ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም … ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) የኢትዮጵያን፣ በተለይም የትግራይን፣ ሕዝብ ከጠላት በሚጠብቀውና ለትግራይ ሕዝብ ብዙ ውለታ በዋለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ሰነዘረ። ጥቃቱንም በርካታ የቡድኑ አመራሮች ጭምር አረጋግጠዋል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግሥትም ቡድኑን ለሕግ ለማቅረብ የሕግ ማስከበር እርምጃ በወሰደበት ወቅት የአገር መከላከያ ሰራዊት የፈፀመው ተጋድሎ የሚረሳ አይደለም። ሰራዊቱ ኃይሉን አሰባስቦ በወኔና በቁጭት በመዝመት አንፀባራቂ ድል አስመዝግቧል። በህ.ወ.ሓ.ት ጥቃት የተፈፀመበት የሰሜን ዕዝ፣ የአገር መከላከያ ሰራዊት ካሉት እዞች መካከል አብላጫው የሰው ኃይልና ትጥቅ የነበረበት በመሆኑ ሰራዊቱ ይህን ወሳኝ ክፍሉን አጥቶና ከህወሓት ጋር ተፋልሞ ለድል ለመብቃት ተዓምራዊ የሆነ የግዳጅ አፈፃፀም ያስፈልገው ነበር። ሰራዊቱ ያን አስገራሚ ድል ማሳካት ችሏል።
ህ.ወ.ሓ.ት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ መከላከያ ሰራዊት ራሱን አደራጅቶ በህ.ወ.ሓ.ት ላይ እርምጃ በወሰደበት ወቅት ስለነበሩት ሁኔታዎችና ስላስመዘገባቸው ድሎች የሰራዊቱ አባላት በወቅቱ ከተናገሩት መካከል በጥቂቱ እንስማ …
የሰሜን ዕዝ የአምስተኛ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር አዛዡ ብርጋዴር ጀኔራል ሙሉዓለም አድማሱ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዲህ ሲሉ ተናግረው ነበር። ‹‹… የትግራይ ልዩ ኃይሎች በዕለተ ማክሰኞ፣ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም ከምሽቱ 4፡30 ያለምንም ርህራሄ ዙሪያውን እንደ ቀለበት ከበውን አጠቁን … የሶስት ቀናት ከበባው በጣም አስቸጋሪ ነበር። 24 ሰዓት ሙሉ ተኩስ ነው። እነሱ ያጠቃሉ፤ እኛ እንከላከላለን፤ ይሄዱና ምግብ በልተው፣ ኃይል ጨምረው ያጠቃሉ፤ ሲታኮሱ የነበሩት ልዩ ኃይሎች ወደ ካምፓቸው ሄደው እረፍት አድርገውና ጥይት ጭነው ይመጣሉ።
እኛ ካለንበት ቦታ ውጭ መፈናፈኛ ስፍራ የለንም። እንደ ቀለበት ዙሪያውን ከበውናል፤ ውሃ፣ ምግብ፣ ጥይት የለም። ያለችንን ነው በቁጠባ የምንጠቀመው። እኔም አልፎ አልፎ እንደ ምሽግ ከተጠቀምኩበት ግንብ ቤት እየወጣሁ ለወታደሮቼ ጥይት በቁጠባ ተጠቀሙ እያልኩ አሳስብ ነበር ሲሉ ይገልጻሉ። እነሱም አላሳፈሩኝም በጽናት ተዋደቁ። የሰራዊታችን በጽናት የመከላከል ሞራል የሚገርም፣ የሚደነቅና ተዓምር የሚያስብል ነው።
አርቢጂ፣ ቦምብ፣ መትረየስና ክላሽ እንደ ዝናብ ቢያርከፈክፉብንም ለሶስት ቀናት ቀንና ሌሊት መክተናል። በፍጹም እንተርፋለን ብለን አላሰብነም፤ ከቻልን እስከ መጨረሻው እንከላከላለን፤ ካልቻልን ደግሞ በመጨረሻ ላይ ራሳችንን እናጠፋለን የሚል አቋም ነበርን። ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት፤ በመከላከያ ሰራዊት ፈጥኖ ደራሽነት ቀለበቱ ተሰብሮ ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግረናል … እኛም በያለንበት በጽናት ተዋግተን መክተናል። አሁን እነሱ ባሰቡት ሳይሆን እኛ ባሰብነው መንገድ እየሄደ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ጦርነቱ ይቋጫል ብለን እናስባለን …›› ብለው ነበር።
ብርጋዴር ጀኔራል ሙሉዓለም እንደተናገሩትም በህ.ወ.ሓ.ት ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ ቀጥሎ የአገር መከላከያ ሰራዊት ከሦስት ሳምንታት በኋላ፣ ኅዳር 19 ቀን 2013 ዓ.ም የትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌን ተቆጣጠረ።
በሕግ ማስከበር ዘመቻው ወቅት ወደ ሰራዊቱ ጥሪ ከተደረገላቸው የጦር መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም እና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ እንዲሁም በምዕራብ በኩል የነበረውን ጦር እየመሩ ረጅም ርቀት ተጉዘው በድል አድራጊነት መቀሌ የገቡት ሌተናል ጀኔራል አበባው ታደሰ የሕግ ማስከበር ዘመቻውን እየመሩ ከዓድዋ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዲህ ብለው ተናግረው ነበር።
‹‹ … መጀመሪያ አካባቢ ጦርነቱ እንዲከብድ ያደረገው ሰራዊቱ ከሁለት አቅጣጫ ነው የተመታው። አንደኛው ከሚያምነውና አብሮት ካለው ከጀርባው ተወጋ። የጀርባውን መነሻ አድርጎ የተዘጋጀ ቡድን ደግሞ ከፊት ለፊት መታው። ከጀርባ የተወጋው ሳንጃ መነቀል አለበት። እርሱን ነቅሎና ግንባር ያለውን አስተካክሎ ነው ወደዚህ ደረጃ የደረሰው። በሰራዊቱ ላይ የደረሰበት ግፍ ሊገለፅ አይችልም። የወያኔን የማፍያ ቡድን የሰው ልጅ አእምሮ ከሚያስበውና ሊፈፅመውም ይችላል ተብሎ ከሚገመተው ግፍ በላይ ፈፅሟል … እኛ ዘንድ የነበሩ የእነርሱ በሙሉ ከእነርሱ ጋር ተሰልፈዋል። ከእነርሱ ጋር ሆነው ነው እየተዋጉ ያሉት …
… የወያኔ ማፍያ ቡድን ውሸት የሚያቆመው ሲሞት ብቻ ነው። ሲሞትም ሊያወራ ይችላል። ሁመራ፣ ሽራሮ፣ ሽሬ፣ አክሱምና ዓድዋ በሰላም ነው ያሉት። አሁንም እየገሰገስን ነው። ግን ‹አልተያዘም› ነው የሚለው። ‹ይህን ትጥቅ ይዘናል› ይላሉ። የያዙት ትጥቅ አለ። እኛን ወደኋላ የሚመልስና የሚያሸንፍ ትጥቅ ግን አይደለም። ከወሰዱት ትጥቅ መካከል 65 በመቶ የሚሆነውን አራግፈዋል፤ ቀምተናቸዋል። እኛ በተሟላ ትጥቅ፣ በተሟላ ዝግጁነት፣ ወኔና የኢትዮጵያዊነት እልህ ዘመቻውን እየጨረስን ነው …
… የሰራዊቱ ጥንካሬ ዋነኛው ምክንያት ኢትዮጵያዊነት ነው። ‹ለምን 24 ሰዓታት ይሰራል/ ይዋጋል?› ተብሎ ቢጠየቅ ይህ አገር በደምና በአጥንት የተገነባ ትልቅ አገር ነው፤ ይህ አገር እግዚአብሔርም የቸረው አገር ነው። ማንም የመንደር ወመኔ አገር ሊገነጥልና ሊያፈርስ አይችልም። ከሚገባው በላይ ትዕግሥት ተሰጥቶታል። ይህ ‹አገር አስገነጥላለሁ› ብሎ የተነሳ ጅብ በብርሃን ፍጥነት መጥፋት አለበት። ኢትዮጵያ ውድ ዋጋ ከፍላም ቢሆን፤ ልጆቿን አጥታም ቢሆን እንደተከበረች ትኖራለች። ኦፕሬሽኑም ይህ ነው …››
ሌተናል ጀኔራል አበባው ሕዝቡ ለሰራዊቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ ወደር የለሽ እንደነበርና ይህም ሰራዊቱ በድል ታጅቦ እንዲጓዝ እንዳስቻለው ሲገልፁም፤ ‹‹በአራቱም ማዕዘን ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተነስቶ ሰራዊቱን በሞራል፣ በሃሳብ፣ በጉልበትና በገንዘብ እያገዘው እንደሆነ ሰራዊቱ ያውቃል። ለዚያም ነው ሰራዊቱ ኢትዮጵያን ለማዳን ከሚገባው በላይ በቁርጠኝነት እየሰራ ያለው። ጠንካራ ሕዝብ ጠንካራ ደጀን እንዳለው ያውቃል። ለዚህ ሕዝብ ያልሞተ ሰራዊት ምን ይሆናል? ይህ አገር የጋራ አገር ነው፤ በጋራ ሆነን ነው የምናቆመው። ስለዚህ የእርሱ ጥንካሬ ነው እስከዚህ ድረስ ይዞት እየመጣ ያለው›› በማለት በከፍተኛ ወኔና አገራዊ ስሜት መናገራቸው አይዘነጋም።
የአየር ወለድ ውጊያን ከአየር ኃይል ጥቃት ጋር አቀናጅተው በፈፀሟቸው ጀብዶች ዝናን ያተረፉት የጥምር ጦር ውጊያ መሃንዲሱና ወደ ሰራዊቱ እንዲመለሱ ጥሪ የተደረገላቸው ሌላኛው የጦር መሪ ሜጀር ጀኔራል ዓለምእሸት ደግፌ፤ ስለሰራዊቱ የግዳጅ አፈፃፀም ሄዋነ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ ‹‹ … ወጣ ገባ የሆነው መሬት ጠላት እመክትበታለሁ፤አቆምበታለሁ ብሎ ያሰበበት ቦታ ነበር። ያሉንን መሳሪያዎች በማስተባበር በጠላት ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረስ በአካባቢው መሽጎ የነበረው ኃይል ለሦስት ቀናት ያህል መራራ ውጊያ ካደረገ በኋላ ተፍረክርኮ እንዲበተን ማድረግ ተችሏል።
… ውጊያ ማለት ተኩስና ንቅናቄ ነው። ንቅናቄውን የሚሰራው እግረኛው ነው፤ በእርግጥ ሜካናይዝዱም ይነቃነቃል። ግን ዋናው ሥራ ተኩስ ነው። ተኩስ በጥሩ ሁኔታ ከተሰራ ጠላት በሙትም በቁስለኛም ጉዳት ይደርስበታል። ለእግረኛው ምቹ ሁኔታ ይጥርለታል። ይህ ሥራ በሚገባ በመሰራቱና ጠላት በሚገባ በመመታቱ ሸሽቶ ሄዷል … በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሕዝባችን የድል ብስራት እናሰማለን ›› ብለው ነበር። በተናገሩት የጀግና ቃላቸው መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የድል ብስራት አሰምተዋል።
የስምንተኛ ሜካናይዝድ አባል የሆነው ሻለቃ ባሻ በየነ መለሰ በበኩሉ ህ.ወ.ሓ.ት በከፈተባቸው ጥቃት ምክንያት እርሱና ጓዶቹ ሸሸቢት ወደሚባል የኤርትራ መንደር ማፈግፈጋቸውን ጠቁሞ፤ ከብዙ ፈተናዎች በኋላ ሰራዊቱ ራሱን አደራጅቶ ህ.ወ.ሓ.ትን ድባቅ መምታቱን ገልፆ ነበር።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ደግሞ የመከላከያ ሰራዊቱ ተጋድሎ ህ.ወ.ሓ.ት ያሻውን ሁሉ ሳይፈፅም ሙከራዎቹ ሁሉ እንዲከሽፉ ስለማስቻሉ ተናግረው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ፤ ‹‹ ተስፋ የቆረጠውና ከሃዲው የህ.ወ.ሓ.ት ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ያልታሰበና የማይጠበቅ ጥቃት በመፈጸም ኪሳራ ሊያደርስ የፈለገ ቢሆንም፤ በአገር መከላከያ ሰራዊት ብርቱ የጀግንነት ተግባር ይህ አንጃ ያሻውን ሳያደርግ ሙከራዎቹ ሁሉ ከሽፈዋል … የአማራ ህዝብና የአማራ ሚሊሻ እንዲሁም የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በአንዳንድ የአማራ ክልል ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶችን እጅግ በሚያስደንቅ ጀግንነት በመከላከል፤ ይህ ኃይል ያሻውን የመንሰራፋት፣ የመስፋፋት ፍላጎት በመግታት፤ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመቀናጀት የጦርነቱን ፋላጎት ባለበት መግታት ብቻ ሳይሆን፤ አስፈላጊ አስፈላጊ ቦታዎችን ለመቆጣጠር ችሏል … ይህ ሁኔታ የማናውቃቸውን ጀግኖች የፈጠረ፣ ዛሬም ኢትዮጵያ ለዓላማቸው ለመለዯአቸው ለባንዲራቸው ለአገራቸው እንዲሁም ለህዝባቸው የሚዋደቁ ለማመን የሚቸግሩ ጀግንነት የሚፈጽሙ የሰራዊት አባላት እንዳላት ማረጋገጥ ችለናል።
ኣዲነብሪድ በተባለች አንዲት ቦታ የነበረች ሻለቃ የተከፈተባትን ጥቃት ለመከላከል፤ ንብረቷንና ማዘዣ ጣቢያዋን ለመጠበቅ ያደረገችው ተጋድሎ እጅግ የሚያስደምምና የሚያስደንቅ ነበር። ከዛ በተጨማሪ በሁመራና በዳንሻ አካባቢ እንዲሁም ቅራቅር በተባለ በአማራ እና የትግራይ ድንበር ላይ በነበሩ ውጊያዎች ጀግናው ሰራዊታችን እንዲሁም የአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ያደረጉት አስደናቂ ተጋድሎ በታሪካችን የሚዘከር ይሆናል … የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መከላከያ ሰራዊትና የአማራ የጸጥታ ኃይል ተቀናጅተው በሰሜን ጎንደር ዞን ቅራቅር በተባለ ቦታ የእብሪተኛው ቡድን የሰነዘረውን የማጥቃት ውጊያ በብቃት በመመከት በዚህ ኃይል ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊና ማቴሪያላዊ ኪሳራ አድርሶበታል።
ሰራዊታችን በዛሬው እለት ከሰዓት በኋላ በወሰደው ቅንጅታዊ የማጥቃት እርምጃ ከቀራቅር በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ከፍተኛ ቦታ ላይ የነበረውን የእብሪተኛው አጥፊ ቡድን ኃይል በከፍተኛ ሁኔታ በማጥቃት ቦታውን በሰራዊታችን ቁጥጥር ሥር አውሎታል። ጀግናው ሰራዊታችን በወሰደው የማጥቃት እርምጃ በዚህ ነብሰ በላ ቡድን ኃይል ላይ ከፍተኛ ሰብዓዊ ኪሳራ በማድረስ የቡድኑን የነብስ ወከፍ መሳሪያዎችንም ማርኳል።
በአገር መከላከያ ሰራዊት ብርቱ የጀግንነት ተግባር ይህ አንጃ ያሻውን ሳያደርግ ዛሬ የሞከራቸው ሙከራዎች ሁሉ ከሽፈው ውለዋል። ይሄንን ጉዳይ በማጠናከር የጀመረውን እኩይ ተግባር ለማቆምና የአገራችንን ሰላምና አንድነት ለማስጠበቅ የአገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደርገውን ጥረት መደገፍ ማገልገል እየቻሉ ልምድ ያላቸው ስመጥር ሶስት ሌፍትናንት ጄኔራሎች ዛሬ ወደ አገር መከላከያ ሚኒስቴር እንዲቀላቀሉ እና ያለውን ኃይል በማጠናከር ተቋሙን ፍጹም ኢትዮጵያዊ አድርገው እንዲገነቡት፤ ኢትዮጵያን የሚከላከልና የሚጠብቅ የሁሉም ህዝቦች በእኩል የሚታዩበትና በእኩል የሚኮሩበት ተቋም እንዲሆን፤ ይሄንንም ተግባር እንዲፈጽሙ ሌ/ጀኔራል አበባው ታደሰ፣ ሌ/ ጀኔራል ዮሐንስ ገ/መስቀል እና ሌ/ጀኔራል ባጫ ደበሌ ይሄንን ተልዕኮ መንግሥት ሰጥቷቸው ሥራቸውን የጀመሩ ሲሆን፤ መላው የሰራዊት አባላት በጀመራችሁት አስደናቂ ጀግንነት በመተባበር እጅ ለእጅ በመያያዝ ይሄንን እኩይ ተግባር ባለበት የማስቆምና የመከላከል አቅማችሁን አጠናክራችሁ ይሄን ሀሳብ እንድታከሽፉ አሳስባለሁ …›› በማለት ተናግረው እንደነበር ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኅዳር 21 ቀን 2013 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ማብራሪያ የአገር መከላከያ ሰራዊትና የክልል የፀጥታ ኃይሎች በሕግ ማስከበር ዘመቻው ላሳዩት ተጋድሎ አድናቆታቸውን ገልጸው ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።
በአጠቃላይ የአገር መከላከያ ሰራዊት የተሰነዘረበትን ጥቃት ተቋቁሞና ከባድ ፈተናዎችን አልፎና መስዋዕትነቶችን ከፍሎ ህ.ወ.ሓ.ት አቅዶት የነበረውን አገር የማፍረስ ምኞቱን እንዳይሳካ ማድረግ የቻለ የአገር ዘብና ጠበቃ ነው።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014