በድንቃድንቅና የመዝናኛ ዜናዎች ‹‹ዛፎች ሙዚቃ አዳመጡ›› ሲባል እንሰማለን:: ሙዚቃ እየሰማች የምትታለብ ላም እንዳለችም ሰምተን እናውቃለን:: እንግዲህ ዛፎች ሙዚቃ ይሰማሉ ከተባለ የእንስሳት ብዙም አይገርመንም ማለት ነው፤ ምክንያቱም ከዛፍ ይልቅ እንስሳት ለሰው ልጅ ይቀርባሉ::
እንስሳት ከሰዎች ጋር ይግባባሉ:: ለዚህም ነው ገበሬዎች ለከብቶቻቸው ስም የሚያወጡላቸው:: ከብቶች ስማቸውን አውቀው ባይግባቡበት ኖሮ ስም ማውጣት ባላስፈለገ ነበር:: የእርሻ በሬዎች የየራሳቸው ስም አላቸው፤ ላሞች የየራሳቸው ስሞች አሏቸው::
ፍየሎችም እንዲሁ የየራሳቸው ስም አላቸው:: ገበሬው ሲያርስ የአጥፊውን በሬ ስም እየጠራ ነው:: ገና ወደ እርሻ ቦታው ሲሄድም እንዲሁ:: ከመንገድ ወጣ ብሎ ሰብል ወይም ሌላ ነገር ለማጥፋት የሚሄደውን በሬ ስሙን በመጥራት ይመልሰዋል:: የላሞችና ፍየሎች ስም ብዙ ጊዜ የሚጠራው በእረኞቻቸው ነው:: እረኛው ያጠፋችዋን ላም ወይም ፍየል ስም እየጠራ ነው እንድትመለስ የሚያደርጋት::
ከብቶች ከእረኞቻቸውና ከገበሬዎች ጋር የሚግባቡበት ሌላም ቋንቋ አለ:: አቅጣጫዎችን ያውቃሉ:: ለምሳሌ ገበሬው እያረሰ አንደኛው በሬ ወደታች ቢስብ የበሬውን ስም ጠርቶ ‹‹ ና ውጣ›› ይለዋል:: ውጣ ማለት ወደላይ ከፍ በል እንደማለት ነው:: በተመሳሳይ ወደላይ እየወጣ የሚያስቸግር ከሆነም ‹‹ና ውረድ›› እያለ እንዲመለስ ያደርገዋል::
እረኞችም ከሚጠብቋቸው ከብቶች ጋር እንዲሁ ይግባባሉ:: ‹‹በላይ፣ በታች፣ ግቢ….›› የሚሉ ቃላትን ይጠቀማሉ:: የታዘዘው ከብትም ወደላይ ሊወጣ ከነበረ ‹‹በታች›› ሲባል ወደታች ይሄዳል::
የበሬ እና ገበሬ ተግባቦት ግን ከዚህም ያልፋል:: በሬውን ልክ እንደ ሰው ልጅ ሁሉ ያወድሰዋል:: ከበሬው ጋር የሚያወሩ ይመስላል:: እርግጥ ነው መልስ ለማይሰጥ አካልም ሙገሳና ውደሳ ይደረጋል:: የበሬና ገበሬው ግን ግብረ መልስ ያለው ነው:: በሬ እና ገበሬ በየትኛውም ወቅት አይነጣጠሉም፤ አይራራቁም::
በእርሻ ወቅት እየተወዳደሱ ያረሱትን አዝመራ በዚህ በመኸር ወቅት ደግሞ ይሰበስቡታል:: ልክ በእርሻ ወቅት እንደሚባለው ሁሉ በመኸር ወቅትም በሬዎች ይወደሳሉ፤ ምክንያቱም ብዙ የሰብል አይነቶች የሚወቁት (ምርቱን ከገለባው መለየት) በበሬ በማበራየት ነው:: ሥራውም ‹‹በራይ›› ይባላል::
በመኸር ወቅት ሰብል የሚሰበሰበው መጀመሪያ አውድማ ተለቅልቆ ነው:: የተለቀለቀው አውድማ ላይ የሚበራየው እህል (ብዙ ጊዜ ጤፍ ነው) ይነሰነሳል:: ከዚያም በሬዎች አፋቸው በልጥ ይታሰርና ወደ አውድማው ይገባሉ:: አፋቸው በልጥ የሚታሰረው እህሉን እንዳይበሉ ነው:: ሲያበራዩ ከቆዩ በኋላ የሚበሉት ይዘጋጅላቸዋል::
በሬዎች ወደ አውድማ ከገቡ በኋላ በሥርዓት እንዲዞሩ ይደረጋል:: ሲዞሩ ታዲያ ከፊት የሚመሩት አባት በሬዎች ናቸው:: ከፊት የሚመራው በሬም ቀያሽ ይባላል:: ወይፈን (ገና ወጣት በሬ) ቀያሽ ከሆነ ከኋላ ያሉት በሬዎች በሥነ ሥርዓት እንዲዞሩ አያደርግም:: ከመሥመር እየወጣ ወደ መሃል ወይም ወደ ዳር ይሄዳል፤ ከዚህ አልፍ ሲልም ጭራሽ ከውድማው ዘሎ ይወጣና ሌሎችን እንዲወጡ ያደርጋቸዋል::
አንዳንዴ ደግሞ ከአውድማው ውጭ ላም ካየ ሥራውን ትቶ ወደ እሷ ይሮጣል:: ላም ባትሆን እንኳን ሌላ ከብት በዚያ ሲያልፍ ካየ ለግጥሚያም ቢሆን ከአውድማው ዘሎ ይወጣል:: ቀያሹ አባት በሬ ከሆነ ግን በስነ ሥርዓት እንዲዞሩ ያደርጋል::
ከፊት ያለው በሬ (ቀያሹ) እየመራ ከኋላ ያሉት ይከተላሉ:: የሚያበራየው ሰው ደግሞ ከኋላ ያለውን በሬ ትከሻ ይዞ ያዞራቸዋል:: ይህኔ ነው እንግዲህ የስነ ቃል ግጥሞች የሚወርዱት:: የበሬውን ትከሻ(ሻኛ) ይዞ የሚያበራየው ሰው ዝም ብሎ አይዞርም:: በሬዎችን የሚያወደሱና የሚያመሰግኑ ግጥሞችን እየደረደረ በማዜም ነው:: ታዲያ አስገራሚው ነገር በሬዎች በዜማው የሚመሰጡ መምሰላቸው ነው (ምናልባት በትክክልም እየተመሰጡም ይሆናል):: ድምጽን ከፍ አድርጎ በማራኪ ዜማ ‹‹እሹሩሩ በሬ›› ማለት ችሎታም ይፈልጋል:: እናም ችሎታው ኖሮት እሹሩሩ በሬ የሚል ሰው ሲያዞራቸው አንድ እንኳን በሬ ሳያፈነግጥ ይዞራሉ::
በእርግጥ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በሬዎች መደበላለቃቸው ይፈለጋል:: ይሄውም የሚወቆቱን ሰብል ቶሎ እንዲሰባብሩት ነው:: ብዙ ጊዜ የሚያበራየው ሰው ወጣት ከሆነ በሬዎችን አንዱን ከአንዱ ጋር እያጋጨ ያመሰቃቅላቸዋል:: ከኋላ ያለውን በሬ ጅራቱን በጠምዘዝ ወይም ሌላ ስስ ብልቱን በመንካት ያሯሩጠዋል::
የሚያበራየው ሰው አዋቂ ከሆነ ግን ቀስ ብሎ ነው የሚያዞራቸው፤ እንዲያውም ወጣቶች እንደዚያ ሲያደርጉ ራሱ ይከለክሏቸዋል:: እሹሩሩ በሬ እያሉ የሚያንጎራጉሩም አዋቂዎች ናቸው:: በሬዎች መንገላታትና መጎዳት እንደሌለባቸው፤ ሥራ የሚሰራው በመጣደፍ ሳይሆን በፈጣሪ ፈቃድ እንደሆነ ያምናሉ:: በእሹሩሩ በሬ ጊዜም እንዲህ ይላሉ::
በሬ በሬ ብየ የምወዘውዘው
እንጀራ አይበላም አምላክ ካላዘዘው::
በዚሁ ወደ ቃል ግጥሞች እንግባ:: እዚህ ላይ ግን የበሬዎችን የውደሳ ስም እንጠቁም:: ‹‹ጎኔ›› በማለት ይጠሩታል:: ጎኔ ማለት አንዱ የሰውነቴ ክፍል ነህ እንደማለት ነው:: በሬ ማለት ለገበሬ ልክ የሰውነቱ ክፍል እንደማለት ነው:: በሬው ቢታመምበት ወይም የሆነ ነገር ቢሆንበት አንዱ የሰውነቱ ክፍል የታመመ ያህል ነው የሚሰማው:: በሬ ለገበሬ ሁሉ ነገሩ ነው::
ገበሬዎች በተገናኙበት አጋጣሚ ሁሉ የሚያወሩ ስለበሬዎቻቸው ነው። በአንጻሩ ደግሞ በሬ የሌለው ሰው ከገበሬዎች ጋር ሲሆን ምን እንደሚያወራ ግራ ይገባዋል። በሬ ያለው ገበሬ እንደ ታታሪ ገበሬ የሚታይ ሲሆን፤ የሌለው ደግሞ በየአረቄ ቤቱ የሚዞርና ሰነፍ ተደርጎ ይወሰዳል። ገንዘቡንም በመጠጥ ይጨርስና ሲቸግረው ልመና ይገባል፤ ወይም ደግሞ ገበሬዎች የጽዋ ማህበር (ሰንበቴ) ሲያደርጉ በየቤተ ክርስቲያኑ እየዞረ ይቀላውጣል። በዚህም ጠላና የእንጀራ ፍርፋሪ ይሰጠዋል። እንዲህ ዓይነቱን ገበሬ ነካ ለማድረግ ገበሬው እህል ሲያበራይ የበሬውን ትከሻ ይዞ እንዲህ ይላል::
በርዬ አንተን ያጡ
ጎንዬ አንተን ያጡ
አተላ ጨለጡ
ማህበር ቀላወጡ
እያሏቸው መጡ::
ገበሬ የበሬውን ውለታ በማመስገን ይገልጻል:: በሬ ከሌለው ሕይወቱ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ በማመን እንደ ሕጻን ልጅ ‹‹እሹሩሩ›› ብሎ የማዘል ያህል ነው የሚንከባከበው:: የበሬውን ውለታም ከሥራ በኋላ ማታ ቤት ውስጥ ተሰባስበው ያወሩታል:: በበራይ ወቅት ደግሞ አውድማ ውስጥ እንዲህ ይለዋል::
እሹሩሩ ጎኔ
እሹሩሩ ጎኔ
የበሬን ውለታ እንጫወት ማታ
እየበላን ንፍሮ በሰፊ ገበታ።
ገበሬ ከበሬው ጋር በስሜት የሚግባቡ ነው የሚመስለው:: ሲደሰት ይደሰታል፤ ሲከፋ ይከፋል:: እርግጥ ነው ሰውየው በበሬው መደሰት ሊደሰት በበሬው መከፋት ሊከፋ ይችላል:: በሬው ግን እንስሳ ነውና ባለቤቱ ሲደሰት ይደሰታል፤ ሲከፋ ይከፋል ተብሎ አይታሰብም:: ገበሬው ግን በሬው አብሮት እንደሚደሰትና እንደሚከፋ ነው የሚያስበው:: ለዚህም ይመስላል እንዲህ እያለ አንጀት የሚበላ እንጉርጉሮ ያንጎራጉራል::
አለኝ አንድ በሬ እንደኔው የከፋው
የሆዴን ብነግረው የጉንጩን ሳር ተፋው!
አንዳንድ ገበሬዎች ገንዘብ ሲያገኙ በሬ ከመግዛት ይልቅ የጦር መሳሪያ ይገዙበታል። የዚህ ዓይነት ገበሬዎች ደግሞ ከመጠጥ ቤት አይወጡም። አንድ ቀን ይሰክሩና ሰው ይገሉበታል። ከዚያውም ከነዘመዶቻቸው ይሰደዳሉ። ገዳዩም ይታሰራል ወይም የሟች ወገኖች ይገሉታል። የዚህን ዓይነት ሕይወት አስከፊነት ታታሪ ገበሬ በጣም ይጠላዋል። ልጆቹና በሬዎቹ እንዲሰቃዩ አይፈልግም። ይህን ለግብርና ያለውን ፍቅርም እንዲህ ሲል ይገልፀዋል።
እኔ አልገዛም ክላሽ ጦሱ ይተርፈኛል
እኔ አልገዛም በቅሎ … ይገማኛል
የበርዬ ትንፋሽ ሽታው ደስ ይለኛል።
ሰነፍ ገበሬ ገንዘቡን ከበሬ መግዣነት ይልቅ ለሌላ ጥፋት ስለሚያውል ከጓደኞቹ በታች ይሆናል። እህል ሊበደር ከታታሪ ገበሬ ደጅ ይጠናል። ድሃ መሆኑን የሚያውቁ ሁሉ ተገቢውን ክብር አይሰጡትም። አካባቢያዊ በዓላት ሲከበሩ ከሱ ቤት አይደገስም። ከደገሰም ተበድሮ ነው። ብድር ካላገኘም ከታታሪ ገበሬዎች ቤት እየሄደ ጠላ ስጡኝ ይላል። ለእንዲህ ዓይነቱ ሰው ነው ገበሬው እንዲህ ያለ::
በሬ አንተን የጠላ ጎኔ አንተን የጠላ
የገና የጥምቀት ይለምናል ጠላ::
ምነው በቅዳሜ ምነው በእሑድ ቢያርሱ
ከባለ ፀጋ ቤት ከሚመላለሱ::
ገበሬው በሆነ አጋጣሚ በሬውን ቢያጣ አንድ አካሉ እንደጎደለ ነው የሚቆጥረው:: በጣም ይደነግጣል:: ለዚህም ነው እንዲህ የሚለው::
በርዬ አንተን አልባ
ጎንዬ አንተን አልባ
አይኔም አያይልኝ
ጆሮዬም አይሰማ!
የበሬ የሥራ ትጋት ከሰዎችም ሆነ ከሌሎች የቤት እንስሳት ይበልጣል:: ለዚህም ነው ገበሬው አብዝቶ የሚያወድሰው:: በእርሻ ወቅት ያርሳል፤ በእንዲህ አይነቱ የመኸር ወቅት ደግሞ ያበራያል:: ለዚህ ውለታውም እንዲህ እያለ ያወድሰዋል::
በሬ እንደ አንተ የሚሆን የሚሽከረከር
ጎኔ እንደ አንተ የሚሆን የሚሽከረከር
እንዝርትም አይገኝ ከፈታይ መንደር::
በርየ ሲሰራ ጎንየ ሲሰራ
ይመስላል ደብተራ
ቤተ ክርስቲያን ገብቶ ቅኔ የሚመራ
በግብርና ሥራ ውስጥ ሌሎች የቤት እንስሳትም ሚና አላቸው:: ለምሳሌ የተወቃውን እህል በሸክም ወደቤት የሚያደርሱት የጋማ ከብቶች ናቸው:: በተለይም ከመኖሪያ ቤት ርቆ የሚመረት ምርት የጋማ ከብቶች ከሌሉ ለማስገባት ያስቸግራል:: ለሸክም የሚያገለግሎት አህያ፣ በቅሎ እና ፈረስ ናቸው:: እዚህ ላይ ታዲያ ከፍተኛውን ሚና የተወጣው በሬ ይረሳና ፈረሶች ይመሰገናሉ:: ምክንያቱም የመጨረሻውን ምርት ተሸክመው ስለሚመጡ ነው:: በዋናነት የሚፈለገው ደግሞ ምርቱ ነው:: ይሄ ሁሉ ሲሆን ግን ገበሬው የበሬውን ውለታ አይረሳም:: አንተ ባታርሰው ኖሮ፣ አንተ ባታበራየው ኖሮ ፈረሱ ከየት የመጣ ምርት ነው የሚሸከም በማለት ይመስላል እንዲህ ይላል::
የበሬን ምስጋና ወሰደው ፈረሱ
ከኋላ ተነስቶ ከፊት በመድረሱ
ታታሪ ገበሬ ምርቱን የሚሰበስበው በወቅቱ ነው:: ከሰው ኋላ መቅረትን አምርሮ ይጠላል:: ሌሊት እና ቀን እያለም ቢሆን ይሰበስበዋል:: ለዚህም ነው በሬውን እንዲህ የሚለው::
መኸር ተከወነ ገባ በየቤቱ
‹‹አውውው›› አለ ጅቡ እኔ ነኝ እራቱ
በማለት ‹‹እባክህ ቶሎ እንጨርስ›› እያለ በሬውን ይማጸነዋል:: አንተ ካላገዝከኝ ውጭ አመሻለሁና ጅብ እንዳይበላኝ ማለቱ ነው::
ከዚህ በላይ ለመሄድ የዚህ ዓምድ ገጽ አይፈቅድልንም:: ከመሰናበታችን በፊት ግን አንድ ነገር ልብ እንበል:: እነዚህ የቃል ግጥሞች ሲወርድ ሲወራረድ በቃል የተላለፉ ናቸውና ከአካባቢ አካባቢ ልዩነት ሊኖራቸው ይችላል:: በሌላ በኩል ደግሞ ጥቅምት የመኸር ወቅት የሚሆነውም በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ላይሆን ይችላል:: በተለይም በደጋማ አካባቢዎች እስከ ጥር እና የካቲት ድረስ ይቆያል:: የጥቅምትና ሕዳር መኸር ወቅትነት እና እነዚህ የቃል ግጥሞች በብዛት በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ ናቸው::
በቀጣይ በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ የጥበብ ሀብቶችን እናስነብባችኋለን፤ መልካም የመኸር ወቅት!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2014