ልክ የዛሬ ዓመት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓም አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የአገርና የህዝብ መከታና ኩራት በሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት መፈፀሙ የሚታወስ ነው። ይህ የሚያሳየው ይህም አሸባሪ ቡድኑ ለኢትዮጵያ ህዝቦች ያለውን ንቀት በገሃድ ያሳየበት ነበር። ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ይህ ኃይል በአገሪቱ ከተከሰቱ አጅግ ዘግናኝ ወንጀሎችና ጭፍጨፋዎች ጀርባ እጁ እንዳለበት ከማንም የተደበቀ አይደለም።
በአሁኑ ወቅት ይህ አሸባሪ ቡድን በአማራ ክልል ሰርጎ በመግባት አንዳንድ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር ጥረት ቢያደርግም በመከላከያ ኃይላችን፣ በአማራ ልዩ ኃይል እንዲሁም በአማራ ፋኖ ብርቱ ቅጣት እየደረሰበት ይገኛል። በዚህም ሀገርን ከመፍረስ፣ ህዝብን ከእልቂት የማዳን ሚናቸውን በሚገባ እየተወጡ ይገኛሉ። በመሆኑም መከላከያ ሠራዊታችን ይህን አሸባሪ ቡድን እያደረገ ያለውን ጉዞ ሙሉ በሙሉ ለማስቆምና ለመግታት ቀጣይነት ያለው ሥራ መሥራቱን ይቀጥላል።
መንግሥት እየወሰደው ካለው የመመከት ዕርምጃ ጎን ለጎንም ህዝቡ በማንኛውም መልኩ ሠራዊቱን መደገፍ፣ ሀገርን ከጥፋት ኃይሎች መጠበቅ እና ከመንግሥት ጎን መቆም ያስፈልጋል። ይህም ሲባል ለመከላከያ ሠራዊቱ ሁሉን አቀፍ ትብብር እና እገዛ ማድረግ እንዲሁም የመንግሥትን ፖለቲካዊ ውሳኔ መረዳት ተገቢ ነው። ይህን ስናደርግ ሀገርን ከመፍረስ ማዳን፣ ህዝብንም ከእልቂት መታደግ ያስችላል፤ አሸባሪው ቡድንም ተፈጥሯዊ ሞቱ የሚፋጠንበት ደረጃ ላይ ያደርሳል።
ስለዚህ ማንኛውም የማህበረሰብ ክፍል ገንዘብ ያለው በገንዘቡ፣ ጉልበት ያለው በጉልበቱ፣ በሃሳብም፣ በእውቀቱም ሊያግዝና ሊተባበር ይገባል። ከሠራዊቱ ጎን በመሰለፍ፤ ለሠራዊቱ ያለንን ወገናዊነትና ክብር
በመግለጽ፣ በሚያስፈልገው ሁሉ በመተባበር ለኢትዮጵያውያን ህዝቦች ነፃነት በቆራጥነት እያደረገ ካለው ተጋድሎ ጎን መሆናችንን ልናረጋግጥ ይገባል። በተለይ ለሠራዊቱ ስንቅ በማቅረብ፣ ገንዘብ በማዋጣት ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሚፈሰው ደሙ መተኪያ ደም በመለገስ የሀገር አለኝታኝነቱን ማሳየት ለነገ የማይባል የቤት ሥራችን መሆን አለበት።
ከዚህ አሸባሪ ቡድን ጋር የሚደረገው ጦርነት የኢትዮጵያን ህልውና ማረጋገጥ በመሆኑ በሽብር የተደራጀውን ቡድን ለሀገር ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ማድረስ ለአንድ አካል ብቻ የሚተው ኃላፊነት ሊሆን አይገባም። ይህን አሸባሪ ቡድን መደምሰስ መቻል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገራዊ ኃላፊነት ሲሆን፤ የሀገርን እና የህዝቦችን ሰላም ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል ከመንግሥትና ከመከላከያ ጎን እንዲቆም የሚደረገው ሀገራዊ ጥሪ ኃላፊነት ከሚሰማው ዜጋ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው።
የሀገር መኩሪያ፣ የህዝብ አለኝታ የሆነው የመከላከያ ሠራዊት የተጣለበትን ኃላፊነትና ግዳጅ እየተወጣ ነው ሲባል፤ ሠራዊቱ በሚሠራቸው ኦፕሬሽኖች፣ በሚፈጽማቸው ስትራቴጂዎች ብቻም ሳይሆን ሠራዊቱ በተጠራበት ሁሉ በመግባት ራሱን መስዋዕት እያደረገ ሀገርና ህዝብን ሲታደግ መቆየቱና አሁንም እየታደገ መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል።
ይህ ቡድን ልክ እንደ ውጭ ወራሪ ኃይል በገዛ ሀገሩና በገዛ በዜጎቹ ላይ የፈጸመው የባንዳነት ተግባር የመጨረሻ የሞት ሞቱን እንዳቀረበው አንዱ ማሳያ እየሆነ መጥቷል። በመሆኑም ከየትኛው የሀገሪቱ ክፍል የተውጣጣው ልዩ ኃይልና ሚሊሻ የዚህን አሸባሪ ቡድን ዕብሪት በማብረድ አገርና ህዝብን እፎይ የሚያስብልበት ወቅቱ አሁን ነው። ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አሸባሪነትን ሲጸየፍና የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በአንድነትና በተባበረ ክንድ መመከት ሲችል ነው።
በአጠቃላይ አሸባሪው ሕወሓት በኢትዮጵያ ላይ የደቀነውን አደጋ ለመከላከል ሕዝቡ በግንባርቀደምትነት በመሳተፍ ላይ ለሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ የየክልሎች ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ መደገፍ እና አጋርነቱን ማሳየት አለበት። በዚህም ኢትዮጵያን ለዓመታት ዕረፍት የነሳት ነቀርሳ የመጥፊያው ጊዜ ይቃረባል፤ በአሸባሪዎች መቃብር ላይ አዲስ ታሪክ ይጻፋል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2014