የትግራይ ሕዝብ እንደ ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ቆም ብሎ በሰከነ መንገድ ላለፉት 50 ዓመታት የመጣባቸውን መንገዶች መመርመር የሚገደድበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ይገኛል። በዚህ ግማሽ ምእተ አመት ባስቆጠረ ዘመን ውስጥ እንደ ሕዝብ ምን አተረፍኩ ፤ምንስ አጣሁ? ብሎ ሊጠይቅና ለጥያቄዎቹም ተገቢውን መልሽ ሊያገኝ ይገባል። ለዚህ የሚሆን ድፍረት መፍጠርም ይጠበቅበታል።
የትግራይ ህዝብ እንደ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የ1960 ሕዝባዊ እንቃስቃሴ አካል ነው። በወቅቱ ተንሰራፍቶ የነበረውን የፊውዳል ስርአት በማስወገድ የተሻለች ሀገር ለመፍጠር በተካሄደው እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም እንደሆነም ይታወቃል። ለዚህም ብዛት ያላቸው የትግራይ የቁርጥ ቀን ልጆች በወቅቱ በነበሩ ብሄራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ ንቁ ተሳታፊ በመሆኑ ብሔራዊ ጭቆናን ከመላው ሀገሪቱ ለማስወገድ ታግለዋል።
ከነዚህ ውስጥ በታሪክ ተጠቃሽ የሆኑትን ታጋይ ተስፋዬ ደበሳይ፣ ብርሀነ መስቀል ረዳ ፣ ዘርኡ ክሕሸን ፣ ክፍሉ ታደሰ ፣ ጸጋዬ /ደብተራው/ መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩና ለመላው ህዝብ ነጻነትና የተሻለ ህይወት ዋጋ ከፍለው ያለፉ የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ከነዚህም ውጪ ብዙ የክልሉ ተወላጆች በወቅቱ በተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች የነበራቸው የነቃ ተሳትፎ እና የከፈሉት ዋጋ ከፍ ያለ ነው።
ብሔራዊ የትግል መነሳሳት ከፍ ባለበት ወቅት የተፈጠረው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ገና ከፍጥረቱ ፣ ከሀገራዊው የትግል መስመር በማፈንገጥ መንደርተኝነትን መርጦ የትግራይን ህዝብ በጠበበና ፍጥረታዊ ማንነቱን /ኢትዮጵያዊነቱን/ አደጋ ውስጥ በሚከት የፖለቲካ መንገድ ለመግራት ብዙ መንገድ ተጉዟል። ይህንኑ እኩይ ተግባሩን ያለሀፍረት በውልደቱ ማግስት ባረቀቀው ማንፌስቶ ውስጥ አካቶ ለአደባባይ አብቅቷል።
በዚህ መንደርተኛ አስተሳሰቡም ኢህአፓንና ኢዲዩን ጨምሮ ሌሎችም በክልሉ ይንቀሳቀሱ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ ግልጽ ጦርነት በማወጅ ለሀገርና ለትግራይ ህዝብ የተሻሉ ነገዎችን ሲመኙ የነበሩ ብዛት ያላቸው የትግራይ ልጆችን ለህልፈት ዳርጓል። ፊውዳል ናቸው በሚል ብዛት ያላቸው አዛውንቶችን ፣ ልጆችቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን አሳድዶ ገድሏል። እስከዛሬም በቡድኑ ታፍነው ተወስደው የት እንደደረሱ ያልታወቁ ቁጥራቸው የትየሌሌ ናቸው።
ቡድኑ በ70ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን በኃይልና በሴራ ካስወገደና ራሱን የትግራይ ህዝብ ብቸኛ ተጠሪ አድርጎ ከሰየመ በኋላ ፣ በውስጡ የተለየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ያላቸውን ግለሰቦች ከማፈንና ከመግደል በዘለለ ምንም ዓይነት ተራማጅ አስተሳሰቦች በድርጅቱ ውስጥ ስፍራ እንዳያገኙ አድርጓል። በዚህም የለየላቸው የአምባገነኖች ስብስብ መሆኑ በተጨባጭ ተመስክሯል።
ስለ ነጻነትና እኩልነት ሲያዜማቸው በነበሩ የአደባባይ መዝሙሮቹ ለትግል የተነቃቁ የትግራይ ወጣቶችን መስዋዕት በማድረግ በ1983 ዓ.ም የማእከላዊ መንግሥቱን ስልጣን ከተቆጣጠረ ጀምሮም ብዙ ለማለለትና ለተገዘተለት የህዝብ ፍላጎት ጆሮውን ዘግቶ በሥልጣን መቆየት በሚችልባቸው የሴራ ተግባራት ፋታ አጥቶ ሲቅበዘበዝ ቆይቷል። በልጆቹ መስዋዕት ለስልጣን ያበቃውን የትግራይ ሕዝብ ሳይቀር አመድ አፋሽ አድርጎታል።
ስለ ነጻነት ፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር በልጆቹ ብዙ ዋጋ የከፈለው የትግራይ ሕዝብ ራሱ ልጆቹ ዋጋ ለከፈሉለት ነጻነት፣ ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ባእድ ሆኖ በገዛ ልጆቹ የመስዋዕትነት ደም በራሱ ላይ አዲስ አምባገነን እንዲሰይም አስገድዶታል።የገዛ ጥላውን እንዲጠራጠር በሚያደርግ የጠበቀ የደህንነት መዋቅር ሰለባ እንዲሆንም አድርጎታል።
ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታትም የትግሉን ሰማዕታትና ቤተሰቦቻቸውን ጭምር ማስታወስ ባልቻለበት የማናለብኝነትና ዘረፋ መንገድ ሲላውዝ የቆየ ሲሆን። በነዚህ ዓመታትም ለትግራይ የመከራና የስቃይ ምንጭ ከመሆን ባለፈ የጨመረለት አንዳች ነገር የለም። ህዝቡ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጋር በፍቅርና በአንድነት እንዳይኖር ተግዳሮት ሆኖበት ቆይቷል።
ቡድኑ በህዝብ ትግል ከስልጣን ተወግዶ መቀሌ ከመሸገ በኋላ የትግራይን ህዝብ ለመጠበቅ ትግራይ ክልል ይገኝ በነበረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የሰነዘረውን የክህደት ጥቃት ተከትሎ በተቀሰቀሰው ጦርነት ከሁሉም በላይ የትግራይን ህዝብ ውድ ዋጋ እንዳስከፈለውና ህይወቱን እንዳመሰቃቀለው ይታወቃል።
የመንግሥትን የተናጠል የተኩስ አቁም ተከትሎ በአፋርና በአማራ ክልሎች ባካሄደው የእብሪት ወረራዎች የትግራይን ወጣት ለዳግም እልቂት ዳርጓል።ቀድሞውንም በብዙ ተግዳሮቶች የተሞላውንና ዕለት ተዕለት ችግሮች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ የሆኑበትን የትግራይ ህዝብ ህይወት የከፋ አደጋ ውስጥ ከትቷል።
ለግማሽ ምእተ አመት ትርጉም አልባ ለሆነ ያልተገባ መስዋዕትነት ልጆቹንና ዘመኑን ሲገብር የኖረው የትግራይ ህዝብ አሁን ነገሮችን ቆም ብሎ እንዲያስብ የሚገደድበት ታሪካዊ ወቅት ላይ ይገኛል። ከአሸባሪው ሕወሓት የሴራ ድምጾች ራሱን አቅቦ ከራሱ ጋር ሊመክር የተገባበት ጊዜ ላይ ደርሷል።
ከአሸባሪው ሕወሓት ጋር በነበረው ጉዞ ስለ ነጻነት ፣ ስለ ዴሞክራሲና ፍትህ በልጆቹ ደም ከከፈለው ዋጋ፣ በድንበር ስም ከተካሄደው አሰቃቂ ጦርነት ፣ ዛሬ ላይ ቡድኑ በለኮሰው ጦርነት ምን እንዳተረፈና እያተረፈ እንደሆነ በአግባቡ ጠይቆ ምላሽ ማግኘት ይኖርበታል።
ከዚህ አሸባሪ ቡድን ጋር በነበረው የግማሽ ምእተ ዓመት ቆይታ ልጆቹ በህይወታቸው ተወራርደው የተመኙለትን የተሻለ ህይወት መኖር በሚችልበት ቁመና ውስጥ ይገኛል፤ ወይስ ከዚህ ሁሉ መስዋእትነትና ዘመናት በኋላ የዕለት ምግቡን ለማግኘት የለጋሾችን እጅ ዛሬም እየጠበቀ ነው፤ ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ማነው?
ነገና ከነገ በስቲያ ደጁን ለሚያጥለቀልቀው የልጆቹ የሞት መርዶስ ራሱን አዘጋጅቷል? ከልጆቹ እልቂት በስተጀርባ ያለውን አሸባሪውን ሕወሓት በኃላፊነት ለመጠየቅ ወገቡን እያሰረ ፣ ስለ ልጆቹ ደም ፍትህ ለማግኘት ከራሱ ጋር እየመከረና ለዚህ የሚሆን ዝግጁነት እና ቁርጠኝነት እየፈጠረ ነው? መልሱ የሱ ነው። ዛሬግን በየዘመኑ ለእልቂት ለተዳረጉ ልጆቹ ዋነኛ ምክንያት የሆነውን አሸባሪውን ሕወሓት በኃላፊነት ለመጠየቅ ወገቡን ጠበቅ አድርጎ ሊነሳ ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም