ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ሀገራዊው ለውጥ መምጣቱ ያስደነገጠው የትግራይ ክልልን ያስተዳድር የነበረው አሸባሪው ትህነግ ክልሉን ምሸጉ አደረገ። በአዲስ አበባ የሚገኙ የፓርቲውና የመንግሥት ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ አንድ አንድ እያሉ ወደ ምሽጉ ገቡ፤ መቀሌ / ትግራይ/ ኢትዮጵያን ለማፍራስ እድሜውን ሙሉ ሲሰራ ለኖረው አሸባሪው ትህነግ የሴራ ማእከል ሆነች።
የትግራይ ክልል መንግሥት የሀገር ሀብት በመዝረፍ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም የተጠረጠሩ የሕወሓት አባላትና ሌሎችን አሳልፎ እንዲሰጥ የፌዴራል መንግሥቱ ቢያሳስብም ጆሮ ዳባ ልብስ አለ። ይባስ ብለውም ተጠርጣሪዎቹን እንዲይዙ የተላኩ የፌዴራል ፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ሥር አውለው አሰንብቷቸው እንደነበርም ሲገለጽ ነበር፤ በትእቢት የተወጠሩ ነበሩና አያደርጉትም አይባልም። ፌዴራል መንግሥቱ በተጠርጣሪዎቹ ላይ በአዲስ አበባ ክስ ይመሰርታል፤ በጋዜጣም በምንም በምንም ለተጠርጣሪዎቹ ጥሪ ያደርጋል፤ ፖሊስ ይዘህ አቅርብ ይባላል፤ ተይዞ የሚመጣ ግን አልነበረም። ከህግ በላይ ሆነው ነበራ።
በዚህ መሀል በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ግጭት እየተጫረ ጥቃት እየተሰነዘረ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ፣ ማፈናቀል ሀብት ማውድም በስፋት መካሄዱ ይቀጥላል። ያኔ ነበር ሀገራችን በሀገር ውስጥ መፈናቀል ከእነ ሶርያ ተርታ እስከ መሰለፍ የደረሰችው።
ህዝቡ የህግ የበላይነት ይጠበቅ እያለ መጠየቁን ቀጠለ፤ መንግሥት የሀገር መከላከያና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎችን በማሰማራት መረጋጋትን ለመፍጠር ሰራ፤ ችግሩ ግን አንዴ ሲበርድ ሌላ ጊዜ እየተቀሰቀሰ ቀጠለ። መንግሥት የችግሩን ሰንኮፍ መንቀል ላይ አተኩሬ እሰራለሁ እያለ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰድ ውስጥ ገባ።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ቡድኑ የተለያዩ ኃይሎችን መቀሌ ድረስ እየጠራ ሀገራዊ ለውጡን ዋጋ የሚያሳጣ ሥራ ውስጥ ተጠመደ። መንግሥት አቅም የሌለው መሆኑን ጭምር ሲያስገነዝብም ነበር። ለእዚህም አዛኝ ቅቤ አንጓች እንደሚባለው በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች እየተቀሰቀሰ ያለው ግጭትና በዚህም እየተጨፈጨፉ ያሉት ንጹሃን ዜጎች ጉዳይ እንደሚያሳስበው ይገልጽ ነበር። ራሱ በድሎ ራሱ አለቀሰ እንዲሉ።
በቡድኑና በመንግሥት መካከል እየጨመረ የመጣው ውጥረት ያሳሰባቸው የተለያዩ ወገኖች ወደ መቀሌ ተመላለሱ። አምባሳደሮች በራሳቸው ተነሳሽነትም መንግሥት እየላካቸውም ትህነግን ወተወቱ፤ ሕወሓቶች የመንግሥት ጉዳይ እዳው ገብስ ነው፤ በቅርቡ ታያላችሁ ፤እናስተካክለዋለን እያሉ መለሷቸው።
የሀገር ሽማግሌዎች ከመንግሥት ጋር እንደሚከር ቡድኑን ለመጠየቅ መቀሌ ድረስ ቢሄዱም በወጉ እንኳ ተቀባይ አላገኙም። የሃይማኖት አባቶችም ጥረት መና ቀረ። እናቶችም እንባቸውን እያፈሰሱ ለማቀራረብ ቢጥሩም የሚራራ አይደለም በቅጡ የሚያዳምጥም አላገኙም። ትእቢት ብዙ ያሰራልና ያሸባሪው የትህነግ ነገር ሁሉም ነገር የትእቢት ሆነ።
ከዚህ ይልቅ ሕወሓት በህገወጥ ተግባሩ ቀጠለበት። የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት ከሚፈቅደው ውጪ በክልሉ ምርጫ እንዲካሄድ አደረገ። ሌላው የቡድኑ ትእቢት ይህ ነው። ራሱ አስረቅቆ ያጸደቀውን የኢፌዲሪ ህገ መንግሥት በሚጸረር መልኩ ነው እንግዲህ ይህ የሆነው፤ ሕወሓቶች ይህ መሆን እንደሌለበት በተለያዩ መልኩ ሲገለጥላቸው የነበረ ቢሆንም፣ የፌዴራል መንግሥቱ ምን ያመጣል ብለው በእብሪታቸው ቀጠሉበት። መንግሥትም መስርተው ሥራችን ያሉትን ቀጠሉ።
ይህን የሚያህል የህግ ጥሰት ተፈጽሞም የፌዴራል መንግሥት ድርጊቱ ሕገወጥ መሆኑን ከመግለጽ ውጪ እርምጃ መውሰድ ውስጥ አልገባም። የተለያዩ ወገኖች መንግሥት ሕገመንግሥቱን እንዲያስጠብቅ ቢያስገነዝቡትም የወሰደው እርምጃ አልነበረም። ነገሮችን በአንክሮ ሲመለከት ነው የቆየው። እያደር ግን በፌዴራል መንግሥቱና በክልሉ መንግሥት መካከል ያለው መሻከር ወደ ከፋ ደረጃ እየደረሰ መጣ።
የሕወሓቶች ትእቢት ከፍተኛ ደረጃ የደረሰው ግን ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም መቀሌ በሚገኘው የሰሜን ዕዝና በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በነበረው የእዙ ክፍል ላይ በሌሊት ጥቃት መክፈታቸውን ተከትሎ ነው።
ሕወሓት ለ20 ዓመታት የሀገር ሉአላዊነትን ሲያስጠብቅ፣ የሚንቀሳቀስበትን አካባቢ አርሶ አደር ሰብል ሲሰበስብ፣ ሰብሉን ከአንበጣ ሲከላከል፣ ትምህርት ቤት የጤና ተቋም እየገነባ የሚንቀሳቀስበትን አካባቢ ህብረተሰብ ልጆች የማህበራዊ አገልግሎት ተጠቃሚ ሲያደርግ የኖረውን የሰሜን እዝ ነው እንግዲህ ቡድኑ ጥቃት የፈጸመበት።
ጥቃቱን ደግሞ የፈጸመው በእዙ ውስጥ በነበሩት የሕወሓት ተላላኪዎች አማካይነት ነው። ያ ጥቃት የተፈጸመበት ቀን በአንዳንድ የሰራዊቱ ክፍል ሰራዊቱ የሚዝናናበት ቀን ነበር። በእዚህ ላይ አንዳንዶቹ የሰራዊቱ አባላት ቀኑን ሙሉ የአርሶ አደሩን አዝመራ ሲሰብስቡ የወሉበት ነበር። ሁሉም ተዳክመው ወደ መኝታቸው በሄዱበት ሰዓት ነው የፈሪ በትሩ የተሰነዘረባቸው።
ዕኩይ ድርጊቱ ሲታሰብ « በሬ ካራጁ ጋር ይውላል» የሚሉትን ብሂል ይመስላል። የሰሜን ዕዝ ጦር አባላት ከግብዣቸው በኋላ ወደ መኝታቸው ሄዱ ፤ በሰራዊቱ ውስጥ ልዩ ተልዕኮ የተሰጣቸው የሕወሓት አባላት በእነዚህ በሀገሪቱ ውድ የክፉ ቀን ልጆች በሆኑት የሰራዊቱ አባላት ላይ በእንቅልፍ ላይ እያሉ ጥቃት ከፈቱባቸው፤ በዚህም በእዙ ውስጥ የነበሩ በርካታ መኮንኖች በአሰቃቂ ሁኔታ ተገደሉ። የእዙ የሬዲዮ ግንኙነትም አቋረጡት።
በዚህ የፈሪ በትር በእሳት የተፈተኑ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች ከጀርባ ተወግተው ለዘላለሙ አሸለቡ። ለሀገር በዋሉበት በዚያ የትግራይ ምድር አስከሬናቸው እንኳ ወግ እንዳያገኝ ተደረገ። በየቦታው ወድቆ ቀረ። ራቁታቸውን ወደ ኤርትራ እንዲሄዱ የተደረጉት ፣ አስከሬናቸው ራቁቱን የተተወው ጀግኖች ሲታሰቡ ትህነግ ምን ያህል ጨካኝ ስለመሆኑ ያመለክታሉ።
አሸባሪው ትህነግ ይህን አሳፋሪ ድርጊቱን ኮራበት። ሰሜን እዝን በ45 ደቂቃ ውስጥ ጭጭ አረኩት አለ፤ እኔን የሚያህል የለም አይነት ንግግርም በመሪዎቹ አስነገረ። ትልቅ ትእቢት። ፍልሚያ ያልገጠመን የገዛ ወንድምን ገድሎ ይህን ያህል ትእቢት የተሞላበት ንግግር መናገር ያሳፈራል።
የቡድኑ መሪም የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት 80 በመቶ አቅም ያለው ሰሜን እዝ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ አሸባሪው ትህነግ ይህን ወታደራዊ አቅም መላበሱን ይፋ አደረጉ። አበጡ፤ ተኮፈሱ። የመከላከያ ከባድ መሳሪያዎች በሙሉ በእጃችን ገብተዋል ሲሉ ተናገሩ። ከዚህ በኋላ ያለው ሁሉም ነገር ቀላል መሆኑን በመጥቀስም፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ያበቃለት መሆኑን የሚገልጽ ማስፈራሪያ አዘል መልእክት አስተላለፉ። ትህነጎች ፊትም ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ይሉ ነበርና በእዚህ ላይ ይህ የሰሞን ድል እጅግ አሳበጣቸው።
ጥቃቱ አይጥ ሞቷን ስትሻ የድመት አፍንጫ ታሸታለች እንደሚባለው ሆነ። ጥቅምት 24 በሰሜን እዝ ላይ የወሰደውን ጥቃት ተከትሎ በሀገር መከላከያ እየወሰደ ያለበትን እርምጃ ተከትሎ የትህነግ እብሪት ፈተና ገጠመው።
በትግራይ ክልል የተጀመረው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ትህነግን መውጫ መግቢያ ያሳጣው ጀመር። ቡድኑ በፈጸመው ክህደት የተቆጣው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከአማራ ክልል ልዩ ኃይልና ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን በቡድኑ ላይ በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት ሰነዘረበት። በ17 ቀናት ውስጥም ቡድኑ ድል ተመትቶ ወደ ዋሻው ገባ፤ የክልሉ ዋና ከተማ መቀሌም በቁጥጥር ስር ዋለች።
የቡድኑ መሪዎች በተሸሸጉበት አካባቢ በተካሄደ ዘመቻም በርካታዎቹ የተገደሉ ሲሆን፣ ሌሎች በርካቶችም በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል፤ ለወሬ ነጋሪ የተረፉት አሁን በየማህበራዊ ሚዲያው ሲለፈልፉ የሚሰሙት ብቻ ናቸው።
ትእቢታቸው ሁሉ እንደ ጉምም በነነ። ትእቢት እንደ ጎማ ተነፈሰ። እነ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው ውሃ በላቸው። የአገሪቱን 80 በመቶ የጦር አቅም በቁጥጥራችን ስር አውለናል ያሉትም ፊትም ቢሆን ያሉትን ያህል ድል ባይቀዳጁም እጃቸው ገብታ የነበረችውን ትንሽ ድልም ለሰሞን ማቆየት አልቻሉም። ይልቁኑም ተቀጠቀጡበት።
ይቤ አብርሃ ከውቤ በረሃ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014