የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አገር የሚጠብቅ፣ ሕዝባዊ የሆነና የእያንዳንዱ ልጅ ነው። ነገር ግን ይህ ተክዶ ለሆዱ ያደረው አሸባሪው ሕወሓት በአጎረስኩ እጄን ተነከስኩ አደረገው። አንዴ ብቻ ሳይሆን ደጋግሞ ሸጠውም። በተለይ የጥቅምት 24ቱ ጉዳይ ደግሞ ሁሉንም ያመመና ያሳዘነ እንደነበር ዓመቱ ያስታውሰናል። ለመሆኑ ምን አይነት ስብዕና ቢኖረው በራሱ ጠበቃ ላይ ይህንን አደረገ ከተባለ መልሱን አሁን ግፍ እየደረሰበት ላለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ እንተወው። አረመኔው ሕወሓት ባህሪያቱ ልዩ ልዩ መሆኑን ኖረን እያየነውም ነው።
ይህንን እየመከተና ስልቱን እየተረዳ የሚታገለው መከላከያ ሰራዊት የዘመናት ጉዞው ምን ይመስል ነበር፤ ዛሬስ የሚሉትን ነገሮች እንዲተነትኑልን በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና የህግ መምህር የሆኑትን ዶክተር አለማው ክፍሌን አነጋግረናል። ያሉንንም እንደሚከተለው አቅርበነዋል። መልካም ንባብ!!
አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ሰራዊት የዘመናት ትግል፣ ስብዕናና አቋም ምን ይመስል ነበር?
ዶክተር አለማው፡– ከስሙ ስንነሳ የኢትዮጵያ ሰራዊት ሲመለመል እንኳን መስፈርት ያለው ነው። ስለዚህም በታማኝነት፣ በስነምግባር፣ በጀግንነትና በብቃት የተሰፈረ መሆን ይገባዋል። ምክንያቱም መከላከል፣ አገርን መጠበቅ ካልቻለ መከላከያ ሊባል አይችልም። ስለሆነም ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ ብናይ እንኳን እነዚህን መስፈርቶች ማሟላት ግዴታው ነው። የስልጣን ተዋረድን ጭምር ያከብራልም። በእርግጥ በዘመነ መሳፍንት ጊዜ ይህ እልቅና የሚሰጠው ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ ውስጥ ተመልምሎ ነው። መኮንን የሚሆኑም አብዛኞቹ የመኳንንቱ ዘር ናቸው። ይሁን እንጂ ምልመላው ቀረቤታን ብቻ የያዘ አይደለም። አገር ወዳድነቱ፣ ብቃቱና ስነምግባሩ እንዲሁም ጀግንነቱ በደንብ ይመረመራል።
በምልመላው ያለፈ ሰራዊት ትዕዛዝ ይቀበላል፣ አገሩን ያከብራል፣ ያስከብራልም። ነገሥታትና መኳንንት ቢሆኑም ከእነርሱ ይልቅ አገርን ያስቀድማሉም። ለመንግሥታቱ ሳይሆን ለአገር አገልጋይ እንደሆነ የሚሰማውና የሚሠራ ነው። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ ሰራዊቱ የተዋቀረበት ሁኔታና የተሰራበት መልክ ነው።
ወደ ንጉሡ ማለትም ወደ ኃይለሥላሴ ጊዜ ሲመጣም አገራዊነት ስርዓቱን አለቀቀም። ከመጀመሪያው የሚለየው በአመላመሉና በስልጠናው ሲሆን፤ ንጉሡ ከአውሮፓ አገራት ጋር በመተባበር የተለያዩ ዘመናዊ ስልጠናዎች እንዲያገኙ አስችለዋል። በአገር ውስጥም በርከት ያሉ ማሰልጠኛ ተቋማትን ለአብነት ሆለታ ገነትና ሐረር ሚሊተሪ አካዳሚዎችን በመክፈት ሰራዊቱ የሚሰለጥንበትን ሁኔታ ፈጥረዋል። ይህ ደግሞ ከባህላዊ ትምህርቱ ባሻገር ዘመናዊ እውቀት ያለው እንዲሆን አድርጎታል። በአደረጃጀት ጭምር ዓለምአቀፍ ተሞክሮን ያነገበ እንዲሆንም እድል ሰጥቶታል።
በንጉሡ ጊዜ ያለው ሰራዊት በመታዘዝ፣ በስነምግባር፣ በእውቀትና በጀግንነት ጠንካራ በመሆኑ መፈንቅለ መንግሥት ቢደረግም መንግሥትን መፈንቀል እንደማይቻል አሳይተዋል። ይህ ደግሞ አገርን የማዳኑ ነገር በስፋት የታየበት እንደነበር ያስታውሰናል። አገርና ሕዝብን መጠበቅ ምን እንደሚመስልም ያሳየ ሆኗል። ለዚህ ደግሞ በዋናነት የሚጠቀሰው የአድዋ ጉዳይ ነው። ጠንካራ ሰራዊት ባይገነባ ኖሮ የነጮች ራት እንሆን ነበር። መከላከያ የአገር ጠበቃና ደጀን እንዲሆን ተደርጎ ባይሰራ ኖሮ ቀኝ ተገዝተንም ነበር። ነገር ግን ከአወቃቀር እስከ ብቃትና አገር ወዳድነት ድረስ ያለው ጀግንነት ደማዊ በመሆኑ ሁሉም ነገር በድል ተጠናቋል።
የአድዋ ድል ሲመጣ ሰራዊቱ የተለየ ጥቅም አግኝቶ አይደለም። የተለየ ደመወዝም አልተከፈለውም። በቂ ስንቅ እንኳን ሳይቀርብለት ነው ለአገሩ የተዋደቀው። በቂ ስልጠና ያገኘም አልነበረም። ምክንያቱም የገጠመው ከጣሊያን ጋር ነው። በብዙ ነገር ይበልጡታል። አንዱን ብናነሳ እንኳን የግብዓት አቅርቦት እጅግ የተራራቀ ነው። በባህላዊ መሳሪያ ዘመናዊ መሳሪያ ገጥሞ ማሸነፍ ጀግንነት ከሌለበት ምንም ሊያመጣው አይችልም። ፍቅር ካላቆመው ማንም ሊታገለው አይችልም። ነገር ግን የነበረው ሰራዊት ከራሱ በላይ አገሩን የሚወድና ጀግንነትን የተላበሰ ስለሆነ ውጤቱን ለአገሩ አሳይቷል።
ዘሎ እሳት ውስጥ የገባው አገሩ ደሙ እንደሆነች ስለሚያምን ነው። ስለዚህም የዚያን ጊዜ ሰራዊት አገርን ቀድሞ የማየት አቅሙ የነበረው ነው፤ የበላይን ትዕዛዝ የማይንቅና እኔ ብቻ የማይልም እንዲሁም የስልጣን ተዋረድን የሚያከብር፤ ጀግንነት የተሞላም ነበር።
በደርግ ጊዜ የነበረውን ሰራዊት ስንመለከትም ይኸው ባህሪ የሚንጸባረቅበት ነው። ከንጉሡ የሚለየው እድገትና ግብዓት የማይቸግረው መሆኑ ነው። ምክንያቱም ከአለፈው መንግሥት ብዙ ነገር ተምሮ ራሱን በማደራጀት ሲሰራና ሲማር ቆይቷል። በዚህም ሕዝብን የሚያይ ሰራዊት መሆን ችሏል። ነገር ግን በሕወሓት ሴራ እንዲሸነፍ ሆኗል። የመጀመሪያው ሴራ ጀነራሎቹ የወያኔና የሻቢያ ሽኩቻ ሰለባ ሆኑ። ሁለተኛ ደርግ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ አመራሮች ገንዘብ እየወሰዱ ሰራዊቱን ሸጡት። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ወያኔና ሻቢያ ተመሳጥረው የሰራዊቱን ልብስ ጭምር ለብሰው መሀላቸው በመግባት አተራመሱት። በዚህም ሰራዊቱ ሥርዓት አልባ ሆነ ተባለ። ከምንም በላይ ለአገሩ የሚገደውና ብቃት ያለው ቢሆንም ወያኔ አሁን ሕዝብ እያመሰ ባለበት ሴራ አጥምዶ ብዙ ዋጋ እንዲከፍል አደረገው።
የወያኔ ሰራዊትን ስናነሳ ሰራዊት የሚለው ስም ራሱ ሊሰጠው የማይገባ ነው። ምክንያቱም ጀነራልነቱ በእውቀት፣ በወሰደው ስልጠና አሊያም በብቃቱና በጀግንነቱ ሳይሆን፤ በዝምድናና በቅርበት ብቻ ነው። ከየቤቱ እየተጠራ ሹመት ተሰጥቶት እማያውቀውን ሙያ ሲንቦጫረቅበት ቆይቷል። ብቃት ኖሯቸው በራሳቸው የሚተማመኑና ለአገር የሚቆሙትን ጭምር እያባረረም ነበር ያልሰለጠነውን የሚከተው። በተለይም ከአንድ ብሔር የተሰበሰበ ሰውን መክተቱና ሰራዊት ማለቱ እጅግ ሙያውን ጭምር ያወረደውም ነበር።
በሥነ ምግባርም ሆነ በአደረጃጀት የተበላሸ አሰራር መስራቱ፤ ለአንድ ብሔር የወገነ ተግባር መተግበሩና ሌሎችን እንደ ሰው አለመቁጠሩ ሕዝብ ጭምር በመከላከያ ላይ ያለውን አመኔታ የቀየረም አድርጎታል። በተለይም ተግባራቸው ከሰራዊት ስብዕና የወረደና የሕዝብን ሀብት ንብረት የሚዘርፉ መሆናቸው ያለመተማመን ብቻ ሳይሆን እኛን ለመጠበቅ አቅሙ የለውም እስከመባልም ያደረሰው ሆኗል።
የወያኔ ሰራዊት ተቋማትን ሁሉ ያፈረሰና የራሱን ስልጣን የጠበቀ ነው። ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ጭምር ለማጥፋት ሲሰራ የቆየና አሁንም በመስራት ላይ ያለ ነው። ሙስናን ያስፋፋና ዛሬ ጭምር ልናስወግደው ያልቻልነውን ነቀርሳ የተከለም ነው። በአጠቃላይ ኢትዮጵያን የውርደት ካባ ያላበሰበት ዘመን ነበር ብሎ መውሰድ ይቻላል። ምክንያቱም ሕዝቡን፣ አገሩን፣ ሰራዊቱን፣ መንግሥታዊ ተቋማትን አዋርዶ ሊቀብረው ትንሽ ቀርቶት ነበር። ለዚህም እንደዋና መሳሪያ የተጠቀመው መከላከያ ብሎ የሰየማቸውን የራሱን ቡድን ሲሆን፤ በግለሰብ ማስታወሻ ፍርድ እስከመስጠት ተደርሶበታል።
ዘመናትን የተሻገረውን ፍልስፍና ያለበት ሙያ፣ የእውቀት ማዕከል የነበረውን ተቋም እንዲረሳና ዋጋቢስ እንዲሆን ሰርቷል። ይህ የሆነው ደግሞ በቡድኑ ብቻ ይሆን በውጭ ኃይሎች እገዛ ነው። በተለይም የግብጻውያን ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ኢትዮጵያውያን በወታደራዊ ኃይል ከተዳከሙ ግብጽ በምስራቅ አፍሪካ ኃያልነቷን እንዳወጀች ትቆያለች። የምትፈልገውን የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በእጇ ታስገባለች። ስለዚህም አገሪቱን በቀላሉ ለመያዝ የሚያስችለውን ምሰሶ ጥላሸት በመቀባትና ሁሉም እንዲነሳበት በማድረግ እንዲሁም ጥቃት በመፈጸም እንዲመናመን ለማድረግም ሞክሯል።
የኢህአዴግ ሰራዊት የመከላከያ ስብዕናም፣ ስልጠናም፣ ፍልስፍናም የሌለው ነው። ከዚያ ይልቅ ኮለኔልነትና ጀነራልነት እንደ እጅ መንሻ ካልቀረበልኝ ብሎ የሚያኮርፉና የስልጣን ሽሚያ የሚያደርግ ነው። ለዚህም በማሳያነት የሚነሳው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሲሞቱና ኃይለማርያም ደሳለኝ ቦታውን ሲይዙ ከአንድ ብሔር 45 ሰዎች ጀነራል መደረጋቸው ነው። በዚህ ተግባራቸው ደግሞ አገሪቱን ደካማ እንድትሆን አድርገዋታል። ሱዳንና ግብጽ እንደፈለጋቸው የፈነጩትም ከሕወሓት ጋር በተስማሙትና በተሰራው ሥራ ነው። ይህ ሰራዊት በብሔሮች ላይ ቁማር የሚጫወትና በእነርሱ ደም ውስኪ የሚራጭም ነበር። የመብት ጥያቄ እንኳን ማንሳት የማይቻልበትና ካነሳ ድባቅ እንዲመታ የሚያደርግም ነበር። መሬት ከልሎ እስከመሸጥም የደረሰ ነው። ለዚህም ወደ ሱዳን የገባውን መሬት መጥቀስ ይቻላል። ስለዚህም አገራዊ ፍልስፍና የሌለው ሰራዊት ነው ብሎ መውሰድ ይገልጸዋል።
አሁን ያለውን ሰራዊት ስንመለከትም ከቀደሙት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ምክንያቱም ወያኔ ሰራሹ ሰራዊት በብዙ መልኩ ተመንጥሯል። በአዲስ አደረጃጀትና መዋቅርም ብዙ ነገሮች እየተስተካከሉ ናቸው። በብቃትና በእውቀትም ቢሆን ዘመኑ ከደረሰበት ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው የሚያስብሉት ብዙ ምልክቶች አሉት። የአገርን ምስጢር የሚጠብቅና ትዕዛዝ አክባሪም ነው። ለሕዝብ የሚሞት ሰራዊት እንደሆነም በደረሰበት ግፍና በደል በደንብ ተመልክተነዋል። የሕዝብ ልጅ እንደሆነም ጥይት ይዞ እንኳን ሲሞት እናያለን። ይህ የመጣው ደግሞ ሕዝብ አልገልም ከሚል ስብዕና ነው።
የመከላከያ ሰራዊት ጦርነት ባለበት ጊዜ መሳሪያ ይዞ የሚዋጋ ከሌለ ደግሞ ሕዝብን በተለያየ መልኩ የሚያገለግልም ነው። ለዚህም ማሳያው የገበሬውን ሰብል ከማረስ እስከ መሰብሰብ ከዚያም ሲያልፍ አንበጣ ማባረርና መሰል ችግሮች ሲያጋጥሙት መፍትሄ እስከመስጠት ድረስ ሲያግዝ መቆየቱ፣ ካለው ደመወዝ ላይ ቀንሶ ትምህርት ቤትና ጤና ጣቢያ መስራቱ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው።
አዲስ ዘመን፡- የአሁኑ የኢትዮጵያ ሰራዊት እርስዎ ከገለጹት አንጻር የሚታይ ከሆነ ለምን ይህ ግፍ እንዲደርስበት ሆነ?
ዶክተር አለማው፡– በየአቅጣጫው ብዙ ፈተናዎች ስለተጋረጡበት ነው። ስለዚህም ይህንን ጥቃት በአራት ዓይነት ምክንያቶች ዘርዝሮ ማየት ይቻላል። አንደኛ ለውጡን በማምጣታቸው፤ ሁለተኛ አገራዊ ስሜት በማንጸባረቃቸው፤ ሦስተኛ ሕዝባዊነትን ማዕከል በማድረጋቸው፤ አራተኛው በዕውቀት፡ በሥነምግባር፤ በትጥቅ ይደራጅ የሚል ጥያቄ በማንሳታቸው የውጭ ሴራውን ስላከሸፉት ነው። ይህ በዝርዝር ሲታይ ደግሞ ለውጡ ሲመጣ አወቃቀሩ ተቀየረ። ይህ ደግሞ ከእነሱ እጅ የሚወጣ ሰራዊት ፈጠረ። ምክንያቱም እነሱ በፊት የራሳቸውን ይዞታ፣ ንብረት፣ የራሳቸው ጉዳይ አስፈጻሚ አድርገውት ነበር። አሁን ደግሞ አገራዊ ሰራዊት ሆነ፤ ሕዝባዊና በሥነ ምግባርና በዕውቀት ተደራጀ። በዚህም ዳግመኛ ሊያገኙት አይችሉምና ቆጫቸው።
ሁለተኛ አገራዊ ስሜቱ አብቦ ሊዘርፉበት የማይችሉ ተቋም መጣ። እነሱ ራሳቸውን ኢትዮጵያዊ አይደለንም ነው የሚሉት፤ ይህ በአዲስ አደረጃጀት የተዋቀረው ሰራዊት ደግሞ የኢትዮጵያ ነው እንጂ የእኛ ሰራዊት አይደለም የሚል የጥላቻ ስሜት ውስጣቸው ተፈጥሯል። በተጨማሪ በአደረጃጀት ለውጡ ጊዜ ብቃት የሌላቸው በጀኔራል ማዕረግ ስም የተቀመጡ ኮንትሮባንዲስቶች ከዚህ ቀደም በመከላከያ በጀትና ስም ነበር ጥይት የሚያስገቡት፤ መኪና ለራሳቸውም ለልጆቻቸው፤ ለዘመዶቻቸውም የሚገዙት፤ ወደ ውጭ ሀገር እየተመላለሱ የፈለጉትን ዓይነት መሳሪያዎች የሚገዙት በመከላከያ በጀትና ስም ነበር። ሆኖም ለውጡ ይህንን እንዳቆመው ሲያዩና ሲባረሩ እንዲሁም መዝረፍ ሳይችሉ ሲቀሩ ቀስታቸውን ሰነዘሩ።
ሦስተኛው የውጭ ሴራ ነው። አሁን እነሱ ተደራጅተን ኢትዮጵያን መልሰን በአንድ ደቂቃ ውስጥ እንቆጣጠራለን የሚል ስሜትና ፍላጎት ነበራቸው። መልሰን ወደ ስልጣን እንመጣለን የሚል ትዕቢትና ትምክህትም አላቸው። ተዋጊ እኛ ነን፤ ገዢ እኛ ነን፤ የበላይ እኛ ነን፤ ስልጡን እኛ ነን ወዘተ. የሚል የተበላሸ አመለካከትም ባለቤት ናቸው። ስለዚህም አሁን ይሄንን ዳግመኛ ማስፈጸም የምንችለው በአዲስ መልክ የተደራጀውን መከላከያ በመስበር ነው የሚል ዕቅድ አወጡ፤ ቁርሳችንን ባህርዳር፤ ምሳችንን አዲስ አበባ እንበላለን የሚል ተስፋን አነገቡ። ከዚያም ወደ ጥቃቱ ገቡ። ይሁን እንጂ መብረቃዊ ምት መተናቸዋል።
እነርሱ ያልሙ የነበረው መከላከያውን መስበር ላይ ነው። ለዚህ ደግሞ በሕዝብ ማስጠላት አንዱ አጀንዳቸው አድርገው ይንቀሳቀሳሉ። ይህ ከተሳካላቸው ደግሞ በሁሉም መልኩ እርሱን መተው አገሪቷን ሊከላከል የሚችል ኃይል እንዳይኖር ያደርጋሉ። ሕዝቡም የሚጠብቀውና የሚከላከልለት ስለማይኖር እንደፈለጋቸው ያሽከረክሩታል። ይህ ደግሞ ዳግም ተመልሰው ወደ ስልጣን እንዲመጡ ያግዛቸዋል። ይሁን እንጂ አሁን ማንም እንደማይፈቅድላቸው መረዳት ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም አሁን ሰራዊቱ ከእጃቸው ወጥቷል፤ እንደገና ወረራ ለመፈጸም የሚያምናቸው የለም፤ አገሪቱን ለውጭ ኃይል ለመሸጥ እየተጉ እንደሆነም ሕዝብ አውቋል። እናም የሚታገሉት ከብሔር ጋር ሳይሆን ከአገር ጋር ለዚያውም ሉአላዊነቷን ከማታስነካው ኢትዮጵያ ጋር መሆኑን መረዳት ይኖርባቸዋል። ህልማቸውም የቀን ቅዠት እንደሆነ ማሰብ አለባቸው።
ሕወሓቶች ከአሜሪካ ጋር መከላከያን አፍርሱት እንጂ የፈለጋችሁትን ትፈጽማላችሁ የሚል ስምምነት ነበራቸው። ስምምነቶቹም እየወጡ ይፋ እየሆኑ ናቸው። የትርምሱ መነሻም ቢሆን ከግብጻውያንም ጋር የገቡት ኢትዮጵያን የማዳከም ስምምነት ነው። አዲስ ቴሌ አቋቁመው፤ አዲስ መከላከያ አቋቁመው፤ ሌሎችንም አዳዲስ ተቋማት አቋቁመው አዲስ አበባ ላይ በኢትዮጵያ ፍራሽ ታላቋን ትግራይ መመስረት ይፈልጉ ነበር። ግን አልሆነላቸውም።
አዲስ ዘመን፡- የኢሕአዴግ ሰራዊት በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ላይ ያደረገው ዘመቻ ጥላቻ ብቻ ሳይሆን ጭካኔም የተሞላበት ነበር። ምክንያቱ ምንድነው?
ዶክተር አለማው፡- እነርሱ በዕውቀት፣ በስብዕና፤ በልህቀት፤ በሥነምግባር የበረቱ ስላልሆኑ ነው። የሚበልጣቸው እንደሚጥላቸው ያውቃሉ። ለመብለጥ ደግሞ አይሰሩም። ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ዕውቀት ባለቤት የሆነውን የሚያሸንፉት በወሬ እንጂ በሥራ እንዳልሆነም ጠንቅቀው ይረዱታል። ስለዚህም ምሳቸውን በተኛበት ሊያነሱ ችለዋል። በእርግጥ መጀመሪያም ቢሆን የሰራዊቱን ስም፣ ገጽታ አጠልሽተውታል። በምርጫ ጊዜ እንኳን መምረጥና መመረጥ የማይችል ብለው ደርግ ኢሠፓ አሉት፤ የደርግ ወታደር ብለው ስሙን አጠለሹት። አኮስምነው አዋርደው በተኑት (ጣሉት)፤ ተቋሙን አፈረሱት።
የውጭም የውስጥም ተልዕኮ ነበር ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበሩት። ትልልቅ ዕውቀት ያላቸው፤ ብቃት ያላቸው፤ አገራዊ ስሜት ያላቸው መልካም ሥነምግባርና ሕዝባዊ አመለካከት ያላቸው ጠንካራ ሰራዊት የነበሩትን ያባርሯቸዋልም። ይህ ግን ዛሬ አይቻልም። ገልብጠው መጥተው የነበሩት የትግራይ ሊሂቃን ነን፤ ኢትዮጵያን ለመምራት የተፈጠርን እኛ ነን፤ ስልጣን መያዝ ያለበት ከእኛ ውጪ መሆን የለበትም ባዮቹ አሁን አይቻልም ሲባሉ ነውጠኛ ኃይሎች ሆኑ። ብዙ ሕዝብንም ዋጋ አስከፈሉ። አሁንም ቢሆን የኢትዮጵያ ሰራዊት የሆኑትን ሆን ብለው የጨፈጨፉ አረመኔነት ተግባራቸው ከዚህ የመነጨ እንጂ ሌላ አይደለም።
አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሰራዊት የተሻለ ቁመና፤ የተሻለ ዕውቀትና አገራዊ ስሜት፤ የተሻለ ሕዝባዊነትና የመሰጠት ስሜት ያለው ነው። ነገሩ ድንገተኛ ጥቃት፤ መሳሪያ ቀምተው፤ ልብሳቸውን አውልቀው፤ ገድለው፡ አቃጥለው አረጉት እንጂ ቢይዛቸው ኖሮ ምን እንደሚያደርጋቸው ያውቁት ነበር። ኢትዮጵያን ከጥቃት፤ ከወረራ ለማዳን ቁርጠኛ የሆኑ፤ በሥነምግባር የታነጹ የሰራዊት አካላትን በተሸነፈ ወኔያቸው ሳያስቡት ማጥቃት ደግሞ ኃያልነት አይደለም። ፈሪነት እንጂ። በእርግጥ እነዚህ ቡድኖች አገራዊ ስሜት የሌላቸው ከሃዲዎች መሆናቸውን በገሃድ ያሳዩ ናቸው። ስለዚህም ከእነርሱ ምን ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን፡- አብዛኛው በሚባል ደረጃ ሕዝቡ መከላከያን እንዳያምነው ሆኗል። ምክንያቱ ምንድነው፤ አሁንስ ምን መሆን አለበት?
ዶክተር አለማው፡– እንደ አገር መከላከያ ላይ ሕዝቡ አመኔታ እንዲያጣ የሆነው የመጀመሪያው በኢሕአዴግ ጊዜ የነበረው አደረጃጀት ሲሆን፤ ይህም ለአንድ ብሔር ቅድሚያ የሰጠ መሆኑ ነው። አንድ ብሔረሰብን የሚያጎላና የሚያበለጽግ እንዲሁም የሚጠብቅ ሌላውን የሚያገልና የሚያንገዋልል ስለሆነም ነው። ለዚህም ከመከላከያ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆኑት ከአንድ ብሔር የተውጣጡ ጀነራሎች መሆናቸው ሙሉ ማስረጃ ነው። ሁለተኛው ድርጊታቸው ሲሆን፤ ከራሳቸው ውጪ የሆነውን ብሔር በብዙ መልኩ እንዲመታ፣ ዋጋ እንዲከፍል አድርገውታል። ሦስተኛው ስልጠና ሲሆን፤ በማንኛውም መልኩ የትምህርት እድል ሲመጣ ተጠቃሚ የሚሆነው ያው ብሔር ብቻ ነው። በኋላም ወሳኙ እርሱ ብቻ ይሆናል። ስለዚህም ሌላው መብት አይኖረውም።
አዲስ ዘመን፡- የሰራዊቱን አሁናዊ ተጋድሎ እንዴት ይገልጹታል ?
ዶክተር አለማው፡– አሁን ያለው ሁኔታ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም አገሪቱ በውስጥም በውጭም ተጽዕኖ ውስጥ የወደቀችበት ነው። የውጪው ተጽዕኖ አገር ውስጥ ገብቶ ማተራመስን የሚፈልግ ኃይል ሲሆን፤ አገር ውስጥ ደግሞ ሸረኛና ትምክህተኛ ቡድን አለና እርሱም በአገሪቱ ላይ እየሸረበ ይገኛል። ይህንን ደግሞ ከሕዝቡ ጋር በመሆን የመከላከል ግዴታው የመከላከያ ነው። እናም መከላከያ አጣብቂኝ ውስጥ የገባበት ጊዜ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ለድርድር አይቀርብም። ስለዚህ አሁን ያለው ሰራዊት በተጋድሎውም ሆነ በአካሄዱ አንደኛ ጀግንነት ያለው፤ ሁለተኛ የሕዝብ ልጅነትን የያዘ፤ ሦስተኛ ሥነምግባር ያለው፤ አራተኛ የስልጣን ተዋረድን የሚያከብር ነው። ብዙ ጊዜ በአገራችን መፈንቅለ መንግሥቶች አይደረጉም። ምክንያቱም የተደራጀና ዕውቅና ተሰጣጥቶ የሚኖር ሰራዊት በመሆኑ ነው። አገራዊ ፍልስፍና፤ አገራዊ ተልዕኮ ያለው ነው። በአጠቃላይ በዕውቀትና በሳል በሆነ መልኩ የተደራጀ ሰራዊት ነው።
ለአገርና ለወገን ውግንና ያለው ሰራዊት በመሆኑም ያም ከሃዲ ቢሆንም ወገን ነው በሚል ስሜት መሳሪያ በእጁ ይዞ እየሞተ ያለ ሰራዊት ነው። አገሬ ነው፣ ሕዝቤ ነው የሚል ስብዕናን የያዘም ነው። መከላከያ ሲጋደልም አገራዊ ፍልስፍናውን አስቀድሞ ነው። ለዚህች አገር፤ ለዚህ ሕዝብ እሞትለታለሁ፤ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ አስተዋጽኦ አበረክታለሁ ብሎ ጠመንጃ ይዞ መግደል እየቻለ ቆሞ እየሞተ ያለ ሰራዊት ነው። ሰራዊቱ በአገር ጀግንነት ጀግና ነው፤ ማንኛውንም ጠላት የሚያንበረክክ ነው፤ በአገሩ ነጻነትና ሉዓላዊነት የማይደራደር ሰራዊት ነው። ብቃት ያለው፤ ዕውቀት ያለው፤ ሥነምግባር ያለው፤ ሕዝቡን የሚያገለግል ሰራዊት ነው።
ጀግንነትን ለመግለጽ የለየለት ጠላት ሲሆን ነው የሚመቸው። እነዚህ ግን የራስ ወገን ሆነው፤ መሀከል ላይ ሆነው በራሳችን አገር፤ የራሳችን ዜጎች መከላከያውን ለማዋረድ የሚሰሩ ናቸው። አሁን ላይ እንዲያውም መከላከያውን ዘርፈው መልሰው አገርን ለማጥቃት ነው ሙከራ እያደረጉ ያለው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ እንደ አገር ሲታሰብ ሊስተካከል የሚገባው ነገር እንዳለ የሚያሳዩ ብዙ ነገሮች ያሉበት ጊዜ ነው። መከላከያም ሥነምግባሩንና ውስጣዊ አንድነቱን፤ ቁርጠኝነቱን መጠበቅ አለበት። ጀግናነቱንና ሕዝባዊነቱን ማጥበቅም ይገባዋል። ቁመናውን ማስተካከልና የውስጥ ችግር ካለ ማጥራት ይኖርበታል። ይህንን አስቸጋሪ የፈተና ጊዜ ለማለፍ አገራዊና ሕዝባዊ ቁመናውን እንደገና አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
አዲስ ዘመን፡- መከላከያው በቀጣይ ምን ዓይነት አካሄዶችን ቢከተል ነው ኢትዮጵያ ድል እንድታደርግ የሚያግዘው ይላሉ?
ዶክተር አለማው፡– ሰራዊቱ አንደኛ አገራዊ መንግሥቱን መጠበቅ አለበት፤ ምክንያቱም መንግሥት ለጥቃት የተጋለጠበት ጊዜ ነው። የውጭ ኃይሎች የአገራችንን መንግሥት ለመቀየርና አሻንጉሊት መንግሥታቸውን ለማስቀመጥ ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። በመሆኑም አካባቢውን ለማተራመስ በተለየ መልኩ ጥረት እያደገሩ ያሉ ኃይሎችን በንቃት መጠበቅ ይኖርበታል። አሁን ላይ ጎረቤት አገር ላይ መጥተው መሪ እስከመቀየር የደረሱበት ሁኔታ አለ። እናም እኛም ጋር ይህ እንዳይፈጠር የአገር ጠበቃ የሆነው መከላከያ አገራዊነቱን ማሳየት ላይ ሊሠራ ያስፈልጋል።
ሕዝቡንም መጠበቅ ይኖርበታል። ከየትኛውም ጊዜ በላይ ዝግጅት ማድረግ አለበት ባይ ነኝ። ሁለተኛው ነጻነቱን ማረጋገጥ አለበት። መከላከያ የማንም ተላላኪ መሆን የለበትም። የማንም ፖለቲከኛ ሱቅና አገልጋይ መሆን የለበትም፤ ራሱን የቻለ ተቋም ሆኖ የዕውቀት፤ የልህቀት፤ የሥነ-ምግባር ማዕከል መሆን አለበት። በዘርፉ ዓለም አቀፍ ደረጃውንና መለኪያውን ያሟላ መሆን ይጠበቅበታል። በሕገ መንግሥቱ የሚንቀሳቀስ እንጂ በመንግሥት ካድሬዎች የሚታዘዝና የሚዘወር ሊሆን አይገባውም። ማንም እየተነሳ እንዲያዘውና እንዲዘውረው መፍቀድም የለበትም። እርሱ የሕዝብ ነው፤ የአገር ነው እንጂ የማንም አይደለም።
አንዲት አገር ዴሞክራሲያዊ እንድትሆን አምስቱ ነገሮች ከማንኛውም ተጽዕኖ ነጻ መሆን አለባቸው። አንደኛ የመከላከያ ሰራዊት ነው። በመሆኑም ነጻነቱን ያወጀ ተቋም መሆን አለበት፤ በተግባርም ማረጋገጥ ይገባዋል። ስለዚህም ገለልተኛ ሆኖ ካልተቋቋመ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፤ የአገር ቀጣይነት አይታሰብምና ይህንን ማረጋገጥ ላይ መሥራት አለበት። ተቋሙ ዘመን ቢለዋወጥ፤ መንግሥት ቢለዋወጥ፤ ፓርቲ ቢለዋወጥ የማይናወጥ እንደሆነም ማሳየት ይገባዋል። ሌሎች አገሮች እኮ መቶና ሁለት መቶ ዓመታትን ያስቆጠረ የመከላከያ ተቋም ያላቸውም ለዚህ ነውና ይህንን ማሰብና መተግበር ላይ ሊሰራ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
ዶክተር አለማው፡– እኛ አገር ፓርቲና መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር የመከላከያ ተቋምን እየቀያየርንና እያዋቀርን መሄድ የለብንም። ተቋሙ ሕዝባዊነቱንም ማስመስከር አለበት። አንዳንድ ግጭቶችና አለመግባባቶች ሊነሱ ይችላሉ። በዚህ መካከል ግን ሕዝባዊነቱን ማሳየት ነው ያለበት። ለአንደኛው አድልቶ አንደኛውን ማጥቃት የለበትም። የለየለት ጠላት ካልሆነ በቀር።
መከላከያ የኔ ነው፤ ይጠብቀኛል፤ ይከላከልልኛል የሚል ሕዝባዊ አመኔታን ማትረፍ ያለበት ተቋም ነው። መከላከያ ከብሔር አስተሳሰብ መውጣት አለበት። መከላከያ የብሔር ሳይሆን የሕዝብና የአገር ነው። አጥንቱን ከስክሶ፤ ደሙን አፍስሶ፤ ውድ የሆነውን ሕይወቱን ሰውቶ የሚጠብቀን ነው። ስለሆነም ሕዝቡም የአገር አለኝታ እንደሆነ አምኖ ሊቀበለው ያስፈልጋል። መደገፍ ያለበትም ዛሬ ላይ ነው። ምክንያቱም ሕወሓት በሴራ ተንኮሉ እርሱን አጥፍቶ አገርን መሸጥ ይፈልጋል። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ ሕዝቡ ባሪያ እንደሚሆን ሊያጤነው ይገባል። ስለዚህም ከጎኑ መሆንን፤ በአካባቢው ራሱን አደራጅቶ አገሩን መጠበቅን ዛሬ ልምዱ ማድረግ አለበት።
መከላከያ ሁሉም ቦታ ላይ ሊገባ አይችልም። ሕዝቡ አሁን ጠላትና ወዳጁን ለይቷል። ስለዚህም የተለየ ነገር ሲያይ መዋጋትና መያዝ እንኳን ባይችል ለሚመለከተው አካል ሊያመለክት ይገባል። ይህም ሲሆን ነው አገር የምትጠበቀው። ሕዝቡም ከሕወሓት ባርነት የሚላቀቀው። ስለዚህ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ዜጋ ትግሉን የጋራ ማድረግ አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡን ማብራሪያ እጅግ አድርገን እናመሰግናለን።
ዶክተር አለማው፡- እኔም አመሰግናለሁ።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014