በስፖርት ዓለም የሚገባቸውን ቦታና ትኩረት ካላገኙት መካከል የሚመደቡት ሴቶች፤ ከስፖርተኝነት ባለፈ በሌሎች ስፖርታዊ ኃላፊነቶች ላይ ያላቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ ሊባል የሚችል ነው፡፡ በአብዛኛው የተለመደው ስፖርተኞች ራሳቸውን ከውድድር ዓለም ካገለሉ በኋላ ያላቸውን ልምድ በሥልጠናዎች አካብተው ወደ አሠልጣኝነት ሕይወት መሸጋገር ነው፡፡ በእርግጥ በጊዜ ሂደት መሻሻል እየታየ ቢሆንም አሁንም ድረስ ግን በዚህ ረገድ ያለው የሴት ስፖርተኞች እንቅስቃሴ ደካማ መሆኑ የነባራዊው ዓለም እውነታ ነው፡፡
ለማሳያ ያህልም በተለያዩ ስፖርቶች ያሉ አሠልጣኞችን ብንመለከት የሴት ቡድኖች የሚመሩት በወንድ አሠልጣኞች ነው፡፡ በአንጻራዊነት የተሻሉ ሴት የስፖርት አመራሮች አሉ በሚባልባቸው አካባቢዎችም ቢሆን ሴት አሠልጣኞች የሴት ቡድኖችን እንጂ የወንድ ቡድኖችን ሲመሩ ማየት የተለመደ አይደለም፡፡
ይህን ችግር ሰብረው መውጣት የቻሉ ጥቂቶች ይኑሩ እንጂ በሚጠበቀው ልክ በታላላቅ ውድድሮችና ሊጎች ላይ ግን አይታዩም፡፡ ይህ ሁኔታ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ አደጉ ከሚባሉት ምዕራባውያን አገራት በድህነት ስማቸው እስከሚነሳው የአፍሪካ አገራት ድረስ ተመሳሳይ መሆኑም ይስተዋላል፡፡ በእርግጥ በአንድ ወቅት የኢትዮጵያ የወንዶች ፕሪሚየር ሊግ ብቸኛ ሴት አሠልጣኝ እንደነበረች ማንሳት ተገቢ ነው፡፡
በበዛው ትግል ተፈትነው እጅ ሳይሰጡ ለሌሎች ነጸባራቅ ከሆኑ ጥቂት አሠልጣኞች መካከል እንግሊዛዊቷ ራሄል ያንኪ አንዷ ናት፡፡ ራሄል በአገሪቷ ልምድ ካላቸውና ብቃታቸውም ከተመሰከረላቸው ጥቂት አሠልጣኞች መካከል አንዷ ስትሆን የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሚሰጠውን የአሠልጣኝነት ሥልጠና ‹‹ኤ ላይሰንስ›› ባለቤት ናት፡፡
ባለፉት 15 ዓመታት ለውጦች እየታዩ መሆኑን የምትገልጸው አሠልጣኟ እርሷ ታዳጊ በነበረችበት ወቅት በስፖርቱ ተሳታፊ ለመሆንም ጭምር መሰናክሎችንና አስቸጋሪ ሁኔታዎችን ማለፍ ግዴታ ነበር ትላለች፡፡ ሁኔታውን ስታስታውስም ‹‹ልጅ ሳለሁ እግር ኳስ ለመጫወት ስል ጸጉሬን እቆረጥ ነበር፤ በዚህም ወንድ ስለምመስል ጥያቄ አይነሳብኝም›› ትላለች፡፡ በዚህ ሁኔታ እግር ኳስ ተጫዋች በመሆን ለአርሰናል ሴቶች ክለብ እንዲሁም ለአገሯ ብሔራዊ ቡድን ተሰልፋ ለመጫወት ችላለች፡፡
እ.አ.አ ከ2004 ጀምሮ እግር ኳስ መጫወት አቁማ ወደ አሠልጣኝነት ስትገባም በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሕፃናትን በማሠልጠን ነበር። ይሁንና በወቅቱ ሕፃናቱ በሴት አሠልጣኝ መመራታቸው ጥያቄ ጭሮባቸው ነበር፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር የሚሰጠውን የአሠልጣኝነት ሥልጠና ‹‹ቢ ላይሰንስ›› ከወሰደች በኋላም ባረንት ለተባለው እግር ኳስ ክለብ ከ18 ዓመት በታች የወንዶች ቡድንን ነበር የተረከበችው፡፡ በዚህ ወቅትም የምታሠለጥናቸው ታዳጊዎች በክለብና በብሔራዊ ቡድን ተሳትፎዋ የሚያውቋት በመሆኑ ጥሩ አቀባበልና ቆይታ ነበር የገጠማት፡፡
ይህም ለሴት አሠልጣኞች የሚሰጠው ግምት በሂደት እየተሻሻለ መምጣቱን የሚያሳይ እንደሆነም ትጠቁማለች። ይሁን እንጂ አሁንም ሴቶች ወደ አሠልጣኝነታቸው የመምጣታቸው፤ አሠልጣኝ የሆኑትም ስኬታማነታቸው አጠያያቂ ከመሆን አልዘለለም፡፡ የእግር ኳስ ስፖርት ተወልዶ አድጎባታል በሚባልላት እንግሊዝ ያለውን ሁኔታ በማሳያነት የምታነሳው አሠልጣኟ በሁለት የሴት ዲቪዚዮኖች ከሚገኙ 20 አሠልጣኞች ሴቶቹ አምስት ብቻ ናቸው፡፡ ይህም በወንዶቹ ቡድኖች ለሚኖረው የሴት አሠልጣኞች ተሳትፎ አስረጂ ነው፡፡
ይህንን ሁኔታ ለማለፍ የሚያስፈልገው ደግሞ፤ ሴት አሠልጣኞች በቂ ልምድ፣ የአሠልጣኝነት ፈቃድ እንዲሁም ጠንካራ ሠራተኝነት ናቸው፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሁሉ ያሟሉ አሠልጣኞች በጾታቸው ምክንያት ከተለያዩ አካላት ሥራ ይነፈጋሉ፡፡ ይህ አመለካከት የሚቀየር ከሆነ ግን የወደፊቱ ሁኔታ መልካም ሊባል የሚችል መሆኑን ነው ራሄል የምትጠቁመው፡፡ በተለይ ብቃት ያላቸው እግር ኳስ ተጫዋቾች በቀጣይ ወደ አሠልጣኝነት ቢገቡና ራሳቸውንም በአሠልጣኝነት ቢያጎለብቱ በስፖርቱ ያለውን ሁኔታ አንድ እርምጃ ማራመድ እንደሚቻልም እምነቷ ነው፡፡
ከሴት ቡድኖች አሠልጣኝነት ባለፈ የወንድ ቡድኖችንም ለመምራት ደግሞ ስኬታማነት ቁልፍ መሣሪያ ነው፡፡ ምክንያቱም ምርጥ አሠልጣኝነት ሊዳኝ የሚችለው በውጤታማነት በመሆኑ ወንድ አሠልጣኞች ጭምር ከስፖርት ቤተሰቡ የሚደርስባቸውን ጫና መቋቋም የግድ ይላል፡፡ ይህንንም በማሳካት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከሚታዩና ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ አሠልጣኞች አንዷ ለመሆን ዘወትር የምትታትረዋ ራሄል፤ እርሷን መሰል አሠልጣኞችም በብርታት መጪውን ትውልድ ይቀርጹ ዘንድ ጥሪዋን ታቀርባለች፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም