ትናንትን በዛሬ ዕይታ፤
የታሪክ መዝጋቢዎች እጅግም ልብ ሳይሉት የሚያልፉትን አንድ ክስተት ወደ መሐል ግድም እንደማስታውስ እየገለጽኩ ወደ መነሻ ሃሳቤ ልገስግስ። በፈተና ተተብትቦ የነበረውና አጠቃላይ የሥርዓቱ ውቅር “ከዝንጀሮ ቆንጆ ምኑ ይመረጣል” ይሉት ብሂልን ከሚያስታውሰን ከዘመነ ደርግ አፍላ ወቅቶች መካከል ከ1969 – 1972 ዓ.ም የነበሩትን ዓመታት በተለየ ሁኔታ ለማስታወስ እንሞክር።
በእነዚህ አራት ዓመታት ውስጥ ኢትዮጵያ ልክ እንደዛሬው በበርካታ አስጨናቂ ፈተናዎች የውጥር ተይዛ የምትቃትትበት ወቅት ነበር። “በደም ግብር” አብጦ ሊፈነዳ የደረሰው የዛሬው አሸባሪ የሕወሓት ቡድን በትግራይ በረሃዎች ውስጥ የጥፋት ቀንዱ እያቆጠቆጠ የማዕከላዊ መንግሥቱን ለመገዳደር ከእንፉቅቅ ለመነሳት የሚውተረተርበት ጊዜ ነበር።
በኤርትራም “መገንጠልን” አልሞ ይንቀሳቀስ የነበረው የሻዕቢያ ኃይል እየተጠናከረ ሄዶ ጡንቻው የፈረጠመበት ወቅት ሲሆን ኦነግም እንዲሁ ጮቤ እየረገጠ “ግፋ በለው!” ቀረርቶ የሚያሰማበት መራር ጊዜ ነበር። ቁጥራቸው በርከት ይል የነበረው “የአርነት” ንቅናቄዎችም “እኔስ ከማን አንሼ” በሚል መንፈራገጥ “እንዳትረሱን” በማለት በየጥጋጥጉ መሽገው “የሳል ድምጽ” የሚያሰሙበት ወቅት ነበር።
ይህን መሰሉ በቀለበት የሚመሰለው አገራዊ የፈተና ከበባ ሳያንስ መኢሶን፣ ኢህአፓ፣ ኢጭአት፣ ሰደድ ወዘተ. በሚሉ ስያሜዎች ያገነገኑት “የፖለቲካ ድርጅቶች” በመሐል አገር እየተገዳደሉና እየተሞሻለቁ እጃቸው በደም የተጨማለቀበት፣ መበቃቀላቸው ገኖ የወጣበት ዓመታት ነበሩ።
እነዚህ ሁሉ የመከራ ዓይነቶች አገሪቱን በሚያመሰቃቅሉበት ወቅት የሱማሊያው መሪ የዚያድ ባሬ ወራሪ ኃይል አጋጣሚው የተመቻቸለት መስሎት የምሥራቁን የአገራችንን ድንበር በእብሪት ጥሶ በመውረር ወደ መሐል እየገሰገሰ እስከ 700 ኪሎ ሜትር ዘልቆ መግባቱ የፈተናውን ጭነት ያከበደ ሌላው ተግዳሮት ነበር።
በአገር ላይ በወረደው በዚህ መልከ ጥፉ መከራና አሳር ምክንያትም በእያንዳንዱ ቤተሰብ ቤት የሞት መልአክ እያንኳኳ በመግባቱ የኀዘን ጨርቅ ያልለበሰ፣ ልጆቹንና ዘመድ አዝማዱን ቀብሮ የኀዘን ፍራሽ ላይ ያልተቀመጠ ይኖራል ተብሎ አይገመትም። የእናቶች እምባ “እንደ ራሄል ወደ ፀባዖት ያሻቀበበት” የአባቶች እህህታ አየሩን ያጠነበት፣ የልጆችና የቤተሰብ አባላት እዮታ ከዳር ዳር ያስተጋባበት ጊዜ ነበር። እንደ ጎርፍ የፈሰሰው የንጹሐን ደም የጦር አውድማውን፣ የከተሞችን ጎዳናና አደባባዮች አጨቅይቶ አገሪቱ በሲኦል የተመሰለችበት ዓመታት ነበሩ።
ከእነዚያ የመከራ ጊዜያት በኋላ በነበሩት ቀሪ የደርግ ዓመታትና የአረመኔነቱን ጥግ ለመግለጽ እስከሚያዳግተን ድረስ በተቸገርንበት የአሸባሪው ሕወሓት የአገዛዝ ዘመን ማብቂያ ዓመታት ድረስ አብዛኞቹ እናቶች የኖሩት ነጠላቸውን እንዳዘቀዘቁና በሀዘን ጨርቅ እንደተቆራመዱ ነበር። አባቶችም እንዲሁ በእህህታ ከመብሰልሰልና ከትካዜ አላረፉም ነበር። የታሪክ ዘጋቢዎች ልብ አላሉትም ለማለት ያስደፈረን ጉዳይም ከእነዚህ እንደ ሰንሰለት ከተያያዙት ክፉ ቀናት ጋር የተቆራኘ አንድ እውነታ ነው።
ክስተቱን እናስታውስ። መከራው ተደራርቦ የወደቀባቸው አብዛኞቹ እናቶች ቀበሌዎች ይጠሯቸው በነበሩ ስብሰባዎች ላይ ይሳተፉ የነበረው ምንም እንኳን የቅርብ ጊዜ ኀዝንና መርዶ ባይገጥማቸውም “ልማድና ባህል” እስኪመስል ድረስ ያዘቀዘቁትን የነጠላቸውን ክንብንብ በፍጹም አያወልቁም ነበር።
የስብሰባ አዳራሾች ውስጥ ተቀምጠውም ቢሆን ለአካባቢያቸውና ለአገር ጉዳይ እንደሚወያይ ጉባዔተኛ ሳይሆን ስሜታቸውን ይገልጹ የነበረው “ትኩስ ሬሳ” ሸኝቶ እንደሚመለስ ለቀስተኛ እየተከዙና እጃቸውን አገጫቸው ላይ አሳርፈው በመቆዘም ነበር። ቢያንስ ለአርባ ዓመታት ያህል። ይህንን ክስተት ልብ ብሎ ለማስተዋል ቀደም ባሉት ዓመታት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዜናና በሐተታ መልክ የተዘገቡ ቪዲዮዎችን ከአርካይቭ አውጥቶ መመልከት ይቻላል።
ዛሬም ያ ትካዜ፣ ያን መሰል የእናቶችና የአባቶች እምባ በለሆሳስ እየተዥጎደጎደ ያለው በስሜት ቀውስ ከሚመነጭ ትውስታ (Trauma) ብቻ ሳይሆን ጨካኙና አረመኔው የሕወሓት ቡድን ምንጩ ስላልደረቀና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዳያቆጠቁጥ ተደርጎ ተነቅሎ ስላልተወገደ ነው።
ይህ የእኩያን ስብስብ ያደገውና የፋፋው የግፍ እምባና ደም እየተጋተ ነው። ስለዚህም ነው አንዳችም ቅሬታ (Remnants) ለወሬ ነጋሪነት ሳይቀር ይህ አሸባሪ ቡድን ተጠራርጎ እንዲወገድ የጦርነቱ ፍልሚያ በሕዝባዊ መርሕ እየተመራ ከዳር ዳር የተቀጣጠለው።
ትግራይን በምናባዊ ዕይታ፤
ሕወሓት ይሉት የኔፊሊም (ዘፍጥረት ምዕ 6 ይነበብ) ስብስብ ቡድን በጭካኔና አገርን ለመበታተን ዓላማ አድርጎ በትግራይ በረሃ ውስጥ በአጋንንታዊ መንፈስ ተማምሎ ከተጸነሰበት ዕለት ጀምሮ ስናደምጥና ስናይ የኖርነው ተግባሮቹ ተወዳዳሪ የላቸውም። አብዛኞቹ የትግራይ ምስኪን እናቶችና አባቶች ስለ ዘነበባቸው መከራ መገለጫ እንዲሆን የተጎናጸፉትን የኀዘን ጨርቅ ለውጠው ለመጽናናት ዛሬም ድረስ አልታደሉም።
ተጽናንተናል ብለው ቢናገሩ እንኳን የልባቸው ጥቁር ቱቢትና ሰንበሩ ከልባቸው ላይ እንደተጋደመ ስለመሆኑ ሊክዱ አይችሉም። ምስክር ካስለፈለገም “የልጆቻችን የደም ፍሬ” በሚሉት የሕወሓት የአገዛዝ ዘመን ሦስት፣ አራት፣ አምስት፣ ስድስት ልጆቻቸውን ገብረው በአደባባይ እምባ እያፈሰሱ ይመሰክሩ የነበሩ እናቶችን ማስታወስ ይቻላል። የአካል ጉድለት የደረሰባቸውንማ ቤቱ ይቁጠር ማለት ይቀላል።
የአሸባሪው ቡድን መሪዎች በሕዝቡ ላይ እንደዚያ የመከራ ዶፍ እያዘነቡና እያስለቅሱት እነርሱ ግን በአገር ውስጥ በዊስኪና በሻምፓኝ እየተራጩ በመቃበጥ “ዋንጫ ኖር!” እያሉ ይፎልሉ ነበር። ልጆቻቸውንና ጀሌዎቻቸውንም ወደ ተለያዩ አገራት በመላክ ሲያቀማጥሏቸው መኖራቸው ዛሬም የሚታይ እውነታ ነው። የአብራካቸውን ክፋይ ለሞት ግብር አሳልፈው የሰጡ ወላጆች በኑሮ ጉስቁልና እየተቀጡ እምባ የዕለት ቀለባቸው ሲሆን ጌቶቹ የሕወሓት መኳንንት ግን ዘር ማንዘራቸውን እያሞላቀቁና እያጨማለቁ አገርም ምድርም ጠበበን በማለት ይይዙት ይጨብጡትን አሳጥቷቸው ነበር።
አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ እንዳይናገር አፉ ተሸብቦ፣ እምቢኝ ብሎ እንዳያምጽ በደህንነት ሰንሰለታቸው ተጠፍንጎ የኖረባቸው ሃምሳ ያህል ዓመታት ብዙ አንገት የሚያስደፋ ታሪክ ያለው ነው። በዓላማ ቢስ ጦርነቶች የልጆቹን ደም እስከ ዛሬ ድረስ እየገበረ ያለው ወዶ ሳይሆን ተገዶ ጭምር ነው።
ዛሬ የፕሮፖጋንዳው ዘመቻ ተዋናይ የሆኑ አንዳንድ እናቶች “ለትግራይ አርነት ሦስትም አምስትም ልጅ ለመስዋዕትነት መገበሬ አግባብ ነበር/ነውም” ብለው በየሚዲያው ሲያቅራሩ የምናደምጠው የሐሰት ድምጻቸውን እንጂ የእናትነት ሆዳቸውን እውነታ ሊወክል በፍጹም አይችልም። ወደፊት እውነታውን ትውልድ በአግባቡ መሰነድ ሲጀምር ያኔ ታሪክም ልጆቻቸውም ለምስክርነት መጠራታቸው አይቀርም።
የጉም ስርቆት ብሂልና አሁናዊ እውነታው፤
የሥነ ልቦና ተመራማሪዎች የሌብነትን ሱስ የሚመስሉት ከደም ካንሰር በሽታ ጋር በማነጻጸር ነው። በደም ውስጥ የተሠራጨ ካንሰር ሰውነትን አመንምኖ ለሞት የሚዳርገው በጊዜ ሂደት ውስጥ ነው። አሸባሪው ሕወሓት ፅንሰቱ በሌብነት፣ ወጣትነቱ በዘረፋ፣ ጉልምስናው በስርቆት ደዌ የተለከፈ መሆኑን ማስረጃዎችን በማጣቀስ በርካታ ጽሑፎችን ካሁን ቀደም ማስነበባችን ይታወሳል።የዘረፋው ዓይነት መጠን አልነበረውም። ወደ ማዕከላዊ መንግሥትነት ሥልጣን እየተረማመደ ይሄድ የነበረው አገር እየዘረፈና መዝረፍ ያቃተውን እያወደመ እንደነበርም አይዘነጋም።
ሥልጣን ላይ በተፈናጠጠባቸው የመጀመሪያ ዓመታት ግድምም ከመሐልና ከዳር አገር የዘረፋቸውን ማሽነሪዎች፣ ተሽከርካሪዎችና ጠቃሚ ነው ብሎ የሚያምንባቸውን የሕዝብ ሀብት በሙሉ ዘርፎ ያጓጉዝ የነበረው በጠራራ ፀሐይ ነበር። ሥልጣኑን ተቆናጦ በአምባገነንነት ከገዘፈም በኋላ የሌብነት ደረጃውን ከፍ አድርጎ ከገፀ ምድርና ከከርሰ ምድር የተፈጥሮ ሀብቶች እስከ መሬት ወረራና ቅርምት፤ ከእርዳታና የልማት ብድሮች እስከ የኪዮስክ መደብሮች ሲቀማና ሲዘርፍ የነበረው በማንአለብኝ እብሪት እየተኩራራ ነበር። ነገሮች ሲረጋጉና ጊዜው ፈቃድ ሲሰጥ እነዚህ ሁሉ የግፍ ስንክሳሮቹ በሚገባ ይፋ እንደሚገለጡ እሙን ነው።
በደማቸው ውስጥ እንደ ካንሰር የወረራቸው የሌብነትና የዘረፋ ሱስና አራራ አልለቅ ብሏቸው ትናንትናና ዛሬ በወረሯቸው የአማራና የአፋር ክልሎች እየፈጸሟቸው ያሉትን አሳፋሪ ሌብነትና የግፍ ጭካኔ በነጋ በጠባ እየተከታተልን ነው። “ያዳቆነ ሰይጣን” እንዲሉ በወረራ የረገጧቸውን የገጠርና የከተማ አካባቢዎች ሙልጭ አድርገው ዘርፈዋል። በርካታ የመንግሥትና የግል ድርጅቶችንና ተቋማትን ያለ ርህራሄ አውድመዋል። ትምህርት ቤቶችንና የጤና ተቋማትን ሳይቀር አራቁተዋል። ለመዝረፍ ያልፈለጉትን ወይንም ያልቻሉትን ደግሞ እሳት እየለቀቁ የዶግ አመድ አድርገዋቸዋል።
ከሀብት ዘረፋው በገዘፈ መልኩም የብዙ ንጹሃንን ነፍስ በግፍ እየነጠቁ ለገሃነም ፍርድ ራሳቸውን አዘጋጅተዋል። የገበሬውን ማሳ ማቃጠላቸው አልበቃ ብሏቸው ያሸተውን አዝመራ ሳይቀር እያጨዱ ወስደዋል። ጓዳውን አራቁተዋል። ለቤት እንስሳት እንኳ ሳይራሩ ጨፍጭፈዋቸዋል። ከዛኒጋባ ጎጆዎች እስከ ታላላቅ ሕንጻዎች የጣሪያ ቆርቆሮዎችን ሳይቀር እየነቀሉ አጓጉዘዋል። ከሊጥ እስከ በሰለ የዕለት ማዕድ ገልብጠው በልተዋል።
የተረፋቸውን ደፍተው፣ ለመሸከም የቻሉትን አንጠልጥለው፣ ኦና የቀረው መኖሪያ ቤትንም ዳግም ግልጋሎት እንዳይሰጥ ጋዝ አርከፍክፈው አቃጥለዋል ወይንም ሙት በድናቸውን ቀብረው አርክሰውታል። የእምነት ተቋማትን ዘርፈዋል አቃጥለዋል። መንፈሳዊ አገልጋዮችንም አዋርደዋል። እንዲህ ዓይነቱን በቋንቋ ለመግለጽ እንኳን የሚያስቸግረውን የግፍ ድርጊት ያቆረባቸው ዲያቢሎስ እንኳን ስለመፈጸሙ ያጠራጥራል።
የፖለቲካው ደመናና የአገሪቱ ወቅታዊ ጭጋግ ግርዶሽ ሆኗቸው የወረራውና የዘረፋው በር ወለል ተደርጎ የተከፈተላቸው ቢመስልም “ቃል ለምድር ለሰማይ” ሊደመሰሱ የቀራቸው አንድ ሐሙስ ብቻ ነው። በጀግናው የመከላከያ ኃይላችንና በቆራጦቹ ሕዝባዊ ሚሊሽያዎችና ልዩ ኃይላት ድሉ የአገርና የሕዝብ ሆኖ በቅርቡ እልልታው መድመቁ አይቀረም። ግርዶሽ ሆኖ ያገለገላቸው ውስብስቡ ጉም ሙሉ ለሙሉ ተገፍፎ የእውነት ፀሐይ መድመቅ ስትጀምር እውነታው መፍረጥረጡ ስለማይቀር ያ ቀን ሩቅ አይደለም። ጉሙን ተገን አድርገው የዘረፉትን ሁሉ ጭጋጉ ሲጠራ መልሰው መትፋታቸው አይቀርም።
ለትግራይ እናቶችና አባቶች ጥያቄዎች አሉን፤
በፈቃዳቸውም ይሁን በግዴታ አፈሳ ልጆቻቸው እየታደኑ ወደ ሞት ሲጋዙ እንዴት የትግራይ እናቶች በአንድነት ድምጻቸውን አስተባብረው “የእኛ” የሚሏቸውን እኩያን በቃችሁ ለማለት ተሳናቸው? እንደምንስ በልጆቻቸው ደም የሚነግዱትን “ኔፊሊሞች” ገስጾ ማስቆም አቅም አነሳቸው? የአሸባሪው ቡድን የደህንነት መዋቅር ምን የረቀቀ ቢሆን፣ የመቀጣጫ ማስፈራሪያውም ምንም ያህል የጠነከረ ቢመስል ብዙኃኑ የትግራይ ወላጅ እንደምን ኢምንት ቁጥር ባላቸው ጀብደኞች ላይ ክንዱን ማጠንከር አቃተው? በውሸት የሚያርከፈክፉትን የፕሮፖጋንዳ ወጨፏቸውንስ ላለመስማት ለምን ጆሮውን መድፈን ተሳነው? በኀዘንና በረሃብ መቀጣትንስ ችሎ የሚዘልቀው እስከ መቼ ድረስ ነው?
ከኢትዮጵያ መለየትን ለማደናገሪያነት እየተጠቀሙ ሲሰብኳቸውስ ግቡና ውጤቱ ምንድን ነው ብሎ ለመጠየቅ ለምን አልደፈሩም? ጥያቄዎቻችን ብዙ፣ የምንጠብቀው ምላሽም ለጊዜው ደብዛዛ እንደሚሆን ቢገባንም ለአብነት የተነፈስናቸው መሟገቻዎች ለጊዜው ይበቁ ይመስለናል። ለቀሪዎቹ ትዝብታችን ለጊዜ ጊዜ ሰጥተን ሁኔታውንና ውጤቱን መከታተል ይበጃል።
የኢየሩሳሌምን መጎሳቆል፣ በኃጢአትና በርኩሰት መጨቅየትና ራስንና የራስን ብቻ ከፍ አድርጎ መመልከት መንፈሱን የሰበረው ኢየሱስ እንዲህ በማለት ከተማዋን ሞግቶ እንደነበር በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ተመልክቷል። “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ! ነብያትን የምትገድል፣ ወደ እርሷ የተላኩትንም የምትደበድብና የምታዋርድ፤ ዶሮ ጫጩቶቿን በክንፏ ውስጥ እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ምን ያህል ወደድሁ? እናንተ ግን እምቢ አላችሁ።” ኢትዮጵያም ትግራይ ልጇን (ምንም እንኳን የእናትነቷን ክብር ብታቃልልም) አፍ አውጥታ ስሜቷንና የልቧን ስብራት በነፃነት መግለጽ ብትችል ከዚህ የተለየ ምን አዲስ ሃሳብ ታክልበት ይሆን? ሆድ ይፍጀው። ሰላም ይሁን።
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2014