በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት በሚደርሱ ግጭቶች ቤተሰቦቹን ያጣውን፣ የተፈናቀለውን፣ንብረቱ እንዳልነበረ የሆነውንና ባዶ እጁን የቀረውን ወገን ለማገዝ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የእርዳታ እጃቸውን ከመዘርጋት ተቆጥበው አያውቁም።
ኢትዮጵያ ውስጥ ሰው ሰራሽም ሆነ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲከሰቱ የአቅማቸውን ከመርዳት የማይቦዝኑት በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በቅርቡ እንኳን በአጣዬና አካባቢው በደረሰው ጥቃት ሰበብ ችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን ለመርዳት በግልም በማኅበርም የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ ነበር። ከነዚህም ውስጥ በስዊዘርላንድ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በምዕራብ ጀርመን በኮሎኝና በቦን ከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት ማኅበር ያበረከቱትን እርዳታ ለአብነት ማንሳት ይቻላል።
አሁንም የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ያሳሰባቸው የህዝቡ ስደትና ለችግር መጋለጥ ያገባኛል ያሉት በፈረንሳይና ስዊዘርላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለወገናቸው ያላቸውን ለመለገስ አልቦዘኑም።ለእኔ ብቻ ይመቸኝ ወይንም ችግሩ እኔን እስካልነካ ድረስ አያገባኝም ሳይሉ በሚችሉት ሁሉ ከወገናቸው ጎን ለመቆም በማሰብ በየሚኖሩበት አካባቢ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት ቤት ለቤት እየሄዱ ኢትዮጵያውያንን በማነሳሳትና ያላቸውን እንዲለግሱ በማድረግም በርካታ ሀብት አሰባስበው ለወገናቸው ልከዋል።
ሀብቶቹ በሚሰባሰቡበት ወቅት በበጎ ፍቃድና በኢትዮጵያዊነት ስሜት በመነሳሳት ዝግጅቱን በማስተባበር ብሎም እራሳቸው ያላቸውን በማዋጣት ተሳትፎ ሲያደርጉ ከነበሩትና በፈረንሳይ አገር ከሚኖሩት ወይዘሮ ነጻነት ጌታቸው ጋር ቆይታ አድርገናል።
ወይዘሮ ነጻነት የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ነው ከአገራቸው የወጡት፡፡ አሁን ኑሯቸውን በሲዊዘርላንድና ፈረንሳይ መካከል በምትገኝ ”ጋዝል” ከተማ አድርገዋል።ወይዘሮ ነጻነት የእንጀራ ጉዳይ ሆኖባቸው ከአገር ከወገናቸው ተለይተው በባዕድ ምድር ይኑሩ እንጂ ሁሌም ልባቸው አገራቸው እንደሆነ ነው የሚናገሩት።አሁንም መንግሥት ተገዶ በገባበት የህግ ማስከበር ጦርነት ላይ ከኖሩበት ቦታ ተሰድደው፣ ከሀብት ንብረታቸው እንደዋዛ ተፈናቅለው፣ የሚልሱት፣ የሚቀምሱትና የሚለብሱት ያጡ ወገኖቻቸው ጉዳይ እጅጉን ስላሳሰቧቸው ከመሰሎቻቸው ጋር በመሆን እርዳታ በማሰባሰብ ወገናቸውን ለማገዝ እየሰሩ ያሉም ናቸው።እኛም እየሰሩ ባሉት በጎ አድራጎት ሥራና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለ መጠይቅ አድርገንላቸዋል።
አዲስ ዘመን፦ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ በተለይም የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመርዳት እያደረጋችሁ ያላችሁት ጥረት ምን ይመስላል?
ወይዘሮ ነጻነት፦ መጀመሪያ ላይ እኔ በምኖርባት ጋዝል ከተማ ላይ ለወገኖቻችን እንድረስላቸው የሚል ጥሪ ቀረበልን።በዚህም የተለያየ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀመርን።በነገራችን ላይ ይህ አይነቱ አገርን የመርዳት እንቅስቃሴ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ከዚህ ቀደምም ለህዳሴ ግድብ እንዲሁም ሌሎች ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አገራዊ ጥሪዎች ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ ሲደረግበት የቆየ ነው። አሁን ደግሞ በስፍራው የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ጉዳዩን በሚሰማበት ጊዜ ድጋፉን የተናጠል ከምታደርጉት ሁሉንም የሚያሳትፍ ሰፋ ያለ ይሁን ማለታቸውን ተከትሎ በርካቶች እንዲሳተፉበት ስዊዝ አቀፍ እንዲሆንና ሰፋ እንዲል አድርገናል። በዚህም መስከረም አምስት ቀን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥሪ አቀረብን። ይህ ጥሪ እውነት ለመናገር ብዙዎችን ያነቃነቀ ነበር ማለት ይቻላል። በእርግጥ ከላይ እንደገለጽኩት በጋዝል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ተመሳሳይ ስራን ሲሰሩ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም።በቅርቡ እንኳን በአጣዬ ከተማ ለተፈናቀሉ ወገኖች በርካታ ሀብት አሰባስበው ልከዋል።ይህ ግን ለየት የሚያደርገው በአካባቢው ራቅ ብለው ያሉ ዜጎችን ሁሉ ያሳተፈ መሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፦ የሆነ ስያሜ ኖሯችሁ ነው የምትሰባሰቡት ወይስ መንገዱ እንዴት ነው?
ወይዘሮ ነጻነት፦ አዎ ከዚህ ቀደም የነበረው የሰዎችም ቁጥር አነስተኛ ስለነበር ስያሜ ነበረው፡፡ ነገር ግን አሁን ሰፋ ስላደረግነውና በመላው ስዊዝ ያሉ ዜጎች በሙሉ እንዲሳተፉበት ስለተደረገ ስያሜውም “የህልውና ዘመቻ” በሚል ለ15 ቀናት እንዲቆይ ነው የጀመርነው። ለምሳሌ እኔ በምኖርበት አካባቢ እኔና ሌላ አንድ ሰው ሆነን ስራዎችን እንሰራለን፡፡ ሁላችንም የአገራችን ጉዳይ ይመለከተናል በማለት በየከተማው በጎ ፈቃደኛ አስተባባሪዎችን ወይም ተወካዮችን በማዘጋጀት በእነሱ በኩል እርስ በእርስ እየተገናኘን ነው የምንሰራው።በነገራችን ላይ ብዙ ኢትዮጵያውያን አይኖሩባቸውም ብለን በምናስባቸው ከተሞች ሳይቀር ተወካዮች እየተመረጡ ሀብት እያሰባሰቡ ለእኛም መረጃ እየሰጡን በዚህ የ15 ቀን እንቅስቃሴ ላይ በርካታ ገንዘብ ብናሰባስብም ህዝቡ ግን እኔ መረጃውን ዘግይቼ ነው ያገኘሁት፤ እኛ አካባቢ አልመጣችሁም በማለቱና ከፍተኛ የሆነ የመሳተፍ ፍላጎት ስለታየ ቀን ጨምረን ማሰባሰብ ጀመርን።
አዲስ ዘመን፦ እንደው የመጀመሪያውን 15 ቀናት ብቻ ምን ያህል ሀብት ሰበሰባችሁ?
ወይዘሮ ነጻነት፦ እርግጠኛ ባልሆንም 58 ሺ የስዊዝ ፍራንክ ይመስለኛል።ከዛ ግን በዚህ ሳናበቃ ቀጥለን እስከ መስከረም መጨረሻ ባደረግነው የማሰባሰብ ጥረትም ሰዎች በእለቱ ከሚሰጡት የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር ብዙ ቃል መግባቶች ለአመት ይህንን ያህል አዋጣለሁ የሚሉ ነበሩ፤ ከሁሉም በላይ እኛን ያስደሰተን ወይንም ደግሞ በስራው እንድንገፋ ያደረገን የሚዋጣው ገንዘብ መብዛትና ማነስ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን ሕብረት አንድነት ነበር። አምባሳደራችንም ይህንን አንድነት በማየታቸው በጣም ተደስተው በእያንዳንዱ ነገር ላይ አብረውን ነበሩ ማለት ይቻላል፤ በዚህ አጋጣሚም መመስገን አለባቸው።
አዲስ ዘመን፦ አዎ እንግዲህ በዲያስፖራው ዘንድ የሚታየው ነገር አገርን ለመደገፍ ቢያስብም እራሱን በፖለቲካዊ አመለካከት በዘር በሃይማኖት ከፋፍሎ ደግሞ ገሸሽ የማለት ሁኔታ ነበርና እንደው በዚህ ስብስብ ላይ ይህ አይነቱን ነገር እንዴት አለፋችሁት?
ወይዘሮ ነጻነት፦ በጣም የሚገርመው ነገር እርሱ ነው፤ ሰዎች በተለያየ የፖለቲካና የሃይማኖት ሁኔታ ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በዚህኛው አገርና ወገንን የመደገፍ ሂደት ውስጥ ግን በጣም የሚገርም አብሮነትና አንድነት ነው ለማስተዋል የቻልነው።አሁን አገራችን ችግር ላይ ናት፡፡ የማንም ደጋፊ እንሁን ለአገራችን መድረስ አለበን በሚል ነው ሁሉም የተነሳው፡፡ አገራችን ችግር ላይ ናት እንድረስላት በማለትም እያደረጉ የነበረው የገንዘብ፣ የጊዜ፣ የጉልበት፣ አስተዋጽኦ በጣም የሚያስደስት እንደ ዜጋም የሚያኮራ ነበር።
በነገራችን ላይ እኔ ባለሁበት አካባቢ እንኳን ተመሳሳይ ስራን የሚሰሩ ሌሎች ቡድኖች ነበሩ፡፡ እነሱም የሚጠይቁት ይህንኑ ዜጋ ነው፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ምንም መሰላቸት ሳያሳይ እዛ ሰጥቻለሁ በቃ ሳይል ለሁሉም አቅሙ የቻለውን ሲያደርግ ማየት በእውነት የሚያኮራ ነው።
ኢትዮጵያውያን በተለያዩ አለማት ሲኖሩ የራሳቸው አመለካከት አላቸው፡፡ እንዲሁም የየራሳቸው የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት አቋምም አላቸው።እናም ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነት አገራዊ ጥሪዎች ሲኖር የመከፋፈል ሁኔታ እንደነበር እሰማለሁ፤ አጋጥሞኝ ባያውቅም።አሁን እየሰራን ያለነው ግን እንደውም ከመከፋፈል ይልቅ እንድነትን ያጎለበተ በጣም የሚገርም ስብስብ ነበር።ለእኔ ይህ በራሱ በቂ ነው።
በሌላ በኩል ግን ያዋጣሁት ገንዘብ የትና እንዴት ነው የሚሄደው፤ ለማነው የሚደርሰው፤ ለዚህኛው ወገን ቢደርስ ብለው ሃሳብ የሚያቀርቡ አይጠፉም፤ የእኛ ምላሽ የሚሆነው እኛ አገራችንን ከችግር ለመታደግ የምንችለውን እናደርጋለን፤ መንግሥት ደግሞ የቱጋ ይህ ገንዘብ ሊጠቅም እንደሚችል ያውቃል የሚል ነበር።እናም በዚህ ሃሳብ ተስማምተው ድጋፋቸውን የቀጠሉ በርካቶች ናቸው።
አዲስ ዘመን፦ የገቢ ማሰባሰብ ሂደቱን በምን መልኩ ነው የተቆጣጠራችሁት? በእጃችሁስ ገንዘብ ትቀበሉ ነበር?
ወይዘሮ ነጻነት፦ እኛ እንግዲህ ያደረግነው በዛ አገር ሁሉም የየራሱ ፍላጎትና በሚመቸው ሁኔታ በቀጥታ ገንዘብ ማስገባት የሚፈልግ በቀጥታ በዲያስፖራ የሂሳብ ቁጥር እንዲያስገባ ይሆናል፤ በሌላ በኩል ደግሞ እኛ የከፈትናቸው ሁለት የባንክ ሂሳቦች ስለነበሩ ወደዛም ማስገባት ይቻላል በማለት ነው የሰበሰብነው፤ አብዛኛው ዜጋ ስደተኛና ባንክ መጠቀም የማይችል ወረቀት የሌለው በመሆኑ እነሱ በየከተማው ላሉ ተወካዮች ገንዘቡን ሰጥተው ወደተከፈቱት የሂሳብ ቁጥሮች እንዲያስገቡ እየሆነ ነበር።በመጨረሻም ሁሉም ገንዘብ ተሰባስቦ በዲያስፖራ የሂሳብ ቁጥር ወደአገር ቤት ይላካል።
አዲስ ዘመን፦ ይህ አገርን ከችግር የመታደግ ተሳትፎ በጣም ትልቅና የሚበረታታ ነው፤ ነገር ግን አገርን በዘለቄታው ለመደገፍ ምናልባትም እርስዎ ባሉበት ማህበረሰብም ሊሆን ይችላል ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ወይዘሮ ነጻነት፦ በትንሹም በትልቁም የተደረጉ ነገሮች በመገናኛ ብዙኃን በስፋት ይሰማሉ፤ ከዛ ውጪ ግን የመጣው ገንዘብ መሬት ላይ ወርዶ ያመጣው ለውጥ በአንጻሩ አይሰማም።ይህ ደግሞ ገንዘብ ያዋጡት አካላት እንዴ አገር ውስጥ ያሉ ሕዝቦች ሥራ አይሠሩም ወይ? የሚል ጥያቄን ይፈጥርባቸዋል። አሁን ያለንበት ሁኔታ ግን ከዚህ ቀደሙ ይለያል፤ ምናልባትም የሁላችንንም ያላሰለሰ ጥረት የሚፈልግ ብዙ መስዋዕትነትንም የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል።ዛሬ ይህንን አደረገን ብለን የምንቆምም ሊሆን አይገባም። ምክንያቱም ጦርነቱ ነገ ቢጠናቀቅ የተፈናቀሉት ሰዎች ወደ ቀያቸው መመለስ የቀድሞ ህይወታቸውን መቀጠል፣ የግብርና ወይም ሌላ ሥራቸውን መስራት መቻል አለባቸው።የፈረሱ ትምህርት ቤቶች@ ሆስፒታሎች፣ መሰረተ ልማቶች ሁሉ ዳግም መገንባት ይኖርባቸዋል፤ በመሆኑም በጣም ብዙ ስራ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፦ እንግዲህ ይህንን ለማድረግ አገራችንን እንደገና ለመገንባት ዲያስፖራው አሁን በጀመረው መልኩ ድጋፉን ማድረጉ በጣም የሚያስመሰግነው የሚበረታታም ነው፤ ነገር ግን እንደተባለው ዘላቂ መፍትሔን ለማምጣት እናንተም አገራችሁ ላይ ኢንቨስት ማድረግ አለባችሁ፤ መንግሥትም በተደጋጋሚ ጥሪ እያደረገላችሁ ነውና እንደው እርስዎ በሚኖሩበት አካባቢ ያለው የኢትዮጵያውያን ፍላጎት እንዴት ይገለጻል?
ወይዘሮ ነጻነት፦ አዎ፤ በትክክል ሁሉም ሰው ይፈልጋል።በውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ህልሙ አገሩ ገብቶ የያዘውን ሀብት ንብረት አገሩ ላይ አፍስሶ ወገኑንም ራሱንም መጥቀም ነው። ግን ይህንን ለማድረግ ያው ብዙ ነገር ማድረግ ስላለባቸው ነው የሚዘገዩት፤ ነገር ግን ሁኔታው የፈቀደላቸውና የተሳካላቸው ደግሞ አገራቸው ገብተው በተለያዩ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ ሥራን እየሠሩ ነው።
እዚህ ላይ ግን ኢትዮጵያዊውም ሆነ የሌላ አገር ዜጋ እንደ ልቡ አገር ውስጥ ገብቶ አልምቶ አገርን ለማሳደግ ቅድሚያ ሰላም ያስፈልጋል። አሁን አገራችን ያለችበት ሁኔታ ደግሞ ትንሽ ወሰብሰብ ያለ ነው፤ ምናልባት ይህንን ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ቋጭተን ወደቀድሞ ሰላማችን ከተመለስን ማንም በውጭ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ የያዘውን ይዞ አገሩ ገብቶ የማይሰራበት ምክንያት ይኖራል ብዬ አላስብም።
አዲስ ዘመን፦ አሁን እርስዎ በሚኖሩበት አካባቢ እንዲሁም ሌሎች አገራት ላይ ኢትዮጵያውያን እየተሰባሰቡ ለአገራቸው ለመድረስ ሙከራ እያደረጉ ነው፤ ነገር ግን ይህ አንድነት ጊዜያዊ ሆኖ እንዳይቀር ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?
ወይዘሮ ነጻነት፦ አዎ ይህ አንድነት ተጠናክሮ መቀጠሉ ለዜጋውም ለአገርም እጅግ ጠቃሚ ነው። ምክንያቱ ደግሞ የአንድ አገር ሃብት የሚለካው ባላት የሰው ቁጥርም ጭምር ስለሆነ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከሌሎች ዓለማት በተሻለ ብዙና አምራች ሃይል ያለን ነን።ይህንን እድል መጠቀም ለብዙ ነገሮች ያግዘናል።
እኔ በበኩሌ የምለው ይህ መሰባሰብ ባለበት ቀጥሎ ለፍሬ እንዲበቃ በተለይም በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን የምንሰማውን መረጃ ትክክለኛነት መመርመር ይጠበቅብናል።ብዙ ሰዎች ለአገራቸው መድረስ ይፈልጉና በሚያገኙት የተሳሳተ መረጃ ምክንያት አይ አገር ቤት ማጭበርበር አለ፤ መንግሥትም የሰበሰበውን ሀብት ለሚፈለገው ዓላማ አያውልም ይላሉ፤ ይህ እንግዲህ ከሚያገኙት የተዛባ መረጃ የሚደርሱበት የተሳሳተ ውሳኔ ነው።
በመሆኑም እነዚህ ሰዎች የአገራቸውን ሌላኛውን ገጽታ ተመልክተው ለመልካም ነገር እንዲነሱ የምንሰራቸው በርካታ ስራዎች አሉ ፤ ነገር ግን እኛ የምንሰራው ስራ ብቻውን በቂ ሊሆን ስለማይችል አገር ቤት ያሉ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች ሕዝቡን ጨምሮ ማለት ነው የተግባር ሰው መሆን ሰርቶ ማሳየት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል።
በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት የስርዓት ዓመታት በአገሩ ላይ ተስፋ የቆረጠም ይኖራልና አሁን በአገሩ መለወጥ ወደፊት መሄድ በሕዝቡ እምነት እንዲያድርበት ማድረግ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፦ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ተገዳ በገባችበት ጦርነት ምክንያት ብዙ ነገሮች እያጋጠሟት በተለይም ደግሞ ምዕራባውያኑ ፍርደ ገምድል በሆነው ውሳኔያቸው ምክንያት ከፍተኛ ጫና እያሳደሩባት ነውና እንደው እናንተ ሀብት አሰባስባችሁ ለወገናችሁ ለመድረስ ከምታደርጉት ጥረት ባሻገር ባገኛችሁት አጋጣሚ ስለ አገራችሁ እውነት ማስረዳት ላይ ምን ያህል ሄዳችኋል?
ወይዘሮ ነጻነት፦ እውነት ለመናገር የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ እውነታውን ለማሳወቅ በጣም ጥረት ይደረጋል። ከዚህ ቀደም በውጭ ዓለም የምንኖር አበሾች ብዙ ቲውተር የመጠቀም ልምዱ አልነበረንም።አሁን ላይ ግን አብዛኛው ለማለት ይቻላል ቲውተር ይጠቀማል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የቲውተር ዘመቻ ተጀምሯል።
እኔ እንኳን የማውቀው የስዊዘርላንድ፣ የፈረንሳይ፣ የአውሮፓ እንዲሁም የአሜሪካን የቲውተር ዘመቻ አለ። በዚህ ደግሞ የመገናኛ ብዙኃን ምን አሉ የሚለው እየተፈተሸ በመካከል የሚሰራጩ በተለይም ጁንታው ቡድን የሚያሰራጫቸውን የሃሰት መረጃዎች የማምከን ስራዎች በሰፊው ይሰራሉ።
በተቻለ መጠን በተለይም የትዊተር ዘመቻ ላይ ሰዎች እየተሳተፉ ብዙ ነገሮችንም እየቀየሩ ስለመሆኑ አምናለሁ። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ ምዕራባውያን ስለ ኢትዮጵያ መልካም ነገር ማውራት እየጀመሩ ነው።ይህ እንግዲህ የህዝቡ የትግል ውጤት ነው ብዬ አምናለሁ።
አዲስ ዘመን፦ በመንግሥት በኩል የመረጃ እጥረት አለ የሚሉ ወገኖች አሉና በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ?
ወይዘሮ ነጻነት፦ አዎ እውነት ለመናገር የመረጃ እጥረቶች ይስተዋላሉ ፤ እኔ ባለሁበት ሁኔታ የምረዳውም ይህንኑ ነው።ነገር ግን በውጭ ያለው ዜጋ ያገኛትን መረጃ ለማካፈል እውነታውን ለማስረዳት ከፍተኛ የሆነ ጥረት ያደርጋል።ከዚህ በላይ ከፍ ባለ ሁኔታ መረጃዎች እንዴት ብለው ሊወጡ እንደሚችሉ ሳስብ እጨነቃለሁ። የሚገርመው ነገር የዛኛው ወገን ውሸትን በደንብ አድርጎ አሳምሮ በሚያሳምን ሁኔታ የማቅረብ አቅም እኛ ጋር ያለውን እውነት እያደበዘዘው ያለ ይመስለኛል። ይህንን ያልኩበት ዋና ምክንያት ደግሞ ኅብረተሰቡ ራሱ እውነት እየነገርከው እንኳን አምኖ መቀበል ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ሲቸገር እናየዋለን፤ ይህ እንግዲህ እንዴት እንደሚሆን አላውቅም።
አዲስ ዘመን፦ በእርስዎ እይታ ግን ይህንን ያመጣው የመረጃ እጥረቱ ነው ብለው ያምናሉ?
ወይዘሮ ነፃነት፦ የኢትዮጵያ መንግሥት በተለይም በመጀመሪያዎቹ አካባቢዎች ላይ መገናኛ ብዙሃንን ተጠቅሞ ስለ እውነቱ ማስረዳት ላይ በጣም ደካማ ነበር።ይህ ሁኔታ ደግሞ ለዛኛው ወገን እድል ፈጠረና ብዙ መረጃዎችን ወጡ፡፡ የአብዛኛውን ሰው አእምሮም ቀየሩ፡፡ አሁን እኛ የተነሳነው ያንን ሁሉ የተዛባ ነገር ለማስተካከል ነው፤ ይህ ደግሞ ከመዘግየታችንም ጋር ተያይዞ ሁኔታውን ከባድ አድርጎታል።
ለነገሩ አስቸጋሪም ቢሆን ግን በተቻለ መጠን መረጃዎችን ወደኋላም ወደፊትም እየሄድን ሕዝቡንም ዓለም አቀፍ ኅብረተሰቡንም በሚያሳምንና በሚያግባባ መልኩ ለመስራት እየሞከርን ነው፤ ውጤቶችም አሉ።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ ቆመው የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ ሲያዩት ምን ይሰማዎታል?
ወይዘሮ ነጻነት፦ በጣም ልብ ይሰብራል።ሁሌም ጸባችን እርስ በእርስ መሆኑ ደግሞ ያማል።በመሆኑም አሁን አንድነታችንን አጠናክረን በተለይም በጥባጩ ቡድን ወደ ቀልቡ ተመልሶ ዓለም የሚቀናባትን አገራችንን ተጋግዘን የሆነ ቦታ ላይ ብናደርሳት ምኞቴ ነው።ግን በተቃራኒው ወንድም ወንድሙን እየገደለ በጥቂት የስልጣን ጥመኞች አገር አስር ዓመት ወደኋላ ስትመለስ ማየት ልብ ይሰብራል።
አዲስ ዘመን፦ በቀጣይ የእናንተ ቡድን ምን ለመስራት አቅዷል?
ወይዘሮ ነጻነት፦ “ዘመቻ ለህልውና” ብለን የጀመርነው ራሳችን በራሳችን ተነሳስተን እንደመሆኑ ከዚህ ቀደም የሰራነው ስራ ጥሩ ነው፤ ያሰባሰብነው ሀብትም ለወገኖቻችን እገዛ እንዳደረገ ከፍተኛ የሆነ እምነት አለን።በቀጣይ ደግሞ በተለይም የመጀመሪያውን ዙር ሳይሰሙ ላለፋቸው ነገር ግን አገራቸውን ማገዝ የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች ስላሉ እነሱን ተደራሽ የሚያደርግ ስራ እንሰራለን። ኮሚቴም እናቋቁማለን ብለን አስበናል።በዚህ ኮሚቴ አማካይነትም ዜጎች አቅማቸው የፈቀደውን እየለገሱ በዲያስፖራ አካውንት ገቢ እየተደረገ ወደ አገር ቤት የሚመጣበትን ሁኔታ እንፈጥራለን ብለናል።
በሌላ በኩል ደግሞ የህዳሴውን ግድብ ፍጻሜው ለማድረስ ከዚህ ቀደምም የሞካከርናቸው ተግባራት እንዳሉ ሆነው አሁን እነሱን አጠንክረን በመሄድ ዜጋው በዚህ በኩልም ተሳትፎውን እንዲገልጽ እናደርጋለን።
አዲስ ዘመን፦ እናንተ አገራችሁን ለመደገፍ ከፍ ያለ ጥረት እያደረጋችሁ ነው እንደው መንግሥት ቢያግዘን ብላችሁ የምትሉት ነገር ይኖር ይሆን?
ወይዘሮ ነጻነት፦ መንግሥት ብዙ ነገሮችን እያገዘን ነው።በተለይም በስዊዘርላንድና ፈረንሳይ ያሉ ኤምባሲዎቻችን በጣም ይተባበሩናል፤ ያልናቸውን ነገር ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው። ይህ በጣም የሚያስደስትና ለስራ የሚያነሳሳ ነው። ነገር ግን እንደ ችግር ላነሳው የምችለው ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ተፈናቃዮች አሁን ላይ ከምግብ በተጨማሪ አልባሳትም ያስፈልጓቸዋል፡፡ ሆኖም ወደ አገር ውስጥ ልባሽ ጨርቆች አይገቡም የሚል ህግ ስላለ ያንን ማድረግ አልቻልንም።ይህ ህግ ለተወሰነ ጊዜ እንኳን ቢሻሻል ብዙ እገዛዎች ይኖሩ ነበር።
ይህንን ያልነው ብዙ ዜጋ ከሚያደርገው የገንዘበ ድጋፍ ባሻገር ለወገኖቹ አልባሳትም ለመለገስ ስለሚፈልግና ብዙ ጥያቄዎችም ስላሉ ነው።እናም መንግሥት በዚህ በኩል ያለውን ነገር ቢያመቻች ብዙ ድጋፎች ይገኛሉ።
አዲስ ዘመን፡- ብረትን እንደጋለ” የሚል የአገራችን ብሂል አለና እንደው ይህ የዲያስፖራው መነሳሳት ሳይቀዘቅዝ ለመጠቀም ብሎም በአገር ውስጥም ያለ ዜጋ አገሩን ካለችበት ሁኔታ ለማውጣት ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
ወይዘሮ ነጻነት፦ እኩል መናበብና መረጃዎች እኩል ማዳረስ ያስፈልጋል።ይህ ከሆነ ምንም የማይቻል ነገር ካለመኖሩም በላይ የማንተማመንበት ሁኔታም ይቀየራል።በመሆኑም መንግሥት ለመረጃ ዝግ መሆን የለበትም፤ ሰዎችም ከመጠራጠር ወጥተው አገራቸውን ከገባችበት ችግር ለማውጣት መነሳት ያስፈልጋል።እውነት ለመናገር አሁን ላይ እኔ ባለሁበትም ሆነ በሌሎች አገሮች ያለው ዲያስፖራ ሃሳቡም ህልሙም ሁሉም ነገሩ አገሩ ላይ ነው።ይህንን ሁኔታ ደግሞ እንደ መልካም እድል መጠቀም ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ወይዘሮ ነጻነት፦ እኔም አመሰግናለሁ።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2014 ዓ.ም