ተከሳሾች እንደቅደም ተከተላቸው አቶ አብዲ የሱፍ አህመድ ፣ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ)፣ አቶ መሀመድ አህመድ (ያልተያዘ) እና አቶ አብዱላሂ ሁሴን ጋኒ ናቸው፡፡
የክሱ ዝርዝር እንደሚያስረዳው የሱማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ከሱማሌ ፕሪንቲንግ ፕሬስ ባለቤት ከሆኑት ቴዎድሮስ አዲሱ ጋር በገባው ውል መሰረት ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች 578,274 የሚሆኑ መማርያ መጻህፍትን በ18,990,000 ብር አሳትሞ ለማቅረብ የግዥ ውል የገባ ቢሆንም ስራው ሳይሰራ ከቀድሞው ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ፣ ከኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማሕበር ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ እና ከቀድሞው ከክልሉ ትምህርት ቢሮ የፋይናንስና ሎጅስቲክስ የሥራ ሂደት ኃላፊ ጋር በመመሳጠር የቅድሚያ ክፍያ ዋስትና ያላግባብ እንዲከፈለው ተደርጓል፡፡
በዚህም መሰረት 1ኛ ተከሳሽ በፌዴራል መንግስት በተመዘገበ ሕዝባዊ ድርጅት (ኒያላ ኢንሹራንስ) አሰራርና መመሪያ ውጭ ያላግባብ ዋስትና በመስጠት፤ 3ኛና 4ኛ ተከሳሾችም ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ሆነው ሲሰሩ ለ2ኛ ተከሳሽ ያላግባብ 15,306,803 ክፍያ እንዲከፈል በማድረግና ገንዘብ እንዲመለስ መጻሀፍቱም እንዲገቡ ባለማስደረግ፤ 2ኛ ተከሳሽም ከመንግስትና ሕዝባዊ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ተመሳጥሮ ያላግባብ ዋስትና እንዲሰጠው አድርጎ ክፍያ በመውሰድ መጻህፍቱም ባለመቅረባቸው በሕዝብና መንግስት ገንዘብና በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ያላግባብ በተከፈለው ገንዘብ በተከፈተ አካውንት በቂ ስንቅ የሌለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቼክ አስቀድሞ ለቅድሚያ ክፍያ ዋስትናው የሚሆን ዋስትና የተያዘ ለማስመሰል ለኢንሹራንሱ እንዲያዝ አድርጓል፡፡
በመሆኑ 1ኛ፤ 3ኛና 4ኛ ተከሳሾች የመንግስትንና የሕዝባዊ ድርጀትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት፤ 2ኛ ተከሳሽም በመንግስትና በሕዝባዊ ድርጅት ሰራተኞችና/ኃላፊዎች በሚፈጸም የሙስና ወንጀል ልዩ ተካፋይ በመሆን በመንግስትና በሕዝብ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ በመሆኑ ሁሉም ተከሳሾች አባሪ ተባባሪ በመሆን በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈጸሙት የመንግስትና የሕዝባዊ ድርጅት ሥራን በማያመች አኳኋን መምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡
ከዚህ ቀደም 2ኛ ተከሳሽ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ከሀምሌ 28-30/2010 በኢትዮ- ሶማሌ ክልል ተከስቶ በነበረው ሁከትና ግጭት ተጠርጥሮ ምርመራው ባለመጠናቀቁ ምክንያት በ80 ሺህ ብር ዋስ እንዲወጡ ፍርድ ቤቱ ፈቅዶለት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሆኖም ግን ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት 2ኛ የተከሳሽ የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ሲሆኑ ጉዳዩን የተመለከተው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ተከሳሹ ዐቃቤ ህግ ያቀረበበባቸውን ክስ በእጃቸው እንዲደርሳቸው በማድረግ ክሱ በችሎቱ ተነቦላቸዋል፡፡
የተከሳሽ ጠበቃም ከዚህ ቀደም ደንበኛየ በሌሎች ታሳሪዎች ጉዳት ስለደረሰበት የሚቆይበትን እስርቤት ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
ፍርድ ቤቱም ተከሳስሽ የሚቆይበትን እስር ቤት ለመወሰን ለ22/06/2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል፡፡