አሸባሪው ሕወሓት የዛሬ ዓመት በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የሰነዘረውን የክህደት ጥቃት ተከትሎ አደጋ ውስጥ ገብቶ የነበረውን የሀገር ህልውና የህግ ማስከበር ዘመቻ በማካሄድ አደጋውን መቀልበስ ችሏል። የህግ ማስከበር ዘመቻውን አስመልክቶም እውነታውም የሚያጠለሹ ፤ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ ግራ የሚያጋቡ የሀሰት መረጃዎች በአሸባሪው ቡድንና አብረውት ሰልፈኛ በሆኑ አገራት ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና የመገናኛ ብዙኃን ሲናፈሱ ቆይተዋል።
ከነዚህም ውስጥ በግጭቱ ወቅት በመንግሥት ኃይሎች የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል ፤ መንግሥት ረሃብን ‘የጦርነት መሳሪያ’ አድርጎ ተጠቅሞበታል ፤ በትግራይ ውስጥ ሆን ተብሎ በመንግሥት ለህዝቡ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ ተከልክሏል የሚሉ ክሶች በስፋት ተደምጠዋል ፤ ዛሬም እየተደመጡ ነው።
እነዚህን ክሶች ከጉዳዩ ጋር ቅርበት አላቸው የሚባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ ፣ ከተመሰረቱበት መርህ ወጥተው ፍጹም ባልተገባ መልኩ በማስተጋባት በመንግሥት ላይ ጫናዎችን ለማሳረፍ በስፋት ተንቀሳቅሰዋል።ይህንኑ መሠረት የለሽ ክስ አንቱ የተባሉ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ ያለ ተጨባጭ መረጃ የእለት ተእለት ዘገባቸው አካል አድርገው ሲያስጮሁት እንደነበርም ይታወሳል።
አንዳንድ ሀገራትም ይህንኑ መሰረተ ቢስ ክስ ከማጣራትና እውነታውን ከማፈላለግ ይልቅ፤ እንዳለ ተቀብለው በመንግሥት ላይ ያልተገቡ ጫናዎችን ለማሳደር ደፋ ቀና ሲሉ ታይተዋል ፤ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥም ማዕቀቦችን የጣሉ ፤ለመጣልም ዳር ዳር የሚሉ አገራት አሉ ።
አሸባሪው ቡድን ግጭቱን “መብረቃዊ ምት” በሚል ስያሜና ዕቅድ የክህደት ጥቃት እንደጀመረ በአደባባይ አፉን ሞልቶ በእብሪት እየተናገረ ባለበት ሁኔታ ፤ እውነታውን በአደባባይ ላለመቀበል፤ ተቀብሎም ቡድኑን ተጠያቂ ላለማድረግ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ አቅም አጥተው የሚያንገራግሩም ብዙ ናቸው።
በማይካድራ በሚገኙ ንጹኃን አማራዎች ላይ ብሔርን መሰረት ተደርጎ የተፈፀመው ጭፍጨፋ ብዙም ስሜት ያልሰጣቸው ፤ ስለ መፈጸሙም አፋቸውን ሞልተው ለመናገር አንደበት ያጡም ብዙ ነበሩ። የወንጀሉ አድራሾችን ከማውገዝ አንስቶ ተጠያቂ ለማድረግ የነበረው ዳተኝነትም የአደባባይ ሚስጥር ነው ።
ይህ ሁሉ በሆነበት ፤ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በመርህ ይገዛሉ የሚላቸው ተቋማቱና የመገናኛ ብዙኃኑ ሳይቀሩ እውነታውን ከመካድ አንስቶ በማድበስበስ አሸባሪው ሕወሓት ስለ ግፍ ሥራው ዓለም አቀፍ ውግዘት እንዳይደርስበትና ከጀመረው የጥፋት መንገድ እንዳይመለስ አቅም ሆነውት ቆይተዋል። ይህም ቡድኑ በወንጀል ላይ ወንጀሎችን በእብሪት እንዲፈጽም አድርጎታል።
እውነታው ግን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጽሕፈት ቤት በጉዳዩ ዙሪያ በጋራ ባደረጉት ምርመራ ትናንት ለአደባባይ በቅቷል። በዚህም በመንግሥት ላይ በተቀናጀ መልኩ ሲካሄዱ የነበሩ ክሶችና ውንጀላዎች መሰረተ ቢስ እንደሆኑ በተጨባጭ ማየት ተችሏል።
የተቋማቱ የጋራ ምርመራ ሪፖርት እንዳረጋገጠው ፤ በግጭቱ ወቅት መንግሥት የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን ማረጋገጥ አልተቻለም፤ ረሃብን ‘እንደ ጦር መሳሪያ’ ይጠቀምበታል ፤ በትግራይ ውስጥ ሆን ተብሎ መንግሥት ለህዝቡ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ ከልክሏል እንዲሁም የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ተፈጽሟል የሚሉ የሀሰት ክሶችም መሰረተ ቢስ ስለመሆናቸው ተረጋግጧል ።
በመከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመክፈት ጦርነት የከፈተው የሽብር ቡድኑ ሕወሓት ከጥቅምት 27 እስከ 30/2013 በማይካድራ የሚኖሩ አማራዎችን በመለየት የዘር ጭፍጨፋ መፈፀሙን ፤ በጭፍጨፋው ሳምሪ ከተሰኘው የወጣቶች ገዳይ ቡድን በተጨማሪ አካባቢውን ያስተዳድር የነበረው የሕወሓት መዋቅር ውስጥ ያሉ የቀበሌ አመራሮችና ታጣቂዎች በቀጥታ ተሳታፊ እንደነበሩ ይፋ አድርጓል፡፡ በጭፍጨፋው ከ1 ሺ በላይ ንፁሃንን በግፍ መገደላቸውን አስታውቋል፡፡
የተቋማቱ የጋራ የምርመራ ሪፖርት የመንግሥትን እውነት በተጨባጭ በአደባባይ ያረጋገጠ ፤ እውነትን በብዙ መሸፈን እና መካድ ቢቻልም ማጥፋት ግን እንደማይቻል፤ ሁሌም በመጨረሻ እውነት አሸናፊ ሆና ስፍራዋን እንደምትይዝ ማረጋገጥ ያስቻለ ነው።
የአሸባሪው ሕወሓት ማብቂያ የሌላቸው የውሸት ትርክቶች የቱንም ያህል አደባባዮችን የሞሉ ቢመስሉም በስተመጨረሻው የቡድኑ ርካሽ ባህሪ መገለጫ ከመሆን ባለፈ በራሳቸው ቆመው ለመሄድም ሆነ ረጅም መንገድ ለመጓዝ አቅም እንደሌላቸው በተጨባጭ ያመላከተ ነው።
የቡድኑን የውሸት ትርክቶች ተከትለው ዓለም አቀፉን ኅብረተሰብ ለማሳሳትም ሆነ በአገሪቱ ላይ ያልተገባ ጫና ለማሳደር ረጅም መንገድ እየሄዱ ያሉ ኃይሎችም ከአፍራሽ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፤ በቀጣይም ባልተጣሩ መረጃዎች በመንግሥትና በሀገር ላይ ተመሳሳይ ጫናዎችን ከማድረግ እንዲቆጠቡ አስተማሪ የሆነ የምርመራ ሪፖርት ነው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/2014