የአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከተማዋን የሚመጥን ተተኪ፣ ታዳጊ እና ወጣት ሯጮች ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት እንደሚገባ አስታወቀ:: ለዚህም የኢትዮጵያና የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከተማን ውጤታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ታዳጊና ወጣት አትሌቶችን በብዛትና በጥራት ለማፍራት እንደሚሠራ ፌዴሬሽኑ ከትናንት በስቲያ ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት አሳውቋል::
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በርካታ የአትሌቲክስ ክለቦች ያሉ ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት በሚካሄዱ አገር አቀፍ ቻምፒዮናዎች ላይ ግን ከተማ አስተዳደሩ የሚያስመዘግበው ውጤት በሚጠበቀው ልክ እንዳልሆነ ጥናቶች ጭምር ያመለክታሉ:: ይህንን ተከትሎም ፌዴሬሽኑ ከተማዋን የሚመጥን ተተኪ፣ ታዳጊ እና ወጣት ሯጮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ተገቢ መሆኑን ገልጿል:: የአዲስ አበባ ከተማ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ቢኒያም ምሩጽ በተያዘው ዓመት በዕቅድ ተይዘው ከሚከናወኑ የአትሌቲክስ ስፖርት ተግባሮች አንዱ፤ ከተማዋን በሚመጥን ደረጃ የላቀ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ መሆኑን በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ጠቁመዋል::
ፌዴሬሽኑ 39ኛው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደ ሲሆን፤ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጉን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በድረገጹ አስነብቧል:: በጠቅላላ ጉባዔው የ2013 በጀት ዓመት የፌዴሬሽኑ የአፈጻጸም ሪፖርት፣ የተገኙ ውጤቶችና ያጋጠሙ ችግሮች በስፋት የተነሱበት ሪፖርት ቀርቧል:: የ2014 ዓም በፌዴሬሽኑ የሚከወኑ ዕቅዶች ከቀረቡ በኋላም በጉባኤተኛው በውይይት ዳብሮ ሊጸድቅ እንደቻለ የከተማዋ ስፖርት ኮሚሽን መረጃ ያመለክታል:: በዚህም የአትሌቲክስ ስፖርት ተሳትፎዎች፣ ሥልጠናዎች ና ውድድሮች ከኮቪድ- 19 ፕሮቶኮልና መመሪያ አንጻር ትኩረት ተሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተጠቁሟል:: የከተማዋን አትሌቲክስ ለማጠናከርም የስፖንሰር ሺፕ እና ሀብት አሰባሰብ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሠራ ተመላክቷል::
ፌዴሬሽኑ ዕቅዱን ለማሳካት ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ቅንጅታዊ አሠራር ዘርግቶ እንደሚሠራ የጠቆመ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለፌዴሬሽኑ ስኬት የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላትም በጉባዔው ላይ ዕውቅና እና የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከምስረታው ጀምሮ ለከተማዋ የአትሌቲክስ እድገት የበኩሉን አሻራ ለማሳረፍ ብዙ ሲጥር መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ያጋጠሙት ኢኮኖሚያዊ እና አስተዳደራዊ ፈተናዎች ሳቢያ በሚፈለገው ልክ ለዋና ከተማዋ አትሌቲክስ እድገት ሰርቷል ብሎ ለመናገር አይቻልም። ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለው ተቋሙን በሰው ሃይልና በቁሳቁስ በጥሩ ሁኔታ ማደራጀት ባለመቻሉ ወረቀት ላይ ያስቀመጣቸውን እቅዶች መሬት አውርዶ ለመስራት የተቸገረበትን አጋጣሚ ብዙ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የነበሩበትን ችግሮች ለይቶ ለቀጣይ ሥራ እንደ አንድ ግብዓት በመውሰድ የከተማዋን አትሌቲክስ ለማልማት አዲስ መንገድ ጀምሯል። ተቋሙ በአዲሱ የለውጥ መንገድ ላይ መራመድ የጀመረው የፌዴሬሽኑን ሥራ አስፈፃሚ በመምረጥ ሲሆን በቅርቡ የሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ልጅ የሆነው ቢኒያም ምሩፅ ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጡ የሚታወስ ነው።
የፕሬዚዳንቱና የሌሎች የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት መምጣትም የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የአደረጃጀት መሻሻል እንዲያመጣ አስችሏል። ለዚህም አትሌቲክሱን ለማልማት ጥሩ የሥራ አካባቢ መፍጠር አንደኛውና ዋነኛው ሲሆን ይህን እውን ለማድረግ የቢሮውን አደረጃጀት በተሟላ ሁኔታ አስተካክሏል። ቢሮውን በሰው ሃይልና በቁሳቁስ በማደረጃትም በጃን ሜዳ ከነበረው ፅህፈት ቤቱ ፍፁም በተለየና በጥሩ ሁኔታ መገናኛ ወደ ሚገኘው ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ ህንፃ ዘጠነኛ ፎቅ በማዘዋወር እንደ አዲስ ማደራጀቱ ይታወቃል::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2014