መረጃ የድል ነሺነት ትልቅ አቅም እንደሆነው ሁሉ ለውድቀትም አደገኛ መንገድ ነው። በዚህ ስልት ውስጥ ተወልደው የኖሩትና ያረጁት አሸባሪው ህወሓትና ቡድኖቹ መረጃን የፕሮፖጋንዳ ዋና መሳሪያቸው አድርገው እየተጠቀሙበት ይገኛል።
ይህ ሲባል ግን መረጃን ለፕሮፖጋንዳ መጠቀም በራሱ ችግር ነው ማለት አይደለም፤ ይልቁኑ ያልተጨበጠ እና ያልሆነን የበሬ ወለደ የፈጠራ መረጃን ለፕሮፖጋንዳ የማዋላቸው ጉዳይ እንጂ።
ይህ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ምንም እንኳን የአሸባሪው ቡድን መለያ ሆኖ የሚታወቅ ሀቅ ቢሆንም፤ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ ቀና ማለትና ወደ ታላቅነቷ ለመገስገስ በተዘጋጀችበት በዚህ ወቅት ከእጃቸው እንዳትወጣ የሚሹ የምዕራቡ ዓለም አገራት በተለያየ መልኩ የሽብር ቡድኑን የሀሰት ወሬ በመቀባበል ወደማራገብ መግባታቸው እጅጉን አስገራሚም፣ አሳዛኝም ተግባር ነው። እነዚህ አገራትም ሆኑ ሚዲያዎቻቸው ከሚከተሉት ርዕዮተዓለም አኳያ ደግሞ ከአንድ ተራ አሸባሪ ቡድን ጋር በማበር በአንዲት ሉዓላዊት አገር ላይ ይሄን መሰል የሀሰት ፕሮፖጋንዳ አካል መሆናቸው አሳፋሪ ነው።
ይሁን እንጂ፣ የምዕራቡ ዓለም አገራት ጉዟቸውም ሆነ ድጋፋቸው ከራሳቸው ጥቅምና ህልውና አኳያ ተመዝኖ የሚሰላ እንደመሆኑ፤ ትናንት እንዳሹት የሚዘውሩት የአሸባሪው ቡድን ዛሬ ላይ ከማዕከል መገፋት ብቻ ሳይሆን የህልውና አደጋ ውስጥ መግባቱ በኢትዮጵያ ላይ እንደፈለጉ እንዳያዝዙ ስለሚያደርጋቸው እጅጉን አሳስቧቸዋል። ለዚህም ነው ትናንት አገር ለማፍረስ አገርንና ወገንን የወጋን ኃይል፤ ዛሬ አፈር ልሶ እንዲነሳ ሲደግፉት የሚታዩት፤ እየደገፉትም ያሉት።
ምዕራባውያኑ አሸባሪ ቡድኑን ለማገዝ በሰብዓዊነት ስም ተሰማርተዋል፤ ሚዲያዎቻቸውን ያለገደብ አሰማርተዋል፤ የጦር እቃዎችንና የመገናኛ መሳሪያዎችን አቀብለውታል፤ የሳተላይት መረጃዎችንም እያደረሱት ይገኛል። በአንጻሩ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ለማሳደር አሰስ ገሰሱን እየሰበሰቡ እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ ይገኛል። አቅማቸው የፈቀደውንም ጫና ለማሳደርና እጅ ለመጠምዘዝ አንድ ሁለት እርምጃ ተጉዘዋል።
ከዚህ ሁሉ ድጋፍና ጫና በኋላም ቢሆን የሚፈልጉት እንደማይሳካ የተገነዘቡት እነዚህ አገራት፤ የአሸባሪውን ቡድን ለማገዝና ለማበረታታት፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ኢትዮጵያውያን ላይ ጫና በመፍጠር ለማዳከም የሚያስችሏቸውን ሰፊ የተቀናጀ እና በሀ ሰት መረጃ ላይ የተመሰረተ ፕሮፖጋንዳ አስፋፍተው ማሰራጨት ጀምረዋል።
ለዚህ የሀሰት እና የተቀናጀ ፕሮፖጋንዳ ደግሞ ከሀሰት ወሬ ፈጣሪ ጀምሮ የሀሰት መረጃ አደራጅና አሰራጭ ድረስ የተናበበ ኔትዎርክ የዘረጉ ሲሆን፤ የተሰራጨውን መረጃ በመቀባበል እና በማባዛት ረገድ በተለያዩ ዓለም አገራት ተሰይመው የተቀመጡ በሰውም በቴክኖሎጂም የሚዘወሩ የመደበኛ እና የማህበራዊ ሚዲያ ቡድኖች አሉ። በዚህም ያልሆነውን ሆነ፤ ያልተደረገውን ተደረገ፤ ያልተባለውን ተባለ፤ ወዘተ. በሚል የሀሰት ወሬ በአንድ ጊዜ አየሩን ይሞሉታል።
“ከሺህ ጦረኛ አንድ ወረኛ” እንዲሉ፤ አሸባሪ ቡድኑ በጦር መፍታትና ማድረግ ያቃተውን በሀሰት ፕሮፖጋንዳ ታግዞ በተለያዩ አከባቢዎች ሰርጎ በመግባት እኩይ ዓላማውን እንዲያሳካ እድል ያገኘ እንዲመስለው አድርገውታል። እናም ከወዲህ ፈረሱ አሸባሪው ቡድን፣ ከወዲያ ጋላቢዎቹ ምዕራባውያን ሁሉን የጨረሱ መስሏቸው አታሞ ሲደልቁ ተስተውሏል። ይሁን እንጂ እውነቱ እያደር ሲጠራ የሆነውና የተባለው ለየቅል ሲሆን፤ በወሬ የተሸበረው ህዝብ በወኔ ተሰብስቦ አሸባሪውን መጥረግ ሲጀምር መደናገጥ ውስጥ ገቡ።
ይሄኔ ነው የሀሰት ፕሮፖጋንዳቸውን ደረጃውን ከፍ በማድረግ ወደ ሽብር ፈጣሪ ፕሮፖጋንዳነት ያሳደጉት። እናም የሽብር ቡድኑ ሙሉ ልሳን ሆነው (በተለይ እነ ሲ.ኤን.ኤን. እና ኤ.ፒ አይነቶቹ) የሽብር መንዣ የሀሰት ፕሮፖጋንዳቸውን በተቀናጀና በተጠና መልኩ ማካሄድ ጀመሩ። ለዚህ ደግሞ ህዝቦችን መከፋፈልና በመካከላቸው ጥርጣሬ መፍጠርን ዋና ስልታቸው አደረጉ።
“አሸባሪዎቹ ሕወሓት እና ሸኔ በአንድ ተገናኝተው ወደ አዲስ አበባ እየገሰገሱ ነው፤ በደረሱበት ሁሉ ህዝቡ በደስታ እየተቀበላቸው ነው፤ የፌዴራል መንግስቱ በውስጡ መከፋፈል እየተፈጠረ፤ ሰራዊቱም እየተበተነ፤ ህዝቡም በፌዴራል መንግስቱ ላይ እምነት እያጣ፤ ባለስልጣናቱም ለስደት እየተዘጋጁ ነው፤ እከሌ የሚባል ብሔር እየተገፋና እየተሳደደ፤ እከሌ የሚባል ብሔር ደግሞ በጦርነቱ እንዲፈጅ እየተደረገ፤ ወዘተ. ነው፤” የሚል አሉባልታ ወደመቀባበልና ወደማራገብ ገቡ።
ይሄን መሰል በህዝቡ ውስጥ ሽብር በመፍጠር የመከፋፈል እና በአንድ ተሰልፎ የሽብር ቡድኑን እንዳይፋለም አቅም የመበተኛ ስልት የሆናቸው የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ታዲያ፤ ዛሬ ላይ ምንም እንኳን የሚፈልጉትን ሊያስገኝላቸው ባይችልም “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” እንዲሉ ውሎ ሲያድር እውነት መምሰሉ አይቀርምና ጥንቃቄ ማድረግ እጅጉኑ ያሰፈልጋል። በመሆኑም ይሄን የተቀናጀ እና የተጠና የምዕራቡ ዓለም የሽብር መፍጠሪያ የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ሁሉም አውቆ ሊጠነቀቀውና ተገንዝቦም ሊዋጋው ይገባል። ይህ ሲሆን ባንዳነት ታሪክ ሆኖ፤ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት አሸንፈው የከፍታ ጉዟቸውን ይቀጥላሉ።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/2014