የዓለም ስልጣኔን በእጅጉ ካፈጠኑና ካረቀቁ ክስተቶች መካከል የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ ይገለፃል። አሁን አሁን ደግሞ ከግብርናውም ሆነ ከሌሎች መሰል ዘርፎች በተለየ ሁኔታ ቀዳሚውን ስፍራ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና መሰል የሳይንስና ቴክኖሎጂ የፈጠራ ውጤቶች በሰው ልጆች የእለት ከእለት እንቅስቃሴ ውስጥ የመሪነት ድርሻውን ወስደው ይገኛሉ።
አገራችን ኢትዮጵያም ዓለም ከደረሰበት የእድገት ደረጃ እራሷን ለማዘመን በዚህ ፈጣን የባቡር ሃዲድ መስመር ውስጥ ማስገባት እንዳለባት የዘርፉ ባለሙያዎች ምክረ ሃሳባቸውን ይሰጣሉ። መንግሥትም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፉን ሚና ለማጉላት ጠንካራ ፖሊሲ ከመቅረፅ አንስቶ ብቁ ባለሙያዎችን ለማፍራት ጉልህ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይናገራል። እያንዳንዱ ዘርፍም በዘመናዊው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲመራ የሚደረገው ጥረት አበረታች ቢሆንም ዓለም ከደረሰበት የልህቀት ደረጃ ሲመዘን ግን ገና ዳዴ ማለት እንዳልጀመረ ለመረዳት አያዳግትም።
ባሳለፍነው መስከረም ወር የአዲስ መንግሥት ምስረታ ይፋ ተደርጓል። በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገር እድገት ቁልፍ ሚና ያላቸው የሚኒስትር መስሪያ ቤቶችና መዋቅራዊ አደረጃጀቶችን ይፋ አድርገዋል። በእነዚህ አስፈፃሚ መስሪያ ቤቶች ብቁ የአመራር ክህሎት አላቸው ብለው ያመኑባቸውን ከፓርቲያቸውም ሆነ ከፓርቲያቸው ውጪ ያሉትን መልምለው ካቢኔያአቸውን አዋቅረዋል።
በዚህ ሂደት ውስጥ ካለፉ የሚኒስቴር መስሪያቤቶች መካከል ደግሞ “የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር” ይገኝበታል። ለኢትዮጵያ ቀጣይ እጣ ፈንታን ይወስናል ተብሎ የሚታሰበው የፈጠራ ቴክኖሎጂን የሚያበረታታው ይህ መስሪያ ቤትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁንታ መሰረት የአብን ሊቀመንበሩ አቶ በለጠ ሞላ እንዲመሩት መሾማቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ሚኒስትሩ የስልጣን ርክክብ እንዳደረጉ ከመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ጋር ትውውቅ ከማድረጋቸው ባሻገር ቀጣይ በኢኖቬሽን ቴክኖሎጂው ዘርፍ ስለሚሰሩ ተግባራት አቅጣጫ አስቀምጠዋል። ከዚህ ባሻገር የልህቀት ማእከላትን በመጎብኘት በሥራ ላይ ያሉት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በግንባታ ላይ የሚገኙ ማእከላትም በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቁ እንደሚሰሩ ነበር ያሳወቁት።
የቡራዩ ታለንት ልማት ኢንስቲትዩት
መንግሥት የቴክኖሎጂ ፈጠራን በከፍተኛ ደረጃ ለማበረታታት የተግባር ሥራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች አሉ። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ወጣት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ክህሎት ያላቸውን ልጆች ለማፍራት “የክህሎት ማእከል” ወይም የታለንት ልማት ግንባታ ማድረግ ነው። ከዚህ አንፃር ደግሞ በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኘው የቡራዩ የታለንት/ተሰጥኦ ልማት ማእክል ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው፡፡ ይህ ማእከል ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ በሳይንስና ቴክኖሎጂው የፈጠራ ዘርፍ ልዩ ተሰጦ ያላቸው ወጣቶችን በብዛት ለማፍራት አይነተኛ ሚና እንደሚጫወት ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚገልፁት።
የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አቶ በለጠ ሞላን ጨምሮ አዲስ የተሾሙት አመራሮች ቀዳሚ አጀንዳቸው በማድረግ የታለንት ልማት ኢንስቲትዩቱ ግንባታ ያለበትን ደረጃ ከቀናት በፊት ጉብኝት በማድረግ በቀጣዮቹ መቶ ቀናት ተጠናቆ በሙሉ አቅም ወደ ትግበራ የሚገባበት ሥራዎች እንደሚከናወኑ አሳውቀዋል።
በጉብኝቱ የማእከሉ ዓላማ፣ የግንባታ ሂደት፣ ግንባታው የደረሰበት ደረጃና ያጋጠሙ ችግሮችን የተመለከተ ማብራሪያ ከፕሮጀክት አማካሪዎች፣ ከተቋሙ ወኪሎች ለሚኒስትሮች ገለፃ ተደርጎ ነበር፡፡ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ምርምር ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ባይሳ በዳዳ (ፒኤችዲ) በርካታ ተግዳሮቶችን በማለፍ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ የተደረገውን ጥረት ከጉብኝቱና ከማብራሪያው መረዳታቸውን ማስተዋላቸውን ይናገራሉ፡፡ ከመንግሥት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ፕሮጀክቱን በቀጣይ መቶ ቀናት በቅድሚያ በማጠናቀቅ ለታለመለት ዓላማ ዝግጁ ለማድረግ በዘርፋቸው ቅድሚያ እንደሰጡት ገልፀዋል፡፡
ማእከሉን ተዘዋውረው ከተመለከቱት የዘርፉ አመራሮች መካከል የአይሲቲ ልማትና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ ዓሊም ይገኙበታል። በጉብኝታቸው ፕሮጀክቱ የደረሰበትን ደረጃ ተመልክተው በአፈፃፀሙ መደሰታቸውን ነው የተናገሩት ።
“የኛ ሥራ ቴክኖሎጂ ማበልጸግ ብቻም ሳይሆን ተሰጥኦዎችን ማበልጸግም በመሆኑ መሰል ተቋማት መጀመራቸው ሊበረታታ ይገባል” ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የፕሮጀክቱን መጓተት ለማስቀረት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ያገኙትን አርዓያነት ተጠቅመው በፍጥነት በማጠናቀቅ ለቃላችን ታማኝ ሆነን መገኘታችንን ማሳየት ይኖርብናል የሚል መልክት አስተላልፈዋል።
የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ በለጠ ሞላ በበኩላቸው የተመለከቱት ፕሮጀክት ግዙፍና ሊያሳካው የታለመለት ዓላማም ትልቅ መሆኑን አንስተዋል ፡፡ ይህን አገራዊ ፋይዳው የጎላ ግዙፍ ፕሮጀክት መዘግየቶችን ያጋጠሙት መሆኑን መገንዘባቸውን ገልፀው፤ ግንባታው የተጓተተ ቢሆንም አሁን የደረሰበት ደረጃ ሲታይ በተቀመጠለት የመጨረሻ መርሐ ግብር ከተጠናቀቀ አበረታች መሆኑን አንስተዋል፡፡ ጥራትን ለማስጠበቅ የተደረገውን ጥረት ማስተዋላቸውን በማንሳትም ፕሮጀክቱ ጥራትን ከጊዜ ጋር ማጣመር ስላለበት ከዚህ በላይ እንዲጓተትና እንዲዘገይ ሊፈቀድለት እንደማይገባ ነው የገለፁት፡፡ ትልልቅ አገራዊ ጉዳዮችን በተቀመጠላቸው ጊዜ ተፈጽመው ለሕዝብ ጥቅም እንዲውሉ መስራት የሁሉም ድርሻ ስለሆነ በዚህ ፕሮጀክትም ፊዚካል ሥራው በተቀመጠለት የመጨረሻ ጊዜ ተጠናቆ ለታለመለት ዓላማ ሊውል ይገባል። በመሆኑም አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ ለቀጣይ የእቅድ ሥራዎቻችን ስኬት የሚሆን ስንቅ በሚሆን መልኩ መፈፀም እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት ፡፡
“የቡራዩ ልዩ ተሰጥኦ ማሰልጠኛ ግንባታ ፕሮጀክት አፈፃፀምን ለመገምገም የግንባታ ሥራው በሚከናወንበት ቡራዩ ከተማ በተደረገው የመስክ ጉብኝት ወቅት የተሰሩ ሥራዎችን፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና ቀሪ ሥራዎችን መለየት ችለናል” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከግንባታው ጅማሬ እስከ ዛሬ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ፕሮጀክቱ ለተደጋጋሚ መጓተት መጋለጡን መሆኑን አንስተዋል። የዚህ ፕሮጀክት ግንባታ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም በታሰበለት ጊዜ ባይሆንም በታሰበለት ዓላማ ልክ ያለ ተጨማሪ መጎተት ከተጠናቀቀ አሁንም ተስፋ ሰጭ መሆኑን መገንዘባቸውን ተናግረዋል። ይህን አጓጊ ፕሮጀክት ያጋጠመውን መጓተት አስቀርቶ አፋጣኝ መፍትሔ ለማስቀመጥ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነው የገለፁት። በተደረሰው ስምምነት መሰረት በአጭር ጊዜ ግንባታው ተጠናቆ የታሰበለትን ዓላማ ማሳካት እንዲቻል የሥራ መመሪያና የአፈጻጸም አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም ፕሮጀክቱ አገራዊ ፋይዳ ያለው እንደመሆኑና የልዩ ተሰጥኦ ያላቸው ዜጎች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ በሳይንስ፣ በኢንጂነሪግና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ተሰጥኦዋቸውን የሚያሳድጉበት ተቋም በመሆን ሥራውን ሊጀምር ስለሚገባው አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት ከግንባታው ፈጣን የማጠናቀቂያ ሂደት ጎን ለጎን እንዲከናወን አቅጣጫ መቀመጡን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ መሰል ተቋማት ዓለምአቀፍ አሰራርን ተከትለው በቀዳሚነት መቋቋምና ከነገም ተበድረን ልናሳካቸው ከሚገቡ ማዕከላት ቅድሚያ የሚሰጣቸውና ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ በመሆናቸው ሁሉም ዜጋ ሊደግፋቸው እንደሚገባ ይናገራሉ።
“በዓለም አቀፍ ደረጃ የተረጋገጡ ፋይዳቸው ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ውጥናቸው ከማንም ቢሆን በትኩረት ፈጽመን ልናሳካቸው እና ለላቀ አገራዊና ሕዝባዊ ጥቅም ልናውላቸው እንደሚገባ ይታመናል” ያሉት አቶ በለጠ፤ መሰል ተቋማት በየክልሎች እንዲስፋፉ ለማድረግም እንዲቻል ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ ተናግረዋል። ከወዲሁ በትብብር አቅዶ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለመግባትም ከሚመለከታቸው ጋር ተቀናጅተን ለመስራት መዘጋጀታቸውን አንስተዋል።
ሌላው የማበረታቻ መንገድ
ከላይ ለማንሳት እንደሞከርነው ኢትዮጵያውያን የቴክኖሎጂ የፈጠራ ባለሙያዎችን ለማበረታታት በመንግሥትም ሆነ በግሉ ዘርፍ በርካታ ጥረቶች ሲደረጉ ይስተዋላል። ለምሳሌ ያክል በፖሊሲና በህግ የተደገፈ የትምህርት ማሻሻያ ስርአት፤ የፈጠራ ባለሙያዎችን በቀጥታ የመደገፍና አዳዲስና ወጣት የብሩህ አእምሮ ባለቤት የሆኑ ወጣቶች ማፍራት እንዲቻል የልህቀት ማእከላት ግንባታ ወሳኝ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነት በመመስረት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን ወጣቶች ሁኔታዎችን እንዲመቻችላቸው የሚደረገው ጥረት ይነሳል። ለዚህ ማሳያ እንዲሆን ከሰሞኑ እየተተገበረ የሚገኝ አንድ ፕሮጀክትን ከዚህ እንደሚከተለው እንመልከት።
የኢኖቬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በቅርቡ በቴክኖሎጂ ፈጠራ ሃሳባቸው ተወዳድረው ወደ ኢንኩቤሽን ማዕከል ለገቡ የቴክኖሎጂ ዘርፍ ሥራ ጀማሪዎች የሥራ ማስጀመሪያ ገንዘብ እንደሚሰጥ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ እድል የተመቻቸው በቴክኖሎጂ ፈጠራ ሃሳባቸው ተወዳድረው ወደ ስልጠና ለገቡ “ቴክኖሎጂስቶች” ሲሆን በሚደረግላቸው ድጋፍ ውጤታማነታቸው ለማረጋገጥ “የቴክ – ስታርታፖች” የሥራ ማስጀመሪያ የመነሻ ካፒታል መስጠት ዋነኛ ግቡ አድርጎ የተነሳ ነው።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ከኮሪያ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በመተባበር ወደ “ስታርታፕ” ለሚያደርጉት ሽግግር ለሁለተኛ ዙር ወደ ኢንኩቤሽን ማዕከል ለገቡ አሥራ ሁለት የቴክኖሎጂ ፈጠራ ሐሳብ ተወዳዳሪዎችን የጀማሪ ኢንተርፕራይዝ ማሳደግ የሚያስችል ቅድመ ስልጠናም ሰጥቷል። ስልጠናው የፋይናንስ፣ የቴክኒክና በማዕከሉ ውስጥ አስፈላጊው እገዛ ተደርጎላቸው የፋይናንስና የቴክኒክ እገዛ የሚያስገኝ መሆኑን መስሪያ ቤቱ ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
አቶ ታደሰ አንበሴ በኢኖቬሽን ልማት እና ምርምር ዳይሬክተር ጀነራል የቴክኖሎጂ ኢንኩቤሽን ልማት እና አስተዳደር ዳይሬክተር ናቸው። ስልጠናው የተሰጠው ከኮሪያው ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ድርጅት ጋር በመተባበር መሆኑን ይናገራሉ። ዓላማውም ለኢኖቬሽን ልማት፣ ለሥራ እና ሃብት ፈጠራ ከተወዳደሩና ከተመረጡ የቴክኖሎጂ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ወደ ጀማሪ ኢንተርፕራይዝ እንዲያድጉ ለማብቃት መሆኑን ይገልፃሉ።
ሠልጣኞቹ ወደ ሥራ ጀማሪ ደረጃ ሲያድጉ የቢዝነስ ሃሳብን በአጭር ጊዜ ማመንጨትና ማቅረብ በሚቻልበት ስልት (pitching training) ላይ ሰልጥነው ራሳቸውን አሳድገው የሃብትና የሥራ ፈጣሪዎች ማዕከል እንዲሆኑ ማስቻል ነው። ሰልጣኞቹ በኢኖቬሽን ዘርፍ “ስታርትአፕ” በመደገፍ የፈጠራ ሃሳብ ያላቸውን አካላት ለማነሳሳት በሚያስችል መልኩ ድጋፍ ተደርጎላቸው ውጤታማነታቸው ከፍተኛ ለሆኑት እስከ አምስት ሺህ ዶላር የሥራ መነሻ ገንዘብ ይሰጣቸዋል።
ማጠቃለያ
መንግሥት በቴክኖሎጂ ልማትና የፈጠራ ክህሎት ላይ ለመስራት የሚያደርገው ጥረትና የሰጠው ልዩ ትኩረት አበረታች ነው። በተለይ ለቀጣዩ ትውልድ መሰረት የሚጥሉ ማእከላት ግንባታን ማስጀመሩና አንዳንዶቹም ወደ ትግበራ ለመግባት ጥቂት ጊዜያት እየቀራቸው መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከተለያዩ አገራትና ተቋማት ጋር ትስስር በመፍጠር ከላይ እንደ ማሳያ ያነሳነው ፕሮጀክት አይነት በስፋት ለማመቻቸት ቢሞከር ከዘርፉ አያሌ ባለብሩህ አእምሮ ወጣቶችን ማፍራት እንደሚቻል የዝግጅት ክፍላችን ያምናል። በግል ጥረታቸው ውጤታማ ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እያስተዋወቁ የሚገኙ ግለሰቦችን መደገፍና ለትብብር ደጅ ድረስ ሲመጡ በቀናነት መቀበልም ከነዚሁ የመንግሥት አካላት የሚጠበቅ ነው። በትንሽ ጥረት ይህን ማድረግ ከቻልን “የሰነቅነው” ራእይና በሳይንስና ቴክኖሎጂ ጠንካራ አቅም የምትገነባ ኢትዮጵያን የማየት ህልም እውን ለማድረግ ጊዜው እሩቅ አይሆንም እንላለን። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2014