እኛ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት የመጣንባቸው መንገዶች ወጣ ገባ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል ታሪክ የማይዘነጋቸው እና ከትውልድ ወደትውልድ ሲሸጋገሩ የመጡ በርካታ የድልና የሥልጣኔ ደማቅ አሻራዎች፤ በሌላ በኩል ደግሞ የዓለም መዘባበቻ ያደረጉን የእርስ በርስ ግጭትና ድህነት እኛን የማይመጥኑና በመንገዳችን ላይ የምናገኛቸው ማንነቶቻችን ናቸው፡፡
በመጀመሪያ ጥንካሬዎቻችንን ስንመለከት አብዛኞቹ ከጥንታዊ የሥልጣኔ አሻራዎቻችን እና ድሎቻችን ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ ዛሬም ድረስ አሻራዎቻቸው ያልጠፉት የቀደምት ሥልጣኔ መገለጫ ቅርሶቻችን በዓለም አደባባይ ስማችን ከፍ ብሎ እንዲታይ አድርገዋል፡፡ የአክሱም፣ ላሊበላ፣ የጎንደር ቤተመንግሥታት፣ የሐረር ግንብ፣ ወዘተ ቅርሶቻችን ዘመን ተሻጋሪ የቀደምት ሥልጣኔ መገለጫዎቻችን ናቸው፡፡ ለብዙ ሺህ ዓመታት የቆየው እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትልቅ ማሳያ የሆነው የገዳ ሥርዓትም ኢትዮጵያ አሁን በለጸግን የሚሉ አገራት የሚመፃደቁበትን ዴሞክራሲ ቀድማ የተገበረች መሆኑን የሚመሰክር እሴት ነው፡፡
የጥቁር ሕዝቦች ሁሉ መመኪያ የሆነው የአድዋ ድልም ኢትዮጵያውያን ለሉዓላዊነታቸውና ለነፃነታቸው ምን ያህል ቀናኢ እንደነበሩ የሚመሰክር የነፃነት ገድላችን ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር ኢትዮጵያ በአፍሪካ ምድር ቅኝ ያልተገዛች አገር መሆኗ ሕዝቦቿ ምን ያህል ስለነጻነታቸው በሕብረት የሚቆሙና ከዚህ የሚያስቀድሙት አንዳችም ታሪክ እንደሌላቸው ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ከመሰረቱ አገራት አንዷ እንድትሆን ያደረጋትም ይኸው ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ያደረጉን በርካታ ጀግኖችንም በጉያዋ አቅፋ የያዘች አገር ናት፡፡ በተለይ በስፖርቱ ዘርፍ በዓለም ላይ ጊዜ የማይሽረው ታሪክ በመስራት ዓለምን ያስደመሙ ስፖርተኞቻችን ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 42 ኪሎ ሜትር በባዶ እግሩ በመሮጥ ነጮችን አስከትሎ የገባው አትሌት አበበ ቢቂላ፤ ማርሽ ቀያሪው ምሩጽ ይፍጠር፣ ማሞ ወልዴ፣ ለበርካታ ጊዜ የዓለምን ሪኮርድ የሰባበረው አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ እና ሌሎች በርካታ ብርቅዬ አትሌቶቻችን ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ስሟ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ በማድረግ በጎ አሻራዎቻችን ከፍ ብለው እንዲታዩ ያደረጉ ናቸው፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብም ቢሆን በዓለም ላይ የነበረንን ጥቁር መጋረጃ በመግለጥ ስማችን በበጎ ጎኑ እንዲነሳ ካደረጉድሎቻችንን መካከል አንዱ ነው፡፡ በርካታ የዓለም ሕዝብ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራሷ አቅም መፈጸም አትችልም የሚል ድምዳሜ በያዙበት ወቅት የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት እነሆ ይህንን ታሪክ ቀይሮ ዛሬ ላይ ብርሃን ሊሰጥ ከጫፍ ደርሷል። የዓለም ማህበረሰብም የነበረውን አቋም እንዲቀይርና እነዚህ ሰዎች የሚናገሩትን ነገር ከመፈጸም የሚያግዳቸው የለም የሚል እውነታን ለዓለም ያሳየን ድላችን ነው፡፡
እነሆ በቅርቡ ያደረግነው 6ኛው አገራዊ ምርጫም በብዙ ጫና ውስጥ ተካሂዶ ምዕራባውያን ከሚመፃደቁበት ዴሞክራሲዊ ምርጫ በተሻለ ሁኔታ በሁሉም ዜጎች ተሳትፎ የተካሄደና ከምርጫው በኋላም ሁሉም የተቀበሉት ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ ምርጫ የኢትዮጵያን ለውጥ ለማይፈልጉ የውጭ እና ጥቂት የውስጥ አፈንጋጮች ባይዋጥም ያለምንም ኮሽታ ተካሂዱ በሰላማዊ መንገድ መንግሥት መመስረት ያስቻለ ድል መሆን ችሏል፡፡ ይህ አዲስ ባህል ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በገዳ ሥርዓት ለዓለም እንዳስተማረች ሁሉ ዛሬም ዘመናዊ የምርጫ ሥርዓትን ለዓለም ማስተማር እንደምትችል ያሳየ ነው፡፡
በአንጻሩ ግን በዓለም ላይ አንገታችንን ዝቅ አድርገን እንድንሄድ ያደረጉን ታሪኮችንም ማስመዝገባችን ሌላኛው የታሪክ ገጽታችን ነው፡፡ ከነዚህ ታሪኮቻችንም ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱት የርስ በርስ ግጭትና አሳፋሪ የድህነት ታሪኮቻችን ናቸው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ጠላት ሲመጣ በአንድ ላይ የመዝመት የሕብረት እና የአንድነት ታሪክ ያለን የመሆናችንን ያህል ርስ በርሳችንም በፈጠርናቸው ችግሮች በርካታ እድሎችን አምክነናል፡፡ ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ የያዘን የልዩነት አባዜና ከዚያ በኋላም እንግሊዞች በዘር ለመከፋፈል በፈጠሯቸው የልዩነት አጥሮች እንዲሁም ለ27 ዓመታት አሸባሪው ሕወሓት በተከለው የመከፋፈል መርዝ ለበርካታ ጊዜያት እርስ በርስ ስንጋጭ ኖረናል፡፡ በተለይ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ጀምሮ ጦርነትና እርስ በርስ መገዳደል የየዕለት ብዙ ዋጋ ሲያሰከፍለን ቆይቷል፡፡ በዚህም በርካታ ዜጎቻችንን አጥተናል፡፡
በሌላ በኩል እኛ እርስ በርሳችን ስንናቆር እና ያለንን ሀብት ለጦርነት ስናባክን ኢኮኖሚያችን ከጊዜ ወደጊዜ እየወደቀ መጥቶ የተፈጥሮ ክስተት መዛባት ታክሎበት ድህነትና ኋላቀርነት መገለጫችን እስኪሆን ድረስ በዓለም አደባባይ መዘባበቻ አድርጎናል፡፡ ይህንን አጋጣሚ ያገኙት የውጭ ጠላቶቻችን የድርቅና የረሃብ ተምሳሌት እስክንባል ድረስ ስማችንን በመዝገበ ቃላት ጭምር እስከማስፈር ደርሰዋል፡፡
ሌሎች ጉዳዮች ሊኖሩ ቢችሉም በአጠቃላይ የነዚህ ሁሉ ችግሮቻችን ምንጮች ደግሞ የብሄራዊ መግባባት ጉድለት ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውን በአንድነት ስንቆም ምን መስራት እንደምንችል በተግባር አሳይተናል፡፡ ድሎቻን የተመዘገቡት በጋራ በመቆማችን ነው፡፡ በጋራ ለመቆም ደግሞ መግባባት የግድ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አሁን የተጀመረው የብሄራዊ መግባባት ሂደት ወሳኝ ይሆናል፡፡ እናም ለጋራ እድገታችንና ብልጽግናችን በጋራ ጉዳዮቻችን ላይ በመግባባት የመስራቱ ሂደት ሊፈጥንና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2014