ወቅቱ የጦርነት ወቅት ነው። ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ የሚወጡ መረጃዎች በአብዛኛው ተዓማኒነት የሚጎድላቸው እና የተለያዩ በመሆናቸው ኅብረተሰቡን ብዥታ ውስጥ እየጨመሩት ይገኛሉ። በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ሕወሓት የሚያሰራጫቸው መረጃዎች በአብዛኛው በውሸት ላይ የተመሠረቱ እንደሆኑ ታይቷል። በአንጻሩ መንግሥት ደግሞ አሁን እየተሻሻለ ቢመጣም በአብዛኛው ዝምታን መምረጡ በመረጃ ፍሰቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ ይነገራል።
በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት እየተከሰተ ባለው የመረጃ መዛባት ሂደት ውስጥ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መዋቅር መፍረስ የፈጠረው ተፅዕኖ እንዲሁም በአሁኑ የመንግሥት መዋቅር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መልሶ መዋቀሩ ችግሩን ለማቃለል የሚኖረውን ጠቀሜታ በሚመለከት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ ወርቁን አነጋግረን እንዲህ አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ተያይዞ የሚወጡ መረጃዎች በአብዛኛው ተዓማኒነት የሚጎድላቸው እና የተለያዩ ናቸው። ይህም ኅብረተሰቡ የተለያየ አቋም እንዲይዝ ሆኗል የሚሉ አሉ፤ ይህ በእርስዎ እይታ እንዴት ይታያል?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ፡- በዚህ ሃሳብ ላይ እኔም ከሞላ ጎደል እስማማለሁ። ምክንያቱም ከጦርነቱ በፊትም አገራችን ላይ ያለው የመገናኛ ብዙኃን ሥርዓት በተዓማኒነት የተገነባ አልነበረም። ስለዚህ በችግር ወቅት ሰዎች የፈለጉትን መረጃ ለማግኘት አምነው የሚቀበሉት የመገናኛ ብዙኃን ማግኘት አልቻሉም። ስለዚህ በደህና ጊዜ የመገናኛ ብዙኃን ስላልተሰራበት፤ ኅብረተሰቡ ‹‹በማንኛውም ሁኔታ ተዓማኒነት ያለው የዜና ምንጬ ይህ ነው›› ብሎ የሚቀበለው የመገናኛ ብዙኃን ተቋም ቢኖር ኖሮ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎችን በቀላሉ የማመን ዕድል እና መረጃዎችን የመቀበል እና በነዛ መረጃዎች ላይ የመንተራስ ሒደት ይኖር ነበር።
አሁን ከመገናኛ ብዙኃኑ የሚገኙት መረጃዎች የወጥነት ችግር የሚታይባቸው ናቸው። ከዋናው መገናኛ ብዙኃንም ሆነ ከማህበራዊ ሚዲያው ከተለያዩ ምንጮች የሚገኙ መረጃዎች እርስ በእርሳቸው የሚጣረሱ ናቸው። የትኛው ትክክል ነው ብሎ መዝኖ ለመቀበል ጊዜ እና ዕውቀት ይፈልጋሉ። ብዙ ግራ የሚያጋባ መረጃ በሚወጣበት ሰዓት ማኅበረሰቡ ብዥታ ይፈጠርበታል። አምኖ የሚቀበለውን መለየት አይችልም። ግራ ያጋባል። ስለዚህ አሁንም ሰዎች መረጃዎችን ሲያዳምጡ ከአንድ መገናኛ ብዙኃን ወደ ሌላ መገናኛ ብዙኃን ሲቀይሩ ወጥነት የሌለው መሆኑ ብዥታ ውስጥ እየጨመራቸው ነው የሚለው ያስማማል። የአቀራረብ ልዩነት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን መሠረታዊ መረጃዎች ላይ ልዩነት መኖር አልነበረበትም። አሁን ግን ይህ ይታያል።
በተጨማሪ አንዱን ዜና አምነው ከተቀበሉ በኋላ ደግሞ የተወሰነ ቆይቶ፤ ዜናው ውሸት ሆኖ ይገኛል። አንድ አድማጭ ወይም ተመልካች ዜናውን እውነት ነው ብሎ ወስዶት ከሁለትና ሦስት ቀን ወይም ከአንድ ሳምንት እና ከአንድ ወር በኋላ ዜናው ስህተት ነበር ብሎ ያው ዜናውን የገለፀው የመገናኛ ብዙኃን ሌላ ዜና ሲያቀርብ ተአማኒነቱን ጥያቄ ውስጥ ይጨምረዋል። እነዚህ በዋነኛነት አድማጭም ተመልካችም ላይ ብዥታ የሚፈጥሩ ጉዳዮች ናቸው የሚል እምነት አለኝ። ምናልባት እነዚህ ችግሮች ባይኖሩ ሰዎች በቋሚነት የሚያገኟቸውን የመረጃ ምንጮች የማመንና ብዥታ ውስጥ ያለመግባት ዕድሉ ከፍተኛ ይሆን ነበር።
አዲስ ዘመን፡- ስለዚህ እነዚህ ችግሮች ኅብረተሰቡ ብዥታ ውስጥ እንዲገባ እና አቋሙን እንዲቀያይር አድርገውታል ማለት ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ፡– አዎ! የራሳቸው አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል። ምክንያቱም አቋም የሚያዘው ትክክለኛ መረጃ ማግኘት ሲቻል ነው። ትክክለኛ መረጃ ካልተገኘ እንዴት አቋም መያዝ ይቻላል? ስለዚህ እነዚህ ጉዳዮች አቋም እንዳይያዝም ችግር ፈጥረዋል ብዬ አስባለሁ። ሰዎች ውሳኔያቸውን የሚቃወሙትን እና የሚደግፉትን ለመለየት ትክክል ነው ወይም አግባብ አይደለም ለማለት የሚሰሙት እና የሚያዩት ላይ እርግጠኛ መሆን ይፈልጋሉ። ያለበለዚያ ምላሽ የሚሰጠው በስሜት ይሆናል። ያ ደግሞ የማኅበረሰቡ ስሜት እንዲቀያየር አድርጓል።
በስሜት የሚመሩ ከሆነ እንዲሆን የሚመኙት ነገር ሲደረግ ጉዳዩን መጋራት እና ማጋራት ይኖራል። በተቃራኒው ሲሆን ደግሞ ስሜትን ስለሚጎዳ ማዘንና መቃወም ይፈጠራል። ስለዚህ የመረጃ አሰጣጥ ሁኔታው ወጥ የሆነ አቋም እንዳይኖር የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል ብዬ አምናለሁ። ትክክለኛ እና ተአማኒነት ያለው የመረጃ ምንጭ ቢኖር ሰዎች በቋሚነት ተአማኒነት ባለው የመረጃ ምንጭ ላይ ጥገኛ ሆነው አቋማቸውን በደንብ ማሳየት ይችሉ ነበር። የሁላችንንም ግራ የመጋባት ዕድላችንንም ይቀንስ ነበር።
አዲስ ዘመን፡- በተለይ በእንዲህ ዓይነት የጦርነት ወቅት የሚተላለፉ መረጃዎች በትክክል ኅብረተሰቡ ጋር እንዲደርሱ ምን መደረግ አለበት?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ፡- አንደኛ መገናኛ ብዙኃን ይህንን አጋጣሚ ተጠቅመው ትክክለኛ እና ወጥነት ያላቸው መረጃዎችን በአግባቡ ማድረስ ይጠበቅባቸዋል። ብዙ የምንስማቸው ዜናዎችና መረጃዎች ‹‹አሉ›› የሚባሉ ዓይነት ጉዳዮች ናቸው። በተጨባጭ መረጃ ላይ (ፋክት) ላይ የተመሠረቱ አይደሉም። ወደ ፕሮፖጋንዳ የሚያደሉ መረጃዎች ይታያሉ። በእርግጥ ፕሮፖጋንዳ በራሱ ለትግሉ የሚጫወተው ሚና ይኖራል። ነገር ግን ደግሞ ሰዎች በተጨባጭ ዕውነታ እና በስሜት መካከል ያለውን ለመለየት እንዳይቸገሩ የሚሠሩ ዜናዎችና የሚሰራጩ መረጃዎች በተቻለ መጠን ዕውነታን መሠረት ያደረጉ መሆን አለባቸው። ነገ የተሠራው ዜና ውሸት አለመሆኑ ከተረጋገጠ ከቀን ወደ ቀን መገናኛ ብዙኃን ተዓማኒነታቸውን እየገነቡ መሔድ ይችላሉ። ነገር ግን ይህ ጊዜ የወሰደ ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃን ባለፉት 27 ዓመታት በመንግሥት እጅ ስር ነበሩ። እነዚህ የመገናኛ ብዙኃን የመንግሥት አፍ ሆነው ያገለግሉ ስለነበረ አድማጭ ተመልካች ላይ ያለው እምነት በጣም የተሸረሸረ ነበር። ስለዚህ ከዚያ ተላቀው የተሻለ ለመሆን ጥረት እያደረጉ አሁን ደግሞ ጦርነቱ መጣ ማኅበረሰቡ ደግሞ አሁንም ከነበረው አመለካከት አልወጣም። አሁንም ኅብረተሰቡ የሚያስበው መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት አፍ ናቸው። ለፕሮፖጋንዳ የሚውሉ ናቸው። የሚያቀርቧቸው መረጃዎች እውነታነት የላቸውም በማለት ነው። ነገር ግን የመገናኛ ብዙኃን እግረ መንገዳቸውን ኅብረተሰቡ ከዚያ እሳቤ ውስጥ እንዲወጣ ማድረግ አለባቸው።
ኅብረተሰቡ አንድ የዜና ምንጭን መርጦ ለመከታተል የሚመዘንበት ወይም የሚያረጋግጥበት የተለያዩ ሁኔታዎች ይኖራል። ይኽኛው የተሻለ እውነተኛ ዜና እያቀረበ ነው። ብሎ የሚመረጥበት ሁኔታ እንዲኖር የመገናኛ ብዙኃን የሚያቀርቡትን ዜና ቢያንስ እውነታዎቹ (ፋክቶቹ) እርስ በራሳቸው ሳይጣረሱ መቅረብ አለባቸው። የአቀራረብ ሂደታቸው እንኳን ቢለያይም መሠረታዊ እውነታዎቹ ወጥነት ሊኖራቸው ይገባል ብዬ አስባለሁ። ወጥነት ሲኖር አድማጭ ተመልካቹ ከአንዱ ጣቢያ (ቻናል) ወደ ሌላው ጣቢያ ሲሸጋገር የሚፈጠርበት ብዥታ ይሰብራል። ጦርነቱ የአገር ጉዳይ ነው። አገርን እያገለገሉ እስከሆነ ድረስ መገናኛ ብዙኃኑ ቢያንስ የተናበበ እና ላይ እና ታች ያልሆኑ መረጃዎች ቢያቀርቡ በሰዎች ላይ የሚፈጠረውን ብዥታ ለመቀነስ አመቺ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ሕወሓት የሚያሰራጫቸው መረጃዎች በአብዛኛው በውሸት ላይ የተመሠረቱ ናቸው። በአንጻሩ መንግሥት ደግሞ አሁን እየተሻሻለ ቢመጣም በአብዛኛው ዝምታን መምረጡ በመረጃ ፍሰቱ ላይ ተፅዕኖ መፍጠሩ ይነገራል። ይህ የሚያስከትለውን ጉዳት እንዴት ያዩታል?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ፡- ጉዳቱ እጅግ ከፍተኛ ነው። አንዳንዴ ዝምታ እንደስምምነት ይቆጠራል ይባላል። ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በማኅበራዊ ሚዲያው የሚወጡ የተለያዩ የሃሰት ዜናዎች ተደራሽነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ ማኅበረሰቡን በአብዛኛው እየበጠበጡ ለከፋ ቀውስ ዳርገውታል። አሸባሪው ሕወሓት በጦርነቱ ትልቁን ሚና እየተጫወተላቸው ያለው የሚለቀው የሐሰት መረጃ ትልቅ ቀውስ ማስከተሉ ነው። ለምሳሌ አንድ ቦታ ሳይገቡ የሆነን ቦታ ተቆጣጥረናል የሚል ፎቶ በመልቀቅ እዚያ አካባቢ የሚኖረው ማኅበረሰብ ተደናግጦ የሚሰደድበት እና አካባቢውን ለቀው የሚሔዱት ሁኔታ ሰፊ ነበር። ይህ የመጣው ማኅበራዊ ሚዲያውን በከፍተኛ መጠን መጠቀም በመቻላቸው ነው። እስከ አሁን የታዩት ብዙ ቀውሶች በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሃሰት መረጃ ላይ ተንተርሰው የሚመጡ ብዙ ነገሮች ነበሩ። ስለዚህ በመንግሥት በኩል በሐሰት የሚመጡ መረጃዎች ላይ በትክክለኛ መረጃ እየተኩ ወዲያው በፍጥነት ማድረስ ካልተቻለ ከዚህ በፊት የተፈጠረው ዓይነት ቀውሶች እየቀጠሉ መሔዳቸው የማይቀር ነው።
በእርግጥ በሁለቱም በኩል ማለትም በመንግሥትም ሆነ በአሸባሪው ቡድን በኩል ለየራሳቸው ፕሮፖጋንዳ አስፈላጊ መሆኑ ይታመናል። ነገር ግን ፕሮፖጋንዳውንም ውጤታማ በሆነ መልኩ እየተጠቀመበት ያለው ማን ነው ከተባለ መልስ መስጠት አያዳግትም። መንግሥት ሥራውን እየሠራ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ስለሚፈጠሩ ነገሮች እና ስላሉ ሁኔታዎች በየጊዜው እየተከታተለ መረጃዎችን ማድረስ ያለበት አካል ትልቅ ክፍተት አለበት።
ሰዎች የመረጃ ክፍተት ባለበት ሰዓት የሚያገኙዋቸው መረጃዎች ሐሰትም ቢሆኑ ከመስማት ወደ ኋላ አይሉም። ስለዚህ በሌላ በኩል ለሚመጡ የተሳሳቱ መረጃዎች እና ፕሮፖጋንዳዎች የመጠቃት ዕድላቸው ሰፊ ነው። ስለዚህ ያ ክፍተት ለአሸባሪው ቡድን የመረጃ ጦርነቱን በመምራት በኩል ትልቅ መንገድ ሰጥቶታል። እንደዚህ ዓይነት የችግር እና የግጭት ሁኔታዎች ላይ ብዙ ጊዜ ሰዎች በቂ መረጃ ማግኘት ይፈልጋሉ። ባሉበት አካባቢ ስለተፈጠረው እና ስለሚፈጠረው ነገር ማወቅ እና ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሊረዱ ይገባል። ለምሳሌ ግጭት ቢኖር ከባድ መሣሪያ ቢተኮስ ሰዎች ምን ማድረግ አለባቸው የሚለውን በአካባቢው ባሉ ባለሥልጣናት እና የመንግሥት አካላት መረጃ መሰጠት አለበት።
በመንግሥት በኩል መረጃው ወጥተህ ተዋጋ፤ አገር ለቀህ ተሰደድ ወይም ቤት ተቀመጥም ሆነ ሌላ መረጃ መሰጠት አለበት። ነገር ግን ምንም ዓይነት መረጃ እየተሰጠ አይደለም። በዚህ ጊዜ ማኅበረሰቡ ምን ማድረግ እንዳለበት መረጃ ይፈልጋል። ለምሳሌ ኮቪድ 19ኝን መውሰድ ይቻላል። ይህ የጤና ዕክል ወይም ወረርሽኝን ለመከላከል ከሰዎች መራቅና ንፅህናን መጠበቅ የመሳሰሉ ጉዳዮች በተለያዩ መንገዶች መረጃዎችን የጤና ሚኒስትሯ እና ሌሎችም የሚመለከታቸው አካላት ሲገልፁ ነበር። ስለዚህ ሰዎች ስለሚፈጠረው ጉዳይ ማወቅ አለባቸው። መንግሥትም ማሳወቅ አለበት።
መንግሥት አንዳንድ ነገሮች ማለትም ወታደራዊ መረጃዎች እና ጥንቃቄን የሚፈልጉ ነገሮች ላይ ሊቆጠብ ይችላል። ይህንን መረጃ መንግሥት እንዲሰጥ አይጠበቅም። ነገር ግን ከዳኝነት አንፃር ሰዎች ቀጥሎ የሚያደርጉትን እንዲያውቁ እና እንዲፈፅሙ ስለሁኔታዎች ቢያንስ በቂ መረጃ መስጠት እና ቀጥሎ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማወቅ ይፈልጋሉ። ይህንን የሚደርግ የመንግሥት አካል መኖር አለበት የሚል አስተያየት አለኝ።
አሁን ላይ ብዙኃኑ በአንድ ጉዳይ ላይ ማንን እንደሚያናግር እንኳ አያውቅም። የሆነ ነገር ቢፈጠር ስልክ በመደወል እንዲህ ዓይነት ነገር በአካባቢዬ አለ። ምን ላድርግ ወይም እየተፈጠረ ያለው ምንድን ነው ተብሎ የሚጠየቅ አካል የለም። የከተማ አስተዳደር የቢሮ ስልኮችም በጣም ውስን ናቸው። በአንዴ ከአንድ ወይንም ከሁለት ሰው በላይ አያስተናግዱም። ስለዚህ ሰዎች ድንጋጤ ውስጥ በሚገቡበት ሰዓት ያገኙትን መረጃ የማመን ዕድላቸው ሰፊ ይሆናል። ድንጋጤ ውስጥ ሆነው ለመጣራት ጊዜ አያገኙም። ስለዚህ ማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚያገኙትን የተሳሳተ መረጃ አምነው በመቀበል ወደ ድርጊት ይገባሉ። ለዚያም ነው ብዙ ጊዜ ከሕወሓት ጋር ተያይዞ በማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚለቀቁ መረጃዎች ቶሎ ተዳርሰው ሰዎች አካባቢውን ለቅቀው የሚሰደዱት። ነገር ግን ማህበረሰቡን የሚያረጋጋ እና ይህንን ክፍተት የሚሞላ አካል ቢኖር ምላሽ የመስጠት ዕድላችን ሰፊ ይሆናል ብዬ አስባለሁ።
አዲስ ዘመን፡- የማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚሰራጨውን የተዛባ መረጃን ለመከላከል መሠራት ያለበት በምን መልኩ ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ፡- በሁለት መንገዶች ነው። አንደኛው በዚያው በማህበራዊ ሚዲያው የተሳሳተ መረጃ መሆኑን በተጨባጭ ማስረጃ ማሳየት መቻሉ የተሳሳተ መረጃ ያገኙ እና የተደናገጡ ሰዎችም ቆም ብለው እንዲያስቡ ያደርጋቸዋል። ትክክለኛ መረጃውን ሲያገኙ ወደ ድርጊት የሚመጡበት ሁኔታ አይኖርም። ይህኛው እንዲህ እያለ ቢሆንም በተቃራኒው የተላለፈውን መረጃ በማየት ትክክለኛው የትኛው ነው የማለት እና ለማጣራት የመንቀሳቀስ ሁኔታ ይኖራል። ዋናዎቹ የመገናኛ ብዙኃንም እነዚህ መረጃዎች ሐሰተኛ ናቸው ማለታቸው የበለጠ በመንግሥት በኩል የሚተላለፈው መረጃ ትክክለኛ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ እና ጥንካሬ የሚሰጥ ይሆናል። መረጃው ሰዎች እንዲረጋጉ እና ባሉበት እንዲቆዩ የማድረግ ዕድልን ሰፊ ያደርገዋል።
ለወትሮ ድሮ ድሮ ወላጆቻችን ሬዲዮ የተናገረው ሁሉ እውነት ነው የሚል ዕምነት ነበራቸው። አሁን ግን ያ ነገር እየመነመነ መጥቶ ይበልጥ የማህበራዊ ሚዲያው ተአማኒነት ማግኘት ጀምሯል። ስለዚህ መንግሥት በዋናው የመገናኛ ብዙኃን እና በማህበራዊ ሚዲያው ሐሰተኛ መረጃዎችን የማጋለጥ ሂደቱን መቀጠል አለበት። ምክንያቱም ማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚቀርቡ መረጃዎች የመዳረስ ፍጥነታቸው በጣም ከፍተኛ ነው። አንድ ሰው መረጃውን ሲጋራ አንድ ሺህ እና ከዚያም በላይ ተከታዮች ካሉት እነዛ ሰዎች በሙሉ መረጃውን ያገኛል። እነርሱ ደግሞ መረጃውን ሲያጋሩ የመባዛት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። በዋናው መገናኛ ብዙኃን በኩል ግን በዚያ ሰዓት እጅ ላይ ሬዲዮ ከሌለ መረጃውን የማግኘት ዕድል ዝቅተኛ ነው። ስለዚህ ፍጥነቱን ለመቆጣጠር መንግሥት መልሶ በዚያው በማህበራዊ ሚዲያው የመረጃውን ሐሰተኝነት ማጋለጥ ላይ መሥራት አለበት። በድጋሚ ዋናው መገናኛ ብዙኃን ላይ ተደግሞ ቢሰራ በማህበራዊ ሚዲያው የተሰራውን ትክክለኛ መረጃ የመስጠትን ተግባር የበለጠ ያጠናክረዋል። ስለዚህ ሰዎችም በደንብ እንዲረጋጉ እና ነገሮችን አስተውለው እንዲወስኑ ያደርጋቸዋል።
አዲስ ዘመን፡- ዓለም አቀፉ ሚዲያ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር የውሸት ምስሎችን እስከ መጠቀም ደርሷል። ለዚህ ሲ ኤን ኤንን እና ሮይተርስን ማንሳት ይቻላል። ይህ ለምን ሆነ? ይህ በኅብረተሰቡ ላይ ጫና እንዳያሳድር ምን መደረግ አለበት?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ፡- ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በአገራቸው አጀንዳ ላይ ተመስርተው የመሔድ ዕድላቸው በጣም ከፍተኛ ነው። ኃያላን አገራት ሚዲያዎችን እንደመሣሪያ ተጠቅመው እነርሱ እንዲታይ የሚፈልጉትን መረጃ ያሳያሉ። እነዚህ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሲ ኤን ኤን እና ሮይተርስን የመሳሰሉት በጣም ኃይለኛ ተደራሽነት አላቸው። አሁን እኛ ላይ ደርሶ ስላየነው እንጂ ከጦርነቱ በፊት አልጄዚራን ጨምሮ እነዚህን የመገናኛ ብዙኃን እንደታማኝ የመረጃ ምንጭ እንወስዳቸው ነበር። ነገር ግን አሁን ደግሞ ስንመለከታቸው ታማኝነታቸው ላይ ጥያቄ ለማንሳት እንገደዳለን። ይህ ከምን የመነጨ ነው ተብሎ ሲታሰብ ኃያላን አገራት ኢትዮጵያ ላይ ለማሳደር ከሚፈልጉት ጫና ጋር አንድ መስመር ላይ ይገኛል። ስለዚህ መንግሥታት በዙሪያቸው ያሉ አካላትን ለማሳመን ይመቻቸው ዘንድ እነዚህን ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸውን የመገናኛ ብዙኃንን በፈለጉት መልኩ እየተጠቀሙባቸው መሆኑ ይሰማኛል።
መንግሥት ማድረግ የሚችለውን እያደረገ ነው የሚል እምነት አለኝ። በዲፕሎማሲ በኩል ጥረት እየተደረገ እንደሆነ እረዳለሁ። ከዚያ ባሻገር የማህበራዊ ሚዲው የእነዚህን ትልልቅ ተቋማት ዜናዎችን ሐሰተኝነት በማጋለጥ ደረጃ ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሆነ አስባለሁ። ምክንያቱም ቲውተር ላይ እየተከታተሉ የሚወጡ መረጃዎች ስህተት እንደሆኑ በማሳወቅ በኩል እየተሰራ ነው። መንግሥትም በተለያዩ ሁኔታዎች በየጊዜው በሚሠሩት ዜና ልክ ባይሆንም ማስተካከያ እንዲያደርጉ ደብዳቤ እና መግለጫም የመስጠት ሁኔታ አለ። ይህ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ከዚያ ባሻገር እውነታውንም አገር አቀፍ መገናኛ ብዙኃንም ሆኑ ሌሎቹ ዓለም አቀፎቹ ሊያገኙ በሚችሉበት መልኩ መረጃ ቢወጣ መልካም ነው። የሚል እምነት አለኝ።
ሁሉም መገናኛ ብዙኃን የራሳቸው ዓላማ አላቸው። ሐሰተኛ ምስሎችን እስከመጠቀም የደረሱት ለዚህ ነው። ያንን መረዳት ያስፈልጋል። አስፈላጊውን መረጃ መስጠትና ሐሰተኛ መረጃዎች በሚለቀቅበት ጊዜ ፈጠን ብሎ በማህበራዊ ሚዲያውም ሆነ በመንግሥትና በግል መገናኛ ብዙኃን የሚመለከተው የመንግሥት አካል መግለጫ በመስጠትም ጭምር የማስተካከያ ሥራዎች መሠራት አለባቸው። ነገር ግን በዋናነት የውጭው ዓለም እያየ ያለው ማህበራዊ ሚዲያውን በመሆኑ መንግሥትም ያንን መደገፍና ግንዛቤ መፍጠር ላይ መስራት አለበት።
አንዱ ትልቁ ችግር እኛ አገር ላይ ሰዎች የሚዲያ አጠቃቀም ዕውቀታቸው እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑ ነው። ስለዚህ እዚያ ላይ ያለው ክፍተት አሁን ላይ ቶሎ መሙላት ስለማይቻል በተቻለ መጠን ሰዎች የማህበራዊ ሚዲያ ኃላፊነትን ተቀብለው የሐሰት መረጃዎችን ማጋለጥ እና ቅስቀሳ መፍጠር ይችላሉ። ሰዎች ቲውተርን መጠቀም ያለባቸው እንዴት ነው የሚል በቴሌቪዢን ለማሳየት የተሞከረበት ሁኔታ አለ። ይህ ጥሩ ጅምር ነው። ነገር ግን ለወደፊት ተጠናክሮ በትምህርት ሥርዓቱም ውስጥ ተካቶ አጠቃቀሙ እንዲታወቅ መደረግ አለበት። አንድ በአገር ውስጥ ለሚመጡ የተሳሳቱ መረጃዎች ተጋላጭነት ይቀንሳል፤ በሌላ በኩል በውጭ የሚተላለፉ የተሳሳቱ ዘገባዎችንም በቀላሉ ለማጋለጥ እና ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ዕድል ይፈጥራል።
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት እየተከሰተ ባለው የመረጃ መዛባት ሂደት ውስጥ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መዋቅሩ መፍረስ አስተዋፅኦ ነበረው ብለው ያስባሉ? በአሁኑ የመንግሥት መዋቅር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መልሶ መዋቀሩስ ለዚህ ችግር ምን ያህል መፍትሄ ይሆናል ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ፡– በመንግሥት ደረጃ የኮሙኒኬሽን ቢሮ መዋቀሩ ጥሩ ነው። ነገር ግን ትኩረት እና ትክክለኛ የሚሔድበት መንገድ ያስፈልጋል። ይህንን ያልኩበት ምክንያት በፌዴራል ደረጃ ባይኖርም በየክልሉ የኮሙኒኬሽን ቢሮዎች አሉ። እነዚህ ትልቅ ክፍተት የነበረባቸው እና አንዳንድ ጊዜም ለግጭት ምክንያት የሆኑበት ጊዜም ጭምር ነበር። ሥራቸውን በአግባቡ የማይፈፅሙ፤ የሰውን የመረጃ ክፍተት የማይሞሉ ለስም ብቻ የነበሩ የኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤቶች ነበሩ። አሁን በፌዴራል ደረጃ ክፍተቱ ታይቶ ቢሮ መቋቋሙ ትልቅ ዕምርታ ነው። ነገር ግን እንደክልሎቹ እንዳይሆን ትልቅ ጥንቃቄን ይፈልጋል። ተቋሙ ሙያተኞችን አሟልቶ በአግባቡ በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ክንውኖች እየተከታተለ ሪፖርት የማድረግ ሐሰተኛ መረጃዎችን የማጋለጥ ትክክለኛ የሆኑ ነገሮች ላይ መግለጫዎችን መስጠት መንግሥትን ወክሎ መስራት መቻል አለበት።
በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ እንደጅምር ጥሩ ነው። ነገር ግን ትልቅ የመረጃ ክፍተት ያለበት ጊዜ በመሆኑ በደንብ ተጠናክሮ በየወቅቱ የተለያዩ መረጃዎችን በመስጠት ያሉ ክፍተቶችን መሙላት መቻል አለበት። ጅምሩ ጥሩ ነው። ነገር ግን ትኩረት ተሰጥቶ መሰራት አለበት።
አዲስ ዘመን፡- ኅብረተሰቡ ከመረጃ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ያለውን ባህል እንዴት ያዩታል? በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችንስ እንዴት መሆን አለበት ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ፡– ከኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን እና ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር ከተወሰኑ ወሮች በፊት ጥናት አድርገን ነበር። የጥናቱ ግኝት የሰዎች የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ማወቅ ተችሏል። ይህ የሆነው በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ስለማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ አለመኖሩ ነው። በመጀመሪያ፣ በሁለተኛም ሆነ በሦስተኛ ደረጃ ትምህርት ላይ ምንም ዓይነት ማህበረሰቡን ስለአጠቃቀሙ ዕውቀት የሚያስጨብጥ ትምህርት የለም። በሌሎች አገሮች አንዳንዶቹ በመጀመሪያ ደረጃ፣ ሌሎች ደግሞ በሁለተኛ ደረጃ ወይም በዩኒቨርሲቲ ደረጃ አካተው የሚያስተምሩ አሉ። እኛ ግን አጠቃቀም ባላወቅን ቁጥር መረጃዎችን የመመርመር ዕድላችን በጣም ዝቅተኛ እየሆነ ይመጣል። ስለዚህ ‹‹አሉ አሉ›› መባባል እንጀም ራለን።
በፊት ሰዎች ማህበራዊ ሚዲያ ስላልነበር በከፍተኛ መጠን የመረጃ ተደራሽነት ያለው ሬዲዮን ነው። ስለዚህ ሰዎች መረጃውን የሚያገኙት ከሬዲዮ ብቻ ነበር። ከመንግሥት እና ከሌሎች ሰዎች መረጃ ሲተላለፍ ሬዲዮ ተናግሯል እውነት ነው ይሉ ነበር። አሁን ግን ቴክኖሎጂው እየሰፋ ተጋላጭነቱ እየጨመረ ሲመጣ በብዛት የሚጠቀመው ወጣት ቢሆንም በዙሪያው ባለው ሰው ላይ በሙሉ ተፅዕኖ ያሳድራል። ወጣቱ ለወላጀቹ እና ለአያቶቹ ሲናገር በፌስቡክ የተባለውን ማመን መጥቷል። ስለዚህ ከባህል ለውጡ እና ዓለም እያደገች ሰዎች ለአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች እየተጋለጡ በመጡ ቁጥር ለነገሮች ያላቸው ግንዛቤ አብሮ እየተቀየረ ነው።
መረጃን የመጠቀም ክፍተት ከምንጩ ብቻ ሳይሆን የተማረ ሰው ራሱ የአንድን መረጃ ዕውነትነት ያለማረጋገጥ እና የግንዛቤ ችግር አለ። ማህበራዊ ሚዲያው ላይ መረጃ ሲያገኙ የሚያመጣውን ውጤት ሳያውቁ ዝም ብለው ይጋራሉ( ሼር) ያደርጋሉ። መረጃው ከየት እንደመጣ ማን እንደተጋራው (ሼር) እንዳደረገው ተንትኖ ያለማየት ችግሮች በብዛት አሉ። ይህ ደግሞ አጠቃቀሙን ካለማወቅ የመጣ ክፍተት ነው። ስለዚህ ሰዎች ስለአንድ ነገር ዕውቀታቸው በዳበረ ቁጥር የሚያደርጉት እና የሚሰሩት ሥራ በዕውቀት ላይ ተንተርሶ ስለሚሆን ጉዳቱ እየቀነሰ ይመጣል። በአገራችን ደረጃ ያለው ሰዎች ስለሚዲያ አጠቃቀም ያላቸው ዕውቀት ዝቅተኛ መሆን አሁን ላለንበት ሁኔታ አስተዋፅ አድርጓል የሚል ግምት አለኝ።
አዲስ ዘመን፡- ኅብረተሰቡ በቂ መረጃ አለማግኘት አደጋው እስከ ምን ድረስ ነው? ወይስ ምንም ችግር የለውም?
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ፡– እዚህ ላይ የተያየ ክርክር አለ። መንግሥት መናገር የማይፈልጋቸውን ነገሮች በወታደራዊ ምስጢር ነው ስም አፍኖ ይይዛል ይባላል። በሌላ በኩል ግን በቀጥታ ወታደራዊ ምስጢር ባይነገርም ሰዎችን ከአደጋ ለመጠበቅ ማወቅ የሚኖርባቸውን መንገር ይገባል ይባላል። ይህ ትክክል ነው። ለምሳሌ፡- ሰው ባለበት አካባቢ አደጋ እያንዣበበበት ከሆነ ሰዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መናገር አስፈላጊ ነው። አይ ወታደራዊ ምስጢር ስለሆነ ዝም ብለን እንቀጥል እና ሲደርስ ይወቁት ማለት ሰዎችን አደጋ ላይ ይጥላል።
በመጀመሪያ የጦርነቱ አላማ የሰዎችን ደህንነት ማረጋገጥ እና ሰላምን ማስፈን እስከሆነ ድረስ አደጋን መቀነስ ታሳቢ ይደረጋል። ነገር ግን የጦርነቱን አቅጣጫ ሊቀይሩ የሚችሉ መረጃዎችን መንገር ያስፈልጋል የሚል እምነት የለኝም። ወታደር ውስጥ የምስጢር ደረጃዎች ይኖራሉ። በጣም ከባድ ሲሆን ከወታደሩ ውስጥ እጅግ በጣም ውስን ሰዎች የሚያውቁት ምስጢር ይኖራል። የተወሰኑ ሰዎች የሚያውቁት ይሆናል። ወታደሩ የሚያውቀውም ይኖራል። ሁሉም መረጃ በዕኩል ደረጃ ሁሉም አያውቀውም። የምስጢር ደረጃዎች ይኖራሉ። መረጃ መጋለጥ የለበትም። ነገር ግን የሚፈጥረው የደህንነት ስጋት እየታየ መረጃዎች መለቀቅ መቻል አለባቸው። የማኅበረሰቡን ደህንነት ለማረጋገጥ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል። በጣም ምስጢራዊ መሆን ያለባቸው መረጃዎች መገለፅ የለባቸውም።
መንግሥት ላይ የሚነሳው ትችት በወታደራዊ ምስጢር ስም የሚሸፋፍንበት ሁኔታ አለ፤ መረጃን አያካፍልም እየተባለ ነው። ነገር ግን በተቃራኒው ደግሞ አሁን ላይ ወታደሩ በማህበራዊ ሚዲያው ምክንያት እያጋጠመ ያለ ችግር አለ። በአካባቢው ያለ ሰው ምስጢር መሆን የሚገባውን ነገር በቦታው ስላለ ፎቶ አንስቶ በእጅ ስልኩ ዛሬ መከላከያችን ወደዚህ እየሔደ ነው ይህንን ሊያደርግ ነው። እያሉ መከላከያን ለአደጋ የሚያጋልጡ መረጃዎችን የሚያጋሩ አሉ። እነዚህም ላይ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ነው። ከጦርነት ጋር የተያያዙ መረጃዎች ተገምግመው ሊያመጡ የሚችለው ጥቅምና ጉዳት ተለይቶ በተወሰነ አካል መውጣት አለባቸው። ነገር ግን ዝም ብለን ጦርነቱ ተካሒዶ ውጤቱን እናሳያችሁዋለን የሚለውም ተገቢ አይደለም።
አዲስ ዘመን፡- ስለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ።
ረዳት ፕሮፌሰር ሙሥጠፋ፡– እኔም በጣም አመሰግናለሁ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2014