ለ2022 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ከጋና ጋር ገለልተኛ ባለችው በደቡብ አፍሪካ መደረጉን የጋና እግር ኳስ ማህበር በመቃወም የስታዲየም ለውጥ እንዲደረግ ለፊፋ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወቃል። የባህርዳር ስቴድየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ መስፈርቶችን አያሟላም በሚል ካፍ ማገዱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ጨዋታውን በገለልተኛ አገር ለማካሄድ ተገዳለች።
በዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአማራጭነት ኬንያ፣ዚምባቡዌ እና ደቡብ አፍሪካ ላይ ጨዋታው እንዲካሄድ መምረጡ ይታወሳል። ሶስቱም አገራት ይህንን ጨዋታ ለማስተናገድ ፈቃደኝነታቸውን መግለጻቸው የሚታወስ ሲሆን የዚምባቡዌ ስታዲየም የዚምባብዌን እና የኢትዮጵያን ጨዋታ ብቻ እንዲያስተናግድ በገደብ የተፈቀደለት እንጂ ሌላ ጨዋታ ማካሄድ ስለማይችል ሳይሳካ ቀርቷል።
ጨዋታውን ለማስተናገድ ኬንያ ፈቃደኝነቷን የገለጸች ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ዚምባቡዌ ለመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታው ማቅናቱ ስለማይቀር፤ በአንድ የአውሮፕላን ጉዞ እና መጠነኛ ወጪ ጨዋታውን በደቡብ አፍሪካ ለማድረግ ወስኗል። በመሆኑም ጨዋታው ፊፋ በሚያስቀምጠው ቀን በደቡብ አፍሪካ ኦርላዶ ስታዲየም እንዲካሄድ ፌዴሬሽኑ ከደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ተስማምቷል።
የጋና እግር ኳስ ማህበር ባለፈው ሳምንት ለካፍ እና ለፊፋ በላከው ደብዳቤ በ2022 የአለም ዋንጫ ማጣርያ ከደቡብ አፍሪካ በ1 ነጥብ ልዩነት በሁለተኝነት ደረጃ በሚገኝበት አገር ላይ መደረጉ ስህተት ነው በማለት የጨዋታውን ቦታ በፍጥነት እንዲለወጥ ጥያቄ አቅርቧል።
የጋና እግር ኳስ ማህበር የአለም ዋንጫ ጨዋታዎች ስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል እንደሌለበት እና በቀሪዎቹ ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ፍትሃዊነት እንዲሰፍን መድረግ እንዳለበት ለፊፋ አመልክቷል። ጋና ወደ ዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከኢትዮጵያ ጋር በምታደርገው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ምድቡን በአንድ ነጥብ ልዩነት እየመራች የምትገኝ ሲሆን ጋና በአንድ ነጥብ ዝቅ ብላ ትከተላለች። በዚህ ሁኔታ ውስጥ የኢትዮጵያና የጋና ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ላይ መካሄዱ ለደቡብ አፍሪካ በብዙ ምክንያቶች ጥቅም እንደሚኖረው በመጥቀስ ጋና ያነሳችው ጥያቄ ምክንያታዊ መሆኑን የሚያነሱ ወገኖች አሉ።
እንዲህ አይነት አከራካሪ ሁኔታዎች በእግር ኳሱ ዓለም የቅርብ ታሪክ የሚታወስ አጋጣሚ ፈልጎ ማግኘት ከባድ መሆኑ ፊፉ ለጋና የሚሰጠውን ምላሽ ተጠባቂ አድርጎታል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ጨዋታውን ደቡብ አፍሪካ ላይ እንዲካሄድ የመረጠችው ከወጪ ቅነሳና ከጉዞ ጋር በተገናኘ የራሷን ጥቅም አስልታ እንጂ ደቡብ አፍሪካን ለመጥቀምና ጋናን ለመጉዳት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። አንድ አገር በሜዳውና በደጋፊው ፊት ጨዋታ እንዳያደርግ ከታገደ ይመቸኛል ብሎ በመረጠው እንዲሁም በፊፋና ካፍ ተቀባይነት ባለው ገለልተኛ አገር የመጫወት መብት እንዳለው የእግር ኳሱ ዓለም አቀፍ ህግ ይፈቅድለታል።
በሜዳው እንዳይጫወት የታገደ አንድ አገር የሚመርጠው ገለልተኛ ሜዳ ከሌለ ወይም የመረጠው ገለልተኛ ሜዳ በካፍና በፊፋ አስፈላጊውን መስፈርት የማያሟላ ከሆነ እንዲሁም ከጸጥታ ጉዳዮች ጋር ስጋት ካለበት ጨዋታውን በተጋጣሚው ሜዳ ለማድረግ እንደሚገደድ ህጉም ይሁን በርካታ ተሞክሮዎች ያረጋግጣሉ። ይህ ማለት ኢትዮጵያ ከጋና ጋር የምታደርገውን ጨዋታ የመረጠችው ገለልተኛ ሜዳ በተጠቀሱት መስፈርቶችና ምክንያቶች በካፍና ፊፋ ተቀባይነት ባይኖረው ጨዋታው በጋና ሜዳ ይካሄዳል እንደማለት ነው።
በዚህ መሰረት ኢትዮጵያ ጨዋታውን በጋና ሜዳ ብታካሂድ ደቡብ አፍሪካም ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳቷ አይቀርም። ይሁን እንጂ ጋና ያነሳችው ጥያቄም ምንም መሰረት የለውም ማለት አይቻልም። ካፍና ፊፋም ይህን ጥያቄ ለመመለስ ከሳምንት በላይ ዝምታን የመረጡበት ምክንያት ጉዳዩ አከራካሪ ስለሆነባቸው ይመስላል።
ያምሆኖ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በምድብ ሰባት የተደለደሉት ደቡብ አፍሪካና ጋና በዘጠኝና አስር ነጥቦች ከምድባቸው ለማለፍ ሰፊ እድል ይዘው ቀሪዎቹን ሁለት የማጣሪያ ጨዋታዎች በጉጉት ይጠባበቃሉ። በ2018ቱ የሩሲያ የዓለም ዋንጫ መሳተፍ ያልቻለችው ጋና ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ለመመለስ ያገኘችውን መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም ትልቅ ፍላጎት አላት።
የቡድን ስብስቧ ከሌላው ጊዜ በተለየ ደካማ መሆኑም ከኢትዮጵያ ጋር የምታደርገውን ጨዋታና ደቡብ አፍሪካ ላይ የመካሄዱን ጉዳይ በቀላሉ አትመለከተውም። ደቡብ አፍሪካ በበኩሏ እኤአ በ2010 አዘጋጅታው ከነበረው የዓለም ዋንጫ ወዲህ ወደ ታላቁ መድረክ ለመመለስ ዘንድሮ ከምድቧ የተሻለ ሁኔታ ላይ እንደመገኘቷ በአንድ ነጥብ ልዩነት የምትከተላት ጋና በኢትዮጵያ ነጥብ ከጣለች ተስፋዋ የበለጠ የሚለመልም ይሆናል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2014