የመስከረም የጥለት ሸማ ከፍ እያለ ከወገቧ ደረስኩ ደረስኩ ከሚለው የመስቀል ቅላጼ ጋር ይዞን ወደሀገር ቤት መንጎዱ የማይቀር ነው። የተሳለ ትዝታና ስል ትውስታ ያለበት ሁሉ አካላቱ እንጂ ነብስና መንፈሱ ከከተማው ጫጫታ መሀል መሆንን እንደ ኩነኔ ያስጨንቀዋል። መስቀል ሲመጣ ጉራጌ፣ ጉራጌ ሲባል መስቀል ይታወሰናል። ዓመቱን ሙሉ ከቀዬው እርቆ፣ ከሥራ ተጣብቆ የከረመው የጉራጌ ልጅ፤ የመስቀል መዳረሻ ብስራት ከሚበሰርበት የመስከረም ጥባት አንስቶ የቻለ በአካለ ስጋ ያልቻለም በሀሳብ ወደቀዬው ይተማል። የሀገር ቤቱ ጠረን በምናቡ ሽው እያለበት ናፍቆቱ ተቀስቅሶ ሽቅብ እየገነፈለ ልቡ መሄድ መሄድ ያሰኘዋል። እኛም ከሚነጉደው ጋር ነጉደን ከጉራጌዎቹ መስቀል ጥበብ የምትሰጠንን “አዳብና” ተቀብለን ጥቂት ብንጫወት ደስታ ነው። የዘንካታዎቹ ወጣቶችና ጉብል ልጃገረዶች ጨዋታ እንደደራ ሰንጋው ተጥሎ ከክትፎው ጉርሻ በፊት በቅቤና አዋዜ ነዶ የሚቀርበው ቅምሻ አላቸው። በልተን ጠጥተን በጨዋታው አዋዝተንና አወራርደን በአዳብና ሸማ ደምቀን እንመለስ። “አዳብና” ቀደም ሲል አዳምና ሔዋን የሚል የስም ትርጓሜ የነበረው ስለመሆኑ የጉራጌ ነገር አዋቂ ሽማግሌዎች ይናገሩታል። ብዙ የታሪክ ጥናቶች እንዲሚያስረዱት ከሆነ 800 ዓመታትን አልፎ የዘለቀ ድንቅ የባሕል ቱባ ነው። በቤተ ጉራጌ ውስጥ የክስታኔዎች ልዩ መገለጫ ነው። በመስቀል ሰሞን ወጣት ወንዶችና ጉብል ልጃገረዶች በሕብረ ባህላዊ ጥበብ በጋራ የሚያሸበርቁበት ነው። ይህን ሁሉ ዓመታትን አስቆጥሮ ዛሬን ቢደርስም ከእንግዲህ ወዲያ የሚያስቆጥረው ሌላ የዘመን ዕድሜው ጠፍቶ ለመቆረጥ ደርሶ ግን ነበር።
የመስቀል በዓል ጥበባዊ የባሕል ትውፊት ከሆነው የአዳብና ጨዋታ ፈርጁ ብዙ ነው። በዋናነትም ከማይጠገበው የጉራጊኛ ጭፈራ ጋር ይጀምራል።
የጭፈራ ስልቱና ዓይነቱም አንድ አይደለም። “የቦላላ” ሞቅ ደመቅ ብሎ ይቆማል። “ጉሮሮ” እና “ማንጎሮም” ከጣፋጮቹ የጭፈራ ገበታዎች መካከል ናቸው። ታዲያ አይጠገቤው ጭፈራ ሲቀርብ የጆሮ ታምቡር በሚበጥስና ልብን በሚያነጥር ዘመን አመጣሽ ስፒከር አይደለም። ድመጸ መረዋ ከሆኑት ወጣቶች መካከል ለግጥምና ዜማ ይሰናዳሉ። በከበሮ ዓመታታቸው ቀልብን ከሚሰውሩት አንድሩን ለማንደር ከአንገት አንግተው ይጠባበቃሉ። የዚያን ሰሞን የክስታኔዎች መንደር ዓለም ዘጠኝ ብቻ አይደለችም። ወጣቶቹ የደስታን ጥግ የሚያጣጥሙበት ነው። ልጃገረዶቹ በነጻነት ዓለም ውስጥ ይንፏለላሉ። ምንም ዓይነት የቤተሰብ ጫና የማኅበረሰቡ ተጽዕኖ አይኖርባቸውም። የታላቋን የቃቄ ውርድዎት ራዕይዎች እውን ሆነው የሚታዩበትም ጭምር ነው። ለአብነትም ሴት ልጅ ውሀ አጣጯን መምረጥ ያለባት ራሷ ናት የሚለውን እሳቤዋን ከፍ የሚያደርጉ ትጭጭቶች በክብረ በዓሉ ላይ የአዳብና አካል ናቸው። በዚያን ሰሞን እንኳን ወጣቱንና ጭፈራው ራሱ ብቻውን አይቆምም። በግራና በቀኝ ያጀቡት ማድመቂያዎች ካዳሚ ናቸው። አጋት ዝላይ፣ ሰባ፣ ነጆ አራጆና ብትር ዝላዮች የወንዶቹ ለአቅመ አዳም ደርሻለሁ ማብሰሪያ ናቸው። የጉብሏን ልብ ለማዘለል በተለይ ብትር ዝላዩን በድል መወጣትና ብቁነቱን ማሳየት ይኖርበታል።
ጥንታዊውና 8 መቶ ያህል ዓመታትን የዘለቀውን የአዳብና ሥርዓትን የሞት አፋፍ ላይ ደርሶ ከገደሉ ለጥቂት ተርፏል። ቀደም ካለው ደማቅ ክንውን እየራቀና እየደበዘዘ መጥቶ ደብዛው ሳይጠፋ መትረፉ እድሜ ለአንድ ማኅበር ያሰኛል። የጉራጌ ክስታኔ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ማሕበር ለዚህ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። በ2013 ዓ.ም ማሕበሩ ሲመሠረት በጥቂት የበጎ ፈቃድ ወጣቶች ነበር። ከሀገር ወጭና በሀገር ውስጥ የሚገኙ ቤተ ጉራጌዎችን በማሰባሰብና በማቀናጀት አባላቱን አብዝቶ ጉልበቱንም አጠንክሯል። ከተነሳበት ዓላማ አንዱ በሆነው የጠፉ የባሕል ትውፊቶችን ዳግም በመቀስቀስ ግብሩ ከአዳብና ጋር ተገናኝቶ ስሩን ደረሰበት። ከአፈር በታች ለቀብር የተሰናዳውን ቱባ የጥበብ ትውፊት እጁን ይዞ አስነሳው። ላለፉት ሦስት ዓመታት አዳብና በክስታኔ መንደሮች ውስጥ በፌስቲቫል ደረጃ ሲከበር ቆይቷል። ባለፈው ዓመት በጢያ ትክል ድንጋይ ዙሪያ በተደረገው ክብረ በዓል ላይ ብዙኀኑን ባስደመመውና በአፍሪካ ድንቃድንቅ ላይ በሰፈረው ግዙፍ የክትፎ ቁልል ላይ የሀሳቡ ፊታውራሪዎች እኚሁ የጉራጌ ክስታኔ ዓለም አቀፍ የወጣቶች ማሕበር አባላት ነበሩ። በዚህ ሳይቆሙ አሁን ደግሞ አዳብናን በዩኔስኮ ለማሰፈር ደፋ ቀና እያለሁ ይገኛሉ። ማን ያውቃል በቅርቡ ደግሞ በዩኔስኮ ማሕደር ውስጥ የራሱን ኮታ ይዞ ከሚገኘው የመስቀል በዓል እቅፍ ውስጥ አዳብናን የምናገኘው ይሆን ይሆናል።
ከሞት ጥላ አምልጦ ዳግም ተወዳጅና ተናፋቂ ለመሆን የበቃው የአዳብና ክብረ በዓል ከመስከረም 16 እስከ ጥቅምት 5 ቀን 2017 ዓ.ም በምሥራቅ ጉራጌ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ባማረና በተዋበ መልኩ ይካሄዳል። በድምቀት ከሚከበርባቸው አንዷ የሆነችው የኬላ ከተማ መስከረም 18 ቀን “የተንቢ!” እያለች እጇን ዘርግታ ታላላቆችን ለመቀበል አሰፍስፋለች። መስቀል በጉራጌ፣ ጥበበን በባሕል፣ ክትፎውን በጉርሻ፣ ጨዋታውን በፌሽታና ደስታ ካሉ በመስከረም ከዚህ ወዲያ ጥጋብ ምን ይኖራል…
አዲስ ዘመን ሐሙስ መስከረም 16 ቀን 2017 ዓ.ም