ሕይወት ብርቱ ሰልፍ ናት፤ በድካም፣ በልፋት በውጣ ውረድ የተሞላች። በሌላ በኩል ብርሃን፣ ፈንጠዝያ ያለባትም ትሆናለች፡፡ ለበጎም ይሁን ለመጥፎ ተራችንን እየጠበቅን የምንኖርባት የዚህ ምድር ስጦታችን በመሆኗም ፊትና ኋላ ሆነን የምንቆምባትም ነች፡፡ ስለዚህም ጉዟችን የተዘበራረቀባት አንዴ የሚመሽባት ሌላ ጊዜ የሚነጋባትም ነች፡፡ በአጠቃላይ በሕይወት ገጽታችን ሰልፈኛ እንደሆንን የምናስብባት ነች፡፡ ስለዚህ እንደሰልፋችን ሁኔታ ትቀያየራለች፡፡ የተስተካከለ ሰልፍ ላይ ከገባን ስኬትን ካልገባን ደግሞ ምሬትን ታቀምሰናለች።
ሕይወት በመልካምነት ቀመር የተሠራ ነው። ለሌሎች መኖርና መሞትም ነው፡፡ በተለይም መልካሙን ብቻ የምንገነባባት ከሆነች ሞተን ጭምር እንድናሸንፍ ታደርገናለች፡፡ ምክንያቱም በጉዟችን ወደፊት እንጂ ወደኋላ የሚጎትተን አይኖርም። የሚጠቅመንም ሆነ የሚጠብቀን ብዙ ነው፡፡ ለሚጠቅመን እንጂ ለማያስፈልገን አንደክምም። ስለዚህ የእኛን ብቻ ሳይሆን የሌሎችንም ብርሃን እያበራን እንቀጥልባታለን። በመኖራችን ውስጥ ሌሎች እንዲኖሩ እንፈቅዳለን። ለዚህ ደግሞ አብነት የሚሆኑ ብዙ ናቸው፡፡ ከእነዚህ መካከል ለዛሬ የ«ሕይወት ገፅታ» አምድ እንግዳችን ያደረግናቸው አቶ ሙሉቀን ተካ አንዱ ሲሆኑ፤ የሕይወት ውጣ ውረዳቸውና ለሰዎች ያላቸው አክብሮት ብዙዎችን የሚያስተምር ነው፡፡ እናም ከተሞክሯቸው ብዙ ልምድን ትቃርሙ ዘንድ ጋበዝናቸው፡፡ መልካም ንባብ!
ጎሽ ለእናቷ ስትል
ብዙ ጊዜ ተረቶች በመልካም መልኩ ሲነሱ በአባትና በእናት ይመሰላሉ፡፡ አንዳንዴ በልጅም የሚወሳበት መንገድ ሊኖር ይገባል በማለት ለልጇ የሚለውን ለእናቷ በሚል ቀይረነዋል፡፡ ምክንያም አቶ ሙሉቀን ለእናታቸው ሲሉ ያልከፈሉት መሰዋዕትነት የለም፡፡ ይህም የሚጀምረው ልጅነታቸው ላይ ነው፡፡ 12 ዓመታቸው ላይ አባት ውትድርና በመሄዳቸው የተነሳ ቤተሰቡን ማስተዳደር የእርሳቸው ኃላፊነት ሆኖ ነበር፡፡
አቶ ሙሉቀን የቤቱ የበኩር ልጅ በመሆናቸው ከእርሻው ባሻገር ከብት ማገዱና ሌሎች የገቢ ምንጮችን ማፈላለግ ግዳቸው ነው፡፡ በተለይም ቤተሰቡ እንዳይራብ ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉት በቀን ሦስት ብር እየተከፈላቸው የቀን ሥራ የሚሠሩት የማይረሳ ትዝታቸው ነው፡፡ በአልጠነከረ ጉልበታቸው ጥልቅ ጉድጓድ ይቆፍራሉ፤ የትርፍ ሰዓት ብለው ለአንድ ብር ጭማሪ እስከምሽት ሦስት ሰዓት በፓውዛ ይለፋሉ፡፡ ከዚያ 50 ደቂቃ በጭለማ ተጉዘው ነው ቤታቸው የሚደርሱት፡፡ ለቤተሰቡ የሚበላ ገዝተው እየሄዱ እርሳቸው ግን ጦማቸውን ውለው ጦማቸውን ያደሩበት ጊዜም እንደነበር ያስታውሳሉ። የእናታቸው ነገር ከምንም በላይ የሚያሳስባቸው ባለታሪካችን፤ ለራሳቸው ሳያስቡ ጭምር የመዋላቸው ምስጢር እርሳቸው እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡
የተወለዱት በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ጎዛመን ወረዳ ገራሞ ደንደራም ቀበሌ ገበሬ ማህበር ሲሆን፤ በዚህ ቦታ ብዙውን የልጅነት ጊዜያቸውን አሳልፈዋል። ይሁንና የልጅነት ሕይወታቸው ሁለት መልክ ያለው ነበር። የመጀመሪያው ፈንጠዝያ የሞላበት ሲሆን፤ እስከ 12 ዓመታቸው ድረስ ያለው ነው፡፡ ቤቱ ሙሉ፣ ጎተራው ከራስ አልፎ የሌሎችን ጉሮሮ የሚደፍንበት ጊዜ ነበር፡፡ በዚህም ተሞላቀውና የፈለጉት ነገር እየተሟላላቸው እንዲያድጉ ሆነዋል፡፡ ከልጆች ጋርም እንደፈለጋቸው ተጫውተዋል፡፡ እኩል ትምህርትቤት ሄደው ተምረዋልም፡፡ እንደሌላው ልጅ በግ ላግድ ፣ እርሻ ልረስን አያስቡም፡፡ ምክንያቱም እረኛና አራሽ ተቀጥሮ ይሠራል፡፡ አባት ዘመቻ ሲሄዱ ግን ይህ ነገር ሙሉ ለሙሉ ተቀየረ፡፡ ሁለተኛው የልጅነታቸው ገፅታ መራራው ጊዜ የመጣውም ከዚህ በኋላ ነው፡፡
ልጅ መባሉ የቆመበትና እንደ አባወራ ቤተሰቡን የሚያስተዳድሩበት ጊዜ ይህ ሆነ፡፡ በዚህም እንደልጅ መቦረቁ ቀረና ቀጥታ ወደ ባሬላ መሸከምና ቁፋሮ ተዛወረ። ይህንን ሕይወት ከዚህ ቀደም አያውቁትም፡፡ ግን ምንም ማድረግ አይችሉምና ተጋፈጡት፡፡ ነገሮች ከአቅማቸው በላይ ቢሆንም እየመረራቸው ተጋቱት፡፡ ምክንያቱም እርሳቸው ካልሠሩ ማዳበሪያ መግዛት አይኖርም፡፡ ቤተሰቡም ወደረሀብ ጎዳና ያመራል፡፡ እናም የሥራ ምርጫ ሳይኖረው ቤተሰቡን ለማትረፍ ከአቅማቸው በላይ ረሀብን፤ እልህ አስጨራሽ ፈተናን ተጋፈጡ፡፡
ትምህርታቸውን ሳይቀር መስዋዕት አድርገው ቤተሰቡን አባታቸው መጥተው ሳይቀር አስተዳደሩ። ይህ ኃላፊነታቸው ከቀን ሥራው ሳይላቀቁ በዚያው በቀያቸው ሆነው እስከ 18 ዓመታቸው የቀጠለ እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ ስለዚህም እርሳቸው ልጅነታቸውን የሚያስታውሱት ለቤተሰባቸው ሲኖሩ ብቻ ነው፡፡ በተለይ ከእናታቸው ፊት መጥቆርና የፈተና ትግል ጋር በተያያዘ በጭንቀት የሚያሳልፉት ጊዜ ቀላል እንዳልነበረ ያነሳሉ፡፡
‹‹እናቴ የፈተናም፣ የድልም፣ የስኬትም ምንጬ ናት›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ እርሳቸውን ሲያግዙ ለሴት ተብሎ የተለየውን ሥራ ጭምር በመሥራት ነው። በተለይም የገብስ አገር በመሆኑ እናቶች ገብሱን በእጅ ፈጭተው ስለሚያዘጋጁ ያ እንዳይሆን ገብስ ይወቅጡ ነበር፡፡ ከገበያ ሲመጡ ደግሞ ቡና ማፍላትና ሽሮ ሠርቶ መጠበቅ ዋነኛ ተግባራቸው ነው። ከሁሉም በላይ የገቢ ምንጫቸውን ለማሳደግም ዶሮ አርብተው ከመሸጥ ጀምሮ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን ያከናውናሉም፡፡ ከብት አደልቦ መሸጥንም በልጅነታቸው ያውቁታል፡፡ ሳህን ገዝተው፣ የእጅ ሥራ ሠርተው ሎተሪ በማዞር መሸጥንም ልጅነታቸው ላይ የጀመሩት ነበር። እናም እንዲህ እንዲህ እያሉ ነው የልጅነት ጣዕሙን ሳይረዱት ጊዜያቸው ወደወጣትነቱ የተሻገረው። ግን የማይቆጫቸውን ነገር እንዳደረጉበት ይሰማቸዋል፡፡ ይህም ቤተሰብ ማስተዳደርን፣ ሥራ ወዳድነትን፣ በሰዎች መወደድን ተምረውበት አልፈዋል፡፡
የሚቀናበት ግን ያልተሳካው ትምህርት
ከትምህርት ጋር የተገናኙት በዚያው በትውልድ ቀያቸው በገራሞ ደንደራም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቤት ሲሆን፤ እስከ ስድስተኛ ክፍል ተምረውበታል፡፡ ከስድስት በኋላ ግን በዚያው መቀጠል አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም ቤተሰቡን የማስተዳደር ኃላፊነት በእርሳቸው ጫንቃ ላይ አረፈ፡፡ እናም ዳግም ከትምህርት ጋር የተገናኙት ከዓመታት በኋላ አዲስ አበባ ሲመጡ ነው፡፡ ይህም ቢሆን ብዙ ፈተና ነበረበት፡፡
ተቀጥረው ጠጅ ቤት ሥራው ማታ በመሆኑ በቀኑ ክፍለጊዜ የሚማሩበት ሲሆን፤ ትምህርት ቤት ሲገቡ ከእንቅልፉ በላይ ረሀቡና ንፅህናቸው ያሳስባቸው ነበር። እስከ ሌሊቱ ሰባት ሰዓት በሥራ አሳልፈው ሦስት ሰዓት እንኳን ሳይተኙ ይነሳሉ፡፡ ምክንያቱም ትምህርት ላይ ስለሚያሳልፉ ከመሄዳቸው በፊት የሚሠሩት ሥራ አለባቸው፡፡ ዐሥር ሰዓት ተነስተው የትምህርት ሰዓት እስኪደርስ ድረስ ቤት ከማጽዳት ጀምሮ ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችን ያከናውናሉ፡፡ በድካም መንፈስም ወደ ትምህርትቤት ይሄዳሉ፡፡ ነገር ግን ይህም ሆኖ ጎበዝና ተሸላሚ ተማሪ እንደነበሩ አይረሱትም፡፡
ሰባተኛ ክፍል መጨረሻ አካባቢ ባለቤታቸውን ያገኙት አቶ ሙሉቀን፤ ስምንተኛ ክፍልን እስኪጨርሱ ድረስ በእርሷ እገዛ ነበር የተማሩት፡፡ የመጀመሪያ ልጃቸውን እንኳን ወልደው አላቆሙም ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ሁለተኛዋ ስትደገምና ወንድማቸውንና የአክስታቸውን ልጆችም ማስተማር ሲጀምሩ ኑሮ ከበዳቸው፡፡ ባለቤታቸው ልጅ ወደማሳደጉ ስለገቡ ብቻቸውን ቤቱን መደጎም ከትምህርት ጋር አልተቻላቸውምም፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ሁለተኛ ልጃቸው በጽኑ ታመመች፡፡ እርሷን ለማሳከም ደግሞ የጋብቻ ቀለበታቸውን እስከመሸጥ ድረስ ደርሰው እንደነበር አይረሱትም፡፡ ስለዚህም ይህንን ሁሉ ጉሮሮ ለመድፈን ታትረው መሥራት ግዴታቸው ሆነ፡፡ እናም የሚወዱትን ትምህርት ዳግመኛ ለቤተሰባቸው ሲሉ ለማቆም ፈረዱበት፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ ዛሬ ድረስ ያሳምማቸዋል። ያስቆጫቸዋልም፡፡
ስለትምህርት ሲናገሩም ‹‹እኔ በሀብትና ንብረት፣ በመኪናና መሰል የቅንጦት ነገር አልቀናም፡፡ የምቀናው በተማረ ሰው ብቻ ነው፡፡ ፕሮፌሰር፣ ዶክተር የሚሉ ነገሮችን ስሰማ በጣም በእነርሱ መንፈሳዊ ቅናት ይይዘኛል። ቤተሰቦቼ ጭምር ሲመረቁ ደስ ቢለኝም እኔም እዚህ ላይ ብደርስ ብዬ እመኛለሁ፡፡ ነገር ግን የሕይወት ዕድሉ ይህንን አልሰጠኝም›› ይላሉ፡፡ አሁን በርቀት አለ ለምን አትማሩም ላልናቸው ጥያቄም ‹‹ብችል ደስ ይለኛል፡፡ ነገር ግን ቆይቶ መማር የበለጠ ያመኛል ብዬ እፈራለሁ፡፡ ምክንያቱም የማይገባው መባልን አልፈልግም፡፡ በዚህም መማርን አላሰብኩም፡፡ ይሁን እንጂ ለሚማር ሰው ሁሌ እጄን ከመዘርጋት ወደኋላ አልልም›› ብለውናል፡፡
ሥራን በ12 ዓመት
የመጀመሪያ ሥራቸው በዚያው በትውልድ ቀያቸው የጀመሩት የቀን ሥራ ሲሆን፤ ቤተሰቡን ለማኖር በሚል በ12 ዓመታቸው በቀን ሦስት ብር እየተከፈላቸው የጀመሩት ነው፡፡ ሥራው በአንድ ኮንስትራክሽን ድርጅት ውስጥ ሲሆን፤ ዋና ተግባራቸው ጉድጓድ መቆፈርና መሙላት ነው። በዚህም ከስድስት ዓመት በላይ በቦታው አገልግለዋል፡፡ ከዚያ የሚያርሱበት በሬ አለመኖሩን ሲመለከቱና ነገሮች ለእርሳቸው ብቻ ሳይሆን ለቤተሰቡም ከባድ እንደሆነ ሲረዱ በቤተሰብ ጫንቃ ላይ መሆን የለብኝም በማለት ለመራቅ ወሰኑ፡፡ ሆኖም እናትም ሆኑ አባት ከሥራቸው እንዲለዩዋቸው አልፈለጉም፡፡ ስለዚህም በዚያው አግብተው እንዲኖሩ ነገሮችን ማመቻቸት ጀመሩ፡፡
የሚያገቧት ሴት መረጣና ለቤት መሥሪያ የሚሆኑ ነገሮች ተመቻቹ፡፡ ነገር ግን የጦርነት ግዳጅ መምጣቱ ተሰማ፡፡ በዚህ ጊዜ አባት የጦርነትን አስከፊነት ስላዩ እንዲዘምቱ አልፈለጉም፡፡ በዚህም ከጎኔ ሁን የሚለውን ተዉና ተሸሸግ አሏቸው፡፡ ወደ እህታቸው ጋር አዲስ አበባ ላኳቸውም፡፡ ሆኖም አክስታቸው ከቤተሰቦቻቸው የሚለይ ሕይወት አይደለምና የሚኖሩት ብዙም ሳይቆዩ ነው ከእርሳቸው ጋር የወጡት፡፡
እንግዳችን የገጠር ልጅ በመሆናቸው ምግብ እንኳን ስጡኝን አያውቁም፡፡ በዚህም አጠራቅመው የሰጧቸውን ገንዘብ ለመቀበልና ሥራ ለመጀመር ይፈሩ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ሥራ ሳይዙ በብዙ ፈተና ውስጥ እንዲያልፉ አድርጓቸዋል። ጠዋት ቁርስ ሳይበሉ ወጥተው ሲዞሩ እንዲውሉ ጭምር ጫና ፈጥሮባቸዋል፡፡ በተለይ ለደላላ 10 ብር ከፍለው ሥራ ለመቀጠር አለመቻላቸው ብዙ እንዳንገላታቸው አይረሱትም፡፡
‹‹አዲስ አበባ ላይ እንጀራ ማንም ሰው ይቸገራል፡፡ እኔ ግን አዲስ አበባ ላይ ውሃ ተቸግሬያለሁ›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ፍራቻቸው ከዚህም በላይ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ያነሳሉ፡፡ ለሁለት ወር ያህልም በስቃዩ ውስጥ የቆዩት ለዚህ ነው። ከዚያ ስቃዩ ሲበረታባቸው ወደአገራቸው ለመመለስ ወሰኑ። ይህም ቢሆን የአክስታቸውን ፈቃድ አላገኘም። እናም ለመቀጠርም ወደ አገርቤት ለመሄድም ዕድል ያላገኙት እንግዳችን በእግር መሄድ እንዳለባቸው አምነው ከቤት እንደወጡ ያስታውሳሉ፡፡
ጉዟቸው የቀና ይሆንላቸው ዘንድ ወደ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ሄደው ለአምላካቸው ጸሎት ካደረጉ በኋላ ግን ውጥናቸው በሌላ ተቀየረ፡፡ ይህም የሆነው በአገራቸው የሚያውቁት ነጋዴን በማግኘታቸው ነው። ነጋዴው አቶ ጥላሁን ብርሃኑ ይባላሉ፡፡ ባስ ውስጥ ሲሳፈር አይተውት ተከትለው ተሳፍረው በማናገራቸውና ችግራቸውን እንዲያውቀው በማድረጋቸውም ነገሮች ለጊዜው ቦታ መያዝ ጀመሩ፡፡ በጊዜው የእርሳቸውን ብሶት የራሳቸው ከማድረግም በላይ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ እንዲጀምሩ አድርገዋቸዋልና የሁልጊዜ ባለውለታዬ ናቸው፡፡
አመሰግናቸዋለሁም ይላሉ፡፡
እንግዳችን በጣም ብርቱ፣ የሰው ሀቅ የማይወዱ፣ ቃል አክባሪ ናቸው፡፡ በዚህም እንደ አቶ ጥላሁን ዓይነት የአካባቢያቸው ነዋሪዎች የአሏቸውን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም፡፡ ሠርቶ ይመልሳል ብለውም ያምኗቸዋል። ያበድሯቸዋልም፡፡ ይሁንና ለአቶ ጥላሁን 18 ብር አበድረኝና አገሬ ልግባ የሚለው ጥያቄ አልተዋጠላቸውም፡፡ እዚያ ከሚሄድ እዚህ ቢሠራ በሕይወቱ ለውጥ ያመጣል ብሎ ያምናሉና ሊሰጧቸው አልወደዱም፡፡ ከዚያ ይልቅ የሚንከባከበውና የሚያሠራቸው ሰው ቢያገኙላቸው ደስተኛ ይሆናሉ፡፡ በዚህም የማር ደንበኛቸው ከሆኑት ከወይዘሮ ጦቢዬ ጋር አስተዋወቋቸው፡፡
ጦቢያ የሚባል ጠጅ ቤት ባለቤት የሆኑት ወይዘሮ ጦቢዬም አቶ ሙሉቀንን ሲያዩዋቸው ገና ነው የወደዷቸው፡፡ ወዲያውም እርሳቸው ጋር እንዲሰሩ ያባብሏቸው ጀመር፡፡ በተለይ አቶ ጥላሁን ስለማንነታቸው ሲያብራሩላቸው ሊለቋቸው አልፈለጉም፡፡ እርሳቸው ግን ስቃዩ ስለበረታባቸው ወይ ፍንክች የአባ ቢለዋ ልጅ አሉ። የሁለቱ ጉትጎታና ተማጽኖ ሲበዛባቸው ግን እንቢ ማለትን ፈርተው በግድም ቢሆን እሺ ወደማለቱ ገቡ፡፡ በጠጅቤት በአስተናጋጅነት ተቀጥረውም መሥራታቸውን ቀጠሉ፡፡
በጠጅ ቤቱ ብቻቸውን ትልቅ አዳራሽ ሙሉ ሰው ያስተናግዳሉ፤ ሲመሽ ደግሞ መቀመጫ ድንጋዩን ያጥባሉ። እዚያው ላይ ተኝተው ዐሥር ሰዓት ተነስተው ሰም ወንበሩን ይቀባሉ፡፡ በአጠቃላይ በቀን ውስጥ 18 ሰዓት እየሰሩ ብዙ ሺህ ብር ያስገባሉ፡፡ ነገር ግን የሚከፈላቸው 30 ብር ብቻ ነው፡፡ ለያውም በቂ ምግብ ሳያገኙ፡፡ የሥራ ጫናው ከአቅማቸው በላይ እየሆነ ሲመጣ ግን መተው እንዳለባቸው አመኑ፡፡ ከጠጅ ቤቱ ወጥተው አዲስ አበባን በደንብ እያወቋት ስለመጡ በተለያዩ ሆቴሎች ውስጥ በአስተናጋጅነት እንዲሠሩ ሆኑ፡፡ ከአንዱ አንዱ ጋር ሲቀይሩም ቢሆን በውድድር ነበር፡፡ በብር ልዩነት እንጂ ተጣልተው ወይም የተለየ ባህሪ ኖሯቸው የለቀቁበት ሆቴልም አልነበረም፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉም የሆቴል ባለቤቶች ዛሬ ድረስ ወዳጃቸው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ የዳሯቸው ጭምር እነርሱ እንደሆኑ አጫውተውናል፡፡
ከሦስት ዓመት የሆቴል አስተናጋጅነት በኋላ ደግሞ ራሳቸውን ጠይቀው በራሳቸው ለመሥራት ወሰኑ፡፡ ነገር ግን ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ገንዘብ አልነበራቸውም። ስለዚህም ሥራቸው መሆን ያለበት የቀን ሥራ እንደሆነ አመኑ፡፡ ምክንያቱም በቀን ሥራ አናጺ መሆን ይቻላል ብለው ያምናሉ፡፡ እናም እንደአሰቡት ወደ ተግባር ገቡበት። ግን የጠበቁትን አላገኙም፡፡ በሆቴል ውስጥ ይሠራ የነበረ እጃቸው የአርማታ ሥራ ሲሆንበት ከበደው፡፡ መፈንዳት ብቻ ሳይሆን በሁሉም ጣቶች መካከል ደም ያጎርፍ ጀመር። ስለዚህ ይህ ሊሆንልኝ አልቻለም ብለው ሌላ እቅድ ወደማውጣቱ ገቡ፡፡
ጀብሎ ማዞሩ የተሻለ ሥራ እንደሆነ ያመኑት አቶ ሙሉቀን፤ 50 ብር ነበረቻቸውና በእርሷ ሶፍትና ማስቲካን የመሳሰሉ ቀለል ያሉ ነገሮች በመግዛት ጀመሩት። በእርግጥ ይህም ቢሆን የት እንደሚሸጥ አያውቁም ነበር። እናም በእግራቸው ከካሳንቺስ እስከ ጎተራና ሳርቤት ድረስ ተጉዘው የሚያገኙት ገቢ አናሳ ነበር፡፡ በዚህም ምሳ ብቻ እየበሉ ጊዜውን ያሳልፋሉ፡፡ ከብዙ ትግል በኋላ የት ቦታ እንደሚሸጥ ሲረዱ ይህ ችግር ተፈታላቸው፡፡ ከፍ አድርገው አልበም፣ ጡት ማሲያዢያ፣ ካልሲ የመሳሰሉትን ወደመሸጡም የገቡት ከዚህ በኋላ ነው፡፡
አልበም በሚሸጡበት ጊዜ ፀሐይ ላይ እንደማይደረግ የማያውቁት እንግዳችን፤ ደርዘን ሙሉ አልበም መክሰራቸውን አይረሱትም፡፡ ግን ከሁሉም የከፋባቸው ይህንን ሥራ ሲሠሩ የሚያርፉበት ቤት አለመኖራቸው ነው። ስለዚህም ኑሯቸው ጎዳና ላይ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ግንብ ስር ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እያሉ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ለመሳተፍ ተመዘገቡ፡፡ አልፈውም ሽኝት ላይ ነበር ሀሳባቸውን የቀየሩት፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ አሁንም እናታቸው ናቸው፡፡ ብዙ ቤተሰብ እየተላቀሰ ሲሸኝ ሲያዩ እናታቸውን አሰቡ፡፡ ዓይናቸው ጠፍቶ ሲሞቱ በህሊናቸው መጡባቸው፡፡ ስለዚህም መዝመቱን ትተው ጊዜ እስኪያልፍ ያለፋል በማለት የምሽት ቤት ውስጥ በአስተናጋጅነት ገቡ፡፡ ለዓመት ያህልም አገለገሉ፡፡
የሁልጊዜ ተስፋቸው ነገ ይነጋል የሆነው ባለታሪካችን፤ ከጠጅቤቱ የለቀቁት ከባለቤታቸው ጋር የተገናኙበት ጊዜ ስለነበረ ነው፡፡ ምክንያቱም እርሷ ብዙ ነገሮቻቸውን ለውጣላቸዋለች፡፡ ብዙ ችግሮቻቸው ሁሉ ነገሬ ናት በሚሏት ባለቤታቸው ድባቅ ተመትቷል፡፡ እርሳቸውም ቢሆኑ ‹‹መጥቆርን፣ መራብን፣ መጎሳቆልን አይቸዋለሁ፤ ወደፊትም ላየው እችላለሁ፡፡›› የሚል እምነት ስላላቸው በቀላሉ አልወደቁም፡፡ ይልቁንም የሁለት ብርቱ ሰዎች ጥንካሬ በሦስት ሺህ ብር ማር ንግድ መንሰራራትን አምጥቷል፡፡
ከገጠር በሰባትና ስድስት ብር በማስመጣት 12ብር 10 ኪሎ በሁለቱም እጃቸው ይዘው እያዞሩ ይሸጣሉ። ማዞሩ ቢያደክምም ካልጨረሱ ምሳም ሆነ እራትን አያስታውሱትም፡፡ ጠዋት በበሉበት የሚያድሩበት ጊዜም ብዙ ነው፡፡ በተለይም ባለቤታቸው ደከመኝ ሰለቸኝ አለማወቋ ሁልጊዜ ያበረታቸውና ያነቃቸው እንደነበርም ይናገራሉ፡፡ በዚህም ችግራቸው ድል እንደተመታ ያነሳሉ፡፡
ከባለቤታቸው ጋር እያሉ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁት አቶ ሙሉቀን፤ የቤት ኪራይ፣ ቀለብና ሌሎች ነገሮችን ለማሟላት ባለመቻላቸው ኑሮ ከብዷቸው ስደትን መረጡ፡፡ በዚህም ወደ ኳታር በሦስት ሺህ ብር በደላላ አማካኝነት ሄዱ፡፡ አወጣጣቸው በመንጃ ፈቃድ ለሹፍርና በ13 ሺህ ብር በሚል ነበር፡፡ ሆኖም የተባሉትና የሆነው አልተገናኘም፡፡ ቦታውም ቢሆን የጠበቁት አልነበረም። ይህ ደግሞ የነበረባቸውን የኩላሊት ጠጠር የበለጠ የሚያባብሰው ነበር፡፡ ስለዚህም ብዙ ሠርተው ቤተሰቡን መደጎም አልቻሉም፡፡
የሥራ ቦታቸው አስፓልት ላይ የሚፈስ ሩዚን የሚባል ምርት የሚመረትበት ሲሆን፤ ብዙዎችን ለካንሰር በሽታ ያጋለጠ ነው፡፡ በአገሪቱ ሕግም ከሦስት ወር በላይ አይሠራበትም፡፡ ነገር ግን እነርሱን የመሥራት አቅማቸውን ስለሚያውቁ በሌሎች አይዲ ያሠሯቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሦስት ወር ሙሉ ህክምና እያደረጉ ጭምር እንዲሠሩ ያስገደዳቸው ነው፡፡ እንደውም ሕክምና በጀመሩ በሰባተኛው ቀን ሥራ ገብተዋልም፡፡ ሥራው ከመክበዱም በላይ ሽንት መቋጠር ስለማይችሉ ካቴተር ተገጥሞላቸው ጀሪካ በአንድ እጃቸው ይዘው መሥራታቸው ዛሬ ድረስ ሲያነሱት እንባቸው ይመጣል፡፡
‹‹እግዚአብሔር ይማርህ በሌለበት ንጹህ ደም እየፈሰሰ መሥራት ለማንም የማልመኘው ነው›› የሚሉት አቶ ሙሉቀን፤ ምን ይዤ ልመለስ የሚለው ነገር ያሳስባቸው እንደነበርና አንድ ዓመት ከአራት ወርም በዚህ ሁኔታ እንደሠሩ ያስታውሳሉ፡፡ ይህም ቢሆን ከሰው የተመለሱበት እንደነበር ይናገራሉ፡፡
ከኳታር ሲመለሱ ባለቤታቸው ይልኩላት የነበረውን ምንም ሳትነካ አጠራቅማ ጠብቃቸው ነበርና 40 ሺህ ብሩን ይዘው ወደ ሲሚንቶ ንግድ የገቡት አቶ ሙሉቀን፤ የባለቤቴ ውለታ ተዘርዝሮ አያልቅም ይላሉ፡፡ ይህንን እንዳልጠበቁም ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱም እርሷ እህትና ወንድሞቻቸውን ብቻ ሳይሆን ልጆቻቸውን ጭምር እያስተማረች ነበር፡፡ ይህንን ሁሉ ወጪ ብቻዋን ትችለዋለች የሚል እምነትም አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን ብርቱዋ ሴት በጥቃቅን ተደራጅተው በአገኙዋት የአርከበ ሱቅ ሁሉንም ምንም ሳይጎልባቸው አኑራቸዋለች፡፡ የአላሰቡትን ሰርፕራይዝም አዘጋጅታላቸዋለች፡፡
ይህ ዕድል የሁለቱንም ሕይወት መቀየር የጀመረበት እንደሆነ የሚናገሩት ባለታሪካችን፤ እርሳቸው የሲሚንቶ ንግዱን ሲያጧጡፉት እርሷ ደግሞ ከሱቁ በተጨማሪ ቡና ጀምራ መሥራቷን ቀጠለች፡፡ ይህም አደገና ምግብ ቤት ከፍተው ገቢያቸውን ማሳደጉን ተያያዙት፡፡ ባዛር ላይ መሳተፍም ጀመሩ፡፡ ይህ ደግሞ እንዲተዋወቁ አገዛቸው። ትንሽ ብር ሲያገኙ መሬት መግዛትና አንድም ባዶውን አለያም ቤት ሠርተው በመሸጥ አቅማቸውን አጎለበቱ፡፡ ገንዘብም ያዙ፡፡
ዕድል ቀናቸውና ከጥቃቅን ወደ መካከለኛ ኢንዱስትሪ የተሻገሩት አቶ ሙሉቀን፤ ሰፊ ቦታ ተሰጣቸው፡፡ ቦታውንም ለፋብሪካ የሚሆን ቤት ያለምንም ብድር ሰርተው አጠናቀቁ። ይህ ሲሆን ደግሞ ቀን ላይ የራሳቸውን ሥራ እየሠሩ ማታና ጠዋት ባለቤታቸውን እያገዙ ነው፡፡ ቤቱ ቢጠናቀቅም ለመሥሪያ የሚሆን ብድር ግን አላገኙም። በዚህም ቦታው ያለሥራ ከሚቀመጥ ብለው ለሕንዶች አከራይተው እየተጠቀሙበት ይገኛሉ፡፡ ከቤት ኪራዩ በተጨማሪ አሁን የሚተዳደሩት የማር ንግድ ሲሆን፤ አራት ማከፋፈያ ሱቆችን ከፍተዋል፡፡ ጎን ለጎን ጠጅ የሚሸጡባቸው ሱቆችም አሉ። በሥራቸው ከ10 በላይ ሠራተኞችን ይዘው እየሠሩም ናቸው።
እንግዳችን ሠራተኞቻቸውን እንደ ልጆቻቸው ነው የሚያዩዋቸው፡፡ እነርሱን ቆመው ሳያበሉ ቁርስም ሆነ ምሳ በአፋቸው አይዞርም፡፡ በየሱቆቹ እየዞሩ የዘወትር ሥራቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ መከታተል ነው። በዚያ ላይ ሥራ ከበዛባቸው ጋወናቸውን አጥልቀው ያግዟቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ሁሉንም በሚባል ደረጃ ሥራ ወዳድ አድርጓቸዋል፡፡ ከዚያም አልፈው ሥራው የእኔ ነው ብለው እንዲሠሩና ለስኬታቸው ምንጭ እንዲሆኑላቸው አግዟቸዋል፡፡ የእናታቸው ጉዳትና ለመሥራት ያላቸው ጉጉት እርሳቸውን ጠንክረው መሥራት እንዲችሉ እንዳደረጋቸው ሁሉ ሠራተኞችም ከችግርና ከቤተሰባቸው ጉዳት ተምረው ጠንካራ ሠራተኛ መሆን እንዳለባቸው ዘወትር ይመክሯቸዋል፤ ኖረውትም ያሳዩዋቸዋል፡፡
የሕይወት ፍልስፍና
ሕይወት መራር ሲሆን ጠንካራ ያደርጋል፣ የልብ መሰበርንም በቀላሉ ለመጠገን ያስችላል፡፡ ከአምላክ ጋር ለመታረቅም መንገድ ይከፍታል፡፡ በተለይም ጠንካራ እምነትን ለመላበስ ብዙ ድካምን አይጠይቅም፡፡ ከዚያ ይልቅ መልካምነትን ይዞ በብርታት ኃይል ለመቦረቅ ዕድል ይሰጣል የሚል ፍልስፍና አላቸው፡፡
ሌላው ፍልስፍናቸው ሕይወት መልካሙን እያዩ ከተራመዱባት በረከትንም ለማግኘት የሚቻልበት መንገድ ትሆናለች ይላሉ፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚያደርጉት መመረቅንና መሥራትን ሲሆን፤ መልካም ያደረገ ይመረቃል፡፡ የሚመረቅ ሰው ደግሞ ይሠራል፡፡ በዚህም በምርቃት የተገነባ ማንነትን ያገኛል የሚለው ነው፡፡ ስለዚህም በእርሳቸው ሕይወት ውስጥ መመረቅና መሥራት እንዲሁም ለሰዎች መኖር ትልቅ ዋጋ የሚሰጣቸው ናቸው፡፡
ብር ሳይሆን እምነት ያበረታው ትዳር
እንግዳችን በአሉበት ሁኔታ መቼም ቢሆን አገባለሁን አስበው አያውቁም፡፡ የዛሬዋን ባለቤታቸውን ተዋውቀዋት እንኳን አብረን እንኖራለንን አያስቡም፡፡ ምክንያቱም ምን ይዤ የሚል ነገር ውስጣቸውን ይፈትናቸዋል፡፡ ነገር ግን ሴት ልጅ ብልሀተኛ ነችና ነገሮችን አስተካከለቻቸው፡፡ እምነተ ጠንካራ መሆኗ ደግሞ የበለጠ ብርታትን ሰጣቸው። ስለዚህም አብሮ መኖሩ ይበልጥ ኃይል እንደሚሆናቸው አምነው ቤት ተከራይተው ትዳርን ሀሁ አሉት፡፡
እርሷ ሰው ቤት ተቀጥራ ትሠራ ነበር፡፡ እርሳቸው ደግሞ ምሽት ቤት፡፡ እናም በባዶ ተነስተው ነው በፍቅር ቤታቸውን የገነቡት፡፡ እንዲያውም አነሳሳቸውን ሲያነሱ ‹‹እርሷ ያጠራቀመችውን ሦስት ሺህ ብር ይዛ እኔ ደግሞ 1200 ብር ጨምሬበት ዋና ዋና የሚሉትን ዕቃዎችን ገዛን፡፡ ከ1200 ብር በላይ መውጣት የለበትም ብላ አብቃቅታ ነው ቀጣዩን ሥራችንን ያቀደችው፡፡ ስለዚህም በእርሷ ሦስት ሺህ ብር የማር ንግዱን እንድንጀምር ሆነናል›› ይላሉ፡፡
አሁን ሁሉ ነገር ተቀይሯል፡፡ ሦስት ልጆችንም አፍርተዋል፡፡ ሁሉም እየተማሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ ግን ሥነምግባር ላይ ከእነርሱ መማር ያለባቸውን ነገር እየነገሩ ነው የሚያሳድጓቸው፡፡ ስለዚህም በእነርሱ ቤት ደስታ ቤተሰብ ሆኖ፣ ደስታ የሰውልጅ ሆኖ ነው የሚኖሩት። ሠራተኛ ልጅ እንጂ የተለየ ሰው ተደርጎም አይወሰድም። ሁሉም ማግኘት ያለባቸውን ፍቅር ይሰጣቸዋል፤ የሚፈልጉት ነገር ይሟላላቸዋል፡፡ ይህንን የሚያደርጉት ደግሞ ግፍ ላለማስቀመጥ ነው፡፡ የእነርሱን ሕይወት ማንም እንዲደግመው አይፈልጉምም፡፡
የሁለቱ ሥራ ወዳድነት ልጆቻቸውን ሰባት ቀን ሙሉ እስከአለማየት ያደርሳቸው ነበር፡፡ ለያውም 300 ሜትር ርቀት በሌለው ቦታ ላይ ሆነው፡፡ በችግር ውስጥ ያለ ሰው ነገውን ለማብራት እልህ አስጨራሽ መሰዋዕትነትን ይከፍላል፡፡ በዚህም ወላጆቻቸው የት ናቸው እየተባለ ሲጠየቅ እንኳን ከሥራቸው ፈቀቅ ሳይሉ ይተጉም ነበር፡፡ ይህንንም እንደ ሥነምግባሩ ሁሉ ልጆቻቸውን ያስተምሯቸዋል፡፡ ብርታታቸው ምን ያህል ስኬታማ እንዳደረጋቸውም ያስረዷቸዋል፡፡ ለሌሎች መኖርን እንዴት እንደጀመሩም በተግባር ጭምር ነው የሚያሳዩዋቸው፡፡ ለዚህ ሁሉ ባለቤታቸው፣ እናትና አባታቸው እንዲሁም ወንድምና እህቶቻቸው እንዳገዟቸውም ይነግሯቸዋል። ለዚህ ስላበቋቸውም እጅግ አድርገው ያመሰግኗቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ከቀደመ ችግራቸው ያወጣቸውን አምላካቸውን ክብር ምስጋና ይግባው ሳይሉም አያልፉም።
መልዕክት
ሰዎች የጎዷቸውንና ያስቀየሟቸውን መበቀልም ሆነ ማዳን የሚችሉት በመግደልና እንዲቸገሩ በማድረግ አይደለም፡፡ በጎ ሠርቶ ህሊናቸውን በመቀየር ነው፡፡ ክፉን መቼም ክፉ ሥራ አይመልሰውም፡፡ እንደሒሳቡ መጠፋፋት ሲችል ብቻ ነው ዜሮ የሚሆነው፡፡ እናም ሰዎችን በመስጠትና በመንከባከብ መመለስ ልምዳችን ይሁን፡፡ መልካምነት ሲበልጥ በበረከት መጎብኘት ይበዛል፤ ብዙ መልካሞችን ማፍራት ይመጣል፡፡ ከሁሉም በላይ አሸናፊነት ያይልና ሰዎች ከችግራቸው ይላቀቃሉ፡፡ አገርም ከመከራ ትድናለች፡፡ ስለሆነም ሰዎች ክፉው እንዲርቅና መልካሙ እንዲገን ማድረግ ላይ መሥራት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ መልካም ማሰብ ብቻ በቂ ነው ይላሉ፡፡
አሁን በአለው አገራዊ ሁኔታ ሰው የሆነ ሁሉ ስለሰው የሚያስብበት ጊዜ ነው፡፡ ሰው ሸክላና ተሰባሪ መሆኑን እያሰበ ለነገ የሚሠራበትም ነው፡፡ በመሆኑም ሀብት ከሁሉም ጋር የሚካፈሉት እንጂ የግል አይደለምና እናጋራው፡፡ በተለይ ልጆቹንና ቤተሰቦቹን የሚወድ ሰው ማድረግ ያለበት ለሌሎች መድረስ ነው፡፡ ምክንያቱም ለደራሽ ደራሽ አለውና ባይ ናቸው፡፡
ሌላው ያነሱት ወጣቱ ላይ ሲሆን፤ ራሱን አክባሪ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ከራስ የጀመረ ክብር ለሌሎችም ይተርፋል ብለው ስለሚያስቡ ነው፡፡ ሱስን እንደሀብት ባይቆጥሩትም ለእነርሱ ሱስ መሆን ያለበት ሥራና ሰው ወዳድነት ነው፡፡ ያን ጊዜ አገርንም ሰውንም ከመከራ ይታደጋሉና ይህንን ልምዳቸው እንዲያደርጉት ይመክራሉ፡፡
‹‹ዝቅ ብሎ መሥራት ከማስገደድ በላይ ያሠራል›› የሚሉት አቶ ሙሉቀን፤ በተለይ ባለሀብቶች ሠራተኞቻቸውን ሲያዙ ራሳቸው አርአያ ሆነው ቢሠሩ ስኬታቸው ቀናት እንጂ ዓመታት አይሆንባቸውም ባይ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ባለንብረቱ ዝቅ ብሎ ሲሠራ ያዬ ሠራተኛ እፍረት ይይዘዋል፤ መቀመጥ ያቅተዋል። ሳይወድ በግድም ይሠራል፡፡ ይህ ነገር ሲደጋገም ደግሞ ሱስ ስለሚሆንበት ሥራ ወዳድ ያደርገዋል፡፡ እናም ሰዎችን ማሠራት የሚቻለው ራስን ማሠራት ሲቻልና መንደላቀቅ ሲቀር ነውና እንደ አገር እዚህ ላይ ሊታሰብበት ይገባል የመጨረሻ መልዕክታቸው ነው፡፡
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም