እነሆ የሽብር ቡድኑ የሃገር መከላከያ ሠራዊትን በመክዳት ግፍ ከፈፀመ ዛሬ አንድ ዓመት ሆነው።በወቅቱም የሽብር ቡድኑ ክህደቱን በአደባባይ እንደጀብድ አውርቶታል።በዚህ ብቻ ሳያበቃም አሁን ድረስ አገር እያወደመ የገዛ ወገኖቹን /ህጻናትን፣ ወጣቶች፣ ሴቶችና አረጋውያንን/ በጅምላ እየጨፈጨፈ ይገኛል።
ከዚህም በተጓዳኝ ንብረት እያወደመና እየዘረፈ፤ ዜጎችንም ለረሃብ ለማጋለጥ ሰብልና እንስሳትን ጭምር እያወደመ ይገኛል።በፕሮፓጋንዳ ዘመቻም ህዝብ ተረጋቶ ስራውን እንዳይሰራ እያደረገ ይገኛል።
እኛም የፕሮፓጋንዳ ሥራው እና በኅብረተሰቡ ውስጥ እየፈጠረ ያለውን ጫና በሚመለከት በደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የስነምግባር እና ስነዜጋ ትምህርት ክፍል ተጠሪና የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ገናናው ጀምበሩን ጠይቀን እንደሚከተለው አቅርበንላችኋል።መልካም ንባብ፡-
አዲስ ዘመን፡- በአገራችን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ በአሸባሪው ሕወሓት በኩል እየተሠራ ያለውን የፕሮፖጋንዳ ሥራ በሚመለከት ምን ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር ገናናው፡- ሕወሓት በፕሮፓጋንዳው ኅብረተሰቡን እያወናበደ መሆኑ ግልፅ ነው።አንድ ቦታ ላይ ሳይደርስ ደርሻለሁ ብሎ የሐሰት ወሬ በመንዛት ቀድሞ እያመቻቸ ውዥንብር የመልቀቅ እና የማምታታት ሥራ ይሠራል።አውቀውም ሆነ ሳያውቁ ይህንን ሃሳብ ገዝተው የሚያራምዱና የሚያሰራጩ ግለሰቦችም አሉ።
በሕዝቡ በኩል ክፍተት አለ።ሕዝቡ ማህበራዊ ሚዲያውን ሲጠቀም እየመረጠ አይደለም።በመንግስት በኩልም በየዕለቱ ግልፅ መረጃ ስለማይሠጠው ኅብረተሰቡ በየትኛውም በኩል የሚለቀቁ መረጃዎችን ወደ ራሱ ወስዶ የመቀበል ዝንባሌ እየታየ ነው።ይህ በዋናነት መንስኤው ከመንግስት በኩል ያለ ችግር ነው።
ሁሉ ነገር የግድ ግልፅ መሆን አይኖርበትም።ነገር ግን ቢያንስ በሎጀስቲክም ሆነ በማንኛውም መንገድ ኅብረተሰቡ ከጎኑ እንዲደግፈው በተወሰነ መልኩ በግልፅ ያለበትን ሁኔታ ማሳወቅ ነበረበት።ይህ ባለመሆኑ የመንግስት መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ ሌሎች መረጃ ሰጪዎች መረጃዎችን በትክክል እያስተላለፉ አይደለም።
በሕወሓት የሽብር ቡድን በኩል ግን በማህበራዊ ሚዲያውም ሆነ በመገናኛ ብዙኃናቸው በስፋት የሐሠት ወሬ በማራገብ ፕሮፖጋንዳ ይነዛሉ።ሰዎች ደግሞ እውነት እየመሰላቸው እየተቀበሉ ነው።የመንግስት መገናኛ ብዙኅን ተከታትለው መረጃዎችን ባለመልቀቃቸው ሰዎች ያገኙትን በሙሉ ለመቀበል ተገድደዋል።ስለዚህ መንግስት እያንዳንዱን መረጃ ለመገናኛ ብዙኃን እየሰጠ ኅብረተሰቡ ተከታታይ ምላሾችን እያገኘ ከሔደ ተአማኒነት እና የህዝብ ድጋፍ ለማግኘት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል።
ነገር ግን እስከ አሁን በዚህ መልኩ እየተሠራ ስላልሆነ አንዳንዴ በውሸት እዚህ ደረሱ የሚል መረጃ ይሰጥና የተሳሳተ መረጃ ቢሆንም በአንድ ጊዜ ይሠራጫል።ኅብረተሰቡም ምንም ሳያይ እየተደናገጠ ለሽብር ቡድኑ አመቺ ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።ወልዲያ እንደዚህ ሆነ ሲባል መንግስት ቶሎ መረጃ ባለመስጠቱ ምክንያት ሰዎች አሁን አሁን ለማመን እየተቸገሩ ነው።የሕወሓት ፕሮፖጋንዳም ኅብረተሰቡ አንድ ሆኖ እንዳይዋጋ እያደረገው ነው።
እዚህ ላይ አንዳንዴ ቀልድ የሚመስሉ ነገሮችም ያጋጥማሉ።እየቆየ ሲሔድ እነርሱ የሚናገሩት እውነት ነው በማለት ኅብረተሰቡ እነርሱን ወደ ማመን ይደርሳል።ያን ያህል ኪሎ ሜትር አቋርጠው ወልዲያ ሲገቡ በትክክል መያዛቸው አልተነገረም።ቆይቶ ግን ይዘውታል ተባለ።እንዲህ አይነት ድርጊት አንደኛ አመኔታን የሚያሳጣ ነው።ደሴም ላይ ስልታዊ ማፈግፈግ ነው እየተባለ መከላከያ ከደሴ በመካነ ሰላም በመርጦ ለማሪያም ይመጣል እያሉ ሰዎች ያወራሉ።ሰዎች እየደወሉ ለማረጋገጥ ይሞክራሉ።ደሴ ካልተያዘ በግልፅ አልተያዘም ብሎ አረጋግጦ መናገር ያስፈልጋል።ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ሕዝብን በሚያሳምን መልኩ በቂ መረጃ የመስጠት ክፍተት አለ።
ሰርገኛ መጣ በርበሬ ቀንጥሱ እንዳይሆን ህዝቡ ተደራጅቶ በአንድነት እንዲመክት ማሰልጠን እየተቻለ ወደ ኋላ መባል የለበትም።ከደረሱ በኋላ መክቱ ቢባል በመደናበር በትክክል መመከት አይቻልም።ብዛት ብቻውን ዋጋ የለውም።የፖለቲካ ሳይንስ ትምህርቶች ላይ እንደሚገለፀው በጦርነት አሸናፊ ለመሆን መናበብ እና የቁርጠኝነት ሥራን ይጠይቃል።ማኅበረሰብ ተነቃቅቶ እዘምታለሁ ሲል የሚሰለጥንበት እና የሚደራጅበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል።ይህ ካልሆነ እርስ በእርስ አለመተማመን ከመጣ በማህበረሰቡ ሥነ ልቦና ላይ ውሃ ይቸለስበትና ሞራል ይወርዳል
መሪዎች ራሳቸው አገር ውስጥ እንዳለ ሰው መሆን አለባቸው።ትዕዛዛቸውን ወዲያው መቀያየር የለባቸውም።ጦርነት የለም እርሻ እረሱ ተብሎ ወዲያው በማግስቱ ብዙም ሳይቆይ ክተቱ መባል የለበትም።አንዴ ላላ፤ ሌላ ጊዜ ጠበቅ እንደገና ኅብረተሰቡን ማቀዝቀዝ መልሶ ማደናገጥ ተገቢነት የለውም።
አሁን አሁን ከመንግስት የሚሰሙ መረጃዎች ላይ ብዙ ሰው ጥያቄ እየተጫረበት ነው።አንዳንድ ጊዜ እውነት አይመስልም።የመንግስት መገናኛ ብዙኃን እያንዳንዱን እየተከታተሉ በግልጽነት ካቀረቡ ኅብረተሰቡ ከመንግስት ጎን ይቆማል።እነርሱ ታማኝ መሆን አለባቸው።
ሕወሓት ብዙ ሃይሉን እያጣ ነው።ቢያንስ ይህን ያህል ሃይል አጥቷል።መከላከያ ይህን ያህል የሕወሓት ኮሎኔሎችን ገድሏል።ሕወሓቶች እንዲህ አይነት ሽንፈት ደርሶባቸሰዋል ተብሎ መረጃ እየተሠጠ አይደለም።እነርሱ ግን የገደሉትን፣ የማረኩትን እና የያዙትን ሳያስቀሩ ለዛውም ጨምረው ጨማምረው በፕሮፓጋንዳቸው ላይ ያቀርቡታል።በዚህ ጊዜ ሕዝቡ ይረበሻል።
በመከላከያ በኩል ብዙ ስኬት እያለ ሳይገለፅ፤ የእነርሱን ብቻ ማየትና መስማት ከሆነ ብዙ አያዋጣም።ይህ ካልተስተካከለ ባልደረሱበት ደርሰናል እያሉ ኅብረተሰቡን በሥነ ልቦና እያዳከሙ በፕሮፖጋንዳ ቀድሞ የማንበርከክ ስልታቸውን ይቀጥሉበታል።
አዲስ ዘመን፡- ይህ ኅብረተሰቡ ላይ እየፈጠረ ያለው ጫና ምን ይመስላል?
ረዳት ፕሮፌሰር ገናናው፡- እውነት ለመናገር ፕሮፖጋንዳ ራሱ አንዱ የጦርነት ሥልት ነው።ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይባላል።የእኛም ማኅበረሰብ ነገሮችን መርምሮ የትኛው ማህበራዊ ድረ ገፅ ወይም የትኛው መረጃ ትክክል ነው? ብሎ ሳያጣራ ይቀበላል።ይህ ለቴክኖሎጂው አዲስ ከመሆን ጋር የተያያዘ ሲሆን፤ በተጨማሪ ማኅበረሰቡ እንዳለ እየተቀበለ ነው።ስለዚህ እነርሱ ሳይደርሱ ደርሰናል እያሉ አንዳንድ ጊዜም ፎቶ ሾፕ እየተሠራ በሚለቁበት ጊዜ በተቃራኒው በመንግስትም ሆነ በመንግስት ደጋፊዎች በኩል ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም።
ይህ የእነርሱን መረጃ እንዳለ የመቀበል እድልን ይፈጥራል።ሕወሓቶች በፍፁም ለንፅፅር የሚበቃ ሃይል ሳይኖራቸው ማኅበረሰቡም በሥሕተት እውነትም ከፍተኛ ሃይል አላቸው ብሎ እንዲያስብ ያደርጋል።ይህ የማኅበረሰቡን ሥነልቦና የሚሠርቅ ሲሆን ውዥንብር ይፈጥራል።ይህ ሁሉንም ያዳክማል።ስለዚህ ማኅበረሰቡ ማህበራዊ ሚዲያዎችን መርጦ አለመጠቀሙ እነርሱ ሰርገው እንዲገቡ ያመቻቻል።ለእነርሱ የማኅበረሰቡ መወናበድ እጅግ በከፍተኛ ደረጃ ይጠቅማቸዋል።ይህ የረዳቸው በሥልጣን በነበሩበት ዘመን በጥቅማጥቅም እና በሥጋ ዝምድና የተሳሰሯቸው እስከ አሁን ያልተነኩ የሽብር ቡድኑ እንዲመጣ የሚፈልጉ አካላት ስለሚደግፏቸው ነው።መሃል ሰፋሪ ሆነው የተቀመጡ የቀድሞ አጋሮቻቸው እና ጓደኞቻቸውም የእነርሱን ፕሮፖጋንዳ ያራግባሉ።የሽብር ቡድኑ መግፋት ወደ ቀድሞ ጥቅማቸው ለመመለስ በር ስለሚከፍትላቸው እስከ አሁንም ፕሮፖጋንዳውን በማመቻቸት በራስ መተማመናቸው እንዲያድግ በከፍተኛ መጠን ለማወናበድ አግዘዋቸዋል።
መንግሥት ቶሎ እየተከታተለ አፀፋዊ ምላሽ መሥጠት አለበት።መንግስት በማንኛውም መልኩ አቅም አለው።በየትኛውም ነገር ማሸነፍ ይችላል።ፕሮፖጋንዳውንም መምራት አያቅተውም።ምክንያቱም ብዙ የተማረ የሰው ሃይል አለው።ብዙ ደጋፊ አክቲቪስቶች አሉ።ብዙ መገናኛ ብዙኃኖች አሉት።ነገር ግን እየተጠቀመበት አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የማህበራዊ ሚዲያውን ያለ አግባብ የመጠቀም ሁኔታ አለ ብለዋል። በአሁኑ ወቅት የማህበራዊ ሚዲያ ለመረጃ መዛባት ያለው አስተዋፅኦ እንዴት ይታያል?
ረዳት ፕሮፌሰር ገናናው፡- አንድ ቦታ ላይ ሳይደርስ ደርሻለሁ ካለ እዛ አካባቢ ያለው ሰው ሲደናገጥ ሰርጎ ለመግባት ይመቸዋል።በሌላ በኩል መሃል ተይዟል በተባለበት አካባቢ ያለ ሰው በእውነት ቦታው አለመያዙን ሊያውቅ ይችላል።ነገር ግን በቅርብ ርቀት አካባቢ ያሉ ሰዎችን የመወናበድ እና የመደናገጥ ሁኔታ ውስጥ ይከታቸዋል።ትክክለኛው መረጃ ያልደረሳቸው ሰዎች መንግስትን ደካማ አድርጎ ማሰብ በመንግስት ላይ ተዓማኒነትን ያለማሳደር ሁኔታ ያጋጥማል።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ በተለይ በእንዲህ አይነት የጦርነት ወቅት የሚተላለፉ መረጃዎች በትክክል ሕዝብ ጋር እንዲደርሱ መንግስትም ሆነ ኅብረተሰቡ ምን ማደረግ አለባቸው?
ረዳት ፕሮፌሰር ገናናው፡- መረጃዎች በሚሰጡበት ጊዜ ትክክለኛ እና ፍሰት ያላቸው መሆን አለባቸው።የሚጣረሱ መረጃዎች መኖር የለባቸውም።እንዲህ አይነት ክተት በሚታወጅበት ጊዜ ለምሳሌ የአማራ ክልል አካባቢ የኛ ብቻ ነው ወይ ለምን ሌላው አያግዘንም የሚል ሃሳብ አለ።ስለዚህ እንደአገር መታወጅ አለበት።
ሕወሓት ሙሉ ለሙሉ አገሪቱን ከተቆጣጠረ የሚያጠፋው አማራን ብቻ አይደለም።ሁሉንም ነው።ላይሳካለት ይችላል ብለን ብናስብም መንግስት የመሆን ራዕይ አለው።መንግስት መረጃዎችን በትክክል በአንድ ቋት እንዲፈሱ በማድረግ ለማኅበረሰቡ ትክክለኛ መረጃ ማድረስ አለበት።የኅብረተሰቡን አንድነት የሚሸረሽሩ ነገሮች መነገርም ሆነ መፈፀም የለባቸውም።ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ መደረግ አለበት።
አሸባሪ ቡድንን ለመውጋት እንኳን አገር ውስጥ ያለ ህዝብ ቀርቶ የጎረቤት አገራት ሳይቀሩ ሊጋበዙ ይችላሉ።ኦሮሞም፣ ደቡብም፣ ሶማሌም አፋርም ሁሉም የራሱን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት መደረግ አለበት።አገር ከፈረሰ ሁሉም ተጎጂ ይሆናል።
በተረፈ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይ ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።የተነገረ ሁሉ እኩል ቦታ አይሠጠውም።በጥርጣሬ ማየት፤ አካባቢን መጠበቅ፤ ተደራጅቶ ሰልጥኖ ባለበት ሆኖ መረጃዎችን እና ጥቆማዎችን መሥጠት መቻል አለበት።ማህበራዊ ሚዲያውን እንደወረደ የመጠቀም ተግባር መስተካከል አለበት።
ኅብረተሰቡ ማኅበራዊ ሚዲያውንም መገናኛ ብዙኃኑንም ሁሉንም ማመን ስላልቻለ ቶሎ የደረሰውን ይቀበላል።አንዳንዴ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል እንደሚባለው በተደጋጋሚ የሚነገር ፕሮፖጋንዳን እውነት ነው ብሎ የማመን ሁኔታ እንዳይኖር መንግስት ይህንን ተከታትሎ ቢቻል በየዕለቱ መረጃ እያቀረበ ሕዝቡም መንግስታዊ ሚዲያዎችን እንዲከታተል ቢደረግ ጥሩ ነው።
አዲስ ዘመን፡- ከመረጃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ኅብረተሰቡ ያለውን እና ያገኘውን ሳያጣራ ከማሠራጨት ባለፈ አንዳንዴም መከላከያን ለአደጋ የሚያጋልጥ መረጃን እስከማሠራጨት የዘለቀ ሥራ ይሠራል።ማኅበራዊ ሚዲያውን ተጠቅሞ መንግስትን የማገዝ ሁኔታ ላይም ሰፊ ተሳትፎ አይደረግም።ለምሳሌ እነርሱ አንድ አካባቢን ሳይዙ ተቆጣጥረናል የሚል መረጃ ሲያሰራጩ በከተማው ያሉ ሰዎች ውሸት መሆኑን አስመልክቶ አይገልፁም።በተቃራኒው አንዱ ተነስቶ መከላከያ በዚህ በኩል እያለፈ ነው ብሎ መረጃ ያሰራጫል፤ እዚህ ላይ በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችንስ እንዴት ያዩታል?
ረዳት ፕሮፌሰር ገናናው፡- ጦርነት በሎጀስቲክ በቀጥታ ሔዶ በመዋጋት እና በተለያዩ መንገዶች ይደገፋል።በማኅበራዊ ሚዲያ ደግሞ የኅብረተሰቡን አንድነት የሚያሥጠብቅ እና የሚያነቃቃ ነገር በመገናኛ ብዙኃንም ላይ መሠራት አለበት።ከዛ ውጪ ግን ሁሉ ነገር ለሚዲያ መቅረብ የለበትም።ለምሳሌ አንዱ መንገድ ላይ ቁጭ ብሎ ቡና እየጠጣ ፎቶ እያነሳ ልዩ ሃይል በዚህ በኩል እየሔደ ነው።መከላከያም እየተንቀሳቀሰ ነው ካለ ይህ ከሽብር ቡድኑ ጥፋት የተለየ ተግባር አይደለም።ስለዚህ ማንኛውም ማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ለአገር የሚጠቅመውን እና የማይጠቅመውን ለይቶ መለጠፍ አለበት።እያንዳንዱን እንቅስቃሴ መግለፅ አለበት ማለት በዚህ መልኩ አይደለም።ሚዲያዎች በዚህ ላይ መሥራት አለባቸው። የሽብር ቡድኑ በማኅበራዊ ድረ ገፁ የሚያራግበው ፕሮፖጋንዳ እንደሆነ ለማኅበረሰቡ ለማሳወቅ መገናኛ ብዙኃን መሥራት አለባቸው።ከዛ ውጪ ግን ለምሳሌ በአካባቢ ማኅበረሰቡን ወደ አንድነት የሚመልስ የሚያረጋጋ መረጃን ማድረስ ይገባል።
መገናኛ ብዙኃን ዝም ካሉ በማህበራዊ ሚዲያው የሚተላለፈውን እንዳለ የመውሰድ ሁኔታ ይፈጠራል።አንቂዎች (አክቲቪስቶች) የሚያሰራጩት መረጃ ለማን እንደሚረዳ ቀድመው ማሰብ አለባቸው።አንዳንዶች የሚያስቡት ቀድሞ መረጃ ይደርሳቸዋል መባልን ብቻ ነው።ዓላማቸው የማይገባ ሰዎች ያጋጥማሉ፤ እያንዳንዱን እንቅስቃሴ ፖስት የሚያደርጉ አሉ።ይህ ነገር መስተካከል አለበት።አንዳንዴ ያለመብሰል ሁኔታ አለ።መከላከያ በአንድ መኪና ሲያልፍ መከላከያ ፈርሶ መጣ በማለት ውዥንበር የመንዛት ሁኔታ ይስተዋላል።አንድ መኪና የመከላከያ ልብስ የለበሱ ሃይሎች ከመከላከያ አንፃር ምን ያህል አነስተኛ መሆናቸውን ማወቅ አያዳግትም።ነገር ግን እዚህ ደረሱ እያሉ አንዳንዶች ሲያወናብዱ ተከትሎ ማውራት አይገባም።ይህ ተግባር በራሱ በጣም ችግር ነው።አንዳንዴ መነገር የሌለበት ነገር ይነገራል።ይህንንም ቢሆን መንግስት ማስተካከል ይችላል።የኅብረተሰቡን ግንዛቤ ማስተካከል ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ሥም አመሠግናለሁ።
ረዳት ፕሮፌሰር ገናናው፡- እኔም አመሠግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014