ፀጉራቸው የጥጥ ንድፍ ሲመስል፣ እድሜያቸው ወደ ዘጠናው ለመዝለቅ ግስጋሴ ላይ ነው። ሆኖም የወጣትነት ዘመን ውበታቸውን ደብዛ ማጥፋትና የፊታቸውን ገጽታ መሸብሸብ ስላልተቻለው ከነወዘናቸው መገኘታቸው እድሜያቸውን እዚህ ደረጃ የደረሰ አያስመስለውም። እንቅስቃሲያቸው ለዓመታት አስተዋሽ በማጣቱና በርካታ ጫናዎችን ሲያስተናግድ በመኖሩ ፈጣን ባይሆንም፤ ከእድሜቸውና ከአምናው ጋር ሲያነፃፅሩት መሻሻል በማሳየቱ እንደልብ ነው ያሰኛል።
አሸባሪው ህወሓት በጀግናው መከላከያ ሠራዊታችን ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ለመደምሰስ የተደረገው የህልውና ዘመቻ በተጀመረ ሠሞን የተቀሰቀሰ ስሜታቸውን ተረድቶ የሚያሳትፋቸው ቢያጡ፤ ቤት ለቤትና በአካባቢያቸው ስንቅ የሚያዘጋጁትን ሴቶች ለማነሳሳት እየፎከሩ፣ እያቅራሩና እየሸለሉ ለመንጎራደድም አስችሏቸዋል።
እንቅስቃሲያቸው መሻሻል ለማሳየት የበቃው አምና ግንቦት ወር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ክረምት በደረሰ ቁጥር ጎርፍ ሰተት ብሎ በመግባት ያስቸግራቸው የነበረውን የጭቃ ቤታቸውን አፍርሰው ከሰሩላቸው በኋላ መሆኑን ይናራሉ። ‹‹አሁን ያለሁበት ኑሮ የተደላደለ ነው›› ሲሉ ለመግለፅ ያስቻላቸውንና አስተዋሽ በማጣታቸው ያሰሙት የነበረውን ምሬታቸውን በደስታ የለወጡላቸውን ከንቲባም ደጋግመው ሲያመሰግኑና ሲመርቋቸው ይደመጣሉ።
እኝህ እናት የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር አደዋ ላይ ከፋሽሽት ኢጣሊያ ጋር ብርቱ ትንቅንቅ ያደረጉትን የአባቶቻቸውንና የእናቶቻቸውን የጀግንነት ፈር በመከተል ከአርባ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያን የወረረውን ፋሽሽት ሙሶሎኒ ለማባረር ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ታላቅ ተጋድሎ ያደረጉ አርበኛ ማሚቴ ምህረቱ ናቸው።
አርበኛዋ እንዳወጉን በደቡብ ክልል ጉርማዩ በሚባል አካባቢ ነው የተወለዱት። ለወላጆቻቸው ማሟጠጫ ልጅ ናቸው። ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን ሲወር ህፃን ልጅ ቢሆኑም ከወላጆቻቸው ጋር በቦረና፣ በያቤሎ፣ በሞያሌና በአጠቃላይ በ12ም ጠቅላይ ግዛቶች ተዘዋውረው ከበላያቸው ከነበሩ እህትና ወንድሞቻቸው እንዲሁም ከእናትና አባታቸው ባልተናነሰ ተዋግተዋል።
አርበኛዋ ይሄን ሁኔታ ‹‹አባቴ በየጫካው፣ በየዱሩና ገደሉ ይዋጉ የነበረው ቤተሰባቸውን ይዘው ነው። እናቴ ደግሞ ከታላቅ እህቶቼ ጋር ለአባቴና ለሌሎች አርበኞች ለእኛም ስንቅ ያዘጋጃሉ። ከዚሁ ጎንም ጦሩ አየል ሲል መሣሪያ ታጥቀው ለውጊያ ይሠለፋሉ። እነሱ በረሀብና ጥማት ሲዋጉ እኔ ከጎናቸው በመሆን በዚህ ሁኔታ ነው የህፃንነቴን ጊዜ ያሳለፍኩት›› ሲሉ ያስታውሱታል።
ጦርነቱ በተጀመረ በመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ህፃን በመሆናቸው አምኖ መሣሪያ በማስታጠቅ በውጊያ የሚያሳትፋቸው ቢያጡም በፋሽሽት ጦር ላይ የድንጋይ ናዳ በመልቀቅ የሚስተካከላቸው አልነበረም። የፋሽሽት ጦር መምጣቱን አውቆ ወገን እንዲሸሽ ጡሩንባ እየነፉ በማሳወቁም ወደር የለሽ ነበሩ። ወንጭፍ በመጠቀም ሁሉ ግዳይ ጥለዋል።
‹‹ያኔ ትዳር የሚመሰረተውም በሰባት፣ በስምንትና ዘጠኝ ዓመት ነው›› የሚሉት አርበኛ ማሚቴ ወደዚሁ ዕድሜ መዝለቅ ሲጀምሩ በውሀ መቅዳቱም ሆነ በስንቅ ዝግጅቱ እየተሳተፉ የታዳጊነት ጉልበታቸውን በማጎልበት ጦርነቱ ሊጠናቀቅ ሁለት ዓመታት ግድም ሲቀረው፤ የአባታቸውን ሚኒሽር አንግበው ጠላትን ወደ መቁላቱ መሸጋገራቸውንም በኩራት ያወሳሉ። በዚያን ዘመን የነበሩ የሴት አርበኞች የጀግንነት ገድል አርአያ እንደሆናቸውም ይጠቅሳሉ።
የአድዋን ጀግና የእቴጌ ጣይቱ ቡጡልን የጀግንነት ጋሻ በማንገብ ከ40 ዓመታት በኋላ በሀገራቸው ላይ ወረራ ያደረገውን ፋሽሽት መድረሻ ያሳጡትን ለሁለት ዓመታት ጣሊያን አግዟቸው የነበረውን የእነ ስንዱ ገብሩን ጨምሮ የእነ ሸዋረገድ ገድሌን፣ የእነ ጽጌ መንገሻን፣ የእነ ፊትአውራሪ በላይነሽ ገብረአምላክን፣ የእነ በርነሽ መላኩንና የብዙ ሴቶችን ለሚያዝያ 27፣1933 ዓ.ም ድል ያበቃ አበርክቶ ተርከው አይጠግቡም።
በጦርነቱ የተሳተፉትና መሪ ተዋናይ የሆኑት እነዚህ ቀርቶ ያልተሳተፉትም ሴቶች የነበራቸው ሚና ቀላል አልነበረም። አብዛኞቹ ሴቶች በጦርነት ባይሳተፉም የአምስት ዓመቱ ጦርነት በድል እንዲጠናቀቅ በማድረጉ ረገድ ስንቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች በመሣተፍ የላቀ ሚና ተጫውተዋል። ከዚህ የላቀ ሚናቸው መካከል በአስቸጋሪና በአድካሚ ሁኔታ ውስጥ ውሃ ከወንዝ ቀድቶ በማቅረብ፤ ሳያሰልስ ከጠዋት እስከ ማታ በሚደረግ አርበኛው ወደ ጦርነቱ ይዞት የሚሄደውን ስንቅ ወይም በወቅቱ አጠራር (አገልግል) ዝግጅት ያደርጉት የነበረው በቀዳሚነት ይጠቀሳል።
እናት አርበኛዋ እንዳወጉን ጦርነት ላይ ሆኖ በዚህ መልኩ ለጦርነቱ አገልግሎት መስጠት እጅግ ፈታኝም ከባድም ነበር። ሆኖም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች በዚህ መልኩ ተሳትፈው ነው ፋሽሽትን በማባረር ጦሩን ለድል ያበቁትና ነፃነታቸውን ያስጠበቁት።
በጦርነቱ ለቆሰሉ አርበኞች ቁስል በማጠብ፣ በመተኮስ፣ በአካባቢው በተገኘው በባህላዊ ህክምና መድኃኒት በማዳን፤ የተጎዳውን በምግብና በተለያዩ መንገዶች በመንከባከብ፣ የሞተውን በመቅበር ሲያደርጉ የነበረው አስተዋጽኦ እንዲህ በቃላት ብቻ ሊነገር የሚችል አይደለም። ‹‹ዘመናዊ ሕክምና የሚሰጡም ሴቶች ነበሩ›› የሚሉት እናት አርበኛ ማሚቴ በተለይ በሙያዋ ነርስ የነበረችውና የአፄ ኃይለስላሴ ልጅ ልዕልት ፀሐይ እንዲሁም የሕክምና ሙያ ጭምር ያጠኑት ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ በተጨማሪም ወይዘሮ ጽጌ መንገሻ ከአርበኝነቱ በተጨማሪ በዚህ በኩል ሲያደርጉት የነበረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ያወሳሉ።
ልዕልት ፀሐይ ቋንቋ በማስተማርና በተለያዩ መንገዶች በርካታ አገልግሎት ስትሰጥ የነበረች መሆኑንም ይጠቅሳሉ። እናት አርበኛ ማሚቴ እንዳጫወቱን በአጠቃላይ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ከአውደ ውግያ ጀምሮ በብዙ መልኩ በመሳተፍ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ሆኖም የአስተዋጽኦአቸውን ልክ ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ የሚገባቸው እንከብካቤ አልተደረገላቸውምና ክብር አላገኙም። በንጉሱ ዘመን ዳረጎት ተብሎ የሚጣለው 10 ብር ነበር። በእርግጥ ያኔ ይሄም ቢሆን ትልቅ ዋጋ አለው። በዚህ ላይ ንጉሱ (ጃንሆይ) አራት ኪሎ ተወካዮች ምክር ቤት ፊት ለፊት የሚገኘውን የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበርን በማቋቋም መሰረት ጥለው ነው ያለፉት።
‹‹ዓላማው በማህበሩ ውስጥ በመሰባሰብ አንድም እያከራየን ሁለትም ከውጪም ከሀገር ውስጥ ድጋፍ በማሰባሰብ እንድንረዳዳበት ነበር›› ይላሉ እናት አርበኛ ማሚቴ። አንዳንድ አመራሮች አላማውን ሳይስቱ ከውጪም፣ ከሀገር ውስጥም ሀብት በገንዘብም በቁሳቁስም በማሰባሰብ ሲደግፏቸው መብቃታቸውን ያስታውሳሉ። ከስኳር ጀምሮ ማኮሮኒ፣ ፓስታ፣ ስንዴ እንዲሁም ጣቃ ልብስ ሁሉ እያስቀደዱ ሲያለብሷቸውና ሲደጉሟቸው መቆየታቸውንም ይጠቅሳሉ።
አንዳንድ አመራሮች ደግሞ በአንፃሩ የወሰዱ አስመስለው ካስፈረሟቸው በኋላ ጣቃውን ልብስ አየር ባየር ሸጠው የውስጥ ልብስ፣ የካኔተራና የካልሲ ውራጅ በመስጠት በደል ሲያደርሱባቸው መኖራቸውንም ይናገራሉ። በተለይ ሴት አርበኞች በዚህ ሁኔታ እየተቸገሩና የድሉ የታሪክ አካል እንዳልሆኑ ሁሉ የሚያስታውሳቸው አጥተው እንደኖሩም ይገልፃሉ እናት አርበኛ ማሚቴ።
እሳቸው እንዳወጉን ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው ሴት አርበኞች መንገድ ላይ ወጥተው ለመለመን እያፈሩ፤ ጧሪና ደጋፊ አጥተው እስከ ወዲያኛው አሸልበዋል። ጧሪ ቀባሪ በማጣት መንገድ ወጥተው የሚለምኑ የሚጎሳቆሉም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም።
አሁን ላይ ሞተው አልቀዋል። በሕይወት ያሉትም በችግር ውስጥ ነው የሚኖሩት። እሳቸው እስከ ባለፈው ዓመት የነበሩበት ችግር ማሳያ ነው። ከወለዷቸው ስድስት ልጆች መካከል በውጭ ሀገር ተምረው ከኢንጅነርነት ጀምሮ ትልልቅ ደረጃ የደረሱትና ይንከባከቡና ይደግፏቸው የነበሩት ሦስቱ ልጆቻቸው ሞተውባቸዋል።
የልጆቻቸው ኀዘንና የዕድሜ ጫና ደጓሚ ከማጣት ጋር ተደማምሮ ሲደቁሳቸው እንደቆየም አልሸሸጉም። ‹‹ብቸገርም የምደሰተው በሕይወት ባሉት ሦስቱ ልጆቼ ነው›› የሚሉት እናት አርበኛዋ እነዚህ ልጆቻቸው እንደእሳቸው ሁሉ ገቢ የሌላቸው ናቸው። በተለይ በእርጅና ምክንያት ቤታቸው ሊፈርስ ሲደርስ አብረዋቸው የሚጨነቁበትና የሚጠበቡበት ጊዜ ቀላል አልነበረም።
በተለይ ክረምት በመጣ ቁጥር ምንም ማድረግ የሚያስችል አቅም ስለሌላቸውና የነበረውን ስጋታቸውን ሲጋሯቸው ነው የኖሩት። ከላይ እና ከታች በሚወርደው ዝናብ ምክንያት እንቅልፍ አጥተው ሲያድሩ እነሱም እንቅልፍ አጥተው ከእሳቸው ጋር ቆመው የሚያድሩበት ጊዜ ብዙ ነበር። በተለይ ባሳለፍነው 2013 ዓ.ም ክረምት ወራት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ባይደርሱላቸው ኖሮ ክረምትን አልፈው መስከረም እስኪጠባ የሚቆዩበት ዕድል አልነበራቸውም። ይሄን ሁኔታ እናት አርበኛ ማሚቴ መለስ ብለው ያስታውሱታል።
ባለፈው ዓመት የአደዋ በዓልን ለማክበር የአርበኝነት ክብር ልብሳቸውን ለብሰው ከሌሎች እናትና አባት አርበኛ ጓደኞቻቸው ጋር ተሰልፈው ነበር። ከበዓሉ ፍፃሜ በኋላ ታድያ ከንቲባዋ ወዲህ አምጡልኝ ብለው እናትና አባት አርበኞች ያሉበትን የኑሮ ሁኔታ ይጠይቃሉ። እናት አርበኛ ማሚቴ ሁሌ በክረምት የሚያስነባቸውንና መቆሚያ መቀመጫ የሚያሳጣቸውን የትንሿን ያዘመመች የጭቃ ቤታቸውን ጉዳይ ያነሳሉ። በበር የዝናብ ጎርፍ ሰተት ብሎ እየገባ፤ ከላይ ቆርቆሮው እያፈሰሰ በአጠቃላይም አርጅቶ በማዝመም ሊፈርስ በመድረሱ መቸገራቸውን እናት አርበኛዋ ሲናገሩ በመስማታቸው ከንቲባዋ ልባቸው ክፉኛ ያዝናል። ዓይናቸውም እንባ ያቀራል። የእኝህን እናት ቤት ባስቸኳይ ስሪላቸው የተባለችው የሥራ ኃላፊ የሚኖሩበትን አካባቢ፣ ስልክ ቁጥራቸውን፣ እና የቤት ቁጥራቸውን መረጃ ትቀበላቸዋለች።
ይህ ሁሉ ሲሆን ‹‹ዕውነት ዕውነት አልመሰለኝም›› የሚሉት እናት በስምንተኛው ቀን ቤታቸው በሚሰራበት ጉዳይ ዙሪያ ስልክ ሲደወልላቸው ማመን እንዳቃታቸውም ያስታውሳሉ።
እሳቸው እንዳጫወቱን በሰኔ 2013 ቤታቸው ፈርሶ እንደ አዲስ ተሰራ። የወደቀው ጭቃ ቤት በሚያምር ድንጋይ ቪላ ሆኖ ተገነባ። ግንባታው በተጀመረ በሦስት ወሩም የክረምቱን ጎርፍ አምልጠው ቤታቸው ገቡ። አዲስ ዓመትንም በአዲሱ ቤታቸው ውስጥ ለማክበር በቁ።
‹‹አሁን ላይ አኗኗሬ ዘምኗል። ባለኪቺን፣ ባለመኝታ ቤትና ባለሳሎን ሆኛለሁ›› የሚሉት እናት አርበኛ ማሚቴ ይሄ ሁሉ የሆነው ሀገር ብትኖር መሆኑንና ሌሎች እንደሳቸው የተቸገሩ እናት አርበኞችም ይሄን ዓይነቱን የእሳቸውን ዕድል እንዲያገኙ የሚመኙ መሆናቸውን በመግለፅ ወጋቸውን ቋጭተውልናል።
ቤታቸው እንደሚባለው በቀላሉ መታደስ ሳይሆን ፈርሶ፤ ከእንደገና ባማረ፣ በዘመነ፣ ጥራት ባለውና በተሻለ ሁኔታ ቢገነባም የቀለባቸው ነገር አብዝቶ ዛሬም ያሳስባቸዋል። ከአርበኞች ማህበር በየወሩ የሚያገኙት ጥቂት ብር በአሁኑ የኑሮ ውድነት እንኳን ለቀለብ፣ ለሻይና ለትራንስፖርት አይበቃም። በመሆኑም እኝህን እናት አርበኛም ሆነ ሌሎቹን ዛሬን እንድንኖር ላበቁን እናቶች እናስታውስ የዛሬው መልዕክታችን ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2014