በኢትዮጵያ ከቅርብ አመታት ወዲህ በተለያዩ ክልሎች ግዙፍ ስቴድየሞች በብዛት እየተገነቡ ቢሆንም ባለፉት አመታት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን በማስተናገድ አገልግሎት መስጠት የቻለው የባህርዳር ስቴድየም ብቻ ነበር። ይህም ስቴድየም ከሳምንት በፊት ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ አስፈላጊ መስፈርቶችን አሟልቶ ባለመገኘቱ የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት በሚመራው ካፍ እንደታገደ ይታወቃል። በዚህም ኢትዮጵያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በቅርቡ ከጋና ብሔራዊ ቡድን ጋር የምታደርገውን ጨዋታ ጨምሮ ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ መስፈርቶችን የሚያሟላ ስቴድየም እስኪኖራት ጨዋታዎችን በገለልተኛ ሜዳ ለማከናወን መገደዷ ይታወቃል።
የባህርዳር ስቴድየም ዓለም አቀፍ ጨዋታዎችን እንዳያካሂድ ከታገደ ወዲህ የኢትዮጵያ ስቴድየሞች ያሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ በበርካታ የስፖርት ቤተሰቦች የመፍትሄ ሃሳቦች አሁንም ድረስ እየተሰነዘሩ ይገኛሉ። በታገደው ስቴድየም ዙሪያም የአማራ ክልል ከሦስት ቀናት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ካፍ ስቴድየሙ ‹‹ማሟላት አለበት›› ብሎ በሰጠው ምክረሃሳብ መሠረት ሥራዎች እየተከናወኑ በሚገኙበት ወቅት መታገዱ ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል። ያምሆኖ ስቴድየሙ አስፈላጊውን መስፈርት አሟልቶ ግንባታው እንዲጠናቀቅ የፌዴራል መንግሥትን ድጋፍ እንደሚሻ ተጠቁሟል።
የፌዴራል መንግሥት የአገሪቱ ስቴድየሞች የገጠሟቸውን ችግሮች ለመቅረፍና እየተገነቡ የሚገኙት ስቴድየሞችም በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቁ የካፍ እገዳ የማንቂያ ደውል ሆኖለታል ማለት ይቻላል። መንግሥት ስቴድየሞቹን በተመለከተ የአጭርም ይሁን የረጅም ጊዜ የመፍትሄ አቅጣጫ ማስቀመጡን ይፋ ባያደርግም እያስገነባ ለሚገኘው ብሔራዊ ስቴድየም ትኩረት እንደሰጠ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሰሞኑን ያደረጉት የመስክ ጉብኝት አመላካች መሆኑ ተጠቁሟል።
የአገሪቱን ስፖርት እንዲመሩ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ከትናንት በስቲያ የብሔራዊ ስቴድየም ግንባታውን ጎብኝተዋል። 62 ሺ ተመልካቾችን የማስተናገድ አቅም አለው የተባለለት እና ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው የ2ኛው ምዕራፍ ግንባታ ጅማሮ በ900 ቀናት ውስጥ ከ5 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠናቀቃል ተብሎ የነበረውን የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ግንባታ አስመልክቶ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩና ሚኒስትር ዴኤታው አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንዲሁም የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን የስቴድየሙን የግንባታ ሂደት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ስምንት ቢሊዮን ብር ወጪ የሚደረግበት የአደይ አበባ ብሔራዊ ስቴዲየም በቻይና የኮንስትራክሽን ኩባንያ እና በኢትዮጵያዊው ኤም ኤች ኢንጂነሪንግ አማካሪነት ግንባታው እየተከናወነ ይገኛል። ከሦስት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አዲሱ አረጋ፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት በተገኙበት የስቴድየሙ የመስክ ጉብኝት ወቅት አጠቃላይ የስቴድየሙ ግንባታ ሂደት ያለበት ሁኔታ እና ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ በአማካሪ ድርጅቱ ማኔጂንግ ዳይሬክተር በዶክተር ኢንጅነር መሰለ ኃይሌ እና የግንባታውን ሂደት በሚከታተሉት በአቶ አስመራ ግዛው ገለፃ ተደርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም መንግሥት ስታዲየሙ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ያጋጠሙ ችግሮችን እንደሚፈታ ገልፀው፣ ግንባታው በአጭር ጊዜ ጥራቱን ጠብቆ እንዲጠናቀቅ እና ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆን የሥራ መመሪያ መስጠታቸው ታውቋል። ይህም በሌሎች ክልሎች እየተገነቡ የሚገኙትን ስቴድየሞች ጨምሮ ብሔራዊ ስቴድየሙ በፍጥነት ተጠናቆ አሁን ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ትልቅ ተስፋ እንዲጣልበት አድርጓል፡፡ ብሔራዊ ስቴድየሙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን አሟልቶ፣ የኦሊምፒክና የዓለም ዋንጫ ውድድሮችን ማስተናገድ በሚችል መልኩ በመገንባት ላይ እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን እስካሁን ባለው የግንባታ ሂደት ከ5 ነጥብ 57 ቢሊዮን ብር በላይ እንደወጣበት መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የ2ኛው ምዕራፍ ግንባታ፤ በዘጠኝ መቶ ቀናት ይጠናቀቃል ተብሎ ከዓመት በፊት የተጀመረ ሲሆን አጠቃላይ የግንባታ ወጪው ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነ ታውቋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ የመጫወቻ ሜዳውን ሳር ማልበስ፣ የመሮጫ ትራክ ማንጠፍ፣ የስቴድየሙን ጣሪያ ማልበስና ወንበር መግጠም እንዲሁም የቴክኖሎጂ ገጠማና አጠቃላይ የስቴድየሙን ዙሪያ የማስዋብ ሥራን ያካትታል። የግንባታውን አፈፃፀምና የደረሰበትን ደረጃ እንዲሁም የቀጣይ የሥራ ዕቅድ በየጊዜው እየተገመገመ የሚገኝ ሲሆን ግንባታው ከተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ባጠረ ጊዜ እንዲጠናቀቅ በቂ የሰው ኃይል ሊሟላ እንደሚገባና አስፈላጊም ከሆነ ተጨማሪ ሰዓት በመጠቀም ፕሮጀክቱን ለመጨረስ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ከዚህ ቀደም አቅጣጫ መቀመጡ ይታወሳል፡፡ የስቴድየሙ ግንባታ በ48 ነጥብ 8 ሄክታር ላይ ያረፈ ሲሆን፤ 62ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅምም ይኖረዋል። የዓለም ዋንጫና ኦሊምፒክን የማስተናገድ አቅም ያለው ስቴድየሙ፤ ከእግር ኳስና አትሌቲክስ ስፖርቶች ባሻገር ለሌሎች ስፖርቶች መወዳደሪያ የሚውሉ ስፍራዎችን በዙሪያው ያጠቃልላል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2014