ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ላስቀመጣቸው መርሆች ተገዥ የመሆን የሕግም ሆነ የሞራል ኃላፊነትና ተጠያቂነት አለበት። በተለይም በዓለም ፖለቲካ ውስጥ ራሳቸውን ዋነኛ ተዋናይ አድርገው የሚያቀርቡ ሀገራት መሪዎች ዓለም አቀፍ ክስተቶችን ከፍ ባለ የኃላፊነት መንፈስ ማየትና ለዚህ በሚመጥን የአስተሳሰብ መሠረት ላይ ቆመው መታየት ይጠበቅባቸዋል።
በተለይ ስለ ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት ብዙ በሚነገርበት፤ ስለ ግሎባላዜሽን በስፋት በሚሰበክበት በዚህ ዘመን ለዚህ ዓለም አቀፍ እውነታ ያልተገዙ፤ ወደ ቀደመው ዘመን የራስ ወዳድነትና የቀደሙ ጥቅሞችን በሴራ የማስጠበቅ የፖለቲካ አካሄዶች ማንንም ተጠቃሚ የሚያደርጉ አይሆኑም።
ይህ ዓይነቱ የተሳሳተ አካሄድ ዓለምን ከቀደመው ዘመን በከፋ መልኩ ከመከፋፈልና የዓለምን ሰላምና ደህንነት አደጋ ውስጥ ከመክተት ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። በተለይም የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው ለመወሰን ተስፋ አድርገው መንገድ ለጀመሩና ለሚጀምሩ የሦስተኛው ሀገራት ሕዝቦች ዋነኛ ተግዳሮት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል።
በአንድ በኩል ስለ ዓለም ሰላምና ደህንነት አፍ ሞልቶ እየሰበኩ ፤ በሌላ በኩል ከዓለም አቀፍ መርሆችና ሕጎች ባፈነገጠ መልኩ ሀገራት ላይ ጫናዎችን ማሳረፍ፤ ስብከቶቹ የቱንም ያህል ውብ በሆኑ ቋንቋዎች ቢሰበኩ፤ የቱንም ያህል የዓለም አደባባዮችን ሞልተው ቢሰሙ ትርጉም አልባ መሆናቸውን ከማመላከት ያለፈ ፋይዳ አይኖራቸውም።
ዓለም አቀፍ መርሆዎችና ሕጎች ያስፈለጉት ፍትሀዊ ዓለም አቀፍ ሥርዓት ለመፍጠርና ለዚህ የሚሆን የኃላፊነት መንፈስ ለመገንባትና ተጠያቂነት ለማስፈን ነው። ይህ ደግሞ ከመሰረቱ ሀገራት በዓለም አቀፍ ደረጃ ካላቸው በእኩል የመታየት እና የመዳኘት መብት የሚመነጭ ነው።
የሀገራትን በዓለም አቀፍ ደረጃ በእኩል የመታየትና የመዳኘት መብት የሚጋፋ የትኛውም አስተሳሰብም ሆነ ከዚሁ የሚመነጭ ድርጊት በአንድም ይሁን በሌላ ለዓለም ሰላምና ደህንነት ለማምጣት የሚደረጉ ጥረቶችን
በአደባባይ ከመቃረን ያለፈ ትርጉም ሊኖረው አይችልም። በጉዳዩ ላይ የቱንም ያህል ምክንያት መደርደርም የትርጉም ለውጥ አያመጣም።
የአንድ ሀገር ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን ሰብአዊ እና ፍጥረታዊ መብት አለው።ይህ ፍጥረታዊ መብቱ በዋንኛነት የሌሎችን ተጠቃሚነት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ሊሸረሸር ሆነ ሊገራ አይገባም። ይህንን ለማድረግ መሞከር በሰው ልጆች ላይ የሚደረግ የከፋ ወንጀል ነው። የሚያስከትለውም መዘዝ በቀላሉ የሚሰላ አይሆንም። የሞራል፣ የሕግ እና የታሪክ ተጠያቂነት ያስከትላል።
በዚህ ወንጀል የሚሳተፉ ሀገራት መሪዎች እውነታውን በአግባቡ ሊያጤኑት ይገባል፣ ወቅታዊ ቁመናቸውን ታሳቢ በማድረግ የሚፈጽሟቸው የማን አለብኝነት ወንጀሎች የሀገራቸውን ቀጣይ ትውልዶች አንገት የሚያስደፉ ስለመሆናቸው ከቀደሙት የዓለም ታሪኮች ተገቢውን ትምህርት ሊወስዱ ይገባል።
በተለይም ኢትዮጵያውያን ከዘመናት መውደቅ መነሳት በኋላ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን የጀመሩትን የለውጥ ጉዞ ለማሰናከል በብዙ መልኩ ከፍ ባሉ ሴራዎች እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሀገራት መሪዎች እውነታውን በአግባቡ ሊያጤኑት ይገባል። ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው አዲስ ክስተት አይደለም፤የታሪክ ሂደት ነው ።ይህን ሂደት ማዘግየት እንጂ ማስቆም አይቻልም።
አሁን በኢትዮጵያውያን ውስጥ የተፈጠረው የአስተሳሰብ ልቀት ሀገሪቱንና ህዝቦቿን ወደ አዲስ የታሪክ ምእራፍ ማሸጋገር የሚያስችል ነው። ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያውያን ባለፈም ለዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በተለይም ድህነትን በራሳቸው መንገድ ታግለው ለመቅረፍ ለሚጥሩ ሀገራት የሚኖረው ፋይዳ አልፋና ኦሜጋ ነው።
ለመላው የዓለም ሕዝቦች የተሻለ ሕይወት ለሚመኙና ለዚህም ቀን ከለሊት ለሚተጉ ሀገራትና ሕዝቦች አዲስ የምስራች ይዞ የሚመጣ፤ በአንድም ይሁን በሌላ የድህነት ሕይወት አልገፋ ላላቸው ሕዝቦችም ከራሳቸው ማንነት የሚመነጭ አዲስ የህይወት ተስፋ መኖሩን በተጨባጭ የሚማሩበት ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2014