የ2014 ዓ.ም ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየርሊግ ጨዋታዎች በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስቴድየም የሦስት ሳምንት ፍልሚያዎችን አስተናግዶ ከብሔራዊ ቡድን ጨዋታዎች መርሃ ግብር ጋር ተያይዞ ከትናት በስቲያ ጀምሮ ለተወሰኑ ቀናት ወደ እረፍት አምርቷል። ፕሪሚየርሊጉን የሊግ ካምፓኒው መምራት ከያዘ ጀምሮ ሊደነቅ የሚገባ በርካታ ለውጦች ቢመዘገቡም በክለቦች በኩል ሜዳ ላይ በሚታዩ ጨዋታዎች ካለፉት ዓመታት የተለየ ነገር መታየት አልቻለም።
አምና ውድድሩ በርካታ ግቦችን በማስተናገድ ጨዋታዎች በተሻለ ሳቢና ፉክክሮችም ጠንክረው የታዩበት እንደመሆኑ ሊጉ አዲስ ቻምፒዮንና የግብ ክብረወሰን በወጣቱ የኢትዮጵያ ቡና አጥቂ አቡበከር ናስር በሃያ ዘጠኝ ግቦች የተሻሻለበት እንደነበር ይታወሳል።
ይህም የዘንድሮውን የውድድር ዓመት ከአምናው የተሻለ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎት ነበር። ይሁን እንጂ የክለቦች የሜዳ ላይ ፉክክር እንዲሁም የጨዋታዎች ግብ የማስተናገድ አቅም እንደተጠበቀው አልሆነም። አምና በበርካታ ግቦች ሊጉን ያደመቁት እንደ አቡበከር አይነት ተጫዋቾችም ዘንድሮ አጀማመራቸው እንደተጠበቀው ስኬታማ አልሆነም። የውድድር ዓመቱ ጨዋታዎች ገና ሦስተኛ ሳምንት ላይ እንደመገኘታቸው ከወዲሁ መደምደም ባይቻልም ከአምናው የውድድር ዓመት አንፃር ዘንድሮ ሊጉ በግብ ድርቅ ተመቷል ለማለት በርካታ መረጃዎችን ማስቀመጥ ይቻላል።
በሊጉ የሦስት ሳምንት ጨዋታዎች ሃያ አራት ፍልሚያዎች ተከናውነው አርባ አምስት ግቦች ከመረብ አርፈዋል። ይህም በአማካኝ በአንድ ጨዋታ 1ነጥብ 88 ግብ ተቆጥሯል ማለት ነው። አምና የሊጉ ተሳታፊ ክለቦች ቁጥር ከዘንድሮው በሦስት አንሶ አስራ ሦስት ክለቦች ብቻ እንደመወዳደራቸው በሦስተኛው ሳምንት አስራ ስምንት ጨዋታዎች ብቻ ናቸው የተከናወኑት። ይሁን እንጂ በነዚህ ጨዋታዎች ሃምሳ ስድስት ግቦች ከመረብ አርፈዋል። ይህም በአማካኝ በአንድ ጨዋታ 3ነጥብ 11 ግብ ተቆጥሯል ማለት ነው። በዚህ ስሌት መሰረት የዘንድሮች የውድድር ዓመት የሦስት ሳምንት ጨዋታዎች ከአምናው ጋር ሲነፃፀሩ ሊጉ በግብ ድርቅ ተመቷል ለማለት አሳማኝ ምክንያት ይመስላል።
በሃያ አራቱ ጨዋታዎች ዘጠኝ ጨዋታዎች በአንድ ለዜሮ ውጤት መጠናቀቃቸውም ተጨማሪ ማሳያ ሊሆን ይችላል። በዘንድሮው የውድድር አመት በርካታ ግቦች የተቆጠሩበት ብቸኛ ጨዋታ በሁለተኛው ሳምንት የሸገር ደርቢዎችን አገናኝቶ ኢትዮጵያ ቡና በቅዱስ ጊዮርጊስ 4ለ1 የተሸነፈበት ጨዋታ ነው። በሁለተኛው ሳምንት ጨዋታዎች በሊጉ አስራ አምስት ግቦች ሲቆጠሩ ከመጀመሪያው ሳምንት በሁለት ያነሰ ሆኖ አልፏል ። በዚህ ሳምንት ሶስት ተጫዋቾች ተመስገን ካስትሮ ፣ አናጋው ባድግ እና ዳዋ ሆቴሳ የቀይ ካርድ ሲመለከቱ ካለፈው ሳምንት ከፍ ብሎ ታይቷል።
የወላይታ ድቻው ስንታየሁ መንግስቱ በሳምንቱ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር የቻለ ብቸኛው ተጫዋች ሆኖ ሲያልፍ በዚህ ሳምንት ከተቆጠሩ አስራ አምስት ጎሎች መካከል አስራ ሁለቱን አዳዲስ ተጫዋቾች ሲያስቆጥሩ አቡበከር ናስር እና ዳዋ ሆቴሳ ብቸኞቹ በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ሆነው አልፈዋል።
በዚህ ሳምንት ከተቆጠሩ አስራ አምስት ጎሎች ውስጥ አምስቱ በመጀመሪያው አጋማሽ ሲቆጠሩ ካለፈው ሳምንት ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሆኖ አልፏል። ሁለተኛ ሳምንት ላይ በደረሰው የቤት ኪንግ ኢትዮጵያ ፕርሚየር ሊግ በድምሩ ሰላሳ ሁለት ጎሎች ከመረብ ሲያርፉ ሃያ ሁለቱ በሁለተኛው አጋማሽ መቆጠር ችለዋል።
የአምናው ቻምፒዮን ፋሲል ከነማ በዘንድሮው የውድድር አመት በርካታ ግቦችን በማስቆጠር የተሻለ ክለብ ሆኖ ከመቅረቡ በተጨማሪ ቻምፒዮን በሆነበት አመት በርካታ ግቦችን በማስቆጠር ትልቅ ሚና የነበረው አጥቂው ሙጂብ ቃሲም ወደ አልጄሪያ ክለብ በማቅናቱ እንኳን ክለቡ ግብ ለማስቆጠር አልተቸገረም። አሰልጣኝ ስዩም ከበደ እንደ አምናው ጠንካራና የተደራጀ ክለብ ይዘው በመቅረብም በሶስት ጨዋታዎች ሙሉ ዘጠኝ ነጥብ መሰብሰብ የቻለ ብቸኛው ክለብ ነው። ባህርዳር ከነማም በአንጻሩ በሁለት ነጥብ ዝቅ ብሎ ጥሩ አጀማመር ያሳየ ክለብ ሆኗል።
አምና በ6ቱ ሣምንት ግጥሚያዎች 36 ጨዋታዎች ተደርገው 107 ግቦች ከመረብ አርፈዋል። ከ6ቱ ሳምንት መሀል በ1ኛ እና 2ኛ እና በ4ኛ ሳምንት በነፍስ ወከፍ አስራ አምስት ግቦች ተቆጥረዋል። በ6ኛው ሣምንት 17፣ በ5ኛ ሳምንት 19፣ በ3ኛ ሳምንት 24 ግቦች ተቆጥረዋል። በ6ቱ ሳምንት ከተቆጠሩ ግቦች 0ለ0 3 ጊዜ፣ 1ለ0 6 ጊዜ፣ 2ለ2 2 ጊዜ፣ 4ለ1 5 ጊዜ፣ 2ለ1 3 ጊዜ፣ 3ለ1 6 ጊዜ፣ 3ለ2 3 ጊዜ፣ 2ለ0 3 ጊዜ፣ 4ለ2 1 ጊዜ፣ 1ለ1 3 ጊዜ የሆነ ውጤት ተመዝግቧል።
ባለፈው የውድድር አመት በ6 ሳምንት ጨዋታዎች ከተቆጠሩ 113 ግቦች መሀል በኮከብ ግብ አግቢነት እየተፎካከሩ የነበሩት የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስርና የፋሲል ከነማው ሙጂብ ቃሲም እኩል ስምንት ስምንት ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል ሀብታሙ ታደሰ ከኢትዮጵያ ቡና ጌታነህ ከበደ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እኩል አራት አራት ግቦች ከመረብ አሳርፈው ነበር። 6 ተጨዋቾች በየግላቸው ሶስት ሶስት ግቦችን ሲያስቆጥሩ ሌሎች 6 ተጨዋቾች በነፍስ ወከፍ ሁለት ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፈዋል። 16ቱ ተጨዋቾች በጋራ 54 ግብ ሲያስቆጥሩ 59 ተጨዋቾች በየግላቸው አንድ አንድ ግቦችን ተጋጣሚ መረብ ላይ ማሳረፋቸው ይታወሳል።
የአምናው ውድድር አመት የግብ ስታስቲኮች ዘንድሮ ገና ከጅምሩ እንደማይደገሙ ማሳያ ሆነው የሚጠቀሱ ምክንያቶች በርካታ ናቸው። የመጫወቻ ሜዳ ምቹነት፣ የተጫዋቾች የአምና ብቃት መውረድና የክለቦች ደካማ አቀራረብ ሚዛን ከሚደፉ ማሳያዎች ዋነኞቹ ናቸው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2014