የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት ተከባብሮ ለዘመናት የኖረ ሕዝብ ነው ሲባል ብዙዎቻችን እንዲሁ በልማድ የሚባል እንጂ በተለይ አሁን ላለው ትውልድ ረብ ያለው አይመስለንም፡፡ ይህንን የኖረ ሀብት የአዛውንቶች ተረት አልያም የፖለቲከኞች ቧልት አድርጎ የሚቆጥረውም አይጠፋም፡፡ እኛ ግን ወድድን ጠላንም ዛሬን መቆም እና እንደ ሕዝብ ህልውናችንን ማስቀጠል የቻልነው በዚህ ዛሬ ላይ ዋጋው በቀለለብን አብሮ የመኖር እሴታችን ነው፡፡
እርግጥ ነው፤ አሸባሪው ሕወሓት መራሹ መንግሥት ላለፉት 27 ዓመታት የዘራብን የልዩነት ሰንኮፍ ዛሬም ዋጋ እያስከፈለን ስለመሆኑ ለማሰብ የሚከብድ አይደለም፤ሰንኮፉም በቶሎ ተነቅሎ እረፍት የሚሰጠን አይመስልም፡፡ አሳራችን መቋጫ አልባ የመሆኑ ምስጢርም የሕገ-አራዊት ሥርዓት ዛሬም እንዲቀጥል የሚናፍቁ ዛሬም በጉያችን ሸሽገናቸው ስለሚገኙ ነው፡፡
ለዚህም ነው ያ ስንጠየፈው የኖርነው ፀረ- ኅብረት እና ፍቅር አስተሳሰብ ኑሯችንን ተጣብቶ ለእርስ በእርስ ግጭቶች ምክንያት እየሆነ ያለው፡፡ ዛሬ ላይ እዚህም እዚያም ‹‹የከሌ ብሔር እከሌን ገደለው፤አቃጠለው፤ ቤት ንረቱን አወደመበት፤ እንዲሰደድ አደረገው›› የሚሉ ዜናዎችን መስማት የቀለለብን ለዚህ ነው። አባዛሽ አትበሉኝና! አንዳንዶቻችን የጥላቻና የልዩነት ወሬዎችን የእለት ጉርስ ከማድረጋችን የተነሳ ጨርሶ ያልሰማነው እለት ቅር የሚለን አንጠፋም፡፡ እንዲያውም የሚያነጫንጨን ስለመኖራችን ደፍሬ መናገር እችላለሁ።
የቀደመው ታሪካችን እንደሚያሳየው ግን በሀገሪቱ የነበሩት መንግሥታት የቱንም ያህል ክፉ ቢሆኑ፤ ከአንድ ብሔርና ሃይማኖት የመጡ ቢሆኑ፤ አገዛዛቸውም ወገንተኛ ነው ተብሎ ቢታሰብ እንኳን ሕዝቡ ግን ለዘመናት በፍቅር እና በእውነተኛ መተሳሰብ አብሮ ኖሯል፡፡ ያ ፍቅራቸውና መታሰባቸውም ስለነበረም ነው ሀገራቸውን ለየትኛውም የውጭ ወራሪ ኃይል አሳልፈው መስጠት ያልቻሉት፡፡ ዛሬ ላይ ግን ያ ሁሉ ተረስቶ የመቻችል እሴት ተሸርሽረው የሀገርን ህልውና አደጋ ውስጥ በሚከት ስጋት ውስጥ ለመኖር እየተገደድን ያለነው፡፡
ትናንት በደስታም ሆነ በሃዘን ሁሉ ከዘመድ ቀድሞ ደራሹ ጎረቤት ነበር። ግና ዛሬ እኛ ቤት ያንኳኳው መከራ እሱ እስከወዲኛው ያልፈው ይመስል በአንዱ ቤት ችግር ላይ ሌላው አጮልቆ ተመልካች እየሆነ ነው።የተጣላን ዋሽቶ አሳታራቂው፤ ያጠፋውን ገስጾና ቀጥቶ የሚመልሰው ያ ቱባ ባህላችን ተመናምኗል፡፡
እንዲህ እንደ አሁኑ በፍቅራችን መሃል ንፋስ ሳንስገባበት በፊት በርካታ ብሔር ብሔረሰቦችና የተለያዩ እምነት ተከታዮች በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባቸው ከተሞቻችን ለአለም ሕዝብ አርዓያ ተብለው ለሽልማት በቅተዋል፡፡ መንደሮቻችን የቱሪዝም መናገሻ ተብለው ለሀገር የገቢ ምንጭ ምክንያንት ሲሆኑ በአይናችን አይተናል፡፡
‹‹ልዩነት ውበት›› በሚለው ትርክታቸው ሸርደደውን አንድ የሚያደርጉን እንቁ ባህሎቻችን በጎርፍ ተጠርገው ሲሄዱ የዳር ተመልካች ሆነናል። በእጅ ያለ ወርቅ እንደሚባለው ሁሉ ያ ለብዙዎች የሚያስቀናው ‹‹አንቺ፤ አንተ ትብስ›› ተባብለን የኖርበት የፍቅራችን ዘመን ላይመለስ የሄደ ያህል ሙቀቱን የምናጣጥመው እሳት ልባችንን እየለበለበው ይገኛል። ትናንት በእኛ መልካም እሴት ሲቀኑብን የኖሩ ባላንጣዎቻችን ዛሬ በሹክቻችን ይሳለቁብን ይዘዋል። እኛው ፈቅደን ባስገባንባቸው የጠብ በር ገብተው ጠባችንን ጮማ ወሬ አድርገውን የመገናኛ ብዙኃኖቻቸው ማድመቂያ አድርገውናል። ሲላቸው አስታራቂ፤ ሳይላቸው ቀጪ አለቃ ሆነው እየቀረቡ ከሀገርነት ወደ መንደርነት የምናደርገውን አስፈሪ ጉዞ ሲያፋጥኑልን እኛም ተመልካች ሆነናል፡፡
ይህ ሁሉ እየሆነ ባለበት ማህበራዊና ፖለቲካዊ አውድ ውስጥ በሀገራችን ህልውና ላይ እየተሴረ ያለውን ሴራ ተረድተንና ነቅተን ዳግም ኅብረታችንን ለመመለስ የየራሳችንን ጠጠር ለመወርወር ወቅቱ አሁን እንደሆነ ይሰማኛል። ለዚህ አብዛኛው ሕዝባችን ፈቃደኛ ቢሆንም ተግዳሮት የሆኑ ስለመኖራቸው ለመናገር የሚከብድ አይደለም።
በረባው ባልረባው የሕዝባችንን አንድነት ለመሸርሸርና የጀመርነውን የመመለስ መንገድ ለማደናቀፍ የሚጥሩ ስለመኖራቸው ለመናገር የሚከብድ። ይህንን ስል ጭፍን ስለሆንክ ሳይሆን ‹‹ብልህ ከሰው ስህተት፤ ሞኝ ከራሱ ይማራል›› ከሚለው ብሄል በመነሳት ነው፡፡ ትናንት የመንና ሶሪያ በእኛው መንገድ ሲጓዙ እና ሲፈራርሱ እያየንና እየሰማን ከንፈር ከመምጠጥ ባለፈ ወደ ራሳችን ለማየት ስላልደፈርን ነው።አባቶቻችን ደምና አጥንታቸውን ማግረው ያቆዩልንን ይህችን ውድ ሀገር በራስ ፍቅር በናወዙ ቡድኖችና ግለሰቦች ተፈትናለች። ከሁሉ በላይ የሚያንገበግበው ደግሞ የሆነው ሆኗል፤ የሞተውና ያጣናው ይበቃል ብሎ ከስህተት ጎዳና ለመመለስ የሚደፍር አለመኖሩ ነው፡፡
አሁን ካለው የገለማ የነጠላትነት ጉዟችን የትንናቱ ኋላ ቀሩ ማንነታችን በስንት ጣዕሙ እንደሚሻል ለመናገር አሁን አስተሳሰቡ በወለደው ችግር እየከፈልን ያለነውን ዋጋ ማየት በራሱ በቂ ነው።ሁላችን ከእኔ ወዲያ ላሳር በሚል ግትር ማንነታችን ተገትረን በእጃችን ያለው ሁሉ አመድ ሆኖ የምናፍሰው ሁሉ አቧራ ሆኖብናል፡፡
‹‹እልፍ ሲሉ እልፍ አለ›› እንደሚባው ዛሬ ላይ ሰንቆ የያዘንን የልዩነት ሰንኮፍ ከውስጣችን ነቅለን መጣል የሚቻለው፤ በቅድሚያ ከሚያጣሉን እና ከሚለያዩን ግትር ማንነታችን እልፍ ስንል ነው። ለእድገታችን ዋነኛ ተግዳሮት ሆኖ የሰለጠኑት መሳለቂያ ያደረገን የርስ በርስ ንትርካችንን ትተን ለሰላማችን የልቦናዎቻችንን በሮች ስንከፍት ነው፡፡
እርግጥ ነው፤ ፍቅርና ሰላም እንዲያው በቃል ብቻ ስለፈለግነው አይመጣም!፡፡ የሚመርና የሚያም ዋጋ መክፈልን ሊጠይቀን ይችላል፡፡ ግን ደግሞ ፍሬው ጣፋጭ መሆኑን መገንዘብ ይገባናል፡፡ ከምን በላይ ደግሞ የሀገራችንን ህልውና የሚያስቀጥል ብሎም የሕዝባችንን አንድነት የሚመልስልን በመሆኑ ወደ ቀደመው እሴታችን እንመለስ፡፡ ለሚበልጠው ጥቅማችን ስንል የልዩነታችን አረም እንቀለው፤ ደንቃራውን ጠባችን በፍቅር ጠበል እናክመው፤ የዛሬ ምክሬም ፤ ጥሪዬም ይኸው ነው!።
ሜሎዲ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21 ቀን 2014 ዓ.ም