በመስከረም ጉርሻ

በመስከረም ጥባት፣ በወጋገኑ የሌት ንጋት በአደይ አበባ መሃል ፀዓዳውን ሸማ ተጎናጽፋ ለቆመችው ጥበብ፤ የኪነ ጥበብ የፍቅር ገጸ በረከቶች እልፍ ናቸው። ያረሰረሳትን ክረምት ሸኝታ በልምላሜ እንቡጥ ፍሬን እንደምታበቅለው፣ በፍካት ሳር ቅጠሉን እንደምታወዛው ምድር፤ ጥበብም እንዲሁ ናት። በወርሃ መስከረም እንቁጣጣሽ፣ በወርሃ መስከረም መስቀል ስር ያለች ጥበብ ጥጋብ ሀሴትን እንጂ እጦት ቁዘማን አታውቅም። ሸማው ካይነት ዓይነቱ፣ ከውበት ደምግባቱ ሙሉ ነው። ነብስን ከምታነጻው ውበት ጋር ስጋና አጥንትንም የሚያለመልሙ እልፍ ጉርሻና ቅምሻዎችም በመስከረም ይበረክታሉ። የምድር በረከት፣ የነብስ እርካታ ከጥበብ ጓዳ ውስጥ ይከታተላሉ። ከሞላው ነገር ላይ መርጦ፣ ከመረጡትም ላይ ጨልፎ ማቅረቡ የዓይን አዋጅ እየሆነ ልብን ቢያዋልልም መምረጡም፣ መጭለፉም እያዳገተም ቢሆን ግድ ነውና አስቀድመን ወደ መጽሐፍት ዓለም በረከት ለማምራትና ከተሰጠን ለመጉረስ ልብ ታጥበን እንሰናዳ። መቼም አንዲት ጉርሻ ታጣላለች እንደምንለው ሁለተኛውን ከመስቀል ክብረ በዓል የቤተ ጉራጌዎቹን ደጅ እረግጠን ከእጃቸው ላይ ቀምሰን እንጎርሳዋለን።

“ጉርሻና ቅምሻ”

በመጀመሪያው የጉርሻ እጅ የተጠቀለለው የመስከረም ወር አንደኛው ገጸ በረከት “ጉርሻና ቅምሻ” የተሰኘ የግለ ታሪክ መጽሐፍ ነው። የዚህ መጽሐፍ ደራሲና የግለ ታሪኩ ባለቤት የሆነው ደራሲ ማቲያስ ከተማ (ወለላዬ) ከአሁን በፊት የሀገሩን አፈር ለመጨረሻ ጊዜ የረገጠው ከ20 ዓመታት በፊት ነበር። ከሀገሩ ባህልና ወግ ሥርዓት ጋር ተሰነባብቶ የባዕድ ውሀ ቢጠጣም ልቦናና ምናቡ ግን ሀገሩ ላይ ከጠጣው በስተቀር ሌላ የጠማቸው አይመስሉም። ከዚህ ቀደም ደራሲውን በምን ሥራው እናስታውሰው ይሆን ብለን ካልን “የኔ ሽበት” በተሰኘው የግጥም መድብሉ ነው። ይህቺን የግጥም መድብል ሲያሳትማትም ሀገር ውስጥ አልነበረም። በጊዜው የሲውዲን ነዋሪ ነበር። አንድ ጊዜ የወጣውን እግሩን የመለሰውም አዲሱን የግለ ታሪክ መጽሐፍ ይዞ በቅርቡ ሲመለስ ነው። እንግዲህ በግጥም መድብሉ እያስታወስን በድርሰቱ ልናነሳው ነው። መጽሐፉ በሚያጎርሰን የብዕር እጅ ውስጥ ጉርሻ ሙሉ ጥጋብ፣ ቅምሻ ሙሉ ጥፍጥና አለው። እሁድ መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም በርካታ የኪነ ጥበብና የስነ ጽሁፍ ጠቢባንን ከወመዘክር አዳራሽ ውስጥ አሳድሞ ለመመረቅ በቅቷል።

ከጠለቀው የልጅነት ጀንበር ከትውስታ ጉድባ ላይ ተቀምጦ የኋልዮሽ ትዝታውን ያወሳበታል። ሙሉ ለሙሉ በእውነተኛ ታሪክ የተሰመሩ ይዘትና ጭብጦች ያሉት ግለታሪክ ሲሆን ታሪኩም ከልጅነት ትውስታ እየፈለቀ፣ ከወጣትነት ቁልቁለት ላይ እየፈሰሰ በስደት ወደ ባሕር ማዶ ይነጉዳል። ዓመታት ላይመለሱ ፊቱን ይዘው ሲገሰግሱ ከሀገሩ ባሕልና ወግ ቢያርቁትም የደራሲውን ትዝታዎች ሊፍቁት ግን አልተቻላቸውም። በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቃለሉት ታሪኮችና መቼቶቹ ከአሁኑ ዕድሜው ጋር ሲስተያይ፤ ከነበረባት ሲውድን የኢትዮጵያን ያህል የተራራቁ ቢሆንም ሲጽፍ ግን በምናብ ትውስታ ሳይሆን በዓይኖቹ እየተመለከተ የነበረ ያህል ነው። አብዛኛዎቹ ሴራዎችና መቼቶች ከዚህቹ የአዲስ አበባ ውጥንቅጥ ውስጥ እየተጋፉና ከሰማይዋ ላይ እየተሽከረከሩ ወደ አንዲት ሸበቶ መንደር ይወስዱናል። ልጅነቱን የቦረቀባት፣ ሕይወትን በፊደላት ያጣጣመባት የቀድሞዋ ውቢት ኮረዳ፤ መርዕድ አዝማች ስብስቴ ነጋሴ ትምህርት ቤት ዙሪያ የትዝታ ክንፉን እየጣለና ከመንደሩ ማኅበረሰብ ጋር ከተጋመደው የኑሮ ዘዬና ወግ ባሕል ጋር ተጣብቆ ትናንትን በዛሬ ይመለከታታል። አይረሴ የትዝታ ማዕድ ጉርሻና ቅምሻዎቹንም የምናገኘው ከዚሁ ነው።

የተለያዩና በርከት ያሉ የታሪክ አቁማዳዎችን ባነገተው “ጉርሻና ቅምሻ” የግለታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ይበል የሚያሰኙ አዳዲስ እይታና የአጻጻፍ ስልት ይታይበታል። አዳዲስ ታሪኮችን ለማንበብ የመጀመሪያዎቹን ገጾች በገለጥን ቁጥር በስንኝ ተቋጥረው በጭብጡ አስኳል የተቀመሙ ግጥሞችን እናገኛለን። በሀገራዊ ቃናና በትኩስ ሽታ የታጀበው ጭብጥ፤ የትዝታው የኋልዮሽ ዳራ የደራሲውን ሳይሆን የግላችን የሆነውን የኛን ታሪክ የምናነብ ያህል እንዲሰማን አሳምኖበታል። ቦርቀቅ ያሉና ሰፊ የሚመስሉ ታሪኮችን ቅልብጭ አድርጎ በሁለትና ሦስት ገጾች ብቻ በሚጣፍጥ ለዛ አኑሯቸዋል። በአንድ የግለ ታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ገጸ ባህሪያቱ ከእውኑ ማንነታቸው ጋር እንዳይጋጩ በማድረግ መሳጭና ተወዳጅ ማድረጉ ልዩ ብቃትን የሚሻ ነው። ትውስታዊ እንጂ ምናባዊ ባለመሆናቸው ደራሲው እንዳሻው ሊስላቸውና ሊወክላቸው አይችልም። በጉርሻና ቅምሻ ውስጥ የምናገኛቸው አብዛኛዎቹ ገጸ ባህሪያት ደራሲው ኖረው ያለፉትን የጻፈው ሳይሆን የጻፈላቸውን የኖሩ ያህል ማራኪ ናቸው። አንዳንዶቹን ከመጽሐፉ ነጥለን በረዥም ልቦለድ ውስጥ ለማየት የምንቋምጣቸው ዓይነት ሆነው እናገኛቸዋለን።

መጽሐፉ ከተሸከመው የታሪክ ቋጥኞች መካከል አሁንም አንድ ጉርሻ ለጥል ነው እያልን ሁለቱን ብቻ እንቀማምሳቸው። ጉርሻው የሚያንቅ ቢሆንም የመጀመሪያው “ጥላ ወጊ” ነው። ለመሆኑ “ጥላ ወጊ” የምትል አዛውንት ፈሊጥ የሰማንም ሆን የምናውቃት ስንቶች እንሆን…ለማንኛውም በዚህ አርዕስት ስር ባለታሪኩ ደራሲ የሚነግረን ነገር ሁሉ ወደ እንጭጭ ልጅነቱ ይወስደናል። በልጅነቱ ጀምሮም በልጅነቱ ያከትማል። ጥላ ወጊው ግን የመንደሩ ሽማግሌ የነበሩ ባሻ አግዴ የተባሉ ሰው ናቸው። ነጭ ወረቀት በመሰለው የልጅነት አዕምሮው ውስጥ ያስቀመጠላቸው ጥላቻና ቂም ነበር። ጥላ ወጊ ናቸው ሲባል ሰምቷል። እንዲያውም የአባቱን ጥላ ወግተው የገደሉት እሳቸው እንደሆኑ ስለሰማ ከዚያን ከሰማበት ቅጽበት ጀምሮ ለሰውዬው ከጽኑ ጥላቻ በስተቀር ምንም አልነበረውም። “…እናቴ ግን በምታገኛቸው ጊዜ ቆማ ሰላምታ ሰጥታ ስለቤተሰብም ተጠያይቃ መለያየቷ ግርም ይለኛል። እኔ ግን ገና ና! ሳመኝ ማሙሽ ሲሉኝ ብሞት አልስማቸውም። …የአባቴን ጥላ የወጉ እኔንስ ቢወጉኝ…አንድ ቀን አመሻሽ ላይ ልጫወት ከቤት ስወጣ ባሻ ብቻቸውን ጀርባቸውን ለቤታችን ሰጥተው ቆመው አገኘኋቸው። ብደነግጥም ቀስ ብዬ እቤት ተመልሼ የእናቴን ሽንኩርት መክተፊያ ቢላ ይዤ ወጣሁ። ባሻ እዚያው እንደቆሙ ናቸው። ቀስ ብዬ ተጠጋኋቸው። አላዩኝም። ከኋላቸው የተዘረጋውን ጥቁር ጥላቸውን ሁለት ጊዜ በቢላው ወግቼ ማንም ሳያየኝ እቤት ተመለስኩ…” እያለ የልጅነትን ቂልነት በሚጣፍጥና ድገሙኝ! በሚያስብል መልኩ አቅርቦታል።

ከሁለተኛው ቅምሻ ትዝታን ብናጣጥም “የስብስቴ

 ትዝታ” ነው። ከትረካው ጅምር ፊት ይህቺ ግጥም ጉብ! ብላበታለች…

ይሞታል የሰው ልጅ ሁሉም ቀኑ ሲደርስ፤

ክፉም ደግም ቢሆን መቼም ትዝታ አይፈርስ።

እኔም ይኼን ታሪክ በልቤ ቋጥሬ፤

ጊዜው ፈቀደና ዘረገፍኩት ዛሬ።

ከዘረገፈው ትዝታ የሆነው “የስብስቴ ትዝታ” የደራሲው የልጅነት ትምህርት ቤቱ ጣፉጭ የጉርሻ ሕይወት አጋጣሚዎቹን የሚያወሳ ታሪክ ነው። በዚህ ውስጥ ከእርሱ በላይ የብዙዎችን እውነተኛ ትዝታ የሚቀሰቅሱ አጋጣሚዎችና የተጠቀሱ ስሞች አሉበት። ንፋስ ስልክ መርዕድ አዝማች ስብስቴ ነጋሴ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ከማይዘነጋቸው መምህራኖች መንደርደሪያ አድርጎ በመነሳት ከአንደኛው ልዩ መምህሩ ጋር ትረካውን ያጠነጥነዋል። “…ከትምህርት ቤቱ አስተማሪዎች መካከል ቆዳ እያሉ የሚሳደቡት ቲቸር ሐጎስ፣ ትምህርት ቤት ተዘግቶ ሲከፈት አንደኛው ዓይኑ ጠፍቶ ጥቁር መነጽር አድርጎ የመጣው ቲቸር መንግስቴ ጀርጀራ…ሳሙኤል አቤ (ሚስተር ጎት) …መልኩን አሳምሮ እንደ ወሎ ፈረስ፣ ንግግር አያውቅም ድረስ የሚላት ነገር ነበረችው። እነዚህ ሊረሱ የሚችሉ አስተማሪዎች አይደሉም። …ወደ ስድስተኛ ክፍል እንዳለፍኩ አንድ የክፍል ኃላፊ መምህር ገጠመኝ። …ከሁሉም አስተማሪዎች ጎስቆል ብሎ የሚታየው እሱ ነው። ሆኖም መኪና ያለው ደግሞ እሱ ብቻ ነው። …አንድ አስተማሪ ወይ ይወደዳል ወይ ይጠላል። እሱን ግን እናክብረው እንወደውና እንፈራው ነበር። ምክንያቱም የተማሪ ስም አይጠራም። …ማስተማር በሚጀምርበት ጊዜ ግን አንዲት ኮሽታ አይፈልግም…” እያለ የሚቀጥለው ግለታሪክ ወስዶ ከአንድ ታሪካዊ ሰው ጋር ያገናኘናል። በደርግ አብዮት ወቅት የመጀመሪያውን ታሪካዊ ጥይት የተኮሰው እሱ ነው የሚባለው የበላይነህ ክንዴ ታሪክ ነው። ትንሹ ማቲያስ ከኢሕአፓው በላይነህ ክንዴ ጋር ቀደም ሲል የነበረው የተማሪና አስተማሪ አጋጣሚ የሚያወሳ ታሪክ ነው።

“ጉርሻና ቅምሻ” ከአርትኦት ሥራው ጀምሮ ጥንቅቅ ያለ ግሩም መጽሐፍ ስለመሆኑ በምረቃው ዕለት ተገኝተው ከሙያቸው ሀሳብ የሰነዘሩ ሁሉ አመስግነውታል። ኃይለ መለኮት መዋል “አበጀህ!” ሲል ስሜቱን በአንዲት ቃል ቋጫት። “ፈረንጅ ሀገር የተቀመጠ ሰው ኢትዮጵያዊ ድርሰት ይዞልን መጣ። እዚህ ያለን እኛ ግን ብዙዎቻችን ይህን ማፍራት አቅቶናል” ያለው ደግሞ ጸሀፊ ተውኔት አያልነህ ሙላት ነበር።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You