የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ የተጣለበትን ሀገራዊና ህዝባዊ አደራ በመወጣት ከፍያለ ታማኝነትና ከበሬታ ያተረፈ ሠራዊት ነው፣ በግዳጅም ሆነ በሰላም ወረዳዎች ባከናወናቸው የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴው ይህንኑ እውነታ በተጨባጭ አስመስክሯል። ብዙዎችም ይህንኑ በብዙ ቃል ያጸኑለታል። በተለይ ደግሞ የትግራይ ህዝብ ለዚህ ሠራዊት መልካ ሥነምግባርና አኩሪ ደጀንነት ህያው ምስክር ነው።
ሠራዊቱ ለትግራይ ህዝብ ያለውን አጋርነት ህይወቱን መስዋዕት ከማድረግ አንስቶ ባለው ውስን አቅም ከራሱና ከቤተሰቡ ጉሮሮ ቀንሶ የትግራይን ህዝብ ሲደግፍ ቆይቷል። ከደመወዙ ቆጥቦ ጤና ጣቢያዎችን ፣ትምህርት ቤቶችን እና የተለያዩ የልማት ተቋማትን ገንብቷል። የገበሬውን እርሻ ከማረስ ጀምሮ ሰብል ሲደርስ በማጨድ ሕዝባዊነቱን አስመስክሯል።የገበሬውን እርሻ ከአንበጣ መንጋ ለመታደግም ወሳኝ አቅም ሆኖ ሰርቷል።
ሠራዊቱ ከ2005 እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በትግራይ ክልል ከ113 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የበጎ አድራጎትና የልማት ሥራዎችን አከናውኗል። በነዚህ ስምንት ዓመታትም ከ113 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የበጎ አድራጎትና የልማት ሥራዎችን አከናውኗል። ከክልሉ ህዝብ ጋር ተጋብቶና ተዋልዶም የቤተሰብ ያህል የሆነበትን እውነታ ፈጥሯል።
በዚህ ሠራዊት ላይ የዛሬ ዓመት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም በአሸባሪው ሕወሓት ታጣቂ ኃይሎች ከፍ ያለ የክህደት ጥቃት ተፈጽሞበታል። በጥቃቱ አሸባሪው ቡድን የቱን ያህል አረመኔ ፣ ለማንምና ለምንም የማይመለስ፣ ህልውናውን በደምና በደም ብቻ ከማስጠበቅ ያለፈ አንዳችም ሰብዓዊ አሴት የሌለው ክፉ መሆኑን በተጨባጭ ያስመሰከረበት ነው።
ቡድኑ በሥልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት ሥልጣኑን ለማስጠበቅ የሄደባቸው የደም መንገዶች መላውን ህዝባችንን ከፍ ያለ ዋጋ እንዳስከፈሉ የአደባባይ ሚስጥር ቢሆንም ፣ በሠራዊቱ ላይ የፈጸመው የክህደት ጥቃትና በጥቂቱ የታየው ጭካኔ በታሪክ ተወዳዳሪና አቻ ይኖረዋል ተብሎ የሚታሰብ አይደለም ።በርግጥ ቡድኑ ከውልደቱ ጀምሮ በብዙ ንጹሀን ደም የተጨማለቀ ፣ ከደምና ከደም ውጪ ለማሰብ ያልታደለና ይህንንም ትምክህት አድርጎ የሚፋንን ፣ በዚህም ለመላው የትግራይ ህዝብ እርግማን ሆኖ በታሪክ ውስጥ የተከሰተ የጥፋት ኃይል መሆኑ ግልጽ ነው። ለሀገርም ቢሆን ከውልደቱ ጀምሮ ፈተና የሆነና ሀገርን ተነግሮና ተዘርዝሮ የማያልቅ ዋጋ ያስከፈለም ነው።
ቡድኑ ከመጣባቸው የሴራ መንገዶችና መንገዶቹ ከፈጠሩበት ስጋት አንጻር በብዙ መቅበዝበዝ ውስጥ የሚገኝ ፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ስልጣንን ከጠብመንጃ አፈሙዝ እውን ለማድረግ ህዝቤ ነው እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ በሀሰተኛ ትርክቶች ግራ አጋብቶና ተስፋ አሳጥቶ ወደ ሞት የሚነዳ ፣ ይህንንም እንደ ትልቅ የፖለቲካ ትርፍ አድርጎ የሚያሰላና በዚህም የሚኮፈስ ነው።
ቀደም ባለው ዘመንም በነጻነት ስም የትግራይን ህዝብ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ፤ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላም ፍጹም አምባገነን በመሆን የራሱን የትግራይን ህዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹን በማፈን ከፍ ያሉ ግፎችን ፈጽሞበታል። በሁሉም ነገር እሱን ጠባቂ እንዲሆን በማድረግም ራሱን እንዳይሆን አድርጎታል። ዛሬም ሊያጠፉህ ነው በሚል ዘረኛ ፕሮፓጋንዳው በብልግናውና ዘረፋው ያጣውን ሥልጣን በንጹኃን እልቂት ለመመለስ የክልሉን ወጣት በጦርነት እየማገደው ይገኛል።
በአማራና በአፋር ክልሎች እያካሄደ ባለው የእብሪት ጦርነት ከተሞችን በከባድ መሣሪያ ከመደብደብ አንስቶ ንጹኃንን በአደባባይ አሰልፎ እስከ መረሸን የደረሰ ከፍያሉ የሽብር ተግባራትን እየፈጸመና ይህንንም እነደጀብድ በመቁጠር እየተኩራራ ነው
ሴቶችን ከመድፈር አንስቶ የሰው ልጅን ሰብዓዊ መብት የሚጎዱ ተግባራትን በታቀደና ያተርፈኛል በሚል ስሌት ተግባራዊ እያደረገም ይገኛል።ትናንት በሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ የፈጸመውን ዘግናኝ ተግባራትን ዛሬም በእብሪት በንጹኃን ላይ እያደረገ ነው። ለዚህም ከማይካድራ እስከ ኮምቦልቻ የፈጸመው ግፍና ጭፍጨፋ ህያው ምስክር ነው።
ስለሆነም ይህንን የሕዝብ ጠላት ፍጥረታዊ ማንነት በመረዳት እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ በሚችለው ሁሉ በመሳተፍ የቡድኑን አይቀሬ ሞት ሊያፋጥን ይገባል። ይህንን በማድረግ ራሱን ከታሪክ ተጠያቂነት መታደግ ብሎም ለልጆቹና ለልጅ ልጆቹ የተሻለች ሀገር ማስረከብ ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ ጊዜው አልረፈደም! አቅሙም ብቃቱም አለን!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 24/2014