ኢትዮጵያውያን ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት በትህነግ (ሕወሓት) ጭቆና ስር ሆነው ከፍተኛ በደል አስተናግደዋል። ዜጎች ፍትህ፣ እኩልነትና ፍትሃዊነትን ተነፍገው በጭቆና ቀምበር ውስጥ አልፈዋል። በማህበራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በአገራቸው ላይ የመወሰን መብት ተነፍገው ከመቆየታቸውም ባሻገር የአገሪቷን ሃብትና ምጣኔ ሃብት ጥቂቶች እንደ ቅርጫ ሲከፋፈሉት የበዪ ተመልካች ሆነው ቆይተዋል።
ይህ የዘመናት በደል ያንገፈገፋቸው ዜጎች የጭቆና ቀንበሩን ለመገርሰስ ለዓመታት የመረረ ትግል አድርገዋል። ተደጋጋሚ ሙከራው ተሳክቶም ትህነግን ከጫንቃቸው ላይ አራግፈውታል። ይሁንና ለበርካታ አሥርት ዓመታት የኮንትሮባንድ መስመሩን፣ የአገሪቱ የገቢና የወጪ ንግዱን፣ በቡድን ተደራጅቶ የመሬትና የማእድን ሃብቱን… ሲመዘብርና ለእኩይ አላማው ሲጠቀምበት የቆየው ትህነግ በቀላሉ ከኢትዮጵያውያን ላይ ለመላቀቅ አልቻለም። ይልቁኑ እራሱን ወደ ትግራይ በማሸሽ ሃይሉን አደራጅቶ የዘረጋውን የዘረፋ መረብ በድጋሚ ለማስቀጠልና ሥልጣኑን ለመያዝ ተደጋጋሚ ሙከራዎችን አድርጓል። አሁንም እያደረገ ይገኛል።
በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ትህነግ ፖለቲካዊና ማህበራዊ በደሉን እንተወውና በኢትዮጵያውያን የምጣኔ ሃብት ላይ አያሌ በደሎችን አድርሷል። ከዚህ ውስጥ እንደ መንግሥት ሳይሆን እንደ ተደራጀ የማፊያ ቡድን ኔትወርክ በመዘርጋት የአገር ሃብት እንዲሸሽ፣ የቡድኑ አባላት ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ እንዲስፋፋ በማድረግ ዘረፋውን ሲያጧጡፈው ቆይቷል። ይህን የሚገታ ህዝባዊ ተቃውሞ ተነስቶ ከድርጊቱ ቢቆጠብም ከተጠያቂነት ለመሸሽ እና ያጣውን ጥቅም መልሶ ለማስጠበቅ እየሠራ ይገኛል። አሁን ላይ በአማራ ክልል ውስጥ መጠነ ሰፊ ወረራዎችን በማካሄድ ፋብሪካዎችን፣ የኢንዱስትሪ መሠረተ ልማቶችንና መሰል ተቋማትን እያወደመ ነው። ይህ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ምጣኔ ሃብታዊ እድገቱን ቁልቁል እንዲወድቅና ዜጎች በከፍተኛ ደረጃ ተጎጂ እንዲሆኑ እየዳረገ ነው።
ባለፉት አሥርት ዓመታት ውስጥ ከተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስና ኢፍትሃዊነት በላይ አሁን በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው ጦርነት በከፍተኛ ደረጃ የአገሪቱን ምጣኔ ሃብታዊ እድገት የሚገታ መሆኑን የሚናገሩት የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቶች ዋና ኃላፊ አቶ ክቡር ገና ናቸው። በተጨማሪ ሁሉንም መደበኛ የምጣኔ ሃብት ትግበራዎች ለጊዜው ገታ አድርጎ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ መሰራት እንደሚኖርበትም ይናገራሉ። ይሁን እንጂ አሁን ባለው አካሄድ ይህ ሁኔታ እየተተገበረ አለመሆኑን ይገልፃሉ። እዚህ ጋር መንግሥት ያለፉትን ሦስት ወራት ሳይጨምር በትግራይ ክልል ለተካሄደው ህግ ማስከበር ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን ይፋ ማድረጉን ልብ ይሏል።
“ፋብሪካዎችም ሆነ ማናቸውም የኢኮኖሚ እድገቱን የሚደግፉ ተቋማት ለተያዘው ጦርነት ግብዓት የሚሆን ምርቶችንና ድጋፎችን ማድረግ ይኖርባቸዋል” የሚሉት አቶ ክቡር ገና በአሁን ሰዓት የቅንጦት ምርቶችና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች ቆመው ለአንድ ዓላማ መሰለፍ እንዳለባቸው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በእርሳቸው ትዝብት በሙሉ አቅም ይሄ እየተተገበረ አይደለም።
ባለፉት አሥርት ዓመታት በምጣኔ ሃብት ፍትሃዊ ክፍፍልና የእድገቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን የተገለለው ዜጋ አሁን ደግሞ የሽብርተኛው ቡድን መልሶ የዝርፊያ መረቡን ለመዘርጋት በሚያካሂደው ጦርነት ምክንያት ተመሳሳይ ጫናዎች እየደረሱበት ይገኛል። አርሶ አደሩ ተረጋግቶ ሰብሉን እንዳይሰበስብ፣ ነጋዴው ሥራውን እንዳያከናውን፣ ታላላቅ ፕሮጀክቶች ግባቸውን እንዳይመቱና የድህነት ቅነሳ ስትራቴጂው ግቡን እንዳይመታ የዚህ ዘራፊ ቡድን የከፈተው ጦርነት አያሌ ጫናዎች እየፈጠረ ይገኛል። ለዚህም ነው የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይህን ጦርነት በአጭር ግዜ ውስጥ ለመቅጨት ሁሉም ፕሮጀክቶች ለጊዜው ጋብ ብለው ወደ ዋናው ጠላት ፊታችንን ማዞር ይኖርብናል የሚል ምክረ ሃሳብ የሚሰነዝሩት።
“ዜጎች መሠረታዊ ሸቀጦችን በቀላሉ ለማግኘት እየተቸገሩ ነው። የዋጋ ንረቱም በእጅጉ እየጨመረ ነው” የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው እና የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤቱ ዋና ኃላፊ ለዚህ እንደ ዋንኛ ምክንያት የሚጠቅሱት በቅርቡ በአገሪቱ የተከሰተው ጦርነትን ነው። ለዘመናት በምጣኔ ሃብታዊ ኢ ፍትሃዊነት ሲሰቃይ የኖረ ህዝብ አሁን ደግሞ በጦርነት ምክንያት በሚፈጠር ተመሳሳይ ችግር መጉላት እንደማይኖርበት በመጥቀስም የህግ ማስከበር እርምጃው በፍጥነት መጠናቀቅ እንደሚኖርበት ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ።
በትህነግ የሚመራው መንግሥት ባለፉት ዓመታት በተለየ መልኩ አርሶ አደሩን፣ የፋብሪካ ሠራተኛውንና ተራውን ዜጋ የሚጠቅም የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይሆን በግል ጥቅም ከተሳሰሯቸው ባለሀብቶችን የሚደግፍ ነበር የሚሉት የኢኮኖሚ ባለሙያው ይሄ ችግር አሁንምድረስ እንደሚስተዋል ይጠቁማሉ። በዋናነትም ዜጎችን የሚጠቅም ምጣኔ ሃብታዊ ለውጦች እንዲመጡ የቀደመው አካሄድን ከመታገል ባለፈ አሁንም የሚታዩ ክፍተቶችን ማስተካከል እንደሚገባም ያነሳሉ።
እንደ ማውጫ
ኢትዮጵያን በተደራጀ መንገድ የዘረፈው አሸባሪው የትህነግ ቡድን ለበርካታ ዓመታት ሃብቱን ሳይቸገር ሊጠቀምበት ወደሚችለው የውጪ ሀገራት አሽሽቷል። በዚህ ሳይገደብ የአገሪቱን የመሬት ሃብት፣ የወጪ ገቢ ንግድ፣ የምንዛሬ ፍሰት እንዲሁም እያንዳንዱን የምጣኔ ሃብት ዘርፍ ለፍላጎቱ ማስፈፀሚያና ለፖለቲካ የበላይነቱ ማስቀጠያ ተጠቅሞበታል።
አሁን ደግሞ በህዝብ ሃይል የተቀማውን ሥልጣኑንና የማድረግ አቅሙን መልሶ ለማግኘት ሲል በሰሜን ዕዝ ላይ በእኩለ ሌሊት የጭካኔ ግድያ ፈፅሞ በመላው ኢትዮጵያውያን ላይ ጦርነት ካወጀ ሰነባብቷል። ዜጎችን ይህን እኩይ አላማውን እየታገሉት ይገኛሉ።
ከትናንት በስቲያ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መግለጫ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ “ የበላይነት የገዢነት የአዛዥነት በሽታ የተጠናወተው ቡድን በምርጫ እንደማይሳካለት አይቶታል ፣ በዴሞክራሲ መንገድም አይቶታል፣ አሁን የመጨረሻ መንገድ የሚከፈለውን ዋጋ ከፍለን ማዘዝ መግባት ማፍረስ አለብን በሚል የገባበት መንገድ ነው፤ ይህ ቡድን ሌባ ነው፣ ታሪክ ይሰርቃል ፣ቅርስ ይሰርቃል፤ የሌብነት ሂደቱ አዲስ አይደለም” በማለት ሁሉም ዜጋ መልሶ ለዝርፊያ አሰፍስፎ የመጣውን ሃይል መታገልና በአጭሩ መቅጨት እንደሚገባ አሳስበዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014