ዓለምን ለመቆጣጠር የት አካባቢ የሚገኙ ቦታዎችን መቆጣጠር ያስፈልጋል በሚለው ዙሪያ የጂኦ-ፖለቲክስ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ልሂቃን ለረጅም ጊዜ ጥናቶችን ሲያካሂዱ ቆይተዋል:: በዚህ ዘርፍ ጥናቶችን ካካሄዱት መካከል ሃሮልድ ማኪንደር አንዱ ነው::
ከነባር የጂኦ ፖለቲካ ንድፈ ሀሳቦች አመንጪዎች መካከል ስመ ጥር የሆነው እንግሊዛዊው ሃልፎርድ ማኪንደር የዓለምን ልብ ፍለጋ ላይ ጥናቶችን አካሂዷል:: የዓለምን ልብ ሲፈልግ የነበረው የዓለምን የልብ ትርታ ወይም ቁልፍ ቦታ የተቆጣጠረ ኃይል ዓለምን ይቆጣጠራል የሚል እሳቤ በመያዝ ነበር:: እ.ኤ.አ በ1904 ሃልፎርድ ማኪንደር የ”Heartland” ንድፈ ሀሳብን ይዞ ብቅ አለ።
በንድፈ ሀሳቡ መሠረት በምሥራቅ አውሮፓ እና በኤሺያ አህጉራት መካከል የሚገኙ ቦታዎችን የሚቆጣጠር ማንኛውም አካል የዓለም የልብ ትርታን እንደሚቆጣጠር ማሳመኛዎችን አቀርቧል። በዚህ ንድፈ ሀሳብ መሠረት ይህን የዓለም አካባቢ የሚቆጣጠር አገር መላውን ዓለምን የመቆጣጠር አቅም እንደሚኖረው አብራርቷል::
ሃሮልድ ማኪንደርን ጨምሮ በወቅቱ የነበሩ የጂኦ ፖለቲክስ አሳቢዎች የዓለም የልብ ትርታ በአውሮፓና በኤሺያ አህጉራት መካከል ማለትም ለመካከለኛው ምሥራቅ ቅርብ የሆነ ቦታ መሆኑን የተለያዩ ማሳያዎችን በማንሳት፤ ይህንን አካባቢ የተቆጣጠረ ዓለምን ይቆጣጠራል የሚል ነበር:: በማኪንደር እሳቤ መሠረት የዓለም ልብ ተብሎ የተሰየመው አካባቢ ከአፍሪካ ቀንድ ብዙም የራቀ እንዳልሆነ መገንዘብ ይቻላል::
የማኪንደርን ንድፈ ሀሳብን ተችቶ የመጣው ደግሞ “rimland” ሪም ላንድ ንድፈ ሀሳብ ነው:: በ1930ዎቹ አጋማሽ አካባቢ ብቅ ያለው እና በዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰሩ ኒኮላስ ስፓይክማን ለዓለም የቀረበው ንድፈ ሀሳብ የዓለምን የልብ ትርታ መቆጣጠር የሚቻለው ከሜዲትራኒያን ውቂያኖስ ጀምሮ ስዊዝ ካናልን፣ ቀይ ባህርን፣ ባብ ኤል ማንደብ እንዲሁም የሕንድ ውቂያኖስ ዳርቻዎችን መቆጣጠር የቻለ ነው ብሏል። በንድፈ ሀሳብ መሠረትም ከላይ የተጠቀሱት የባህሮች እና ውቂያኖሶች ዳርቻዎች የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ሙሉ በሙሉ የሚያጠቃልል ነው::
በሁለቱም ንድፈ ሀሳቦች የዓለምን የልብ ትርታ ለመቆጣጠር ቁልፍ ቦታዎች ናቸው ተብለው የተጠቀሱ ቦታዎች ከአፍሪካ ቀንድ ብዙም የራቁ አይደሉም::
በተለይም በሪም ላንድ ንድፈ ሀሳብ የተጠቀሱ አካባቢዎች የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ሙሉ በሙሉ የሚያጠቃልሉ ናቸው:: ከሁለቱ ንድፈ ሀሳቦች በመነሳትም የአፍሪካ ቀንድ በዓለም ጂኦ ፖለቲክስ ውስጥ ያለውን ከፍ ያለ ቦታ መገንዘብ ይቻላል::
ይህ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በተግባርም እየታየ ያለ እውነታ ነው:: የዓለም ልዕለ ኃያላን እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ትኩረት በአፍሪካ ቀንድ ላይ መሆኑ በግልጽ እየታየ ነው:: ለዚህ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል:: ሁሉም ልዕለ ኃያላን አገራት በቀይ ባህር እና በሕንድ ውቅያኖስ ዳርቻዎች የጦር ሰፈራቸውን ገንብተዋል:: የቻይና የሮድ ቤልት ኢንሼቲቪ ዋነኛው መዳረሻ የአፍሪካ ቀንድ ነው:: ከዚያ ባሻገርም በዓለም ላይ የቻይና የጦር ሰፈር ያለው ብቸኛው አካባቢ የአፍሪካ ቀንድ ነው:: ጂቡቲ ውስጥ::
የዓለም ከፍተኛ ንግድ የሚተላለፍበትን ቀይ ባህር ለመቆጣጠር ከቀይ ባህር በምዕራብ አቅጣጫ የሚገኙ ዳርቻዎችን መያዝን ይጠይቃል:: እነዚህ ዳርቻዎች ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ አገራትን የሚያካትቱ ናቸው:: ኢትዮጵያ በዚህ ዳርቻዎች ውስጥ ከሚካተቱት አገራት መካከል ተጠቃሽ ነች:: የአፍሪካ ቀንድ እምብርት የሆነቺው እና ከሁሉም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ጋር የምትዋሰነው ኢትዮጵያን መቆጣጠር የዓለምን የልብ ትርታ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖረው ለመገንዘብ አይከብድም::
ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር በስተምዕራብ ከምትገኝ ቁልፍ አገር አንዷ ከመሆኗ ባሻገር ካላት ታሪክ እና ከሕዝብ ብዛት አንጻር ይህችን አገር መቆጣጠር ዓለምን ለመቆጣጠር ለሚደረገው ትንቅንቅ መንገድ ጠራጊ እንደሚሆን አያጠያይቅም::
አንድ ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተከትሎ ምዕራባውያን አገራት ቀን ከሌሊት ስለ ግጭቱ መግለጫ ሲያወጡ፣ የተመድ የጸጥታ ምክር ቤትን በተደጋጋሚ ስብሰባ ሲጠሩ፣ ማዕቀብ ለመጣል ሲዝቱ ለተመለከተ ሰው ምዕራባውያን በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ላይ ልዩ ትኩረት መስጠታቸው ለኢትዮጵያውያን ከማሰብ እንዳልሆነ ግልጽ ነው::
በትግራይ ክልል ውስጥ ሲካሄድ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ የተፈጠሩ ጉዳቶች ስላሳሰባቸው እና ለትግራይ ሕዝብ የተለየ ፍቅር ስላላቸውም አይደለም:: ምዕራባውያኑ የአፍሪካውያን ስቃይና መከራ እንደማያሳስባቸው በርካታ ማሳያዎችን መደርደር ይቻላል:: የቀደሙ ታሪኮቻቸውም ተጨባጭ ማሳያ ናቸው።
ከዚህ ይልቅ ምዕራባውያኑን አንድ ብርቱ ጉዳይ ቻይና በአካባቢው የምታደርገው እንቅስቃሴ ነው። ጩኸት አልባው የቻይና እንቅስቃሴ በቀጣይ በአካባቢው ባለው ጥቅሞቻቸው ላይ ስጋት ይዞ እንደሚመጣ በርግጠኝነት መስማማት ላይ የደረሱ ይመስላል።
በተለይም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምታደርገው እንቅስቃሴ እንቅልፍ ከነሳቸው ውሎ አድሯል:: የአፍሪካ ቀንድ ለቻይና ወደ አፍሪካ መግቢያ በር ሊሆን እንደሚችል የተረዱ ይመስላል:: በቤልት ኤንድ ሮድ ኢንሼቲቪ እንዲሁም በጂቡቲ የጦር ሰፈሯን መገንባቷ ምዕራባውያን ዓለምን ለመቆጣጠር እያደረጉ ባለው እንቅስቃሴዎች ላይ ዋነኝ ተግዳሮት እንደሚሆንባቸው የተረዱ ይመስላሉ::
ይህንን ስጋታቸውን ለመቀልበስ በአፍሪካ ቀንድ በነሱ የሚዘወር ሞግዚት መንግሥታትን መፍጠር ይፈልጋሉ :: ለዚህም ሲሉ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት ባለጉዳይ ለመሆን ሲጥሩ እየተስተዋለ ነው:: የአካባቢው አገርት መንግሥታት ለሚያደርጓቸው የፖለቲካ ጫናዎች የማይንበረከኩ ከሆነም አማጽያን ኃይሎችን በመደገፍ መንግሥታት እንዳይረጋጉ ሲያደርጉ ማየት የተለመደ ነው::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2014