አገር የህልውና አደጋ ውስጥ ስትገባ የክተት አዋጅ አውጆ ስጋቶችን መቀልበስ የተለመደ አሰራር ነው፤ በተለይለኢትዮጵያውያን እውነታው በብዙ የድል ታሪኮች የተጀበ ፤ በታሪክም ውስጥ ጎልቶ የሚነበብና የሚሰማየአሸናፊነት መንፈሰ መገንቢያ ክስተት ነው። በአንድም ይሁን በሌላ የታላላቅ የተጋድሎ ታሪኮቻችን ዋነኛ ጡብምይሄው ሆኖ እንገኘዋለን።
የቀደመው ዘመን መሪዎች እንደ ዛሬም አገር አደጋ ውስጥ ስትገባ “እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላትአጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፤ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ። ከእንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉም ነውና ስለእኔ ሞት አላዝንም። ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም፤ ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም።
አሁንም አገር የሚያጠፋ፤ ሃይማኖትን የሚለውጥ፣ በፊት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል። እኔምየአገሬን ከብት ማለቅ፤ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር። አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም።
የአገሬ ሰው ከአሁን ቀደም የበደልሁህአይመስለኝም። አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም። ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ። ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣ለምሽትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል —” ብለው የክተት አዋጆችን በማወጅ መላውን ሕዝብ አሰልፈው ባካሄዷቸውየሕልውና ጦርነቶች ከፍ ባለ ተጋድሎ ሐገርን ለትውልድ ማሻገር ችለዋል። ብዙ ትውልድ ተሸጋሪ ጀግኖችን ማፍራት፤ ታሪክም መጻፍ ችለዋል።
የክተት አዋጆቹም በታወጁባቸው የታሪክ ምእራፎች መላው ሕዝብ በሰላም ጊዜ ሊፈጠሩ የሚችሉ ቁርሾዎችንእና ኩርፊያዎችን ወደ ጎን በመተው፤ አንድነቱን በተሻለ መንገድ አጠናክሮ ከፍ ባለ መደማመጥና መናበብ ብሔራዊ ስጋቶችን ቀልብሷል። በድልም ማግስት ተጨማሪ አገራዊ አቅም በመፍጠር ቀጣይነት ያለው ብሔራዊ ስሜትና ማንነት መገንባትም ተችሏል።
በአብዛኛው የብሔራዊ ማንነታችን መሠረት የሆነው ስለአገር ቀነኢነት እና ከዚህ የሚመነጨው ለአገር በክብር የመሰዋት ሁለንተናዊ ዝግጁነት፣ ከትውልድ ትውልድ በብዙ የመስዋእትነት ታሪክ ታጅቦ ዛሬም ባለው ትውልድ ውስጥ ከፍ ያለ ስፍራ እንዳለው በተጨባጭ እየታየ ነው።
ዛሬም ስለ አገር ክብር መሞት ከፍ ያለ ብሔራዊ እሴት ስለመሆኑ በተለያዩ ወቅቶች የተላለፉ የክተትአዋጆችን ተከትሎ ለአገር የክብር ሞት ለመሞት ከሀዲውን የሕወሓት ቡድን ቀና እንዳይል አርጎ ለመደምሰስ በልበ ሙሉነት እየተመመ ያለውን ዜጋ መመልከት በራሱ በቂ ፤ ከበቂም በላይ ነው። ትውልዱ አገራዊ ክብርን ለማስቀጠል ዛሬ ላይ ራሱን መስዋእት ለማድረግ በመቁረጥ የአባቶቹ እውነተኛ ልጅ ፤ ወራሽም ስለመሆኑ በተጨባጭ እያሳየ ነው።
በየክልሉ ከሀዲው የአሸባሪው ሕወሓት ቡድን በአገር ላይ እያደረሰ ያለው የክህደት ተግባር ፤ ተግባሩየፈጠረው ቁጭት፤ ከዚህ የመነጨው አገርን የመታደግ ከፍ ያለ መነሳሳት፤ መነሳሳቱ እየፈጠረ ያለው ብሔራዊ አንድነት የቡድኑን እኩይ ተግባር ከማምከን ባለፈ አዲስ ብሔራዊ የታሪክ ምእራፍ መፍጠር እንደሚያስችል ይታመናል።
የበለጸገች አገር ለመፍጠር ያለምነውን ትልቅ ህልም ከፍ ባለ ብሔራዊ የአንድነት መንፈስ እውን ለማድረግየተሻለ እድል የሚፈጥርልን፤ በቀጣይም ባንዳነት የአገር ስጋት እንዳይሆን አስተሳሰቡን እና ድርጊቶቹን ገድለንና ቀብረን መሻገር የሚያስችለንን አቅም የምንላበስበት ጭምር ነው።
ከዚህ ተጨባጭ እውነታ በመነሳት መላው ሕዝባችን በክልል መንግስታትም ሆነ በፌደራል መንግሥቱየታወጁ የክተት አዋጆችን የአገርን የሕልውና ስጋት ከመቀልበስ፤ አገራዊ ማንነትን ከማስጠበቅ፤ ለነገ ተስፋ ያደረግናትን የበለጸገች አገር ከመፍጠርና የተሻለች አገር ለትውልዶች ከማስተላለፍ አንጻር አልፋና ኦሜጋ እንደሆነ በአግባቡ ሊያጤነው ይገባል።
አዲሱ አገራዊ የታሪክ ምእራፍ ጅማሪው ለዘመናት ለአገር ስጋት በነበረው፤ አገርና ህዝብን በየዘመኑ ከፍያለ ዋጋ ባስከፈለውና ዛሬም እያስከፈለ ባለው ባንዳነት መቃብር ላይ መሆን አለበት ። ዛሬ ላይ ባንዳነት የመጨረሻው ደረጃ ላይ ደርሷል። በአደባባይም የክብር አስተሳሰብ እስኪመስል የማንነት ትምክህት እየሆነ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት ለርካሽ የስልጣን ጥማቱ ከታሪካዊ ጠላቶቻችን ሳይቀር የባንዳነት ተልእኮ ተቀብሎ አገርለማፍረስ እስከ ሲኦል እንደሚወርድ በድፍረት በአደባባይ መናገር የሚያስችል የልብ ድንዳኔ ውስጥ ይገኛል።
እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰ ባንዳነት በታሪካችን አልተጻፈም ፤ አልተሰማም።ይህ ተግባር የባንዳነት የመጨረሻው ደረጃ እንደሚሆንም ጤናማ አእምሮ ላለው ሰው ለማሰብ የሚከብድ አይደለም። የጥፋቱም ደረጃ አገርን እንደአገር የማፍረስን ከፍ ያለ እርግማን የተሸከመ ነው። የዚህን እርግማን ሰንኮፍ መንቀል ደግሞ የነገዋን ባለተስፋ አገር በጠንካራ መሠረት ላይ የማዋቀር ተልእኮን በስኬት የመወጣት ያህል ነው።
የክተት አዋጁ ለዚህ ተልእኮ አልፋና ኦሜጋ መሆኑን ሁሉም ዜጋ በአግባቡ በመረዳት ራሱን ለአዲስና ተሻጋሪታሪክ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። በዚህ ታሪካዊ ዘመቻ ውስጥ መሳተፍ ማለት አገርን ከስጋት ከመታደግ ባለፈ የቀደሙት ትውልዶች ተስፋ ያደረጓትን፤ እኛም የምንጠብቃትን የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችል አቅም መገንቢያ፣ ባንዳነትንም ታሪክ የሚያደርግ ጭምር ነው !
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/2014