ህብረተሰቡ የትራንስፖርት ጥገኝነቱን በመቀነስ ጤናውን መጠበቅ አለበት ሲሉ የአዲስ አበባ ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ለሁሉም ቴክኒክ ሀላፊ አቶ አለምነህ ስዩም ገለፁ፡፡
አቶ አለምነህ ይህን ያሉት ‹‹ከመኪና ነፃ መንገድ ለሰው›› በሚል የሚከበረው አራተኛው ከተሸከርካሪ ነፃ እንቅስቃሴ መንገዶች ቀንን በማስመልከት ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ነው፡፡
ማንኛውም ሰው ጤናውን ለመጠበቅ በየቀኑ ለግማሽ ሰአት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ አለበት ያሉት አቶ አለምነህ ህብረተሰቡ በስራና በትምህርት ቦታዎች ላይ እንቅስቃሴ ካለማድረጉ የተነሳ ተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች እየተጋለጠ ነውም ብለዋል፡፡
ለመጀመርያ ጊዜ በአራዳ አካባቢ የመክፈቻ ፕሮግራሙ በመቀጠል ጀሞ ከዚያም ሜክሲኮ የቀጠለውና የፊታችን እሁድ ዳግማዊ ምኒሊክ በተለምዶ ሰንደይይ ማርኬት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የመክፈቻ ፕሮግራሙ የሚካሄደው ከተሸከርካሪ ነፃ እንቅስቃሴ መንገዶች ቀን በየወሩ በእግር ጉዞና በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡
ከተሸከርካሪ ነፃ መንገዶች ቀን ሲከበር በዋናነት ህብረተሰቡ መሳተፍ ብቻ ሳይሆን በባለቤትነት መንፈስም ጭምር በመሆን ዘላቂቱንም እንዲያስቀጥል ጥሪ የቀረበ ሲሆን ፕሮግራሙን የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ| የአዲስ አበባ ሰፖርት ኮሚሽን | የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም የከንቲባ ፅ/ቤት በመተባበር አዘጋጅተውታል፡፡
በዳግማዊት ግርማ