ልጆች እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው? ልጆች ከበፊት ጀምሮ ማንበብ የእውቀት መግቢያ በር፤ የምስጢር ማወቂያ ቁልፍ እንደሆነ ሁልጊዜ እነግራችሁ የለ? አዎ.. ይሄንን እውነት የሚያረጋግጥ ከልጅነቷ ጀምሮ መጽሐፍትን ማንበብ የምትወድ ስታድግ ደግሞ ኢትዮጵያ ሪድስ የሚባል በልጆች ንባብ ዕድገት ላይ ትኩረት አድርጎ የሚሠራው ድርጅት ውስጥ በበጎ ፈቃደኝነት ስታገለግል የቆየች ደራሲ ነፃነት ፈለቀ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የተዘጋጀው «የበሮቹ አድማ» የሚል ስያሜ ያለው የሕፃናት የተረት መጽሐፍ ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም ቀበና በሚገኘው «ኢትዮጵያ ሪድስ» ግቢ አስመርቃለች፡፡
ልጆች አንባቢነት ተሰጥኦን ለይቶ ለማወቅ ከማገዙም በላይ በጠቅለላ እውቀት የተቃኙ በሁሉም በኩል ብቁ ልጆችን ለማፈራት እጅግ በጣም ጠቃሚ ነው። ስለዚህ አንባቢ የነበራችሁ ልጆች ጎበዝ አንባቢ ለመሆን በደንብ መለማመድ፣ አዳዲሶቹ ደግሞ ጥሩ አንባቢ ለመሆን ዛሬ አንድ ብላችሁ መጀመር አለባችሁ።
መጽሐፉ የተመረቀ ዕለት የመጽሐፍ ዳሰሳ፣ መዝሙርና የመጽሐፉ ታሪክ በድራማ መልክ በልጆች የቀረበ ሲሆን ልጆቹ ባቀረቡት ትያትር መጽሐፉ ነፍስ ዘርቶ አፍ አውጥቶ እንዲናገርም አድርገውት ነበር።
ልጆች እናንተን ከልባቸው የሚወዱ ሰዎች የልጆች መጽሐፍትን ቢያዘጋጁም እንዲህ በደመቀ መልኩ የልጆች መጽሐፍ በማስመረቅ ብዙም አልተለመደም ነበር። በመጽሐፍ ምረቃው ዕለት ግን የልጆች ጉዳይ ጉዳዬ ነው ያሉ የዘርፉ ምሁራን፣ ወላጆች፣ ልጆችና ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች አንድ ላይ በመሆን አዝናኝና አስተማሪ ጊዜም አሳልፈው ነበር።
ልጆቹ መዝሙርና መጽሐፉን በትያትር መልክ ሲያቀርቡ ትልልቆቹ ሰዎች ደግሞ በልጆች ንባብ ዕድገት ላይ በወላጆች፣ በባለድርሻ አካላትና በመንግሥት ምን መሠራት አለበት በሚለው ላይ ውይይት አድርገዋል።
ደራሲዋ ነፃነት ፈለቀ በእንግሊዝኛ ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪዋን የያዘች ሲሆን በኢዱኬሽናል ሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪዋን እየተማረች ትገኛለች። በኢትዮጵያ ሪድስ እና በሌሎች ልጆች ላይ በሚሠሩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ላይ በበጎ ፈቃደኝነት መሥራቷ ‹የበሮቹ አድማ› የተሰኘውን የልጆች ተረት መጽሐፍ ለመድረስ እንዳነሳሳት ገልፃለች፡፡ ደራሲዋ ከልጆች ጋር በመዋሏ ለልጆች ተረት ለመፃፍ መነሳሳቷን ተናግራ ከእንግዲህ አንባቢ ልጆች የሚበዙላት ከሆነ ብዙ መጽሐፍትን ልትጽፍ ቃል ገብታለች።
በዕለቱ ገጣሚና ደራሲ ይታገሱ ጌትነት መድረኩን የመራው ሲሆን የልጆች መጽሐፍ በመድረስ የሚታወቁት እማማ ሜሪ ጃፋር በመጽሐፉ ላይ ዳሰሳ አድርገዋል፡፡ የዚህ ዘመን ልጆች ዕድለኛ ናቸው የሚሉት እማማ ሜሪ ጃፋር ‹በእኛ ዘመን በወረቀት ህትመትም ሆነ ውስጡ የሚኖሩ ምስሎችን በዚህ ደረጃ አሳምሮና በጥራት የሚሠራልን አልነበረም፤ አሁን ግን እንዲህ ያማረ መጽሐፍ ለማሳተም መቻሉ የሚያስደስት ሲሆን መጽሐፉ ለልጆች እንዲመጥን ተደርጎ በጥሩ ቃላት ተፅፏል፡፡› ብለዋል፡፡
ልጆች ደራሲም ገጣሚም ዶክተርም መምህርም ጋዜጠኛም በአጠቃላይ ሁሉንም ለመሆን መሠረቱ እውቀት ነው። እውቀት ደግሞ የሚገኘው ብዙ በማንበብ ብዙ በመመርመር ነው፤ ባላችሁበት ዘመን ዓለም የደረሰችበት ሥልጣኔ ጋር እኩል ለመሮጥ በእውቀት በልጣችሁ ተገኙ እሺ….. እወዳችኋለሁ መልካም የትምህርትና የማንበቢያ ጊዜ ይሁንላችሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም