር ዐቢይ እስካሁን ያሳዩን ነገር አገራቸውን መለወጥ የሚሹ መሪ መሆናቸውን ነው። በተለይም በሌሎች አገራት አይተው የቀኑባቸውን ልማቶችና ቴክኖሎጂዎች ወደ አገራቸው ለማምጣት ደፋ ቀና የሚሉ ብርቱ ሰው እንደሆኑ ነው የማውቀው። እንደደርግ በመሳሪያ አስፈራርተው ሳይሆን ችግኝ ትከሉ ያሉን ራሳቸው በመትከል ነው። ከቤተመንግሥት ጀምሮ በመላው አገሪቱ ያከናወኑት የፅዳትና የእድሳት ሥራ ወደፊትም ቢሆን ታሪክ የሚያነሳቸው ባለውለታ ናቸው። አንዳንዶች ግን እሳቸው ችግኝ እየተከሉ ሰው ሲገደል ዝም እንዳሉ ይናገራሉ፤ ግን ይህንን የሚናገረው ሰው ራሱ ቢሆን ምንም ሊያደርግ እንደማይችል አውቃለሁ። ምክንያቱም እኔ ጣሊያን አገር ለ60 ሰዎች ያሉበትን ማህበር እንኳን መምራት ምን ያህል ፈታኝ እንደሆነ ፕሬዚዳንት ሆኜ አይቼዋለሁ። ስለዚህ 110 ሚሊዮን ሕዝብን መምራት እንዴት ሊከብድ እንደሚችል ማወቅ አይከብድም።
የእኛ ሰው ሌላው በሠራው መልካም ሥራ ራሱን ማሳየትና መድመቅ የሚፈልግ ነው። ሲጎድልና ችግር ሲያጋጥም ደግሞ ለመክሰስ የሚቸኩል ነው። ከማገዝ ይልቅ በእያንዳንዱ እርምጃሽ ድንጋይ የሚያስቀምጠው በርካታ ነው። አማራው ‹‹አሮሙማ አደረጉብን›› ይላል። ኦሮሞው ‹‹አማራማ›› ሊያደርጉብን ነው ይላል።
ታዲያ እኚህ ሰውዬ ከየትኛው ይሁኑ? እኔ ግን ለላፉት ሶስት ዓመታት በሙሉ ‹‹ኢትዮጵያ›› ሲሉ ብቻ ነው የሰማሁት፤ ለኢትዮጵያም ዋጋ ሲከፍሉ አይቻለሁ። ለአንድ ብሔር የተለየ ነገር ለማድረግ ሲጥሩ አላየሁም። ይልቅ የእሳቸውን ሃሳብ ደግፈን ብናግዛቸው ነው ለአገራችን ለውጥ ልናመጣ የምንችለው። እነዚህ የሚተቿቸው ሰዎች አንድ ነገር ለሕዝባቸው አድርገው አያውቁም። እኛ እንኳን በምናሰበስበው ድጋፍ ትንሽ አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ሲጠየቁ በየነገሩ ምክንያት የሚፈጥረው ሰው ቁጥሩ ቀላል አይደለም።
በመሆኑም እኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬም ሆነ ወደፊት ሰው የፈለገ ቢለኝ እደግፋቸዋለሁ። ይህንን የማደርገው ግን ለእኔ ብዬ ሳይሆን ለልጆቼ ብዬ ነው። እኚህ ሰው ኢትዮጵያን የተሸከሙ ሰው ናቸው፤ ስለዚህ እንዳይወድቁ ሁላችንም ባለን አቅም ሁሉ ልንደግፋቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ። ቢያንስ ይህችን አምስት ዓመት እንያቸው፤ ከዚያ በኋላ መቃወም ብንጀምር ብዙም አይገርምም።
እስካሁን ድረስ ግን ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወኑ አይተናል። የደካሞችን ቤት አፍርሶ ከመገንባት ጀምሮ ከተሞቻችን ለመኖር ምቹና የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ በአጭር ጊዜ ያሳዩት ነገር ሊደነቅ ነው የሚገባው። በአጠቃላይ ለእኔ ጉብዝና ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሠሩትን በየማህበራዊ ሚዲያው ማንቋሸሽ ሳይሆን ልክ እንደእሳቸው ለሕዝብ የሚጠቅም ሥራ ሰርቶ ማሳየት ነው።
አዲስ ዘመን፡- እንደሚታወቀው አሸባሪ የሕወሓት ቡድን በሕዝብና በመንግሥት የተሰጠውን በሠላም የመኖር እድል ባለመቀበል አገሪቱ ወደ ውጥንቅጥ እንድታመራ ያደረገበት የተለየ ምክንያት አለው ብለው ያምናሉ?
አቶ ጥበበ፡– እኔ ይህ ለውጥ ከመምጣቱ በፊትም ሕወሓትን በኃይል ከማስወገድና እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የዘረፉትን ሃብት እንደያዙ ይቅርታ ጠይቀው በምህረት የሚኖሩባት አገር እንድትፈጠር ነበር ምኞቴ። ያለፈውን ሁሉ በይቅርታ በመተው ሁሉም ሰርቶ
የሚያድግባት አገር እንድትኖረን ነበር የምፈልገው። የተመኘሁት አልቀረም፤ ፈጣሪ እንደዚያ አይነት መሪ ሰጠን። ግን ምን ዋጋ አለው፤ እነዚህ ሰዎች ይህንን እድል ሊጠቀሙበት አልፈለጉም። እንዳልሽው ምርጫ ያደረጉት ሕዝብ ማሸበርና አገር ማተራመስ ነው። አሁን ላይ እኮ በየውጭ አገሩ እንደፈለጋቸው የሚበትኑት የእኛኑ ብር ነው። ብልሆች ቢሆኑ የሰረቁትን ብር አገራቸው ላይ ኢንቨስት ባደረጉበትና እድገት ባመጡ ነበር።
እነሱ አሻፈረኝ ቢሉም ይህ የተባረከ ሰው በእነሱ ፈንታ የኢትዮጵያን ህዝብ ጎንበስ ብሎ ይቅርታ ጠይቋል። እነሱም በቃ ብለው ኑሯቸውን መኖር ሲገባቸው ሁልጊዜ የበላይነትን ነው የሚፈልጉት። ያ ደግሞ የሚሆን አይደለም። ጊዜው ተለውጧል፤ እንደቀድሞ የበታችነቱን አምኖ የሚኖር ሕዝብ የለም። እርግጥ ሕዝቡ በይቅርታ አልፏቸው ነበር፤ እነሱ ግን አርፈው መቀመጥ አልፈለጉም። ልክ እንደነሱ አብረዋቸው ሕዝብን ሲበድሉ የነበሩ ሌሎች ባለሥልጣናት እኮ ጥፋታቸውን አውቀው ይቅርታ ጠይቀው በሠላም እየኖሩ ነው። ማንም አልነካቸውም።
ዶክተር ዐቢይ ወያኔዎችን ‹‹ጦርነት አያስፈልግም›› ብሎ ሲለምናቸው ‹‹ፓስተር ነው፤ ፈሪ ነው›› ሲሉት ሳይወድ በግድ ወደ ጦርነት ገባ። ሁላችንም እንደምናውቀው ወደ ጦርነት የተገባው ድንቁን የመከላከያ ሠራዊታችንን በመንካታቸው ብቻ ነው። ከዚያ በፊት ‹‹ተዉ!›› እየተባሉ ምርጫ ቢያካሂዱም ምንም አልተባሉም። የጦር መሪም ለመቀየር ሲሞከር ‹‹አይቻልም›› ብለው አባረዋል። እንግዲህ ያንን ሁሉ ካደረጉ በኋላ በመጨረሻ የአገርን ዳር ድንበር በሚጠብቅ ምስኪን ወታደር ላይ የግፍ ግፍ ፈፀሙ። አስቀድሜ እንዳልኩሽ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጦርነቱ ሲገባ አቅም አለኝ ብሎ ሳይሆን ተገዶ ነው።
በነገራችን ላይ ወደፊት ምንአልባት እውነታው ይገለጣል፤ የጠላቶቻችን አቅም የቱንም ያህል ቢበረታ ሁልጊዜም ቢሆን ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቃታል። ለዚህም ነው እናዳሰቡት ኢትዮጵያ እስካሁን ያልፈረሰችው። እንደነሱ እቅድ አገራችን አሁን ላይ ብትንትኗ ወጥቶ ነበር፤ ግን ፈጣሪ ለዚህች አገር የገባውን ቃልኪዳን የማያጥፍ በመሆኑ ዛሬም አለች። መከላከያችንም ቢሆን በጣም ጠንካራና የማይበገር እንደሆነ ስለማምን ወደፊትም አገራችን አትፈርስም። በመሆኑም ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን የሚመጣውን ነገር መጋፈጥ ነው እንጂ የሚገባን ወያኔ እዚህ ደረሰ እያልን ስላወራን አገራችንን መታደግ አንችልም። አሁንም ደግሜ ደጋግሜ መናገር የምፈልገው ነገር የኢትዮጵያ ሕዝብ ቆሞ የመጣውን ወራሪ ኃይል በአንድነት እንዲመክት ነው። ለወሬና ለአሉባልታ ቦታ መስጠት የለብንም ባይ ነኝ።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ሰዎች ለዚህች አገር ብሔራዊ እርቅ ነው የሚያስፈልጋት ይላሉ። ለመሆኑ እንደ ሕወሓትና ኦነግ ሸኔ ባሉበት አገር ውስጥ ብሔራዊ እርቅ ይሳካል ተብሎ ይታሰባል?
አቶ ጥበበ፡- ብሔራዊ እርቅ የሚባል ነገር መንግሥትም ቢሆን የሚቀበለው አይመስለኝም። በተደጋጋሚም ተናግሮታል። ሁለተኛው ነገር ይህ አሸባሪ ቡድን እኮ በሰው ልጅ ላይ ብቻ አይደለም ጭፍጨፋ የፈፀመው፤ ምንም በማያውቁ እንስሳቶችንም ነው ሲገድል የከረመው። እኔ ዛሬም ድረስ እንስሳቶቹ ምን እንደበደሉት እንቆቅልሽ ነው የሚሆንብኝ። እነዚህ ሰዎች በዓለም ታሪክ ላይ ያልተደረገ ነገር ነው ያደረጉት። ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ጤነኞች ናቸው ብዬ አላስብም። አንድ ሰው እኮ የሚደራደረው ጤነኛ ከሆነ አካል ጋር ነው። እነዚህ እኮ እብዶች ናቸው። ደግሞም ዛሬ የሚሰጡት መግለጫ ነገ አይደግሙትም። እየሰከሩ ወይም ሀሽሻቸውን እየወሰዱ እንደሆነ አይታወቅም፤ የሚናገሩት ነገር ሁሉ እርስ በርስ የሚጣረሱ ናቸው። ዛሬ ቁጭ ብለን ስናወራ እድሜያችንን በሚመጥን መልኩ ነው የምናወራው። ከእድሜያችን ወርደን ማውራት አይጠበቅምን።
አሁንም ኃላፊነት አለብን ብለው የሚያስቡ ከሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሰብ ያለባቸው መልካምነታቸውን ነው። እኛም ከዶክተር ዐቢይ የተሻለ ሥራ ሰርተው ነው ማየት የምንፈልገው እንጂ እየገቡ እየዘረፉ፤ እያጨዱ፤ እየወሰዱ፤ ሰውና ከብት እየገደሉ ሊቀበላቸው የሚችል ኢትዮጵያዊ የለም። ደግሞስ ማነው በምን ሞራል ከእነሱ ጋር የሚደራደረው?። እንደእኔ እምነት የኢትዮጵያ መንግሥት የቱንም ያህል የዓለም ጫና ቢከብደው ከአሸባሪ ጋር አይደራደርም። ምክንያቱም እነዚህን ሰዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግደን ኢትዮጵያ በሠላም የምትቀጥልበት ሁኔታ ነው መፍጠር ያለብን።
አዲስ ዘመን፡-አሸባሪው ቡድን ህፃናትና ነፍሰጡሮችን ሳይቀር በገፍ በጦርነት እያሳተፈ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንዳንዶች በመንጋ የመጣ ጠላትን ማሸነፍ የሚቻለው በመንጋ ነው ይላሉ። እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
አቶ ጥበበ፡– እኔ ደብረዘይት ተወልጄ አድጌ ከወታደሮች ጋር ቅርበት ቢኖረኝም፤ በዚህ ላይ ጥልቅ ወታደራዊ ትንታኔ መስጠት ይከብደኛል። ይሁንና ባለፈው ሁለት ሳምንት ጎንደርና ጎጃም ላይ በሕዝብና ቤተሰብ ስም የተሰበሰበ ገንዘብ ለማድረስ ሄደን ነበር። እናም በዚያ አካባቢ የሚታየው ድባብ ወጣቱ ካለማንም አነሳሽነት በጠዋት ተነስቶ ወታራዊ ሥልጠና እየወሰደ መሆኑን አይተናል። በከፍተኛ ደረጃ ወጣቱ ተዘጋጅቷል። እንዳንዶቹን ስናነጋግራቸው ያላቸው ስነልቦና የሚያስደንቅ ነው። ብዙዎቹ ‹‹ከዚህ በኋላ መሳሪያ ባይኖርም እንኳን እነሱ በሕዝብ መንጋ እንደተሰለፉት እኛም ከእነሱ እጥፍ ሆነን በመሰለፍ ሠራዊታችንን አናስደፍርም›› የሚል ምላሽ ነው የሰጡን። ዱላም ሆነ ቢላና ማጭድ ይዘው ለመታገል መቁረጣቸውን አይተናል። ከዚያ አልፈው ወደ ወሎ ተመው በመሄድ ቆራጥነታቸውን እያሳዩ ነው ያሉት።
በሌላ በኩል ደግሞ የጦርነት መልካም ባይኖረውም ወታደሩ ብቻውን ስንቱን ፈጅቶ ይችለዋል። ስለዚህ እንደተባለው በርካታ ሕዝብን አሰልፎ የመጣን ወራሪ ኃይል ማሸነፍ የሚቻለው በሕዝብ በመመከት ነው። ይህንን ማድረግ ከታቸለ የሚተርፉትን ወታደሩ ልክ የሚያስገባቸው ይሆናል። በነገራችን ላይ ይህንን ማድረጉ የወታደሩ ኃይል አስቀድሞ እንዳይዳከም ያደርገዋል። ደግሞም በጦርነት ሕግ ወደኋላ ማፈግፈግ ያለ ነው። የመጣውን ኃይል አቅምና ሚዛኑን አይቶ ማፈግፈግ ራሱ ለማሸነፍ እድል የሚሰጥ ነው። በተጨማሪም የተወሰነውን የጠላት ሠራዊት ቆርጦ ለማስቃረት የሚያግዝ በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ተመራጭ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በዚህ አጋጣሚ በወያኔ ፕሮፖጋዳ ለሚሸበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መልዕክት ያስተላልፉልን?
አቶ ጥበበ፡– ድሮ ጦርነትን የሚመራም ሆነ የሚፈፅመው ወታደሩ ነው። አሁን ላይ ግን እየሆነ ያለው ከወታደሩ በፊት የፌስቡኩ ወሬ እየቀደመ ሕዝብ እያሸበረ ነው። ስለዚህ ጦርነቱን ለወታደሩ ትተን በአቅማችን የየራሳችን ጠጠር ለመወርወር መዘጋጀት ነው ያለብን። የኋላም ሆነ የፊት ደጀን ሆነን ሠራዊቱን እና የተጎዱትን መደገፍ ይገባናል። አሁንም ብዙ ሰዎች መሰለፍ ይፈልጋሉ። ኢትዮጵያ የሰው እጥረት የለባትም። ግን ደግሞ ይህንን ሕዝብ ማስተባበር ያስፈልጋል። ሥራዎች እንዲሰሩ የፋይናንስ ድጋፍ ማድረግም ከሁላችን ይጠበቃል።
እኛ ዲያስፖራዎችም ብንሆን መንግሥት ማዕቀብ ፈርቶ እጅ እንዲሰጥ አንፈልግም። መንግሥታችን የውጭ ምንዛሬ ካስፈለገው እኛ ዲያስፖራዎች ተሰባስበን ከደመወዛችን ላይ የተወሰነውን እየለቀቅን መደገፍ አለብን። ለተወሰነ ጊዜ መልበስና ማጌጥ ትተን መንግሥታችንን ለመርዳት መሞከር ይጠበቅብናል። በዚህ አጋጣሚ ለዶክተር ዐቢይ ማስተላለፍ የምፈልገው መልዕክት ውጭ ያለነው ኢትዮጵያኖች ሁላችንም ዶክተር ዐቢይን በቋሚነት መርዳት እንደሚገባን ተግባብተናል። ምክንያቱም ዶክተር ዐቢይን መርዳት ማለት ኢትዮጵያን መርዳት ማለት ነው። ዶክተር ዐቢይ እንደ ወያኔ ሌባ አይደለም። አለመሆኑን ደግሞ በዚህ ሶስት ዓመት ሰርቶ አሳይቶናል። የግሉን ገንዘብ እንኳን ያገኘውን ለትምህርት ቤቶች፤ የደካሞችን ቤት በመገንባት ሲያውል ተመልክተነዋል። ስለዚህ ዶክተር ዐቢይ ሌሎች ሰዎች የማይነኩት እሱ ብቻ የሚመራው አካውንት እንዲከፍትልን እንፈልጋለን። ያ አካውንት ካለ ከእኔ ጀምሮ በቀን አራት ሰዓት ተጨማሪ እየሰራን የምናገኘውን ገንዘብ ወደእዚህ እንልካለን። ሌላው ደግሞ ከእኔ በበለጠ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለው አውቃለሁ። ስለዚህ አካውንት እንዲከፍቱልን በዚህ አጋጣሚ ጥያቄውን ማቅረብ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፡- በአሜሪካም ሆነ በሌሎች የምዕራቡ ዓለም የሚያደርጉትን ጫና ከመከላከል አኳያ ምን መሰራት አለበት ብለው ያምናሉ?
አቶ ጥበቡ፡– የምዕራቡን ተፅዕኖ ለመከላከል በእኛ በኩል መሥራት ከጀመርን ትንሽ ቆይተናል። እኛ ባለንበት አሜሪካ በርካታ የኢትዮጵያ ሚዲዎችን በመጠቀም ብዙ ቅስቀሳዎችን እያደረግን ነው ያለነው። ለምሳሌ በኡስታአዝ ጀማል ‹‹የአባይ ንጉሶች›› የአቤ ቶክቻው ‹‹ሃቅና ሳቅ›› ፣ ‹‹መሃል ሜዳ›› የደሱ፤ የኮር ዳዊት ‹‹ትኩስ መረጃ›› እንዲሁም፤ የደረጀ ሃብተወልድ ፕሮግራም ሕዝቡ የሚሳተፍበት የራሳቸውን ጥረት እያደረጉ ነው ያሉት። በዚያ ውስጥ እኛም እየተሳተፍን እንገኛለን። በእርግጥ ትግሉ ቀላል አይደለም። እኛ እነሱ ጋር ገብተን የእነሱን አናዳምጥም። እነሱ ግን እኛ ጋር እየገቡ የተሰባሰበውን ኢትዮጵያዊ ለመረበሽ ብዙ ጥረት ያደርጋሉ።
ከዚህ አንፃር እነዚህን የሚዲያ ሰዎች እያጠናከርን ነው ያለነው። ከዚህም አልፈው በእነዚህ ሚዲያዎች አማካኝነት ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና ለሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ድጋፍ እያደረግን ነው ያለነው። ከዚያ በተጨማሪ የዲሲ ግብረሃይል እጅግ በጣም ትልቅ ሥራ እየሠሩ ነው ያሉት። በዚያ ውስጥም እሳተፋለሁ። እነዚህ ሥራዎች ታዲያ የወያኔ አፈ ቀላጤዎች የሚያደርጉትን ሴራ ለማክሸፍም ሆነ የምዕራብውያኑን ተፅዕኖ ለመከላከል እያገዘን ነው። ይህንን ሁሉ የምናደርገው ለውጥ እንደሚመጣ ስለምንረዳ ነው። የወያኔ ተላላኪዎች እየወጡ ቢንከባለሉም የእኛ ዲያስፖራ ቀድሞ ሴራውን እያከሸፈ የበላይነቱን መያዝ ችሏል። ይሁንና ከዚህ በላይ ተቀናጅቶ የወያኔ ተላላኪዎችንም ሆነ የምዕራብውያኑን ሴራ ማክሸፍ ይገባናል።
አዲስ ዘመን፡- አሜሪካ ሰሞኑን እያካሄደች ባለችው ምርጫ ተፅዕኖ ከመፍጠር አኳያ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያኑ ምን ይጠበቃል?
አቶ ጥበበ፡- እኔ ዜግነቴን ባለመለወጤ በምርጫው መሳተፍ አልችልም። ሆኖም ብዙዎቹ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵውያን በአሁኑ ምርጫ የአገራቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚያስችል ተፅዕኖ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሱ መሆናቸውን አውቃለሁ። ባለፈውም ቢሆን የባይደኑ ዲሞክራት ፓርቲ በጣም በጥቂት ነጥብ ልዩነት ተንጠልጥለው ማሸነፋቸው ይታወቃል። በዚህም ምርጫ በየቦታው የሚገኙ ኢትዮጵያዊ ተዘጋጅቶላቸዋል። ምርጫ መርጦ የማያውቀው ሳይቀር ዲሞክራቶችን ለመጣል ተዘጋጅቶ ነው ያለው። በዚህ ምርጫ ቅስቀሳ ከፍተኛውን ሥራ እየሠሩ ያሉ አሉ። ዲሞክራቶች እንዲያሸንፉ የኢትዮጵያውን ሚና ከፍተኛ እንደነበረው ቢታወቅም እነሱ ግን ውለታችንን ዘንግተው ዲሞክራቶች ከአሸባሪው ቡድን ጋር ነው የተሰለፉት። ስለዚህ እኔ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርሽ ኢትዮጵያውያን በድምፃቸው ለመጣል ከፍተኛ ሥራ እየሠሩ ነው። ደግሞ ዶክተር ዐቢይን የመሰለ መሪ ፈጣሪ ሰጥቶናል። ስለዚህ የቀድሞው ተሰሚነታችን ይመለሳል የሚል እምነት አለኝ። በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያኖች እጅ ለእጅ ተያይዘንና በአንድነት ቆመን ይህችን አገር ከፍተኛ ደረጃ እንድትደርስ መረባረብ አለብን።
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ ጥበበ፡– እኔም በጣም እዚህ ድረስ መጥታችሁ ቃለ ምልልስ ስላደረጋችሁኝ በጣም አመሰግናለሁ።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2014