አሸባሪው ሕወሓት በትግራይ ክልል መሽጎ በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ በተከፈተበት የህግ ማስከበር ዘመቻ በመረጠው የመሳሪያ ትግል በጦርነት ቋንቋ በድል ተጠናቅቋል፡፡ ቡድኑ ወደ ተፈጠረበት ዋሻ ተመልሶ መግባቱም ይታወሳል፣ አብዛኞቹ መሪዎቹም በወረንጦ ተለቅመው ላይመለሱ አሸልበዋል፤ በርካቶቹም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
ቡድኑ በጦርነቱ ክፉኛ ተፈትኗል፡፡ ይህንንም ራሳቸው ወሬ ነጋሪ ሆነው የተረፉት አመራሮቹ በይፋ አረጋግጠውታል፡፡ ይህን ያየ ቡድን ፊቱን ወደ ጦርነት ይመልሳል ተብሎ ጨርሶ አይገመትም፡፡ ግን ይህ አሸባሪ ቡድን ከስህተቱ የሚማር አይደለምና ተመለሰ፡፡
መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ሠራዊቱን ከትግራይ ሲያስወጣ ይህን ለሰላም ሲባል የተወሰደን ትልቅ እርምጃ በመናቅ በአማራና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ የፈጸመው ቡድኑ ፣ ህጻናትን፣ እናቶችን፣ አዛውንቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን በገፍ ከፊት ለፊት አሰልፎ በፈጸመው ወረራ አያሌ ንጹሃን የአማራና የአፋር ክልል ነዋሪዎችን በግፍ በጅምላ ጨፍጭፏል፤ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አፈናቅሏል፡፡ ሀብትና ንብረታቸውን ዘርፎ ወደ መቀሌ አግዟል፤ መውሰድ ያልቻለውን አውድሟል፡፡ የአርሶ አደሩን ከብቶች አርዶ በልቷል፤ ወደ ክልሉ ነድቷል፤ በጥይት ደብደቦ ገድሏል፡፡
የአፋርና የአማራ ከልሎች ልዩ ሃይሎች፣ሚሊሺያዎችና ህዝቡ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ባደረጉት የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ቡድኑ ተቆጣጥሮት የነበረውን የአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ ለቆ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ በዚህም ከፍተኛ የሆነ ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሰራም ደርሶበታል፡፡ በአፋር ክልል በኩል አድርጎ የወደብ መስመርን የመቆጣጠር ህልሙ ቅዠት ሆኖ ቀርቷል፡፡ ይዞት ከነበረው የአማራ ክልል ደቡብና ሰሜን ጎንደር ዞንም እንዲሁ ተእአንዲወጣ ተደርጓል፡፡ በዚህም ቢሆን የደረሰበት ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡
ከስህተቱ የማይማረው ቡድኑ ግን ወረራውን ወደ ደቡብ ወሎ በማስፋት ላይ ቢሆንም እዚህም ተመሳሳይ እርምጃ እየተወሰደበት ነው፡፡ የመከላከያ ሰራዊትና የክልል የጸጥታ ሃይሎች ቡድኑን እያሳደዱት ይገኛሉ፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ያደረገውን የክተት ጥሪ ተከትሎም በርካታ ዜጎች ከአማራ ክልል የተለያዩ ዞኖች ወደ ደቡብ ወሎ ዘምተው ጠላታቸውን ገጥመዋል፡፡
ቡድኑ ይህን ያህል ሊፈነጭ ወይም ሊወራጭ የቻለው በወታደራዊ መስኩ ባለው አቅም አይደለም፡፡ በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በሀሰተኛ መረጃ በመጠቀምና ሕዝብን በማደናገር እንጂ፡፡ በማሕበራዊ ሚዲያው በከፈተው ዘመቻ ያልተቆጣጠራቸውን አካባቢዎች ተቆጣጥሬያለሁ በማለት ፣ በከተሞች ባሰማራቸው ጀሌዎቹ ሽብር በመንዛትና ሕዝቡ ከተሞችን ጥሎ እንዲወጣ ለማድረግ ሞክሯል፡፡
ከተሞችን የተቆጣጠረው እንደ ወታደር አድፍጦና እንደ እባብ እየተሳበ አይደለም፤ ሰተት ብሎ ነው የገባው፡፡ ይህን ምቹ ሁኔታ የፈጠረለት ደግሞ የከተሞች ነዋሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው መውጣታቸው ነው፡፡ አሸባሪ ቡድኑ ወደ ከተሞች ይዟቸው የሚገባ ኃይሎችም ቢሆኑ የየከተሞቹ ሕዝብ ተባብሮ ሊመከታቸው የሚችል ብዙም መሳሪያ ያልታጠቁ መሆናቸው ይገለጻል፡፡ ከዚህም የምንረዳው ሀቅ ቢኖር የነዋሪዎች በከንቱ ወሬ በመሸበር አካባቢውን ለቆ መውጣት ለቡድኑ ሰርግና ምላሽ እንደሆነለት ነው፡፡
በአንጻሩ በወሬና ሽብር ሳይበገሩ በጋራ ሆነው አካባቢያቸውን ሳያስደፍሩ የቆዩ አካባቢዎች ሕዝቡ የአሸባሪውን የውሸት ፕሮፓጋንዳ በማክሸፍ ሽንፈትን እንዲከናነቡ አድርጓቸዋል፡፡ ሕዝብ ተደራጅቶ አካባቢውን ሲጠብቅና ከአሸባሪ ሲከላከል መከላከያና ልዩ ኃይል ደርሰው ድሉን ቅርብ ያደርጉታል። የሕዝብ ከተማን ለቆ መውጣት ቡድኑ ከተሞችን በቀላሉ የሚቆጣጠርበትን፣ የቀረውን ነዋሪ የሚጎዳበትን ፣ አንድም ንብረት ሳይቀር ሊዘርፍ የሚችልበትን ዕድል ይፈጥራል፡፡
ስለሆነም ነዋሪው በሀሰተኛ መረጃ በቀላሉ እየተሸበረ አካባቢውን፣ ቤቱን፣ ንብረቱን እየተወ የሚሸሽበት ሁኔታ ከዚህ በኋላ በጭራሽ መደገም የለበትም፡፡ መንግሥት ሁሌም አካባቢያችሁን በጋራ ጠብቁ፣ በሀሰተኛ መረጃ አትደናገጡ እያለ ማሳሰቢያ እየሰጠ ነው፡፡ ይህን ማሳሰቢያ ተጠቅሞ ራስንም፣ አካባቢንም ሀገርም መታደግ ያስፈልጋል፡፡
የአሸባሪውን ሕወሓት ሐሰተኝነት የሚያውቅ ማህበረሰብ ይህን ያህል በወሬ መሸበር አልነበረበትም፡፡ ቡድኑ ሥልጣን ላይ እያለም በወሬኛነቱ፣ በሀሰተኛ መረጃ ሰሪነቱና አሰራጭነቱ ይታወቃል፤ አንዲያውም ይህ መገለጫ ባህሪው ነው፡፡ ያልተመረተውን ተመረተ፣ ያልያዘውን አሸባሪ ያዝኩ እያለ ሀሰተኛ ምስል ጭምር እያቀነባበረ አገርና ሕዝብን ሲያታልል መኖሩም የሚረሳ አይደለም፡፡
ያን የሀሰተኛ መረጃ ፋብሪካውን ነው በዚህ የወረራው ወቅትም እያንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ደሴን ፣ ኮምቦልቻን፣ ወዘተ ተቆጣጥሬያለው እያለ የደቡብ ወሎ ሕዝብን በሀሰተኛ ወሬ ሲያምስ ሰንብቷል፤ ቡድኑ ከዚህ ቀደም ብሎ እንጦጦ ደርሰናል ሲልም ነበር፡፡ ይህ የቡድኑ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ስራ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን አዲስ መሆን የለበትም፤ መቼም አዲስ ሊሆን አይገባም፡፡
ሁሌም አዲስ እየሆነ ያለው ለቡድኑ ሀሰተኛ መረጃ ቦታ አትስጡ እየተባሉ በሀሰተኛ መረጃው ላይ ተመስርተው የሚሸበሩና የሚያሸብሩ አሁንም መኖራቸው ነው፡፡ ሰው ከስህተቱ ይማራል፤ የዚህን ቡድን መረጃ ይዞ ወደ እርምጃ መግባት አሁንም ታሪካዊ ስህተት መድገም ይሆናል፡፡
በመሆኑም የቡድኑን የማህበራዊ ሚዲያ እና የተለያዩ ማሰራጫዎች መረጃ በጭራሽ አለመከታተልና መረጃው ከተገኘም በሌላ ምንጭ ሳያረጋግጡ መጠቀምና ለሌላ ወገን ማስተላለፍም የሚያስከፍለው ዋጋ ከፍተኛ ስለመሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡
መንግሥትም ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያመክን ስራ መስራቱን አጠናክሮ መቀጠል ፤ አማራጭ የመረጃ ምንጮችን ማስፋትና ህዝቡ ትክክለኛ መረጃዎችን እንዲያገኝ ማድረግና በጠላት በኩል የተሰራጩ መረጃዎች የተሳሳቱ መሆናቸውን ማስገንዝብ ይኖርበታል፡፡
በውትድርናው መስክ መወሰድ ስላለበት እርምጃ መከላከያ የሚያደርገውን ያደርጋል፡፡ ሕዝቡ ይህ ዘመቻ በስኬት እንዲጠናቀቅ ደጀንነቱን በገንዘብ እና በቁሳቁስ ድጋፍ ብቻ አይደለም መግለጽ ያለበት፡፡ ይልቁኑ መረጃዎች ሳያጣሩ ወደ እርምጃ ባለመግባትና በተለይም ሀሰተኛ መረጃ ከሚያሰራጩ ኃይሎች በመራቅ፣ እንዲህ አይነቶችን አካላት ለሚመለከተው አካል አሳልፎ በመስጠትም ነው፡፡
ከሀሰተኛ መረጃ ማዳመጥ፣ ማስተላለፍ እና መጠቀም በመታቀብ አካባቢን መጠበቅ በራሱ የመከላከያ እና የልዩ ኃይል አጋርነትን ይበልጥ ማጠናከር ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው ደግሞ የአሸባሪው ሕወሓትን ሀሰተኛ መረጃዎች ባለመጠቀም ጭምር መሆኑን በአግባቡ ማስተዋል ያስፈልጋል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም