በዩጋንዳ አስተናጋጅነት እየተካሄደ በሚገኘው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ(ሴካፋ) ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ቻምፒዮና እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአስደናቂ የድል ጎዳና መጓዙን ቀጥሏል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ሦስተኛ ጨዋታውን ትናንት ረፋድ ከታንዛኒያ አቻው ጋር አድርጎ ሦስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።
ከፍተኛ ሽኩቻ ባስተናገደው ጨዋታ የሉሲዎቹ ተተኪዎች በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ መሳይ ተመስገንና ንቦኝ የን አከታትለው ባስቆጠሩት ሁለት ግቦች በመምራትና የጨዋታ ብልጫ በመውሰድ አስደናቂ እንቅስቃሴ አሳይተዋል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሰባት ደቂቃ ሲቀር ታንዛኒያዎች በባዶ ከመሸነፍ ያዳነቻቸውን ብቸኛ ግብ አስቆጥረዋል። መደበኛው ዘጠና ደቂቃ የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ታንዛኒያዎች ግብ ማስቆጠር ቢችሉም በረዳት ዳኛዋ ከጨዋታ ውጪ ሆኖ በመሻሩ ታንዛኒያዎች ከዳኛዋ ጋር ለጸብ ሲጋበዙ ታይተዋል።
በዚህም ታንዛኒያ ትልቅ ቅጣት ይጠብቃታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ ይህም ለዩጋንዳ ትልቅ ዕድል የሚሰጥ እንዳይሆን ተሰግቷል። ምክኒያቱም በቀጣይ የኢትዮጵያና ዩጋንዳ ጨዋታ በአቻ ውጤት የሚጠናቀቅ ከሆነ ሁለቱን ቡድኖች የሚለየው በታንዛኒያ ላይ ያስቆጠሩት የግብ ብዛት ስለሚሆን ዩጋንዳ ታንዛኒያ ላይ የምታስቆጥረው የግብ ብዛት የሚወስን ይሆናል። ኢትዮጵያ በቀጣይ ቅዳሜ ቡሩንዲና በመጪው ማክሰኞ ዩጋንዳን ካሸነፈች የዋንጫ ባለቤት መሆን ትችላለች።
የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በዋና አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እየተመራ በዩጋንዳ አስተናጋጅነት ከጥቅምት 20 እስከ ጥቅምት 30/2014 ዓ.ም ለሚካሄደው የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ አገራት ውድድር (ሴካፋ) ጥሩ ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን፣ አሰልጣኙ ወደ ውድድሩ ከማቅናታቸው በፊት በሰጡት መግለጫ ‹‹አሁን የምናደርገው የሴካፋ ውድድር የስድስት አገራት ቡድኖች የሚሳተፉበት ነው፡፡ እኛም ለእነዚህ ቡድኖች የሚሆነውን ዝግጅት በተለያየ ዓይነት ዝግጅት ስናደርግ መቆየታችንን መግለጽ እፈልጋለሁ›› ማለታቸው ይታወሳል። አሰልጣኙ ስድስት ተጫዋቾች ወደ ዋናው ቡድን ካደጉ በኋላ በምትካቸው ተጫዋቾችን አምጥተው ከሩዋንዳው ጨዋታ በኋላ በስምንት ቀናት ልዩነት ለሴካፋው ውድድር አዳዲስ ተጫዋቾችን ጨምሮ ጥሪ ተደርጎላቸው ልምምድ ሲሠሩ ቆይተዋል።
በሴካፋው የመጀመሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ጅቡቲን ሰባት ለዜሮ በሆነ ሰፊ ውጤት ማሸነፍ የቻለች ሲሆን፣ በጨዋታው ረድኤት አስረሳኸኝ ሦስት ግቦችን አስቆጥራ ሐትሪክ ስትሠራ ፣ ቱሪስት ለማ ሁለት ግቦችን፣ እፀገነት ግርማና ቤተልሔም በቀለ አንድ አንድ ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል። የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን በሁለተኛው ጨዋታውም ከኤርትራ አቻው ጋር ያደረገውን ጨዋታ ሰፊ በሆነ የአምስት ለዜሮ ውጤት ማሸነፍ ችሏል። በጅቡቲው ጨዋታ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረችው ረድኤት አስረሳኸኝ ኤርትራ ላይ ሁለት ግቦችን ከመረብ አሳርፋለች። ቱሪስት ለማ፣ መሳይ ተመስገንና ብዙየሁ ታደሰ አንድ አንድ ግቦችን ማስቆጠር የቻሉ ተጫዋቾች ሆነዋል።
በዘንድሮው የሴካፋ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ውድድር አዘጋጇ ዩጋንዳ፣ ኢትዮጵያ፣ ታንዛኒያ፣ ኤርትራ፣ጅቡቲና ቡሩንዲ እየተሳተፉ የሚገኙ ስድስት አገራት ሲሆኑ፤ ውድድሩ ባለፈው ነሐሴ ሊካሄድ ታስቦ እንደተራዘመ ይታወሳል። ይህ ውድድር ለመጨረሻ ጊዜ እኤአ 2019 ላይ በዩጋንዳ አዘጋጅነት ተካሂዶ ታንዛኒያ ኬንያን በፍጻሜ ጨዋታ አሸንፋ ዋንጫ ማንሳቷ ይታወቃል። የዘንድሮው ውድድር ላይ ጥቂት አገራት ብቻ እንደመሳተፋቸው የውድድሩ ይዘት አሸናፊውን ለመለየት በምድብ ጨዋታዎች ሳይሆን በነጥብ ሆኗል።
ይህም የዋንጫው አሸናፊ በአምስት ጨዋታዎች ትልቁን ነጥብ መሰብሰብ የቻለ አገር ይሆናል። ኢትዮጵያ በሦስት ጨዋታ ዘጠኝ ነጥብና አስራ ሦስት ግብ ይዛ ቻምፒዮን ለመሆን የተሻለ ዕድል አላት። ኢትዮጵያ በመጪው ቅዳሜ ከቡሩንዲና የፊታችን ማክሰኞ ከአዘጋጇ ዩጋንዳ ጋር የምታደርጋቸው ወሳኝ ጨዋታዎች የሚጠበቁ ሲሆን፤ የውድድሩ ቻምፒዮንን ለመለየትም የእነዚህ ሁለት ጨዋታዎች ውጤት አጓጊ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2014