አዲስ አበባ፡- አገርን ለማዳን ከመቼውም ጊዜ በላይ የአመለካከት እና ተግባር አንድነትን በማጠናከር መከላከያን መደገፍ እና ዘመቻውን መቀላቀል አስፈላጊ መሆኑ ተመላከተ።
የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና ምክትል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አካሂደዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ የአመለካከትና የተግባር አንድነት የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
አሸባሪው ሕውሓትና ኦነግ ሸኔ ዓላማ ኢትዮጵያን ማፍረስ መሆኑን መገንዘብ እና መታገል ያስፈልጋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አሸባሪው ሕውሓት የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጠላት ነው፤ በመሆኑም ይህንንም ህዝብ እንዲረዳው ማድረግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
የክልሉ መንግሥትና ህዝብም መከላከያ ሠራዊትን በሎጅስቲክስና በሞራል መደገፍ የቀጣይ ቁልፍ ሥራዎች መሆናቸውን አመላክተዋል፡፡
ሀገርን ከመታደግ ጎን ለጎንም እየተከናወኑ ያሉ የልማት ሥራዎች ተግባራት ማጠናከር እንደሚገባም ጠቁመው፤ የሠራዊትን የሰው ኃይል ለማጠናከር በክልሉ የተጀመረው የመከላከያ ምልመላ በተጠናከረ መልኩ እንደሚካሄድ ታውቋል።
በተለይም ህዝብን ባሳተፈ መልኩ የአካባቢን ሰላም ማስጠበቅ በትኩረት ይሠራል ሲሉ ርዕሰ መዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡
“እንደ ሀገር የገጠሙ ችግሮችን ለማለፍ በአንድነትን በሙሉ አቅም መረባረብ ይገባል” ያሉት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ናቸው።
በዋናነትም ሁሉም አካላት የአካባቢን ሰላም መጠበቅ ፣መከላከያን መደገፍ እና ዘመቻውን መቀላቀል አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
እንዲሁም በጦርነቱ የተፈናቀሉ ዜጎችን የመደገፍ ሥራም በትኩረት መሠራት አለበት ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በውይይቱ የተሳተፉ አመራሮችም የአሸባሪው ሕውሓትን ሀገር የማፍረስ ተግባር ለመመከትና ሀገርን ለማዳን እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23 ቀን 2014 ዓ.ም