በመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሻምፒዮና በ1963 ዓ.ም የሊሴ ገብረማርያም ተማሪ ነበርኩ፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ስፖርት ክለብ አባል ሆኜ በአሎሎ እና ዲስከስ ውርወራ ተሳትፌያለሁ። በአሁኑ ጊዜ በአሰልጣኝነትና በአስተማሪነት ከስፖርቱ ህብረተሰብ ጎን ቆሜ እተባበራለሁ። ውጪም እየኖርኩም ሆነ ሀገሬ ጠቅልዬ ከገባው አንስቶ አትሌቲክሱን ሁሌም በቅርብ እከታተላለሁ።
ለአትሌቲክስ አሰልጣኞች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ካንዴም ሁለት ጊዜ ሰጥቻለሁ። የኢትዮጵያን አትሌቲክስ በቅርቡ ስለምከታተልም የስፖርቱን ጠንካራ እና ደካማ ጎን በጥልቀት ለማወቅ ችያለሁ። እነዚህ መልካም አጋጣሚዎች የግማሽ ምዕተ ዓመቱን የሀገራችንን የአትሌቲክስ ጉዞ ለመተንተን አስችለውኛል።
ይህን ጥናታዊ ጽሁፍ ለማዘጋጀት በመረጃ ምንጭነት የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ድረገፅን ዊኪፔዲያን (በተለይ ከ2002 በጎርጎሪየስ ቀመር አቆጣጠር በእያንዳንዱ ሜዳ ተግባር ዝርዝር ውጤት) ተጠቅሜያለሁ፤ እንዲሁም ከ2002 በፊት ሜዳሊያ ያገኙትን አትሌቶች ብቻ ያስቀመጠ አንድ የእንግሊዝ አትሌቲክሰ ድረገፅ መረጃ ተጠቅሜያለሁ።
አትሌቲክስ በተለያዩ የሜዳ ተግባራት የተመሰረተ አጠቃላይ ስፖርት ነው። ወንዶች በ24 ውድድሮች ሲካፈሉ ሴቶች በ23 ይሳተፋሉ። አትሌቲክስ በወስጡ 11 አጭር፡ መካከለኛ እንዲሁም ረጅም ርቀት ሩጫዎች፣ ለሴት 1 ለወንድ 2፣ የእርምጃ ውድድሮች፣ 3 የመሰናክል ሩጫዎች (2 አጭር እና 1 ረጅም) ያካትታል። በተጨማሪም 4 የተለያዩ ውርወራዎች፣ እንዲሁም 2 የዱላ ቅብብል ሩጫዎች፣ በመጨረሻም ለወንዶች በ10፣ለሴቶች በ7 የሜዳ ተግባራት ጥምረት የተገነቡ ውድድሮች ይገኙባቸዋል። በአራቱም ውርወራዎች ሴቶች ቢሳተፉም ከወንዶች ጋር የሚለዩት በቁሳቁስ ክብደት ልዩነት ብቻ ነው። የሴቶች ተወርዋሪ ቁሳቁሶች ቀለል ይላሉ።
ስፖርት ለአገር መልካም ገፅታ ግንባታ ያለው አዎንታዊ አስተዋጽኦ፡- አትሌቲክሳችን ለአገራችን መልካም ስም ያበረከተው ውለታ ከፍተኛ እንደሆነ ማንም ይገነዘበዋል። የሚገርመው በ2ኛው የኦሊምፒክ ተሳትፎ አስደናቂ እና የማይረሳ ውጤት ጀግናው አትሌት አበበ ቢቂላ በሮማ አስመዘገበ፤ አበበ ይህን ውጤት ከ4 ዓመት በኋላ በቶኪዮ ደገመው፤ ማራቶን የኢትዮጵያ ንብረት ናት እስከሚባል ድረስ በሜክሲኮ ማሞ ወልዴ ለ3ኛ ጊዜ የወርቅ ሜዳሊያን ለአገሩ አመጣ። ከ32 ዓመት ድርቅ በኋላ ገዛኸኝ አበራ ማራቶንን ቤቷ መለሳት።
እግር ኳሳችን ከመጀመሪያ 2 ያልተሳካ ሙከራ በኋላ በ3ኛው የአፍሪካ ዋንጫን አሸነፈ። ሆኖም እንደ አትሌቲክሳችን መንገዱ የተቃና አልሆነለትም። እያደረ የቁልቁለት ጉዞውን ቀጠለ። ለ3 አሥርት ዓመታት ከአህጉራዊ ውድድሮች ርቀን ቆየን። ከ31 ዓመት በኋላ ብሔራዊ ቡድናችን ብቅ ብሎ እንደገና ተመልሶ ጠፍቶ አሁን ከ8 ዓመት በኋላ ተመለሰ።
ስለሆነም የአገራችን አትሌቲክስ ያለምንም ጥርጣሬ ባለውለታችን ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን አትሌቲክሳችን የተፈለገውን ውጤት አምጥቷል ወይ ብለን መጠየቅ ይገባናል። አትሌቲክስ ረጅም ሩጫ ብቻ አይደለም እኮ! ሀገራችን የታወቀችው እና የምትሳተፈው በረጅም ሩጫ ብቻ ነው። በዚህም ተሳትፏችን ውጤታማነታችን ምንም አያጠራጥርም። ሆኖም በሌሎቹ የሜዳ ተግባራት ስለማንሳተፍ የምናመጣው ውጤት በጣም ውስን ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በአፍሪካ አህጉራዊ ውድድር ሲገመገም የሀገራችንን አትሌቲክስ ስንገመግም በየትኛው መስፈርት ተጠቅመን ነው መሆን ያለበት? የተለያዩ የአገራችን የሜዳ ተግባራት ውጤት እንዲሁም ክብረወሰኖቹ ከአህጉር እና ከዓለም አቀፍ ውጤቶች ጋር ሲነፃፀሩ ምን ትርጉም አላቸው?
የኢትዮጵያ ስፖርት በመጀመሪያ ደረጃ የሚለካው በአህጉር ውስጥ በተመዘገቡት ውጤቶች ነው። አትሌቲክስን ከወሰድን የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ለአህጉሩ ሻምፕዮና የሚያስቀምጠው መለስተኛ የመወዳደርያ ተሳትፎ ውጤት ወይንም ሚኒማ በየውድድሩ ያወጣል። እስቲ የኛ የአገራችን የአትሌቲክስ ውጤት እንዲሁም ክብረወሰኖች ምን ያህል ከአህጉሩ ውጤቶች ጋር ይነፃፀራሉ? ከተቀመጠው ሚኒማ በስንቱ በልጠን እንገኛለን? በስንቱስ የሜዳ ተግባራት ሚኒማ እናሟላለን? በመጨረሻም በስንቱ ሚኒማ ሳናሟላ እንቀራለን?
በአብዛኛቹ የሜዳ ተግባራት ሚኒማ ማሟላት ያልቻለ አትሌቲክሳችን፡- በውድድር ለመሳተፍ ሚኒማ በ ኤ/A እና በ ቢ/B ይመደባል። የኤው/A ከፍተኛ ደረጃ ላላቸው ስፖርተኞች የተቀመጠ መስፈርት የቢው/B ደግሞ ተስፋ ላላቸው ወጣት ተወዳዳሪዎች እድል እንዲያገኙ የተቀመጠ መርህ ነው።
ኢትዮጵያ በወንዶች በ100-200-110 እና 400 ሜትር (ሜ) መሰናክል- በአራቱም ውርወራዎች ፣በአራቱም ዝላዮች፣ የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፕዮና ውድድር ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ አንዴም ሚኒማ ማሟላት አልቻለችም። በ100 ሜ ሚኒማው ከ10፡ 20 እስከ 10፡44 ሴኮንድ (ሴ) ሲሆን፣ የአገራችን ክብረ ወሰን 10፡61 ነው፤ በ200 ሜ ሚኒማው ከ21፡00 እስከ 21፡24 /ሴ/ ሲሆን፣ ከፍተኛ የአገራችን ውጤት 21፡74 /ሴ/ ነው።
የ400 ሜ ሚኒማ ከ46፡5 እስከ 46፡ 64 ሴ ሲሆን፣ አንድ ጊዜ ብቻ የአገራች አትሌት 45፡97 /ሴ/ ገብቶ ፍጻሜ ደርሷል። ለ110 ሜ መሰናክል የተቀመጠው ሚኒማ ከ14፡00 እስከ 14፡24 /ሴ/ ነው፤ አገራችንን ወክሎ የተወዳደረው ያመጣው ከፍተኛ ውጤት 14፡73 ሴ ነው።
በርዝመት ዝላይ ሚኒማ 7.80 ሜ ነው፤ የአገራችን ተወዳዳሪ ከፍተኛ የተባለው ውጤት 7.58 ሜ ነው። የስሉስ ዝላይ ሚኒማ 16 ሜ ሲሆን፣ የአገራችን ወኪል 15.50 ሜ ነው መዝለል የቻለው። በአሎሎ ውርወራ ሚኒማው 16.80 ሜ ሲሆን፣ የአገራችን ተወዳዳሪ 15.18 ሜ ነው መወርወር የቻለው። በጦር ውርወራ ለመሳተፍ የተቀመጠው ሚኒማ 69 ሜ ነው፤ የአገራችን አትሌት ከፍተኛ ውጤት 65.87 ሜ ነው። የዲስከስ ውርወራ ሚኒማ 53 ሜ ሲሆን፣ የአገራችን ተወዳዳሪ 44.26 ሜ ነው መወርወር የቻለው።
እነዚህን ሁሉ ውጤቶች ስንመረምር የሚያሳየን ከረጅም ሩጫ በስተቀር የአገራችን አትሌቲክስ የአህጉሩን መለስተኛ የመወዳደሪያ መስፈርት/ሚኒማ ማሟላት ያልቻለ እንደሆነ በግልጽ ያመለክታል። ከ400 ሜ በስተቀር በሁሉም አጭር ሩጫዎች ግማሽፍ ፍጻሜ ያለፈ አንድም አትሌት የለንም።
ዝላዮቹን ስንገመግም ከርዝመት ዝላይ በስተቀር በሌሎቹ ውድድሮች ውጤቶቻችን በጣም ከሚኒማ የራቁ እንደሆኑ ያመለክታል። ውርወራም እንደዝላይ ውድድሮች ተመሳሳይ ገፅታ ያሳያል። በአጭር ሩጫዎች፣ ውርወራዎች እና ዝላዮች የአገራችን የአትሌቲክስ ውጤት የተቀመጡትን ሚኒማዎች ልክ እንደማይታለፍ የሒማላያ ተራራ የተደቀነባቸው ይመስላሉ።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22 ቀን 2014 ዓ.ም