በሰው ልጅ ውስጥ ትልቅ ቦታ ካላቸው መካከል ልብ እና አዕምሮ (አንጎል) ዋነኞች ናቸው።ልብና አዕምሮ መላ ሰውነትን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ሊቆጣጠር የሚችል ተዓምር የመስራት አቅም አላቸው።ሰዎች አንድን ነገር ያስባሉ።
በአንጎላቸው ወይም በአዕምሯቸው አብሰልስለው በልባቸው ያምኑታል።በዚህ ጊዜ በቃል ሊገለፅ የማይችል ሃይል ስለሚኖራቸው ተዓምር ይሠራሉ።
ሥራው ግን በጎ ብቻ አይደለም፤ ክፉም ሊሆን ይችላል። በ1878 ቶማስ ኤድሰን አዕምሮውንና ልቡን ተጠቅሞ በኤሌክትሪክ የአምፖል ብርሃንን ፈለሰፈ።
ይህ በጊዜው ሊታመን የማይችል ተዓምር፤ ለዓለም ብርሃንን አጎናፀፈ።በተመሳሳይ መልኩ በ1903 በምድር ለመንቀሳቀስ ብቻ የተፈጠረ የሚመስለውን የሰው ልጅ እንደ እርግብ በሰማይ በሮ ያሰበበት እንዲደርስ ለማስቻል አውሮፕላንን ያስተዋወቁት፤ ሁለቱ ወንድማማቾች፤ አዕምሯቸውን ተጠቅመው በልባቸው ያኖሩትን ተዓምረኛ እውነት አረጋገጡት።
የሰው ልጅ በሰማይ እንዲበር በማድረግ ዓለምን ከማስደነቅ አልፈው እልፍ አዕላፍን ጠቀሙ።እነዚህ በበጎ ቢጠቀሱም በሌላ በኩል ደግሞ በዓለም በክፉ የሚነሱም አልጠፉም። የጀርመኑ የናዚ ፓርቲ መሪ አዶልፍ ሂትለር ከ1933 እስከ 1945 ጀርመንን መርቷል።
በሂትለር የአምባገነንነት ዘመን፤ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በቅርብ በመሳተፍ ስድስት ሚሊዮን የሚጠጉ አይሁዶች እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ላይ እልቂት እንዲፈፀም ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል።
የእኛዎቹ ጉዶች እንደነቶማስ ኤደሰን አዕምሮና ልባቸውን ተጠቅመው ተዓምር የሚሰሩት በመልካም ተግባር ሳይሆን እንደሂትለር በአረመኔያዊ ሥራ ላይ ተሰማርተው ተዓምር ለመሥራት አዕምሮና ልባቸውን እየተጠቀሙበት ነው። ሃሳባቸው ልክ እንደሂትለር ሃይለኛና ከባድ ነው።
ኢትዮጵያን ማጥፋት ዋነኛ ግባቸው ነው።ይህ ሃሳብ የሚናቅ እና ቀላል አይደለም።የክፋት ሃሳብን ዓቅደው አብሰልስለው እና በልባቸው አምነው ተከታዮችን ማሰለፍ ችለዋል።ክፉ ሰው ከክፉ ልቡ ክፋት ያወጣል እንደሚባለው የሕወሓት የሽብር ቡድን መሪዎች ሕዝብ ለመጨረስ እና አገር ለማፍረስ በክፉ አንደበታቸው እየሰበኩ አካላቸው ያልጠና ህፃናትን አነሳስተዋል።
የሰው ልጅ እያንዳንዱን የአካሉን ክፍል ተጠቅሞ መላ ትኩረቱን የሰዎችን ኑሮ የተሻለ በማድረግ ጥበብ ላይ ሲሠማራ ያልታደሉት የሽብር ቡድኑ መሪዎች ግን፤ የገዛ ወገናቸውን ወደ ዕልቂት የሚያስገባ ዕቅድ ነድፈው ለመተግበር እየተጉ፤ የክፋታቸው ዕቅድ ግብ እንዲመታ እየሠሩ ነው።ዛሬም በአዕምሯቸው ተጠንስሶና ተብላልቶ ወደ ሌሎች የተዛመተው የክፋት ስሜት በህፃናትና በአረጋውያን ውስጥ ሳይቀር አስርፀውት አሁንም የጥፋት ሹመኛ እና ንጉሥ ሆነው ቀጥለዋል።
ብዙ ሰዎችን ግራ የሚያጋባቸው የነጌቾ በስሜት መነዳት እና መጨረሻ ላይ የሚያጋጥማቸውን ውጤት አለማወቃቸው ነው።እነጌቾ ከዚህ ጦርነት በኋላ፤ ይህንን ሁሉ ሕዝብ ከጨረሱ በኋላ ምን እንደሚሆኑ እንዴት አያስቡም ? ሲሉም ይጠይቃሉ። ነገር ግን የእነጌቾ መጨረሻ በውርደት ሬሳቸውን የሚቀብረው አጥተው አስክሬናቸው የአውሬ ዕራት እንደሚሆን አያጠራጥርም።
ከውስጣቸው ተነስቶ ወደ ሌሎች እየሰረገ የቆየው እና ሁሉንም የሚነዳቸው የክፋት ስሜት እነርሱን ከመቆጣጠር አልፎ በሌሎች ላይም ሲጋባ የመጨረሻው የጦርነቱ ውጤት ብለው ለውሳጣቸውም ሆነ ለተከታይ ጀሌዎቻቸው የሚናገሩት፤ ‹‹የመጨረሻ ግባችን ኢትዮጵያን ማፍረስና ትግራይን መጠበቅ ነው›› ብለዋል።
በተጨማሪ የትግራይን ሕዝብ እያስጨረሱ ህዝቡን ዘር እና ትውልድ አልባ እያደረጉ ትግራይን መጠበቅ እና ትግራይን እንደአገር እንገነባታለን ብሎ ማሰብ ምን ዓይነት የዕብደት ሃሳብ ይሆን?ይህንን ህልም አይሉት ቅዠት አይነት የክፋት ሃሳብ፤ አሁን የደረሱበት ደረጃ ላይ አድርሷቸዋል።ዛሬም ልባቸውን እና አዕምሯቸውን ወደ መልካምነት መመለስ አልቻሉም።የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅመው የሰዎችን ስሜት እያነሳሱ የተዳፈነውን እሳት ንፋስ እየሰጡ በማራገብ ሕዝብ ማስጨረሱን ተያይዘውታል።
የትግራይን ሕዝብ አዲሱ መንግሥት መሬቱን ሊነጥቀውና ሊዘርፈው አልፎ ተርፎ ሊጨርሰው ነው የሚል የበሬ ወለደ የሐሰት ወሬን በማስወራት የትግራይ ሕዝብ ሙሉ ለሙሉ እንዲያልቅ የሚቻላቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው። ሰዎች በንዴትና በሐዘን እንዲነሳሱ በመግፋት፤ ተቆጣጥረዋቸው እንዲነዱ በማድረግ በኩል አዕምሯቸውን የተዓምር ያህል እየተጠቀሙበት ነው።
በተለያየ መልኩ ሕዝብን ለጦርነት አሳምነውና አስገድደው ከማሰለፍ ጀምሮ፤ የቀደመው ሲያልቅ ሌሎች የሚተኩበትን ሁኔታ ማመቻቸታቸው የሚያስገርም ነው።በተዓምረኛ አዕምሯቸው ሕዝቡን በመቆጣጠራቸው እነርሱ ላይ የትግራይ ህዝብ እንዳያምጽባቸው ማድረግ መቻላቸውና አልፎ አልፎ የሚነሱ ጥያቄዎችንና አመፆችን መቆጣጠራቸው የሚያስገርም ነው።
አንዲት የትግራይ እናት አራት ልጆቿ የጥፋት ጦርነት ለማካሔድ ሲሰለፉ እና በወጡበት ሲቀሩ፤ ቆማ መሔድ መቻሏ ያስደንቃል።ይህች እናት ልጆቿ የሚወድቁት ለነጌታቸው የክፋት ዓላማ መሆኑ ደግሞ እጅግ ያሳምማል።ሰው ለበጎ ሥራ ቢሰዋ ክብር ነው።ነገር ግን ለዚህ ዕኩይ የሰው ልጅ ሊያስበው ለማይገባ ህዝብ የማስጨረስ እና የተፈጠሩባትን የኖሩባትን እና ያደጉባትን አገር ማፍረስን መሠረት ላደረገ ጦርነት የሰዎች በተለይም የለጋ ወጣቶች መሞት በእጅጉ ያሳምማል።
እንደው ይህን የመሰለ ህፃናትን ለግድያ የማሰማራት ክፉ ሃሳብ በሰው ውስጥ ይህን ያህል እንዴት ስፍራ ሊያገኝ እንደቻለ ማሰብ በራሱ አድካሚ ነው።ድንቅ ጭንቅላት ትልቅ ነገር አስቦ ዓለምን ያስደንቃል።
ይኸው የነደብረፂሆን ጭንቅላትም ዕድሜ ሳያስተምረው በከፍተኛ የክፉት መንፈስ ተወልዶ እና አድጎ እዚህ ደርሷል።የአገርን መልካም ታሪክ አጥፍቶ የራሱን የመጥፎነት ታሪክ በመከተብ ላይ ተጠምዷል።ምን ማድረግ ይቻላል? ከዚህ ይሰውረን።አሜን!
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014