የህልውና ጉዳይ ከመኖርና ካለ መኖር ጋር የተያያዘ፤ በታሪክ ውስጥ ያለን ማንነት ከማስቀጠልና ከመጥፋት ጋር የተቆራኘ ነው። ነገን ግራ በተጋባ ማንነት ከመጠበቅና ነገን ከትናንት ማንነት ላይ ተመስርቶ አሳድጎ ከማስቀጠል ጋር የተያያዘ እውነታ ነው። ከዚህ የተነሳም የጀመርነው የህልውና ዘመቻ ከየትኞቹም ዘመቻዎች በላይ ከፍ ያለ ቁርጠኝነት እና ከዚህ የሚመነጨ መስዋዕትነት የሚጠይቅ ነው።
አሸባሪው ሕወሓት ከፍጥረቱ ጀምሮ የአገርን ህልውና አደጋ ውስጥ የሚከቱ ተግባራትን ሲፈጽም ቆይቷል። የትግራይን ሕዝብ ከፍጥረታዊ የማንነቱ ምንጭ ከኢትዮጵያዊነቱ ለመነጠል ከመሞከር አንስቶ መላውን የአገሪቱን ሕዝብ በዘር እና በሃይማኖት በመለያየት የተከፋፈለች አገር ለመፍጠር ብዙ መንገድ ተጉዟል።
የአገርን ሀብት መዝረፍን ጨምሮ በተደራጀና በተጠና መልኩ የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር የሄደባቸውም ሴራዎች የሕዝባችንን ማደግና አድጎም በራሱ የመተማመን መንፈስ ሲያቀጭጭ ቆይቷል። ለታሪካዊ ጠላቶቻችን የልብ ልብ የሚሰጡ፤ አገርን እንደ አገር አደጋ ውስጥ የሚከቱ እኩይ ተግባራትንም ፈጽሟል።
ከሥልጣንና ከሥልጣን ለሚመነጭ ያልተገባ ጥቅም ብቻ እራሱን ያስገዛውና ከፍጥረቱም በዚሁ መንገድ የተገራው ይህ ቡድን፤ በሕዝባዊ ትግል ከሥልጣን ከተወገደ ማግስት ጀምሮ የአገርና የሕዝብን ህልውና አደጋ ውስጥ በሚከቱ የሴራ ተግባራት ተ ጠምዶ ቆይቷል።
በተለይም በሥልጣን ዘመኑ አገርን በማዳከምና በመከፋፈል የሠራቸውን ሴራዎች የአቅሙ ምንጭ በማድረግ በውስጡ የፈጠረው ያልተገባ እብሪት ከራሱ አልፎ እንደ አገር መላው ሕዝባችንን፤ እንደ ክልል ደግሞ የትግራይን ሕዝብ ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። ልጆቹን ባልተገባ መንገድ ላልተገባ አላማ ለእልቂት እየዳረገ ነው።
ቡድኑ ከጥፋት መንገዱ ላለመመለስ ከያዘው ግትር አቋም የተነሳም በጥፋት መንገዱ የትግራይ ሕዝብ ለነገዎቹ ተስፋ ያደረጋቸውን ልጆቹን ላልተገባ ጦርነትና ጊዜ ባለፈበት የጦርነት ስልት ለእልቂት እየዳረገ ነው። ይህን እውነት ዛሬ ላይ ከትግራይ ሕዝብ ለመደበቅ ቢቻልም ነገ ግን የአደባባይ ምስጢር መሆኑ የማይቀር ነው።
ቡድኑ በአንድ በኩል ከመጣበት በንጹሀን ደም ከተገነባ የአሸናፊነት እና የተሸናፊነት ትርክት ለመውጣት የሚያስችል አስተሳሰብ ዝግጁነት በማጣቱ ለአሸናፊነት የትግራይን ሕዝብ እንደ ሕዝብ ማስያዣ አድርጎ የጀመረው ቁማር ዘመኑን የማይመጥን መሆኑ፤ በሌላ መልኩ ሽንፈቱን ቀድሞውኑ በአስተሳሰብ ደረጃ የራሱ ያደረገውና በምንም መልኩ ሊቀለብሰው የሚችል አለመሆኑን መረዳት አለመቻሉ ራሱ እንደ ቡድን ሊከፍልም ሆነ የትግራይን ሕዝብ እንደ ሕዝብ እያስከፈለ ያለው ዋጋ ትርጉም አልባ ያደርገዋል።
ቡድኑ በአሁኑ ወቅት እያካሄደ ያለው፤ ባልተገባ የአስተሳሰብ መሠረት ላይ የተመሠረተ፤ ፍጹም ጭፍንና በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መንፈስ የተቃኘ፤ በአጥፍቶ ጠፊነት የተስፋ መቁረጥ ጽልመት የተገራ አገር የማፍረስ ሴራ ሁሉም ዜጋ በአግባቡ ሊረዳው የሚገባ ነው። በተለይ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ በስሙ የሚነገድበት ከመሆኑ አንጻር ከፍ ባለ ትኩረት ሊከታተለው ይገባል።
የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ቡድን አገር የማፍረስ ሴራ ራሱን በማቀብ፤ በየዘመኑ ከፍያለ ዋጋ በመክፈል ለዚህ ትውልድ ያደረሳትን አገሩን ከዚህ አሸባሪ ቡድን ለመታደግ በሚካሄደው የህልውና ዘመቻ እንደ ዜጋ፤ የዜግነት ኃላፊነቱንና ግዴታውን ለመወጣት ራሱን በአዲስ መልክ ማዘጋጀት ይጠበቅበታል።
የትግራይ ሕዝብ ማንነት በአንድ አገር ጠል በሆነ፤ ከአገርና ከሕዝብ ይልቅ የቡድንን ፍላጎት በሚያስቀድም፤ ለዚህም ሲል አገርን የመስዋእት በግ አድርጎ ለማቅረብ ወደ ኋላ በማይል ቡድን የሚወሰን አይሆንም። ይህ በመጪዎቹ ዘመናት የታሪክ ተጠያቂነትን ሊያመጣ እንደሚችል በአግባቡ ለማጤን ጊዜው አሁን ነው።
ከዚህ ታሪካዊ እውነታ በመነሳትም የትግራይ ሕዝብ አገሩን እንደሚወድና በዘመናት ውስጥም ስለ አገሩ ብዙ ዋጋ እየከፈለ እንደመጣ ሕዝብ ነገሮችን ሰከን እና ቆም ብሎ ሊያስተውል ይገባል። ማንነቱን ከፍ ያለ ራስ ወዳድነት በተጠናወተው እና አገር ጠል በሆነ ቡድን እንዲወሰንለት ዕድል መስጠት ሆነ መፍቀድ አይኖርበትም።
እስከዛሬ በመጣበትም መንገድ ይህ ቡድን በስሙ እየማለና እየተገዘተ የፈጠረለት ነገር የለም። ባለፉት 27 አመታት እንኳን ብቻ ለትግራይ ሕዝብ በተጠና መልኩ ጠላት ከመፍጠርና ሕዝቡን እንደ ሕዝብ ስጋት ውስጥ እንዲገባ ከማድረግ ባለፈ ያመጣለት ሆነ የፈጠረለት አንዳች ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ በስሙ ከፍ ባለ ዘረፋና ሌብነት፤ አገር የማዳከምና የማፍረስ ሴ ራ ውስጥ ተጠምዶ መቆየቱ የአደባባይ ም ስጢር ነው።
አሸባሪ ቡድኑ የትግራይን ሕዝብ ሲጠብቅና ሕይወቱን ብቻ ሳይሆን ጉልበቱን ጭምር ለግሶ ሲያገለግለው በነበረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት በመፈጸም በተጨባጭ የትግራይ ሕዝብ ጠላት መሆኑን አስመስክሯል።
ይህ ነፍሰ ገዳይ አሸባሪ ቡድን አገር ለማፍረስ እያደረገ ያለውን የአልሞትባይ ተጋዳይነት መወራጨት መደገፍ በራሱ የቡድኑን ፍጥረታዊ ሞት ባያስቀረውም፤ በታሪክ ተጠያቂ ስለሚያደርግ እውነታውን በአግባቡ ማጤን ተገቢ ነው። በተለይም የትግራይ ሕዝብ ለዚህ ቡድን ዕድሜ መግዣና መሸሸጊያ ሊሆን አይገባም።
ከዚህ ይልቅ ቡድኑ ዕድሜውን ለማርዘም በከፈተው የእብሪት ጦርነት በየተራራውና ጢሻው ወድቀው ስለቀሩ ልጆቹ መጠየቅ የሚገባውን ለመጠየቅ ራሱን ከወዲሁ ማዘጋጀት ይኖርበታል። አሁን የጀመረውንም አሸባሪውን የመቃወም ተግባር አስፋፍቶና አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል።
መላው ሕዝባችንም የህልውናው ዘመቻ የህልውና ጉዳይ፤ በታሪክ ውስጥ ያለን ማንነት ከማስቀጠልና ከመጥፋት ጋር የተቆራኘ መሆኑን ተገንዝቦ፤ ዘመቻው በሚጠብቀው ደረጃ ራሱን በማዘጋጀት በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ይህም በታሪክ ከፍያለ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑንም በአግባቡ መረዳት ያሻል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2014