ከሰሞኑ ከአሸባሪው የትህነግ መንደር ብዙ አስገራሚና አዝናኝ ነገሮችን እየሰማን ነው። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሚያደርገው የህልውና ዘመቻ መጠናከር የተደናገጠው ይህ አገር አፍራሽ ቡድን “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” የሚለውን የአባቶቻችን ብሂል ለእኩይ አላማ ሲጠቀምበት እያስተዋልን ነው።
በየ ጦር አውድማው መፈናፈኛ አጥቶ እየተደቆሰ ቢገኝም በተቃራኒው የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨት በመሳሪያ ያጣውን ድል በወሬ ለማካካስ ሲፍጨረጨር ማየት አስገራሚ ጉዳይ ሆኗል።
ለማይቀረው የህልውና ጦርነት ተዘጋጅቶ አሸባሪው ትህነግን በሚገባው ቋንቋ እያናገረው የሚገኘው የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚኒሻና ፋኖው ቅንጅት ከምንም ነገር በላይ የሚያኮራና ታሪክ ሲዘክረው የሚኖረው ነው። በተለይ የወሎ ህዝብ ህይወቱን የሚሰዋለት ሰራዊት ደጀን በመሆን አኩሪ ገድል እየሰራ ይገኛል።
ይህ መናበብ ያስበረገጋቸው የቡድኑ አፈ ቀላጤዎቹ በመረጡት የጦርነት ሜዳ ላይ ከመፋለም ይልቅ በሚዘውሩት የፕሮፓጋንዳ ሚዲያ ላይ የሃሰት መረጃዎችን በመንዛት ኀብረተሰቡን ለማወናበድ እየሰሩ ይገኛሉ። እያንዳንዱ ህዝብ ግን “ እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል” በማለት በየጊዜው የሚያሰራጩትን ጥቁር መረጃ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ በህልውናው ዘመቻ በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ በወሎ ግንባር ሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች የትህነግ የሽብር ሰራዊት መፈናፈኛ እንዲያጣ በማድረግ “ምሳቸውን” እንዲያገኙ እያደረገ ነው። ቡድኑ የትግራይ እናት መከራዋን አይታ ያሳደገችው ወጣት በከንቱ እብሪት በየገደሉ እየገባና የጥይት እራት እየሆነ የአሞራ ሲሳይ እንዲሆን ፈርዶበታል።
በዚህ ሳያበቃ “ድሉ የኛ ነው፣ በሳምንት ውስጥ አዲስ አበባ እንገባለን፣ እዚህ ገብተናል በዚያ ታይተናል” በሚል የማወናበጃ ወሬ ተጠምዷል። ከዚህም ባለፈ የትግራይ ህዝብን ከቀሪው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመነጠል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም ። አሁን ደግሞ ለተጫዋቹም ለአጫዋቹም የማያምር የመጫወቻ ካርድ እየመዘዙ ይገኛሉ።
ከቀናት በፊት በፕሮፓጋንዳ ማሽናቸው በሆነው የቴሌቪዥን ጣቢያ ብቅ ያለው የሽብር ቡድኑ መሪ ደብረ ፂዮን “ተዋዶና ተጋምዶ የኖረውን የትግራይና የአማራ ህዝብ ለማጫረስ እየሰሩ ነው። እኛ ከህዝብ ጋር ጠብ የለንም” በማለት ወረራውን “ቅዱስ” ጦርነት ለማድረግና የትግራይና የአማራ ህዝብ ተቆርቋሪ መስሎ ለመታየት ሲቃጣው አስተውለን በግርምት እጃችንን አፋችን ላይ እንድንጭን አድርጎናል ።
በዚህ ሳያበቃ ለዘመናት በጥላቻ መርዝ እየዘራ ከመላው ኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ሲያጋጨውና መከራውን ሲያበዛበት የኖረውን “የአማራ ህዝብ” በጨነቀው ጊዜ ጉያህ ወስጥ ካልወሸቅከኝ በማለት ሲያላዝን መስማት ሳንወድ ተገደን እንድንስቅ የሚያስገድደን ቀልድ ሆኗል።
እውነታው አፈ ቀላጤው ጌታቸው እረዳና የሽብር ቡድኑ መሪ ደብረፅዮን እንደሚሉት እንዳልሆነ የችግሩ ሰለባ ለሆነውና ጉዳዩን በንቃት ለሚከታተለው የአማራ ህዝብ የተሰወረ አይደለም ።
መላው የኢትዮጵያ ህዝብ “ሰንኮፉን” ትህነግ ለመንቀልና እባጩን ለማፍረጥ ወደ ግንባር ዘምቶ ክንዱን እያሳየው በሚገኝበት በዚህ ጊዜ ለምን ይሆን አፈቀላጤዎቹ የአማራን ህዝብ ለይተው ለማወናበድና “የህዝብ ወዳጅ” መስለው ለመታየት የዳዳቸው ? ። የዚህ ጥያቄ መልሱ በተለይ ለአማራ ህዝብ ብዙ የሚከብድ አይደለም ።
መውጫና መግቢያ አጥተው የጥይት እራትና የአፈር ማዳበሪያ የሚሆኑት የሽብር ቡድኑ አባላት በግንባር ያጡትን ድል በወሬ ለማካካስ “የሎስ” ሳይቀድማቸው መንጫጫትን ምርጫቸው አድርገዋል። ለዚያ ነው “እኛ ከህዝብ ጋር ጠብ የለንም” የሚል ትርክት ይዘው ብቅያሉት።ከህዝብ ጋር ጠብ ከሌላቸው የህዝብ መገልገያዎችን መዝረፍ ማውደም ከምን የሚመነጭ ይሆን፤ከህዝብ ፍቅር !?።
ይሄን ለጆሮ የሚከብድ ነጭ ሃቅ የሰማን የኢትዮጵያ ህዝቦች እንዲህ ብለን መጠየቅ እንሻለን “ አልበላሽምን ምን አመጣው?” አሁነኛ እውነታው ላለፉት ዘመናት የአማራን ህዝብ በጠላትነት ፈርጆ የዘር ፍጅት እስከመፈፀም፣ ወላድን እስከማምከን፣ የዘር ፍሬ እስከማኮላሸትና ሌሎች በርካታ ይቅር የማይባሉ በደሎችን እስከመፈፀም ደርሶ የነበረው አሸባሪው ህወሓት ምን አገኘው የሚያስብል ነው።
የትግራይን ህዝብ ከወዳጅ እና ከጎረቤቱ የአማራ ህዝብ ጋር ታሪካዊ ጠላት እንዲሆን አድርጎ በማኒፌስቶው ቀርፆ ሲንቀሳቀስ የነበረው አሸባሪው ህወሓት ዛሬ ላይ ለመጥፋት አንድ ሐሙስ ሲቀረው “አይናችሁን ጨፍኑና” ላሞኛችሁ ቢል የሚሰማው ይኖር ይሆን?
እውነት የአማራ ህዝብ አሸባሪው ትህነግ የፈፀመበትን “ዋል አደር ያለ በደል” ቢረሳ ከሰሞኑ በእርስቱና በግዛቱ ውስጥ አይኑ እያየ የፈፀመውን ግፍ ክህሊናው ፍቆ ከወዳጅነት መዝገብ የሚያሰፍረው ይመስለው ይሆን? በፍፁም! ።
አሸባሪው ትህነግ ሆነ አላማውን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀስ የቡድኑ አባላት አገር አፍራሽ መሆናቸውን መላው ህዝባችን ጠንቅቆ ያውቃል።የአማራ ህዝብ ደግሞ ከዚህ በኋላ ቡድነ ጸረ አማራ መሆኑን ይረዳል።
በደሃ ጉልበቱ ከተራራው ጋር ተጋፍቶ ያበቀለውን አዝመራ አይኑ እያየ አጭደው ወስደውበታል። የተቦካ ሊጥና የተፈጨ ዱቄት ሳይቀር ከጎስቋላ ጓዳው ገብተው ዘርፈውታል። በጅምላ ፈጅተውታል። በጎጆ ቤቱ እንተቀመጠ እንደ ጠላት በመድፍ ደብድበውታል። ጋዝ እያርከፈከፉ በቁሙ አቃጥለውታል።
ታዲያ በምን ሂሳብ ነው ይህ ግፈኛና ኢትዮጵያዊ ስብእና የሌለው ቡድን “የአማራ ህዝብ” ወዳጅ ሊሆኑ የሚችለው? ደርሶ ወዳጅ ለመሆን የዳዳው በምን ሞራል ነው ? እውነታው ግን ግልፅ እና ለማንም ሊሰወር የሚችል አይደለም ። የሽብር ቡድኑ በሞት አፋፍ ላይ ነው ። ሁሌም ጣር ላይ ሲሆን የትግራይና የአማራ ህዝብ ጉያ ውስጥ የመወሸቅ አባዜ እንዳለበት ከራሱ በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ያውቃል። ስለዚህ “ጨፍኑ ላሞኛችሁ” ቢል የሚያዳምጠው አይኖርም።
በእድሜ ዘመኑ ጀምሮ በስልጣን ዘመኑ ሳቀረው በህገ መንግሥት የተደገፈ ጥላቻን በአማራ ህዝብ ላይ ሲዘራ ቆይቷል። ዛሬም ለበርካታ ዓመታት የጠነሰሰውን ሴራ ተግባር ላይ በማዋል ደጃፉ ድረስ በመምጣት የቻለውን ግፍ ሁላ አድርሶበታል። ይህን የተረዳው ኢትዮጵያዊ ሁሉ የህልውና ጦርነቱን ተቀላቅሎ እየመከተው ይገኛል። ጊዜ ቢፈጅም በቅርቡ የሽንፈት ፅዋውን ይጎነጫል። “እንደታረደ ዶሮ” መንደፋደፉና ሁከት መፍጠሩ የማይቀር ነው።
እስከዚያው ድረስ ህዝብ ነቅቶ ይጠብቅ። ህይወቱን ለሚሰዋለት ሰራዊት ደጀን ይሁን። ሰርጎ ገቦችን አጋልጦ ይስጥ። ከምንም በላይ በአፈ ቀላጤዎች “ወሬ አይፈታ”። በጦርነት ወቅት በሚነዛ ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል ጥፋት እንደሚደርስ ለዘመናት አገረ መንግሥቱን ከዚህ መሰል በሽታ በንቃት ጠብቆ ላቆየ ህዝብ የሚነገር አይደለም። እውነት ያሸንፋል። የመጨረሻዋንም ሳቅ እኛ እንስቃለን። ሰላም!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2014