ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ መንግሥታትን አይታለች:: ሁሉም መንግሥታት በቻሉት ሁሉ ለኢትዮጵያ መልካም በመስራት ስማቸውን በታሪክ ድርሳን ላይ ከትበው ያለፉ ናቸው:: ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ የተፈጠረው የአሸባሪው ሕወሓት መንግሥት ግን ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ታጥቆ የተነሳ ከመሆኑም በተጨማሪ በአስነዋሪ ድርጊቱ መልከ ደማሟን ሀገር ጥላሸት የቀባ ነው:: ሀገሪቱ በታሪኳ አይታው የማታውቅ የግፈኖች ስብስብ ቡድን ነው:: ስሙ የጎደፈ፣ ምግባሩ የተበላሸ በሌሎች ስቃይ ሀሴትን የሚያደርግ ነበር::
የኢትዮጵያን የታሪክ ድርሳን የበረበረ ሰው በየትኛውም መልኩ ስለ ሀገሪቱ የሚደመምበት ድንቅ ታሪክና፣ የሕዝቦች ባሕል እንደሚያገኝ ጥርጥር የለውም:: ምክንያቱም የትላንቷ ኢትዮጵያ ፈርሐ እግዚአብሄር ባላቸው ሕዝቦቿ የተቃኘች፤ በፍቅርና በርሕራሄ የተሞሉ ስለነበሩ ነው:: መሪዎቿም ቢሆኑ በየትኛውም ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑም በሀገር ፍቅር የሚታሙ አልነበሩም::
በአሸባሪው ሕወሓት ዘመን ግን ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ሆኗል:: ቡድኑ ከሀገራዊ ተጨባጭ እውነታዎች በመውጣት ሌላ ሀገርና ሕዝብ ለመፍጠር ሞክሯል:: ብሄር እና ቋንቋን መሰረት ያደረገ ትውልድ፣ ጥላቻና ርግማንን የመረጠ ትውልድ ለመፍጠር ረጅም መንገድ ተጉዟል:: እኛነትን ገሎ እኔነትን ያገነነ የአስተሳሰብ መሰረት ለመጣል ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም::
ይሕ የቡድኑ 27 ትጋት መሰረት ናቸው:: በዚሕም የሀገሪቱን አንድነት ሆነ የሕዝቦቿን አብሮ የመኖር ዘመናት የተሻገረ እሴቶች በብዙ ሸርሽሯል። በዚሕም ብዙዎች ለስደትና ለሞት ለከፋ የሥነ ልቦና ቀውስ ተዳርገዋል። ትውልዱም በብዙ ጫና የአሸባሪውን ሕወሓትን አመጽ ፍሬ እንዲበላ ተደርጓል:: በዚሕም ብዙ ዋጋ እንዲከፍል ተደርጓል።አዲስ ማንነት ያሻዋል:: የሕወሓትን አስተሳሰብ በመዋጋትና ታሪክ በማድረግ ከሞት መነሳት ግድ ይለዋል:: ለዚሕ ደግሞ ጊዜው አሁን ነው:: ሕወሓትን በመቃወም ከሚጮሁት ድምጾች ጋር ሊያብር ይገበዋል እላለሁ:: ኢትዮጵያዊነትን ለመመለስ ይሄ የመጨረሻው ተስፋችን ነው::
የአሸባሪው ሕወሓት የሥልጣን ዘመን በአዳፋ ገጾች የተሟላ ነው:: ቡድኑ በእጁ ላይ የበርካቶች ደም አለበት:: ሀገሪቱን እንዲሕ ጥሎት ለሚሄደው ሥልጣን ሲል በዘርና በብሄር ከፋፍሎ ያልተገባ ዋጋ እንድትከፍል አድርጓል:: በልቡ ርሕራሄ የሌለው፣ ኢትዮጵያን አበላሽቶ የሳለ፣ ኢትዮጵያዊነትን አዛብቶ የተረከ የትውልድ ባለ ዕዳ ነው:: እንደ ርብቃ ልጆች ለብኩርና የሚጋፋ፣ ወንድሞቹን ገሎ አሸናፊ ለመሆን የሚታትር ነው::
በወገኖቹ ሞትና ስቃይ የሚስቅ፣ በሕዝቦች መከራና እንግልት የሚነግድ ሕሊና አልባ ቡድን ነው:: ያለፉት 12 ወራቶች የዚሕን ቡድን የጭካኔ ጥግ የታየበት፤ ለብዙዎች የመከራ ጊዜያት ነበሩ:: ዛሬም ተፈጥሯዊ ሞቱን ላለመሞት በሚያደርገው መፈራገጥ የብዙዎችን ሕይወት ፈተና ውስጥ እንደከተተ ነው።
ቡድኑ ፍጹም በሆነ በዓለም ታሪክ ባልታየ መልኩ የክልሉን ሕዝብ ሲጠብቅ በነበረው፤ለሀገርና ለሕዝብ ከፍያለ ዋጋ የከፈለውን፤ለመክፈልም ዝግጁ የነበረውን የሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ክሕደት ፈፅሟል። በዚሕም የሕዝባችንን ልብ የሰበረ የባንዳነት ተግባር ፈፅሟል። ጥቃቱን ተከትሎ ባሉት 12 ወራት ውስጥም ብዙ ጭካኔ የተሞላባቸው ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል። በማይካይድራ ታሪክ የማይረሳውን ግፍ ፈጸሟል:: ዘር ተኮር የሆነው ይሕ ጥቃት የኢትዮጵያውያን የጋራ እንባ… የጋራ ሲቃ ሆኖ በትውልድ ልብ ውስጥ ለዘላለም ይኖራል::
አሸባሪው ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅ የኖረውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በተኛበት ማረዱ ሳያንሰው ምንም የማያውቁ ንጹሀንን በብሄራቸው ብቻ ቤት ለቤት እየዞረ ለዚሁ ተግባር ባሠለጠናቸው አራጆች አርዷል። በዚሕም ለአማራ ሕዝብ ያለውን ሥር የሰደደ ጥላቻ በተግባር አሳይቷል::
ከአብሮነት በቀር ምንም የማያውቁ፣ ቧርቀው ያልጠገቡ ሕጻናትን፣ ወጣቶችንና አዛውንቶችን ሳይቀር በግፍ በዓደባባይ አርዷል። አማራ ጠሉ ይሕ ቡድን የአማራን ታሪክ ለማጠልሸት እና የሕዝቡን ሕልውና አደጋ ውስጥ ለመክተት ያላደረገው ጥረት አልነበረም:: ከትላንት እስከዛሬ በአማራ ሕዝብ ላይ በርካታ በደሎችን ሲፈጽም እንደኖረ የዓደባባይ ሚስጥር ነው::
ሌሎች ታሪኮችን ትተን ቡድኑ ምን ያክል ለአማራና ለአማራውያን ጥላቻ እንዳለው ማይካድራን ማየቱ ብቻ በቂ ነው:: ከሰውነት በራቀና መቼም ይቅር ሊባል በማያስችል ሁኔታ ክቡሩን የሰው ልጅ በብሄሩ ብቻ እየለዩ ገድለዋል። ትልቁን የሰው ልጅ እንደ ተራ ነገር በመቁጠር ሬሳውን በየመንገዱ በመጣልና በመጎተት ሊደረግ የማይችል አውሬያዊ ባሕሪ አሳይተዋል::
ክብር በሌለው ለእንስሳ እንኳን በማይገባ ሁኔታ በጅምላ ከመቅበራቸውም በላይ ሰዎችን ከነነፍሳቸው በመቅበር የጭካኔ ጥጋቸውን አሳይተውናል:: አርሶ ከመብላት ውጪ ፖለቲካ ምን እንደሆነ የማያውቅን ሰው ለመግደልና ለማሰቃየት ወጣት ከማደራጀት በላይ ጭካኔ የለም:: ወጣቱን ለልማት ከማደራጀት ይልቅ ብሄርን መሰረት ባደረገ ሁኔታ ዘር እንዲያጠፋ ማሰልጠን ቡድኑ የመጣበትን ትላንትናዊ ጎዳና በግልጽ ያሳያል::
ወጣቱ ሀገርና ሕዝብ እንዲጠቅም በሥነ ምግባር ከማነጽ ይልቅ በወንድም ሕዝቦቹ ላይ እንዲነሳ የጥላቻ ንግግሮችን አስተምረውታል:: ዛሬም ድረስ ቦርቀው ያልበቃቸውን አንድ ፍሬ ሕጻናት በአደንዛዥ እጽ ሕሊናቸውን በማሳት ለጦርነት እያሰለፉ በአዲሱ ትውልድ ላይ ሳይቀር መጥፎ ወንጀል እያስፈጸሙ ይገኛሉ::
በቀደመው ዘመን የጀርመን ናዚ ቡድን የጭካኔ ጥግ ተደርጎ የመወሰዱ እውነታ የአደባባይ ሚስጥር የመሆኑን ያሕል የአሸባሪው ሕወሓት የጭካኔ ጥግም በተመሳሳይ መንገድ የአደባባይ ሚስጥር ሆኗል። ለሁለቱም እኔነት እንጂ እኛነት አይሰራም:: በእነሱ ፊት ሰውነት ምንም ነው:: ፋሺስት ናዚ በታሪክ ብዙ ንጹኃን ያለቁበትን ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ለጀርመናዊያን ስለ አይሁዶች መጥፎ ወሬዎችን ይነዛ ነበር:: ጀርመናዊያንም በመሪያቸው የሚነገራቸውን የተሳሳተ ወሬ በመስማት በአይሁዳውያን ላይ ጥርሳቸውን መንከሳቸውም ይታወሰል::
በዚሕም በታሪክ ምንም የማያውቁ ስድስት ሚሊየን ያክል ንጹኃን ዜጎች ያለቁበት ጦርነት የጥላቻ ንግግር የተጀመረ ነው:: የሕወሓት 27 ዓመታት የስልጣን ጉዞም ከዚሕ የተለየ አልነበረም:: የጥላቻ ንግግሮችን ጨምሮ ይሕንን የሚሸከሙ ትርክቶችን ፈጥሮ በብዙ ተንቀሳቅሷል። ታሪክ እንዲያበላሹ በቀጠራቸውና ይሁንታ በሰጣቸው ግለሰቦች በመታገዝ ብሄርን ከብሄር ለማጣለት ከፍ ባሉ ሴራዎች ተገልጿል::
የቡድኑ ነውሮች ጫፍ የላቸውም:: በትላንትና በዛሬ በነገም መካከል የሚገለጡ በርካታ ነውረኛ ተግባራትን ፈጽሟል:: ወጣቱን በእውቀት ለሀገሩ ጠቃሚ ሆኖ እንዲሰራ ከማድረግ ይልቅ የጥላቻ ወሬዎችን በመንዛት አዕምሮውን በእኔነት ስሜት መርዞታል:: ከአንድነት ይልቅ መለያየትን በመስበክ በሕዝቦች መካከል የጠብ ቁርሾን በመፍጠር የሥልጣን መደላድሉን ሲያመቻች ነበር::
በተለይም በትግራይና በአማራ ወንድማማች ሕዝቦች መካከል የለየለትን ደም አፋሳሽ የውሸት ትርክት በመፍጠር በብዙ ነገር የተሳሰረን ሕዝብ ለመለያየት የሄደበት ርቀት ሁነኛ ችግር ሆኖ የቱን ያሕል ሁለቱን ሕዝቦች ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለ ስለመሆኑ ተራኪ የሚያስፈልገው አይደለም:: ቡድኑ ወደ አማራ ክልል ገብቶ እያደረሰ ያለው ውድመትና ጥፋት የዚሕ ማሳያ ነው።
ባሳለፍነው አንድ ዓመት ብቻ በቡድኑ ታጣቂዎች ይሄ ነው የማይባል ስቃይና መከራ በአማራ እና በአፋር ንጹኃን ላይ እየደረሰ ነው:: የቡድኑ ታጣቂዎች ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል እጅግ ከሰብዓዊነት የወጡ አውሬያዊ ድርጊቶች እየፈጸሙ ነው:: ነፍሰ ጡር እናቶች ሆዳቸው በስለት እየተቀደደ ከሰው ልጅ አዕምሮ በላይ የሆነ እጅግ አረመኔያዊ ተግባራትን ተፈጽሟል ::
ሕጻናትን ሳይቀር ደፍረዋል፣ ንፁኃን ቤት ተዘግቶባቸው እሳት ተለቆባቸዋል፣ ልጆችን ወላጅ ፊት በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል መጨረሻ የሌለውን አረመኔያዊ ድርጊቶች ተፈጽመዋል::በአሸባሪው የሕወሓት ቡድን በማይካድራ ብቻ ከ600 በላይ አማራዎች በብሄራቸው ብቻ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገለዋል:: አማራነት ነውር እስኪመስል ድረስ ሰዎች አማራ በመሆናቸው ብቻ መታወቂያቸው እየታየ ከአዕምሮ በላይ በሆነ የጭካኔ ተግባር በአሰቃቂ ሁኔታ ይሄን ዓለም ተሰናብተዋል::
ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሸባሪ ሕወሓት የሥልጣን ዘመን የደረሰባትን ያክል ኪሣራ መቼም አጋጥሟት አያውቅም:: በእያንዳንዳችን ትላንት ውስጥ በቡድኑ የተጻፉ በርካታ አዳፋ ታሪኮች አሉ:: ዛሬ ላይ እንደ ወጣት ሀገርና ሕዝብ ከመጥቀም ይልቅ በማይጠቅመን የብሄር አስተሳሰብ ውስጥ ተዘፍቀን የምንኖረው ያለፈው ስርዓት ያሳደረብን ተጽዕኖ ነው::
በሰው ልጅ ላይ ተጀምረው በሰው ልጅ ላይ የሚያበቁ በርካታ ሰዋዊ ግፎች መነሻቸውም ሆነ መድረሻቸው የቡድኑ የተንኮል ሴራ ነው:: ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሀገርና ሕዝብ ባልቆሙ ራስ ወዳድ ቡድኖች ለ27 ዓመታት የኋሊት ተጉዛለች:: እነዚሕ ቡድኖች ከጥፋታቸው ከመማርና ሕዝቡን ይቅርታ ከመጠየቅ ይልቅ ዛሬም በዚሕ ጥንታዊ እሳቤያቸው ውስጥ ሆነው የተስፋ ጎሕ የቀደደላትን ሀገር ካላጨለምን እያሉ ነው:: ያለፈው ሳያንሳቸው ዛሬም ጦራቸውን ሰብቀውበናል:: እነዚሕን ኃይሎች በተባበረ ክንድ ልናቆማቸው ይገባል::
በተለይም የሴራዎች ሁሉ ባለቤት የሆነው አሸባሪው ሕወሓት የተንኮል ሴራ በዋናነት አማራነት ላይ ያጠንጥን እንጂ ሁሉንም ብሄር የሚነካ ነው:: ለሀያ ሰባት ዓመታት የተሰሩብን የብሄር እሳቤዎች የጋራ ችግሮቻችን ናቸው:: በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የተዘረፉ የሀገር ሀብቶቻችን የጋራ ንብረቶቻችን ናቸው:: የሕወሓት ተንኮል በሁላችንም ሕልውና ላይ እጁ አለበት ነው:: እጆቹ መልካም የሚመስሉ የተንኮል እጆች ናቸው:: እየዳሰሱ የሚሻክሩ፤እየዳበሱ የሚያሙ::
ሊቆጨን ከተገባ በቡድኑ የሥልጣን ዘመን ያለፉት እነዛ 27 ዓመታት ሊቆጩን ይገባል:: በእኔነት ውስጥ የበቀሉ፣ እኛነትን የገደሉ ብዙ መርዛም አሻራዎች የተፈጠሩበት ነው:: እንደ ሀገር ሀገራዊ መልካችን እንኳን በአንድም ይሁን በሌላ ይኸው አሻራ የሚታይበት ነው:: አሁናዊ ሥነ ልቦናችን ያለፈው ስርዓት የፈጠረው አግድም አደግ እሳቤ የሚታይበት ነው::
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ ከአሸባሪው ሕወሓት ሌላ ሀገር ለማፍረስ ሥልጣን የያዘ መንግሥት የለም:: ሀገር ከሚጠቅም ይልቅ ሀገር በሚጎዱ ጉዳዮች ላይ ጥልቅ ውይይትን የሚያደርግ፣ ሕዝቦችን በዘርና በብሄር በመለያየት ግላዊ አጀንዳውን ሲያስፈጽም የኖረ መሪ እና ቡድን የለም::
ሀገራችን ኢትዮጵያ በታሪክ ዋጋ ካስከፈሏት ጉዳዮች ውስጥ አንዱ ራዕይ በሌለው የሕወሓት መንግሥት መመራቷ ነው:: ቡድኑ እንደ ድርጅት ሲመሰረት ዓላማና እቅዱ በብሄረሰቦች መካከል መለያየትን በመፍጠር የአንድ ብሄር የበላይነትን ማቀንቀን ነበር:: እንዳሰበውም ለዘመናት ተዋደው የሚኖሩ ሕዝቦችን በመከፋፈልና የጠብ ቁርሾ በመፍጠር የበላይነቱን ሲያስጠብቅ ቆይቷል::
ብሄር ተኮር እሳቤያችን የተፈጠረው በዚሕ ድርጅት የሥልጣን ዘመን ነበር::ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ከሚያውቁ አባቶቻችን አብራክ በቅለን ቡድኑ በጫነብን የዘር እሳቤ ታመናል:: በአባቶቻችን ዓይን የምናይ፤ በአያቶቻችን ጆሮ የምንሰማ አይደለንም:: እንደ ቀደመው ትውልድ ሀገርና ሕዝብ የሚል ልብ እያጣን መጥተናል:: ከዚሕ ነውረኛ እውነታ መውጣት ይኖርብናል።
ሀገር ታሪክና ትውልድ ሁሌም ይኖራሉ:: ከእኛ የሚጠበቀው ለሀገርና ለትውልድ የሚበጅ መልካም ታሪክን መጻፍ ነው:: ዛሬ ላይ የምንጽፈው ታሪክ ነገ ለሚፈጠረው ትውልድ ክብር ወይም ደግሞ ውርደት ነው:: በጋራ ታሪክ፣ በጋራ ሀሳብ፣ በጋራ ብዕር ሀገራችንን ተጋግዘን እንሳል እላለው::
እንዲሕ ሲሆን የተናጠል ታሪክ አይኖረንም:: እንዲሕ ሲሆን የብቻ ሕይወት አይኖረንም:: ሀገር ለብቻ አትሳልም:: ዓለም ላይ ሀገሩን ለብቻው የሳለ ግለሰብ የለም:: ሀገር አስተሳሰብ ናት:: ሀገር የእኔና የእናንተ የሌላውም ሰው አሻራ ናት:: ብዙ ሀሳብ፣ ብዙ እውቀት ነው የሚፈጥራት:: በጋራ የተሳለች ሀገር የትውልድ ክብር፣ የትውልድ ጌጥ ናት:: ዛሬ የጻፍነው መልካምም ይሁን እኩይ ሥራችን የሚመጣው ትውልድ ገልጦ የሚያነበው ድርሳናችን ነው:: በዛሬያችን ላይ የምንጽፈው እያንዳንዱ ነገር ነገ ላይ ተመስጋኝም ሆነ ተወቃሽ ሊያደርገን ይችላልና ትውልዱን የዋጀ መልካም ታሪክ እንጻፍ:: ቸር ሰንብቱ::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2014