ወጣቷና ባለተሰጥኦዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ለተሰንበት ግደይ በአስደናቂ የዓለም ክብረወሰኖቿ ዓለምን ማስደመም ቀጥላለች። በረጅም ርቀት ንግሥቷ ጥሩነሽ ዲባባ ከዐሥራ ሁለት አመታት በላይ ተይዞ የቆየውን የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ከአመት በፊት ቫሌንሲያ ላይ በመስበር የማይቻል የሚመስለውን ስኬት የተጎናጸፈችው ለተሰንበት የውድድር አመቱን ለማመን የሚከብድ ሌላ ክብረወሰን በመስበር ነበር ያጠናቀቀችው። ይህም በሪዮ 2016 ኦሊምፒክ አስደናቂዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አልማዝ አያና ያሻሻለችው የ10ሺ ሜትር ክብረወሰን በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፋን ሃሰን ባለፈው አመት ተሰብሮ አርባ ስምንት ሰዓት ሳይሞላው ለተሰንበት በኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር ሄንግሎ ላይ የግሏ ያደረገችበት ታላቅ ስኬት ነው።
በሁለቱ ታላላቅ የዓለም ክብረወሰኖች ደምቃ ወደ ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ያቀናችው ለተሰንበት በታላቁ የስፖርት መድረክ በ10ሺ ሜትር ኢትዮጵያን ወክላ የጠበቀችውን ወርቅ ማጥለቅ ባትችልም የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፏ ይታወሳል። ይህም ውጤት ከጠበቀችው የወርቅ ሜዳሊያ አኳያ ያስከፋት ነበር። ለተሰንበት በኦሊምፒክ የጠበቀችውን ወርቅ አጥታ ስሜቷ ተጎድቶ ቢያስለቅሳትም ነገም ሌላ ቀን ነውና ባለፉት ጥቂት ወራት ጠንክራ ሰርታ የኦሊምፒክ ቁጭቷን በሌላ ተጨማሪ የዓለም ክብረወሰን ማካካስ ችላለች።
ለተሰንበት ከኦሊምፒኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትናንት በስቲያ በተወዳደረችበት የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ውድድር የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን በመስበር አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ የሦስት ታላላቅ የዓለም ክብረወሰኖች ንግሥት ሆናለች። ለተሰንበት በርቀቱ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ብትወዳደርም የቀድሞውን ክብረወሰን ከአንድ ደቂቃ በላይ በማሻሻል ዓለምን አስደምማለች። ለተሰንበት ርቀቱን 1:02:52 ያጠናቀቀች ሲሆን የቀድሞው ክብረወሰን ባለፈው ሚያዝያ በኬንያዊቷ አትሌት ሩዝ ቺፕጌቲች 1:04:02 በሆነ ሰዓት የተመዘገበ ነበር።
የ23 አመቷ ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት ባለፈው አመት የ5ሺ ሜትር ክብረወሰኑን በጨበጠችበት ቫሌንሲያ ከተማ የግማሽ ማራቶን ክብረወሰን በመድገሟ ‹‹ቫሌንሲያ ትመስገን፣ በመጀመሪያ የግማሽ ማራቶን ውድድሬ የዓለም ክብረወሰን በማሻሻሌ በጣም ተደስቻለሁ›› በማለት ውድድሯን ስትፈጽም ተናግራለች። በመጀመሪያ የዓለም ክብረወሰኗ የዓለም መነጋገሪያ ያደረገቻት ቫሌንሲያም በግማሽ ማራቶን ከ63 ደቂቃ በታች ውድድሯን የፈጸመች በታሪክ የመጀመሪያዋ አትሌት እንድትሆን አድርጋታለች።
ለተሰንበት በወንድ አሯሯጭ ታግዛ ከውድድሩ መጀመሪያ አንስቶ ከሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ጋር ያደረገችው አስደናቂ ፉክክር ለክብረወሰኑ መሰበር ትልቅ ሚና ነበረው። አትሌት ያለምዘርፍ በቅርቡ በሰሜን አየርላንድ ባደረገችው የግማሽ ማራቶን ውድድር ርቀቱን 1:03:44 በሆነ ሰዓት የዓለም ክብረወሰን ብታሻሽልም ያስመዘገበችው ሰዓት እውቅና እንዳልተሰጠው ይታወሳል። ያለምዘርፍ በዚህ እልህ ለሌላ ክብረወሰን ከለተሰንበት ጋር አስደናቂ ፉክክር ብታደርግም እስከመጨረሻ መጓዝ አልቻለችም። ያምሆኖ 1:03:51 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ሰዓት ቀድሞ በኬንያዊቷ አትሌት ከተመዘገበው የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል። በተመሳሳይ ሦስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኬንያዊቷ ሼላ ቺፕኪሩይ ያጠናቀቀችበት 1:04:53 ሰዓትም ከቀድሞው ክብረወሰን የተሻለ ፈጣን ሰዓት ሆኗል።
በተመሳሳይ በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር የሁለት ጊዜ የ5ሺ ሜትር የዓለም ቻምፒዮኑ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሙክታር ኢድሪስ ትልቅ ያሸናፊነት ግምት ቢሰጠውም ውድድሩን 58:40 በሆነ ሰዓት ስድስተኛ ሆኖ አጠናቋል። ኬንያውያን በበላይነት ባጠናቀቁበት ውድድር አቤል ኪፕቹምባ 58:03 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ያስመዘገበው ሰዓት በርቀቱ በታሪክ ስድስተኛው ፈጣን አትሌት አድርጎታል። ሌላኛው ኬንያዊ ሮኔክስ ኪፕሩቶ 58:09 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ዳንኤል ማቴኮ 58:26 በሆነ ሰዓት ሦስተኛ ሆኗል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2014