ያለፉት አስራ ሁለት ወራቶች ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ምን አይነት እንደነበሩ ሁላችንም የምናውቀው ነው። እኚህ ወራቶች እያንዳንዶቻችንን አስለቅሰውና አሳዝነው ያለፉ ጥቁር ወራቶች ነበሩ። እሸባሪው የሕወሓት ቡድን ለዘመናት ሲጠብቀው የኖረውን መከላከያ ሠራዊት ከኋላው ወግቶ በኢትዮጵያውያን ላይ ጦርነት እስካወጀበት ጊዜ ድረስ በዚህ ከሀዲ ቡድን ብዙ ነገራችንን አጥተናል።
ያለፉት አስራ ሁለት ወራቶች በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ጠባሳን ትተው ያለፉ ከመሆናቸውም በላይ ሕወሓት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በደንብ እንድንረዳ ያደረጉን ወራቶች ናቸው። እኚህ ወራቶች ሁላችንንም ዋጋ አስከፍለውናል።
የለውጡ መንግሥት ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት በአሸባሪው ሕወሓት አገዛዝ የደረሱብንን ግፍና በደሎች እያስተካከለና ሕዝብ በአንድ ልብ ለጋራ ዓላማ በጋራ እንዲሰራ አስቻይ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ደፋ ቀና በሚልበት ወቅት “ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” በሚል አሸባሪው ሕወሓት የተንኮል ግብሩን ሀ ሲል በተጠናና በተደራጀ መንገድ ጀምሯል።
ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የሰራብን ግፍና የፖለቲካ አሻጥር ሳያንሰው የተስፋና የለውጥ ብርሃን ባየንበት ማግስት ክንዱን አገር ለማፍረስ መጠቀሙ ሁላችንንም ያስቆጣ የጋራ ስሜት ሆኖም አልፏል።
የቡድኑ ዓላማ ከትናንት እስከዛሬ አንድና አንድ ነው። አገር ማፍረስና ታሪክ ማበላሸት ነው። በአስተሳሰብ ውስጥ አገርና ህዝብ፣ ታሪክና ትውልድ የለም። ሕዝብ ለምን ብሎ እንዳይጠይቅ መረን በወጣ የፖለቲካ ሥርዓት አንቆ ሲያስተዳድር ነበር። ይሄ መረን የወጣ የፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ ሀገር ከማፍረስ ትውልድ ከማምከን ባለፈ የሚፈይደው አንድም ነገር የለም።
መሪን እንጂ ተመሪን አይጠቅምም። አንድን ቡድን እንጂ ለብዙሃኑ ዋስትና አይሆንም። አሸባሪው ሕወሓት ከውልደቱ ጀምሮ ዓላማው ራስን እንጂ ሕዝብን ማገልገል አልነበረም። ለዚህ ዓላማው የሚበጀውን ሥርዓት መፍጠር ግድ ነበረበትና አገርና ሕዝብ፣ ታሪክና ትውልድ የሌሉበትን የራሱን እኩይ የፖለቲካ ሥርዓት ፈጥሯል።
እንዳሰበውም አገርና ታሪክን አበላሸ ፤ ትውልዶችን አመከነ፤ ባህል፣ ወግና ሥርዓት ተበላሸ። እንዳሰበውም በውሸትና በማጭበርበር ሃያ ሰባት ዓመታትን ገዛ። በጣም የሚገርመው ደግሞ ዛሬ እንደ ትናንት መስሎት ለተመሳሳይ ዓላማ መሰናዳቱ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን ድጋሚ እድል አልሰጠውም ፣ አይንህ ላፈር ብሎ ሸኮና ሸኮናውን ብሎ አባረረው እንጂ።
አሸባሪው ሕወሓት ምን አይነት እንደነበረና አሁንም ምን አይነት ዓላማ እንዳለው ትናንትና ዛሬን ማየቱ የተሻለ ነው እላለሁ። ከእኔነት ያልተለየ ኋላ ቀር አስተሳሰብን የሚያራምድ ለዘመኑ የማይመጥን ቡድን መሆኑ በኢትዮጵያ ላይ ያደረሰው በደሎች ምስክሮቹ ናቸው። ትናንት በውሸትና በማጭበርበር ሕዝብን ከሕዝብ እያባላ ሥልጣኑን ሲያረዝም ነበር።
ትናንት በንጹሃን ደም፣ በመልካሞች ነፍስ ሲነግድና ሲያተረፍ ነበር። ትናንት ሥልጣኑን ተገን አድርጎ የሕዝብ ሀብት ሲዘርፍ ነበር። ዛሬም እንደዛው ነው። ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንደሚባለው ዛሬም ሀገር በማፍረስና ህዝብ በማስጨነቅ ተግባሩ እንደቀጠለ ነው። በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ እንኳን የቡድኑ የጭካኔ በትር ያላረፈበት የማህበረሰብ ክፍል የለም።
ኢትዮጵያ አገራችን በቡድኑ እንደደረሰባት አይነት ግፍና በደል ደርሶባት አያውቅም። ዓለም ብዙ መልካምና ጨካኝ ሰዎች አሏት። የሁሉም ጭካኔና መልካምነት ደግሞ በምክንያት የታጀበ ነው። የሁሉም ጭካኔ በጠላቶቻቸው ነው የሕወሓት ጭካ ግን በእናት አገሩ ላይ ነው። ወልዳ ባሳደገችው፣ ለቁም ነገር ባበቃችው አገሩ ላይ ነው።
ከሌለው ላይ ሰጥቶ ባስተማረውና ለክብር ባበቃው አገርና ሕዝቡ ላይ ነው። እንዲህ አይነት ጭካኔ በየትኛውም ዘመን በየትኛውም አገር ታይቶ አይታወቅም። ትናንት የኢትዮጵያን ክብር፣ የሕዝቦቿን ፍቅር ሲያጎድፍ ነበር። ትናንት አገር አፍርሶ ታሪክ አበላሽቶ የራሱን ቤትና የጥቂት ወዳጆቹን ቤት ሲሰራ ነበር።
ትናንት እጅግ በረቀቀ ሴራ አገር አደብዝዞ ራሱን ብቻ አድምቆ ሲጽፍ የነበረበት የፖለቲካ ሥርዓት ነበር። ዛሬም በትናንት እኩይ ግብሩ መጣ እንጂ አልተሻለም። ትናንት አገር ለማፍረስ ጫካ ነበር ዛሬም አገር ለማፍረስ ጫካ ገብቷል። ትናንት አገርና ሕዝብ ጉዳዩ አልነበሩም ዛሬም አገርና ሕዝብ ጉዳዩ አይደሉም። ትናንት በውሸት እና በማስመሰል ህዝብ ሲያጭበረብር ነበር ዛሬም በለመደው ውሸት ሕዝብ በማጭበርበር ላይ ነው።
ይህ ቡድን ታዲያ ለኢትዮጵያ ምንድነው? መልሱን ራሳችሁን ጠይቁ። አገር በጥያቄ ውስጥ ናት። አገር የእኔና የእናተ ቀና ልብ ነጸብራቅ ናት። ዛሬ እንዲህ የምንሆነው የሕወሓት የክፋት ልቦች በፈጠራቸው እኩይ አስተሳሰቦች ነው። የአገራችን አሁናዊ አዳፋ መልኮች በሕወሓት የፖለቲካ ፍልስፍና የተሳሉ ናቸው።
መልካም ሃሳብ መልካም አገርና ትውልድ ይፈጥራል በተቃራኒው እኩይ ሃሳብ ደግሞ አገርና ታሪክ ያበላሻል። ቀጣይ ለምትፈጠረው ኢትዮጵያ ሕወሓትና አስተሳሰቡን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ታግለን መጣል ይኖርብናል። በክፋት ልብ ውስጥ ቀና መንገድ የለም። በግፈኛ ነፍስ ውስጥ ጽድቅና የለም።
አገራችን ኢትዮጵያ በመንጋት ዘመን ላይ ናት። የለውጡ መንግስት ለኢትዮጵያ ሀገራችን እያደረገ ያለው ትጋት በአሸባሪው ሕወሓት ዘመን የከሰረ እኛነታችንን የሚያድስና የሚመልስ ነው። ከለውጡ መንግሥት ጎን ቆመን የኢትዮጵያ ጠላቶችን መታገል ይኖርብናል። እኔና እናተ መልካም አገር ታስፈልገናለች። የሚመጣው ትውልድ የተከፋፈለ አገርና ህዝብ ሳይሆን በአንድነቱ የተደነቀ ማህበረሰብ ግድ ይለዋል።
ይሄ እንዲሆን እንደ አሸባሪው ሕወሓት ያሉ እኩይ አስተሳሰብ ያላቸውን ግለሰቦችና ቡድኖች ከእግራችን ስር መጣል ይኖርብናል። ከለውጡ መንግሥት ጎን በመቆም ኢትዮጵያዊነትን መመለስ፣ ሕዝባዊነትን መቀለም ይጠበቅብናል። ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የመክሰር ዘመናት ነበሩ።
ኢትዮጵያዊነት የደበዘዘበት፣ አብሮነት የመከነበት፣ ታሪክ ፣ ትውልድ ፣ አገርና ሕዝብ የተዛቡበት የሴራ ፖለቲካ ፣ ውሸት እና ማጭበርበር የነገሱበት ፣ ፍቅር ተስፋ እውነት የሞቱበት የራስ ወዳዶች ቁማር ያተረፈበት .. በዚህ ሁሉ ውስጥ መኖር እንዴት መከራ ነው?
በኢትዮጵያ ታሪክ .. በኢትዮጵያ ትናንትና ውስጥ በሕዝብ አንድነት የተሰፉ ብዙ አለላ ሰበዞች በሕወሓት አሸባሪ ቡድን ተመዘው ዛሬም ድረስ ጎደሎ ነን። ኢትዮጵያዊነት ክብርና ዋጋ ካጣባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የሕወሓት ሥስልጣን ዘመን ነው። ራሱን እንደ አንድ አውራ ፓርቲ በመቁጠር ሳይፈለግና ሳይወደድ በሃይል አገርና ሕዝብ የመራ ብቸኛው ፓርቲም ነው። የቡድኑ ስረ መሰረት አዳምና ሄዋንን ከገነት ካስባረረው ሳጥናኤል ጋ አንድ ነው። ለዚህ ደግሞ በውሸትና በማጭበርበር ሕዝብ ያወናበደበት ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አመላካች ናቸው።
አንድ ዓመት በመከራና በስቃይ ሲሰላ ምን ያክል ነው? አስራ ሁለት ወራት በንጹሀን እንባና ሞት ቢቀመር እስከ የት ድረስ ነው? ያለፉት አስራ ሁለት ወራቶች እንዲህ ናቸው.. የሰቆቃ ወራቶች። ያለፈው አንድ ዓመት እንዲህ ከሆነ ያለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ምን እንደነበሩ መገመት ይከብደናል።
አስራ ሁለት ወራት በደስታ ሲታጀቡ እንጂ በመከራ ሲታጀቡ የክፍለ ዘመናት ያክል ሩቅ ናቸው። አንድ ዓመት በመከራ ውስጥ አንድ ክፍለ ዘመን ነው። በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የሕወሓትን የግፍ ጽዋ የቀመሱ አንድ መዓት ንጹሀን አሉ። አሁንም ድረስ ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው ጎዳና ላይ እየተሰቃዩ ያሉ ብዙ ነፍሶች የዚህ ከሀዲ ቡድን ሰለባዎች ናቸው።
በማይካድራ፣ በጉራ ፈርዳ፣ በወለጋና በሌሎች ስፍራዎችም የጭካኔ በትሩን ያሳረፈባቸው ብዙ ናቸው። መንግሥት ዓገር ለመለወጥ ሲሰራ አሸባሪው ሕወሓት ዐገር ለማፍረስ ይሰራል። መንግሥት ለእርቅና ለይቅርታ ሲዘጋጅ ከሀዲው ቡድን ከእውነት ሽሽት ጫካ ይገባል።
ጦርነት ለአሸባሪው ሕወሓት ያደገበት ነው። መግደል ለሕወሓት ተራ ነገር ነው። ይሄን ደግሞ ካለፉት በርካታ ዓመታት በበለጠ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ለማየት ችለናል። ከትናንት እስከዛሬ ሲገድልና ሲያሰቃይ የመጣ ቡድን ነው። ለዘመናት ሲጠብቁት በነበሩ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጭካኔውን አሳይቶ ጦርነት እንደጀመረ ሁሉም የሚያውቀው ነው። ዓላማው አገር ማፍረስ ባይሆን ኖሮ መንግሥት በሰጠው የይቅርታና የእርቅ እድል ይጠቀም ነበር። ግን አገር ከማፍረስ ሌላ ዓላማ ስላልነበረው ወደ ጦርነት ገባ ፤ የሚገርመው ደግሞ እንዳሰበው ሳይሆን ቀርቶ ራሱ በለኮሰው እሳት እየተቃጠለ መሆኑ ነው።
አሁን ላይ ወደ ጦርነት በመግባቱ እንደ አሸባሪው ሕወሓት የሚጸጸት ቡድን አለ ብዬ አላስብም። ምክንያቱም ነገሮች ሁሉ እንዳሰበው እየሄዱለት አይደለም። የእሱ ሃሳብ ትናንት በለመደው የውሸትና የጭካኔ እርምጃ ተራምዶ አራት ኪሎ ቤተመንግሥት መግባትና እንደለመደው በአንባ ገነን ሥርዓት አገርና ሕዝብ ማስጨነቅ ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ይሄን እድል አልሰጠውም። ቀፎው እንደተነካ ንብ በአንድ ላይ ተነስቶ አፈር ድሜ አስጋጠው እንጂ። ሕዝብ ሲቆጣ እንዲህ ነው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ አይቆጣ እንጂ ከተቆጣ የሚያቆመው የለውም። የኢትዮጵያውያንን ትዕግስት ሳይ ፈጣሪ ሃይሉን ለሀበሾች አልብሶ ወደ ሰማይ ያረገ ነው የሚመስለኝ። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፈጣሪ ላመል አነስ ያለ ከኢዮብ የሚተልቅ ብዙ ትዕግስት አለው እላለሁ። ምክንያቱም ሃያ ሰባት ዓመት ሙሉ የሕወሓትን አገዛዝ ታግሶ የኖረ ሕዝብ ነው። የትኛውም አገርና ሕዝብ የኢትዮጵያን ያክል ትዕግስት አለው ብዬ አላስብም። በለውጡ ማግስት የሆነውን የደስታና የእልልታ ድምጽ ደግሞ ሁላችሁም የምታውቁት ነው። ሕዝብ ምን ያክል ለውጥና አዲስ ነገር እንደናፈቀው የለውጡን መንግሥት ድጋፍና ይሁንታ ማየቱ ብቻ በቂ ነው እላለሁ።
ሕዝብ ትናንትም ዛሬም የአሸባሪውን ሕወሓት አገዛዝ አይፈልገውም። ለዚህ ነው ያለውን ሁሉ እየተወ ከመከላከያ ጎን የቆመው። ለዚህ ነው በሬ ያለው በሬውን እየሰጠ፣ ገንዘብ ያለው በገንዘቡ ድጋፍ እያደረገ መከላከያን ሲያግዝና ሲደግፍ የነበረው። ይሄ ቡድን የኢትዮጵያን ጸዓዳ መልክ ያበላሸ፣ የዘመናት አብሮነትን ያሻከረ ከሀዲ ቡድን ነው።
በሕወሓት ትናንትና ውስጥ ያልተነገሩና ጊዜ የሚሹ በርካታ የሕዝብ ሮሮዎች አሉ። በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ የሆነውን ብናየው እንኳን ንጹሃንን እየገደለና እያሰቃየ የፖለቲካ ትርፍ ለማትረፍ ሲሞክር ነበር። ነፍሰ ጡር እናቶችን አሰቃቂ በሆነ ጭካኔ ሆዳቸውን በስለት እየቀደደና እየደፈረ እኩይ ተግባሩን በአደባባይ ሲያሳየን ነበር።
የአሸባሪው ሕወሓት የአስራ ሁለት ወራት የሴራ እርምጃ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ይሄን ቡድን ከነአስተሳሰቡ ለመቅበር ትክክለኛው ጊዜ አሁን ነው። ከለውጡ መንግሥት ጎን በመቆም በኢትዮጵያ ጠላቶች ላይ እንዝመት እያልኩ ላብቃ ፤ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2014