በኢትዮጵያ ቀስ በቀስ በማኅረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረሱ ካሉ የጤና ችግሮች ውስጥ አንዱ የዐይን ሕመም ነው። በዐይን ጤና ችግር ዙሪያ የተጠኑ ጥናቶች የቆዩ ቢሆንም ቀረብ ያሉት ጥናቶች እንደሚያሳዩት 1 ሚሊዮን 760 ሺ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ዓይነ ስውር ወይም የዕይታ ችግር ያለባቸው ናቸው። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ 80 ከመቶ ያህሉ መከላከል ወይም መታከም ሲችሉ እይታቸውን ያጡ መሆኑን ጥናቶቹ ያመለክታሉ።
አነስተኛ የዐይን ሕክምና ተቋማት መኖር፣ ከሕዝቡ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን የዐይን ሕክምና ባለሙያ አለመኖር እና ዐይነስውርነትን ወይም የእይታ ችግርን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት አነስተኛ መሆን ደግሞ በአገሪቱ እየተባባሰ ለመጣው የዐይን ጤና ችግር ቀዳሚዎቹ ምክንያቶች ስለመሆናቸው በስፋት ይነገራል።
ከዚህ አንፃር በመንግሥትም ሆነ በግል ተቋማት የዐይን ጤና ችግርን በሁለንተናዊ መልኩ ለመቅረፍ ጥረቶች እየተደረጉ ቢሆንም አሁንም ችግሩ በስፋት ይታያል። የዐይን ጤና ችግሮች በአብዛኛው የሚከሰቱት አስቀድሞ መከላከል ወይም መታከም በሚችሉ ምክንያቶች ቢሆንም በዚህ ረገድ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ ዝቅተኛ መሆን ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል።
ይሁን እንጂ ኅብረተሰቡ ስለ ዐይን ጤንነት በቂ ግንዛቤ ኖሮት የዐይኑን ጤና እንዲጠብቅ የዓለም እይታ ቀን በየዓመቱ በጥቅምት ወር የዐይን ሕክምና አገልግሎት በሚሰጥባቸው የመንግሥትና የግል ሕክምና ተቋማት እንዲሁም በትምህርት ቤቶች ውስጥ ይከበራል።
የዘንድሮው የዓለም እይታ ቀንም ‹‹አይናችንን እንከባከብ›› በሚል መሪ ቃል በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ግዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ግዜ በተለያዩ ዝግጅቶች ከሰሞኑ ተከብሯል።
አለርት ሆስፒታልም በዓሉን አስመልክቶ ሲ ቢ ኤም ከተባለ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር እድሜያቸው 40 እና ከዚያ በላይ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በነፃ የግላውኮማ ወይም የዐይን ግፊት ምርመራ በማድረግ በዓሉን አክብሯል።
ዐይነስውርነት ወይም የእይታ ችግር በቀላሉ መከላከል በሚቻሉ ምክንያቶች የሚከሰት ነው። ለመሆኑ ዐይነስውርነትን ከመከላከልና ኅብረተሰቡም ግንዛቤ አግኝቶ የዐይኑን ጤንነት እንዲጠብቅ ምን እየተሰራ ነው?
ዶክተር ሰለሞን ቡሳ በአለርት ሆስፒታል የዐይን ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪምና የዐይን ሕክምና ክፍል ኃላፊ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በኢትዮጵያ 1 ሚሊዮን 760 ሺ የሚሆኑ ሰዎች የዐይነስውርነት ወይም የእይታ ችግር ያለባቸው ናቸው። ከነዚህ ውስጥ እስከ 85 ከመቶ የሚሆኑት ደግሞ መከላከል ወይም መታከም ሲችሉ እይታቸውን ያጡ ወይም የእይታ ችግር ያጋጠማቸው ናቸው።
በኢትዮጵያ አሁን ለሚታየው የዐይነስውርነትና የእይታ ችግር እንደመጀመሪያ ምክንያት የሚጠቀሰው አነስተኛ ቁጥር ያለው የዐይን ሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት መኖር ሲሆን አሁን ባለው መረጃ መሠረት በአገሪቱ 52 ብቻ የዐይን ሕክምና መስጫ ተቋማት ይገኛሉ። እነዚህም በመንግሥት፣ መንግሥታዊ ባልሆኑና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
አነስተኛ የዐይን ሕክምና ባለሙያ መኖር በተለይ ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ካለው ሕዝብ ጋር የሚመጣጠን አለመሆንም ለዐይነስውርነት ችግር ትልቅ አስተዋፅዖ አድርጓል። በአገሪቱ በአሁኑ ወቅት 170 የዐይን ስፔሻሊስት ሐኪሞች፣ 298 የኦፕታሚክ ነርሶች፣ 54 ካታራክት ሰርጂኖች እንዲሁም 520 ኦፕቶሜትሪስት ወይም መርምረው መነፅር የሚያዙ ሐኪሞች ያሉ ሲሆን ቁጥራቸው ከአገሪቱ የሕዝብ ብዛት ጋር ፍፁም ተመጣጣኝ አይደለም።
እንደ ዶክተር ሰለሞን ገለፃ ዐይነስውርነትን ለማከም ወይም ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ዝቅተኛ መሆንም በአገሪቱ የሚታየውን የዐይን ጤና ችግር አጉልቶታል። በተለይ በታዳጊ አገራት አብዛኛው የጤና አገልግሎት ትኩረት የሚያደርገው እንደነ ቲቢ፣ ኤች አይ ቪ ኤድስ፣ ወባና በመሳሰሉት ገዳይ በሽታዎች ላይ በመሆኑ ለዐይነስውርነትና የእይታ ችግር የተሰጠው ትኩረት አናሳ ነው። በተለይ ደግሞ ዐይነስውርነት የማይገድል የጤና ችግር ስለሆነ ብዙ ትኩረትም አይሰጠውም።
ከዚህ አንፃር የዐይነስውርነትን ችግር ለመቅረፍ ከጠቅላላው የጤና አገልግሎት ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰጥ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ለዚህም በየዓመቱ የዓለም ዕይታ ቀን በዓለም አቀፍና በአገር አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል። የዘንድሮው የዓለም ዕይታ ቀን ዋና ዓላማም በዐይነስውርነት ዙሪያ ለኅብረተሰቡ ግንዛቤ በመስጠት የዐይኑን ጤና እንዲጠብቅ ለማድረግና በየግዜው ወደ ዐይን ሕክምና መስጫ ተቋማት በመሄድ የዐይኑን ጤና እንዲፈትሽ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም መንግሥታዊና ሲቪል ድርጅቶች የዐይን ሕክምና አገልግሎቱ የሚስፋፋበትንና ባለሙያዎችም በብዛት እየሰለጠኑ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን ሁኔታ እንደሚመቻች ለማስቻል ነው።
በጤና ሚኒስቴር የዐይን ጤና ቴክኒካል አማካሪ አቶ አክሊሉ ኃይሌ በበኩላቸው እንደሚገልፁት በኢትዮጵያ የዐይን ጤናን በሚመለከት በቅርብ ግዜ የተሰሩ ጥናቶች የሉም። በዐይን ጤና ዙሪያ ጥናት የተካሄደውም ከአስራ አምስት ዓመት በፊት ነው ። በዚሁ ጥናት መሠረትም በኢትዮጵያ ዐይነስውርነት 1 ነጥብ 6 ከመቶ ሲሆን አሁን ካለው ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር አንፃር ሲሰላ ከፍተኛ ነው።
በአስራ አምስት ዓመታት ውስጥ የተሰሩ የዐይን ሕክምናዎች በመኖራቸውና የተጠና ጥናትም ባለመኖሩ በትክክል በኢትዮጵያ ያለውን የዐይነስውርነት ደረጃ መናገር ያስቸግራል። የእይታ ችግርን በሚመለከት ደግሞ 3 ነጥብ 7 ከመቶ ሲሆን አሁን ያለውን አኃዝ በትክክል ለማወቅ ተመሳሳይ ጥናት ማድረግ ይጠይቃል።
የኅብረተሰቡ የአኗኗር ሁኔታን መቀየር፣ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መጨመር፣ ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶች/ሞባይልና ስልክ/ መጠቀም ጋር ተያይዞ በዐይን ጤና ላይ ተጨማሪ ችግሮች ስለሚያመጡ ዐይነስውርነትና የዕይታ ችግር አሁን ያለበት ደረጃ ከዚህም በላይ ሊሆን ይችላል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለውን የዐይን ጤና ችግር በሚመለከት ለማወቅም ጤና ሚኒስቴር ከኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን እየሰራ ይገኛል። ሚኒስቴሩ ለእቅድ ግብዓትነት ጥቅም ላይ እያዋለ ያለውም ቀደም ሲል የነበረውን የጥናት ዳታ በመቀየር ነው።
እንደ አቶ አክሊሉ ገለፃ የዓይን ጤና ሕክምና አገልግሎት አሰጣጥም አሁን ካለው የሕዝብ ቁጥር አንፃር በቂ አይደለም። በአገሪቱ ሁለተኛ ደረጃ የዐይን ሕክምና መስጫ ተቋማት በተለይ እንደ ካታራክትን የመሰሉ የዐይን ሞራ ቀዶ ሕክምና አገልግሎትን መስጠት የሚችሉ ተቋማትም 52 ብቻ ናቸው። ያሉትም የዐይን ሕክምና መስጫ ተቋማት በአብዛኛው የሚገኙት በከተሞች አካባቢ ነው። ከዚህ አኳያ ተጨማሪ የዐይን ሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ማስፋፋት ያስፈልጋል።
የጤና ሚኒስቴር ለጤና ተቋማት በተለይ ደግሞ ለሆስፒታሎች ጤና ባለሙያዎችንና ባለሙያዎችን መመደብ ዋነኛ ተግባሩ እንደመሆኑ በቅርቡ በ78 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዙ 53 የዐይን ቀዶ ሕክምና ማይክሮስኮፖችን አሰራጭቷል። ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበርም ተጨማሪ በሂደት ላይ ያሉ የዐይን ሕክምና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እየተገነቡና የሕክምና መሳሪያዎች ግብዓት ግዢና ባለሙያ ምደባ እየተከናወነ ይገኛል። ይህም በቂ ባለመሆኑ በመጀመሪያ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ የዐይን ሕክምና ዩኒቶችን ለማስፋት ጤና ሚኒስቴር ተጨማሪ ሥራዎችን በቀጣይ ያከናውናል።
ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር በተያያዘም በአሁኑ ወቅት ያሉት የዐይን ሕክምና ባለሙያዎች ቁጥር ካለው የሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀር በቂ ባይሆንም ከበፊቱ ጋር ሲነፃፀር ግን መሻሻል አሳይቷል። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የዓለም የጤና ድርጅት ከሚያስቀምጠው መመዘኛ አንፃር በቂ አይደለም።
የዐይን ሕክምና ባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግም በአሁኑ ወቅት ትምህርታቸውን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እየተከታተሉ የሚገኙ አሉ። ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበርም ተማሪዎች በስፖንሰርሺፕ ተጨማሪ ትምህርት እንዲያገኙም ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። አሁንም ተጨማሪ ተማሪዎችን ለማስተማር እቅድ ተይዟል።
የዐይን ሕክምና ከጤና ተቋማት በተጨማሪ የሌሎች ባለድርሻ አካላትን አጋርነት የሚፈልግ በመሆኑ ጤና ሚኒስቴር ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከተለያዩ ስልጠና ከሚሰጡ ኮሌጆች ጋር በትብብር እየሰራ ይገኛል። የዐይን ህክምና አገልግሎቱን ከማስፋት አንፃርም ልክ እንደ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶች በሆስፒታሎች ውስጥ እንዲሰጥ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2014